አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ዘጠኝ በዚህችም ቀን ሃይማኖታቸው የቀና 318ቱ_ቅዱሳን_አበው_ሊቃውንት_በኒቅያ አርዮስን ያወገዙበት ዕለት ነው፤ የእስክንድርያ አገር አርባ አንደኛ ሊቃ ጳጳሳት ቅዱስ_አባት_ይስሐቅ አረፈ።
ኅዳር ዘጠኝ በዚህችም ቀን የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ በኒቅያ ከተማ በጻድቅ ንጉሥ በቈስጠንጢኖስ ዘመን ሆነ። ከእርሳቸውም ጋራ አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት አሉ እሊህም አባ እለእስክንድሮስ የእስክንድርያ አባ ዮናክንዲኖስ የሮሜ አገር አባ ሶል ጴጥሮስ የቊስጥንጥንያና የአንጾኪያም ሊቀ ጳጳሳት አባ ኤዎስጣቴዎስ ናቸው። ስብስባቸውም የሆነበት ምክንያት በእስክንድርያ አገር ቄስ ሁኖ ስለ ነበረው ስለ አር*ዮስ ነው። እርሱ ስቶ የክብር ባለቤት ወልድን በመለኮቱ ፍጡር ነው በማለቱ ነው።
ከእሊህም ቅዱሳን ተጋዳዮች አባቶች ከውስጣቸው እንደ ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ በሽተኞችን የሚፈውሱ ድንቆች ተአምራትን የሚያደርጉ አሉ ብዙ ዘመናትም ስለ ቀናች ሃይማኖት የተሠቃዩ አሉ። ከእርሳቸውም የእጃቸውንና የእግራቸውን ጥፍሮች ያወለቋቸው አሉ ዳግመኛም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን የቆረጧቸው አሉ። ጥርሶቻቸውን የሰበሩአቸውና ጐናቸውን የሠነጠቋቸውም አሉ።
ከውስጣቸውም ስሙ ቶማስ የሚባል የሀገረ መርዓስ ኤጲስቆጶስ አለ ከሀድ*ያንም ሃያ ሁለት ዓመት አሥረው ርኅራኄ የሌለውን ሥቃይ አሠቃዩት በየዓመቱም ወደርሱ በመግባት ከሕዋሳቱ አንዱን ይቆርጣሉ እንዲሁም በማድረግ እጆቹን እግሮቹን ከንፈሮቹን አፍንጫውን ጆሮዎቹንም ቆርጠው ጨረሱ። ጥርሶቹንም ሰበሩ በእሳትም ተለብልቦ እንደ ጠቆረ ግንድ አደረጉት የርሱ ወገኖችም እንደሞተ አስበው እንደ ሌሎች ሰማዕታት በየዓመቱ መታሰቢያውን አደረጉ።
እሊህ አባቶችም ወደ ኒቅያ ከተማ በደረሱ ጊዜ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ ታላቅና ሰፊ የሆነ መሰብሰቢያ አዳራሽ አዘጋጀላቸው በውስጡም ለየአንዳንዳቸው ወንበሮችን አኖረ የእርሱንም ወንበር ከእነርሱ ወንበሮች ዝቅተኛ አደረገ መሳለምን በመርዓስ ኤጲስቆጶስ በቅዱስ ቶማስ ጀመረ ሰገደለት ሕዋሳቶቹ ከተቆረጡበት ላይ ተሳለመው። እንዲሁም አባቶችን ሁሉንም ተሳለማቸው። ከዚህም በኋላ በትረ መንግሥቱን ሰይፉን ቀለበቱን ሰጣቸውና እንዲህ አላቸው እነሆ አሁን በካህናት ሁሉና በመንግሥት ላይ ሃይማኖቱ እንደናንተ የቀና ከሆነ ታኖሩት ዘንድ ሃይማኖቱ የቀና ካልሆነ ግን ከምእመናን ለይታችሁ ታሳድ*ዱት ዘንድ ሥልጣንን ሰጠኋችሁ።
እነርሱም ሕግንና ሥርዓትን ሠሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመካከላቸው ይቀመጥ ነበር ልቡናቸው በመንፈስ ቅዱስ የበራላቸው ሰዎች አይተውታልና በሚቆጥሩአቸው ጊዜ ግን ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ቁጥር ሁነው ያገኙአቸዋል።
ከዚህም በኋላ ለካህናትና ለሕዝባውያን ለነገሥታት ለመሳፍንት ለሚገዙና ለሚሸጡ ነጋዴዎች ለድኆችም ለሽማግሎችና ለጐልማሶች ለሙት ልጆችም ለወንድና ለሴት ሥርዓትን ሠሩ። ከዚህም በኋላ ወልድ በመለኮቱ ከአብ ጋር ትክክል እንደሆነ እያስረዱ የቀናች ሃይማኖትን አስተማሩ የተረገመ አርዮ*ስንና በረከሰች ትምህርቱ የሚያምነውን አው*ግዘው ለዩ።
የሠሩዋት ያስተማሩዋትም የሃይማኖት ትምህርት ይቺ ናት እንዲህ ብለው ሁሉን በያዘ ሰማይና ምድርን የሚታይና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን።
ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል። ሁሉ በርሱ የሆነ ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የሆነ የሌለ በሰማይም ያለ በምድርም ያለ። ስለእኛ ስለ ሰው ስለ መዳናችን ከሰማይ ወረደ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ።
ሰው ሆኖ በጰንጤናዊ ጲላጦስ ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ ታመመ ሞተ ተቀበረም በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ። በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ ዳግመኛም ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።
ከዚህም በኋላ የመንፈስ ቅዱስ ጠላት ስለሚሆን ስለመቅ**ዶንዮስ በቊስጥንጥንያ ከተማ መቶ ሃምሳው ኤጲስቆጶሳት በተሰበሰቡ ጊዜ ከዚህ የቀረውን ሠሩ። እንዲህም አሉ ጌታ ማሕየዊ በሚሆን ከአብ በሠረፀ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋራ በነቢያት የተናገረ። ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እናምናለን። ኃጢአትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀትም እናምናለን ። የሙታንንም መነሣት የሚመጣውንም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን።
እሊህም አባቶቻችን ይችን የሃይማኖት ትምህርት ምእመናን ሁሉ በቀንም በሌሊትም በጸሎታቸው ጊዜ እንዲአነቡዋት በቅዳሴም ጊዜ እንዲጸልዩባት አዘዙ ወንዶችና ሴቶች ሽማግሎችና ልጆች አገልጋዮችም ሁሉ እንዲማሩዋት አዘዙ። ሠርተው ወስነው ለቤተ ክርስቲያን የሃይማኖትን ፋና ከአቆሙላት በኋላ ወደ የሀገራቸው በፍቅር አንድነት ተመለሱ።
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ አንደኛ የእስክንድርያ አገር ሊቃ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ይስሐቅ አረፈ።
ይህም ቅዱስ ቡርልስ ከሚባል አገር ነው ወላጆቹም እግዚአብሔርን የሚፈሩ እጅግም ባለጸጎች ናቸው ከረጅም ዘመንም በኋላ ይህን ቅዱስ በወለዱት ጊዜ በታላቅ ደስታ ደስ ተሰኙበት። ከዚህም በኋላ ያጠምቀው ዘንድ ወደ ኤጲስቆጶስ በአቀረቡት ጊዜ ኤጲስቆጶሱም ሲያጠምቀው በሕፃኑ ራስ ላይ የብርሃን መስቀልን አየ በዚያንም ጊዜ የሕፃኑን እጅ ይዞ በራሱ ላይ አኖረ። እንዲህም ብሎ ትንቢት ተናገረለት ይህ ሕፃን በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ላይ ይሾማል አባቱንም እንዲህ አለው ይህን ልጅ ጠብቀው እርሱ ለእግዚአብሔር የተመረጠ መሣሪያ ይሆናልና።
ጥቂትም በአደገ ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ጽሕፈትን አስተማሩት የቅዱሳንንም ዜና የሚያነብ ሆነ ወላጆቹንም ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በአበ ምኔቱ በአባ ዘካርያስም ዘንድ መንኩሶ በገድል ተጠመደ።
በአንዲትም ዕለት አንድ ጻድቅ ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አየው በእርሱም ላይ ይስሐቅ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ይሾም ዘንድ አለው ብሎ ትንቢት ተናገረ።
በዚያም ወራት ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ ጸሐፊ የሚሆነውና የሚረዳው ብልህ ሰው ፈለገ ስለ አባ ይስሐቅም ነገሩት እርሱም መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ይጽፍለትም ዘንድ ደብዳቤ ሰጠው እርሱ ግን አባ ይስሐቅ እያወቀ ጽሕፈቱን አበላሽ ሊቀ ጳጳሳቱ እንዲተወውና ወደ አስቄጥስ ገዳም እንዲመለስ ነበር የዚህን ዓለም ክብር ይጠላልና።
ሊቀ ጳጳሳቱም እንዲተወውና እንዲአሰናብተው አውቆ ማበላሸቱን በአወቀ ጊዜ በጥሩ ጽፈሃል ከዚህም እንድትሔድ እኔ አልተውህም አለው አባ ይስሐቅም እንደማይለቀው አውቆ የሚያውቀውን ሁሉ ጥበቡን ያማረ ጽሕፈቱንም ገለጠለት ሊቀ ጳጳሳቱም በእርሱ እጅግ ደስ አለው ።
ከጥቂት ወራትም በኋላ አባ ይስሐቅ ወደ አስቄጥስ ገዳም ተመለሰ አባ ዮሐንስም የሚያርፍበት ቀን በደረሰ ጊዜ ስለርሱ ሊቀ ጵጵስና የሚሾም ማን እንደሆነ ያስረዳው ዘንድ ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው ጌታም በራእይ ከአንተ በኋላ ለዚች ሹመት የሚጠቅም ረዳትህ ይስሐቅ ነው አለው።
ከዚህም በኋላ ሕዝቡን ጠራቸውና ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ የሚሾም ረዳቱ ይስሐቅ እንደሆነ አስረዳቸው ከዚህም በኋላ አባ ዮሐንስ በአረፈ ጊዜ ይህን ቅዱስ አባት ይስሐቅን ይዘው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት በዘመኑም ቤተ ክርስቲያን ብርሃን ሆነች ብዙዎች አብያተ ክርስቲያንንም አደሳቸው ይልቁንም የወንጌላዊ ማርቆስን ቤተ ክርስቲያን አሳምሮ አደሳት የሊቀ ጵጵስናውንም ቤት አደሰ ።
ይህንንም አባት ብዙ ችግርና መከራ ደርሶበታል በወንጌላዊ ማርቆስ መንበርም ሰባት ዓመት ተኩል ኑሮ አረፈ። በዚህም ቅዱስ አባት በመጽሐፈ ገድሉ ከእሑድ ቀን በቀር ሊቀ ጳጳሳት እንዳይሾም የሚያዝ ጽሑፍ አለ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶች ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment