ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 10 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, December 9, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 10

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ኅዳር ዐሥር በዚህች ቀን ቅዱሳት ንጹሐት መነኰሳይያት ደናግል እናታቸው ቅድስት_ሶፍያም በሰማዕትነት አረፉ፤ ቅዱሳን አባቶቻችን ስለ ጾም ሥርዓት የአንድነት ስብሰባ አድርገው የቅዱስ_ዲሜጥሮስን_ቀመር_አቡሻህርን በሁሉም ዘንድ እንዲጠቀሙበት በጉባኤ ወሰኑ፡፡

ኅዳር ዐሥር በህች ቀን ቅዱሳት ንጹሐት መነኰሳይያት ደናግል እናታቸው ሶፍያም በሰማዕትነት አረፉ። እሊህም ቅዱሳት ከተለያዩ አገሮችና ቦታዎች ሲሆኑ መለኮታዊ ፍቅር በአንድነት ሰበሰባቸው የምንኲስናንም ልብስ ለበሱ ይኸውም የመላእክት ልብስ ነው። በሮሜ አገር ከአሉ ገዳማትም በአንዱ የሚኖሩ ሆኑ ቅድስት ሶፍያም በእነርሱ ላይ እመ ምኔት ሆነች።
እርሷም ጸጋንና ዕውቀትን የተመላች ናት የቅዱሳን መነኰሳትን ገድል በማንበብ እየጾሙ እየጸለዩ በምድር ላይ እንደ መላእክት እስከ ሆኑ ድረስ መንፈሳዊ ዕድገትን አሳደገቻቸው ከእነርሱም በአንድ ገዳም ውስጥ ሰባ ዓመት ያህል የኖሩ አሉ ከውስጣቸውም ልጅ እግሮች የሆኑ አሉ።
ከሀዲ ንጉሥ ዑልያኖስም ከፋርስ ንጉሥ ከሳቦር ጋር ሊዋጋ በሮሀ ሀገር በኩል በሚያልፍ ጊዜ እርሱ ሳቦር ሊወጋው ወደርሱ እንደሚመጣ ሰምቷልና አልፎ ሲሔድም በውስጡ እሊህ ደናግል ያሉበትን ገዳም አይቶ ይህ ምንድን ነው ብሎ ጠየቀ ሰዎችም ይህ የደናግሎች ገዳም ነው አሉት።
በዚያንም ጊዜ ወደዚያ ገዳም ገብተው ደናግሎችን እንዲገድሏቸው በገዳሙ ውስጥም ያለ ገንዘባቸውን ሁሉ እንዲዘርፉ ወታደሮቹን አዘዘ ወታደሮችም ገብተው እሊያን ደናግል በሰይፍ ገደሏቸው ገዳሙንም አጠፉ የገዳሙን ገንዘብ ሁሉንም ዘረፉ።
ከሀዲውን ንጉሥ ግን ስለ መንጋዎቹ በቀል እግዚአብሔር ተበቀለው ይህም እንዲህ ነው ያጠፋው ዘንድ ሰማዕት መርቆሬዎስን አዘዘው መርቆሬዎስም በአካለ ነፍስ ሒዶ በጦር ወጋውና በክፉ አሟሟት ሙቶ ወደ ዘላለም ሥቃይ ሔደ። እሊህ ቅዱሳት ደናግል ግን ወደ ዘላለም ተድላ ደስታ ገቡ።

በዚችም ዕለት በእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት በድሜጥሮስ ዘመን ስለ ጾም ሥርዓት ቅዱሳን ሊቃነ ጳጳሳትና የኤጲስቆጶሳት የአንድነት ስብሰባ ተደረገ። በዚህም የአንድነት ጉባኤ የመሰብሰባቸው ምክንያት እንዲህ ነው የክርስቲያን ወገኖች በጥር ዐሥራ አንድ ቀን በከበረች በጥምቀት በዓል ተጠምቀው በማግሥቱ የከበረች የአርባ ቀንን ጾም መጾም ይጀምራሉ እስከ የካቲት ሃያ ሁለት ቀንም ጾመው ጾምን ይፈታሉ።
ከዚህም በኋላ በመጋቢት በሃያ ሦስት የሕማማትን ሰሞን መጾም ይጀምራሉ በዚህም ወር በሀያ ሰባት የስቅለቱን በዓል ያከብራሉ በሃያ ዘጠኝም ክብር ይግባውና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤውን በዓል ያክብሩ ነበር።
ይህ ድሜጥሮስም በእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ በተሾመ ጊዜ በእርሻ የሚተዳደር መጻሕፍትን የማያውቅ ጨዋ ሰው ሲሆን እግዚአብሔር በመለኮታዊ ስጦታው ልቡን ብሩህ አድርጎለት የብሉይንና የሐዲስ መጻሕፍትን የቤተ ክርስቲያንንም ሕግ አወቀ ከእርሳቸውም ብዙዎችን ተረጎመ።
ከዚህም በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ባሕረ ሐሳብ የተባለ የዘመን ቁጥርን ጻፈ ይህም ክብር ይግባውና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጽዋማትና በዓላቶቹ የሚታወቁበት እሊህም የከበረች የአርባ ቀን ጾም የሆሣዕና ዑደት ስቅለቱ ትንሣኤው በአርባ ቀን ዕርገቱ ከትንሣኤውም በኋላ በኀምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ናቸው።
ይህንንም ጽፎ ወደ ሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ፊቅጦር ላከ ሁለተኛም ወደ አንጾኪያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ መክሲሞስ ላከ ዳግመኛም ወደ ኢየሩሳሌም አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ አጋብዮስ ላከ እነርሱም በአነበቧት ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኙባት።
የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ፊቅጦርም በሮሜ አገሮች ሁሉ ያሉትን ኤጲስቆጶሳቶቹን አዋቂዎችን ብዙዎች ሊቃውንትንም ሰበሰባቸው ይህንንም የዘመን ቁጥር አስነበበላቸው እጅግ በጣም ጥሩ ሁኖ አግኝተውት ደስ ተሸኙበት በደስታም ተቀበሉት አባዝተውም በመጻፍ ለሁሉ አገሮች ላኩት እስከዚች ዕለትም ጸንቶ ተሠርቶ ኖረ። ከዚህም በኋላ ልዩ ሦስት የሆነ አንድ እግዚአብሔርን ፈጽሞ እያመሰገኑት ወደየሀገራቸው ገቡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ደናግላን ሰማዕታት እና ሥርዓትን በሰሩልን አባቶች ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages