ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 16 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 16

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን የከበረ #ቅዱስ_ፊላታዎስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የከበረ አባት ተጋዳይ የሆነ #ቅዱስ_ጰላድዮስ አረፈ፣ የከበረ አባት #አባ_ዮሐንስ አረፈ፣ የሶሪያ ሰው ሊቅ #ማር_ዳንኤል አረፈ፡፡


ጥር ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን የስሙ ትርጒም የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ የከበረ ፊላታዎስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ከአንጾኪያ ሀገር ሰዎች ወገን ነው ወላጆቹም መረግድ የሚባል ላም ያመልኩ ነበር የተፈተገና የበሰለ በሰሊጥ ቅባትና በማር የተለወሰ ስንዴ ይመግቡታል ሁል ጊዜ ሦስት ጊዜ የተወደደ የሽቶ ቅባት ይቀቡታል የወይን ጠጅም ያጠጡታል ለክረምትና ለበጋም ማደሪያ አለው በአንገቱም የወርቅ ዛንጅርና ድሪ አለ።
ይህ ቅዱስ ፊላታዎስም መልኩ እጅግ የሚአምር ነበር ዐሥር ዓመትም በሆነው ጊዜ ለዚያ በሬ ይሰግድ ዘንድ ወላጆቹ ተናገሩት ሕፃን ፊላታዎስም ቃላቸውን አልሰማም እነርሱም እርሱን ስለሚወዱት ልቡን ሊያሳዝኑት ስለአልፈለጉ አላስገደዱትም።
የከበረ ፊላታዎስም ያን ጊዜ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አያውቀውም ነበር ፀሐይም አምላክ ይመስለው ነበር በፀሐይም ፊት ቁሞ እንዲህ አለ አንተ ፀሐይ አምላክ ከሆንክ ታስረዳኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው። በዚያንም ጊዜ ከወደላይ እንዲህ የሚል ቃል ወደርሱ መጣ እኔ አንተ ልታወቀውና ስለ ከበረ ስሙ ደምህ ይፈስ ዘንድ ያለህ አምላክ አይደለሁም።
ሕፃን ፊላታዎስም ይህን በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና ዳግመኛም በዚያች ሰዓት ወደርሱ መልአክ ተላከ እርሱም የአምላክን ምሥጢር አስረዳው የሚነግረውንም ያስተውል ዘንድ ልቡናውን ከፈተለት ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ ሰው እስከሆነበት ድረስ የሆነውን ይነግረው ጀመረ በልቡናውም እጅግ ደስ አለው።
ከዚያችም ዕለት ወዲህ ሁል ጊዜ አብዝቶ የሚጾምና የሚጸልይ ሆነ ከብቻው እንጀራና ጨው በቀር አይበላም ለድኆችና ለምስኪኖችም ምጽዋት ይሰጣል።
ከዓመትም በኋላ ወላጆቹ አሰቡ ለልጃቸው ባልንጀሮች ምሳ አዘጋጁ ሳይበሉና ሳይጠጡ አስቀድሞ ልጃቸው ፊላታዎስ ለዚያ በሬ ዕጣን እንዲአሳርግ ፈለጉ ሕፃኑ ፊላታዎስም በበሬው ፊት ቁሞ ሰዎች የሚያመልኩህ አንተ በእውነት አምላክ ነህን አለው።
ያን ጊዜ ከበሬው እንዲህ የሚል ቃል ወጣ እኔ አምላክ አይደለሁም ሰይጣን በእኔ ላይ አድሮ ሰዎችን እንዳስት አደረገኝ እንጂ ይህንንም ብሎ ያ በሬ ተነሥቶ የቅዱስ ፊላታዎስን ወላጆች በቀንዶቹ ወግቶ ገደላቸው ፊላታዎስም ያንን በሬ ይገድሉት ዘንድ አመድ እስከሚሆንም በእሳት አቃጥለው በነፋስ ይበትኑት ዘንድ አገልጋዮቹን አዘዛቸው እርሳቸውም እንዳዘዛቸው አደረጉ።
የወላጆቹም በድኖቻቸው ወድቀው ነበር እግዚአብሔርም ጸጋውን አሳድሮበታልና ቅዱስ ፊላታዎስ በወላጆቹ በድኖች ላይ ጸለየ ነፍሳቸውም ተመልሳ በዚያን ጊዜ ተነሡ በሲዖልም ከአዩት ሥቃይ ነገሩት። ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፊላታዎስና ወላጆቹ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት በጸሎቱ በሽተኞችን የሚፈውስ ሆነ።
ወሬውም በንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ ተሰማ መልከተኞችንም ልኮ ወደርሱ አስቀረበውና ለአጵሎን ዕጣን ያሳርግ ዘንድ አዘዘው ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት ባልሰማውም ጊዜ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ። በአላንጋዎች ገረፉት በሆዱም ላይ የሚከብዱ ደንጊያዎችን አደረጉ እርሱ ግን በክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የጸና ነው።
ከዚህም በኋላ ንጉሡንና የረከሱ አማልክቶችን ሊረግማቸው ጀመረ ንጉሡም አፉን ይመቱት ዘንድ ምላሱንም ይቆርጡ ጥርሶቹንም ይሰብሩ ዘንድ አዘዘ ጌታችንም ያለ ጥፋት ጤነኛ አደረገው።
ከዚህም በኋላ ንጉሡ ይሸነግለው ዘንድ መልካም ቃል ሊናገረው ጀመረ የከበረ ፊላታዎስ ግን ሲዘብትበት ለጣዖቶቹ እንደሚሠዋ ቃል ገባለት ንጉሡም እውነት ስለመሰለው ደስ አለው አጵሎንንና አገልጋዮቹን ለጠዖትም የሚገዙትን ሁሉንም እንዲአመጡአቸው አዘዘ ዳግመኛም በከተማው ውስጥ ዓዋጅ ነጋሪ ይዞር ዘንድ አዘዘ እንዲህ እያለ ሁላችሁ አሕዛብ ኑ ፊላታዎስ ለአማልክት ሲሠዋ ታዩ ዘንድ አሕዛብም ሁሉ ወደ ፍርድ አደባባይ ተሰበሰቡ።
ጣዖታቱንም በጐዳና ውስጥ ሲያመጡአቸው የከበረ ፊላታዎስ የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ጣዖታቱንና አገልጋዮቻቸውን ጣዖተ አምላኪዎችንም ሁሉንም ምድር አፍዋን ከፍታ ትውጣቸው ዘንድ ለመነው ዋጠቻቸውም። በአደባባዩም ውስጥ ታላቅ ጩኸትና ሽብር ሆነ። ይህንን ድንቅ ሥራ አይተው ብዙዎች በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ንጉሡም ተቆጥቶ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ቆረጡአቸውም የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀብለው ወደ ዘላለም ሕይወት ገቡ።
የከበረ ፊላታዎስንም ማሠቃየቱን ንጉሡ በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የከበረ አባት ተጋዳይ የሆነ ጰላድዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከዋሻው ሳይወጣ የሴቶችን ፊት ሳያይ ሃምሳ ዓመት ኖረ ድንቆች ተአምራቶችን የማድረግና የትምቢት መናገር ሀብት ተሰጠው ዜናውም በቦታው ሁሉ ተሰማ።
በምስር አገር አንድ ነጋዴ ነበር ይነግድም ዘንድ በመርከብ ተጭኖ ሔደ ማዕበልም ተነሥቶበት ለመሥጠም ደረሰ በአባ ጰላድዮስ ጸሎት ተማጽኛለሁ ከሞት ከዳንኩ መቶ የወርቅ ዲናር ለእርሱ እሰጣለሁ ብሎ ጮኸ በዚያንም ጊዜ በመስቀሉ መርከቡን ሲቀዝፍ አባ ጰላድዮስን አየው ወደ ወደብም አደረሰው።
ከዚህም በኋላ ወደ አገር ውስጥ በደረሰ ጊዜ ያ ነጋዴ ፈረስ ተከራይቶ ያንን መቶ የወርቅ ዲናር ይዞ ወደ አባ ጰላድዮስ ሔደ በመሸም ጊዜ በአንዲት አገር በእንግዳ ማደሪያ ውስጥ አደረ። በዚያም ሞሪት የሚባል ሰው አግኝቶ በልቡ ያለውን ሁሉ ምሥጢሩን ነገረው ሞሪትም እኔ ቦታውን አውቀዋለሁና ወደርሱ አደርስሃለሁ አለው በማግሥቱም ሁለቱም ወደ አባ ጰላድዮስ ሔዱ በደረሱም ጊዜ ሰላምታ ሰጡት ነጋዴውም ያን ያመጣውን ወርቅ ሰጠው። አባ ጰላድዮስም አይቶ ባረከው እንዲህም አለው ወደዚህ ወርቅ ፍላጎት የለኝም ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ጠቃሚ እንዲሆንህ ሒደህ ለድኆችና ለችግረኞች በትነው አለው ነጋዴው ግን ይቀበለው ዘንድ ከእግሩ ሥር ወድቆ ማለደው ጥቂትም ወሰደለትና እንዲህ አለው ለበረከት ይህን ተቀብየሃለሁ የቀረውን እንዳዘዝኩህ አድርገው አለው።
ነጋዴውም ወርቁን ይዞ ተመለሰ ከተራራውም ወርዶ ከወንዝ ደረሰ በዚያንም ጊዜ ሰይጣን በሞሪት ልብ አደረና ገንዘቡን ሊወስድ ወደደ በአደገኛነትም በላዩ ተወርውሮ ገደለው በሌሊትም በድኑን ተሸክሞ ወስዶ ከአባ ጰላድዮስ ደጅ ጣለው በማግሥቱም ወደ አገረ ገዥ ሒዶ ስለ ሟቹ ነገረው።
መኰንኑም ወደዚያ በደረሰ ጊዜ አባ ጰላድዮስን ይዞ ጽኑ እሥራትን አሠረውና ስለ ሞተው ሰው ሊመረምረው ጀመረ። እርሱም እኔ አልገደልኩም አለው ወደሞተውም ቀርቦ ቃሬዛውን ይዞ ረጅም ጸሎትን ጸለየ በድን ሆይ ማን እንደገደለህ ተነሥተህ ትናገር ዘንድ በእግዚአብሔር ስም አዝዝሃለሁ አለ ወዲያውኑ የሞተው ተነሥቶ ስለ ገንዘቡ ሞሪት እንደ ገደለው ተናገረ መኰንኑም ይህን ድንቅ ተአምር በአየ ጊዜ ደነገጠ ለአባ ጰላድዮስም ሰገደለት በላዩም ክፉ ስላደረገ ተጸጸተ ሞሪትንም ሊገድለው ወደደ አባ ጰላድዮስም አስተወው። ከብዙ ተጋድሎም በኋላ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝቶ አገልግሎ በመልካም ሽምግልና አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ስምንተኛ ነው።
ይህ አባት ከታናሽነቱ በአስቄጥስ ገዳም በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንኲሶ ፍጹም ተጋድሎን ተጋደለ። በጾም በጸሎት በመትጋት የተጠመደ ሆነ በእግዚአብሔርም ተመርጦ በሰማዕቱ ቅዱስ ሚናስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ቅስና ሾመው የቤተ ክርስቲያኑንም ገንዘብ ሁሉ ምድሩንም በውስጧ የሚገባውን መባና ስዕላቱንም አስረከቡት መልካም አስተዳደርንም አስተዳደረ በሰላም በፍቅርም አገለገለ።
ከእርሱ አስቀድሞ የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚናስ በአረፈ ጊዜ የሚሾሙትን ሊቀ ጳጳሳት ይመርጡ ዘንድ ኤጲስቆጶሳቱና መምህራኑ ተሰበሰቡ ብዙዎችንም መርጠው ስማቸውን በክርታስ። ጻፉ አንድ ጻድቅ ሰውም በሰማዕት ቅዱስ ሚናስ ቤተ ክርስቲያን የተሾመውን ቀሲስ ዮሐንስን ለምን ረሳችሁት አላቸው ሁሉም በእውነት እርሱ ለዚች ሹመት የተገባ ነው አሉ።
ከዚህም በኋላ ስሙን በክርታስ ጽፈው ከእነዚያ ጋር ቀላቀሉት በመሠዊያ ላይ አድርገው ሦስት ቀኖች ሲጸልዩና ሲቀድሱ ኖሩ ከዚህም በኋላ ሕፃን አምጥተው አንዷን ክርታስ እንዲአነሣ አዘዙትና በውስጧ የዚህ ቅዱስ ስም ያለባትን አነሣ አይተውም መልሰው ከክርታሶች ጋር ቀላቀሏት።
ሌላ ሕፃንም አመጡና እርሱም ያቺን ክርታስ ደግሞ አነሣት አይተው እንደ ቀድሞው መልሰው ቀላቀሏት። ሦስተኛም ሕፃን አመጡ እርሱም የዚህ አባት ዮሐንስ ስም ያለባትን ያቺን ክርታስ አነሣ እግዚአብሔርም እንደ መረጠው ተረዱ ከዚህም በኋላ ያለ ውዴታው ይዘው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።
በተሾመም ጊዜ እንደ ሐዋርያት አጠባበቅ መንጋዎቹን ጠበቀ ወደ እግዚአብሔርም የሚያደርሱ መጻሕፍቶችን ያነቡላቸው ነበር በበጎ ሥራና በቀናች ሃይማኖት የሚያጸናቸው ሆነ ችግር ላለበት ሰው ሁሉ አብዝቶ የሚራራና የሚመጸውት ሆነ።
በዘመኑም አንድ መስፈሪያ ሥንዴ ዋጋው ሁለት የወርቅ ዲናር እስኪሆን በግብጽ አገር ታላቅ ረኃብ ሆነ ድኆችና ችግረኞች ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ ወደ ቤቱ ደጃፍ ይሰበሰቡ ነበር። ረዳቱ ማርቆስንም በአብያተ ክርስቲያናት ገንዘብ ላይ ሁሉ ሾመው ጌታችንም ከሰዎች ላይ ቊጣውን እስከ አራቀ ድረስ ለችግረኞች ሁሉ በጥዋትና በማታ የሚሰጣቸው ሆነ ስለዚህም ይህ አባት ዮሐንስ መሐሪ ተብሎ ተጠራ። ከዚህም በኋላ ይህ አባት አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ በጌጥ ሁሉ አስጌጣቸው።
ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ለካህናቱ የሚያርፍባትን ቀን ነገራቸው እንዲህም አላቸው እኔ ጥር ዐሥራ ስድስት ቀን ተወለድኩ በዚችም ቀን ሊቀ ጵጵስና ተሾምኩ ደግሞ በዚች ቀን አርፋለሁ። ይህንንም ሲላቸው ኤጲስቆጶሳቱ አለቀሱና አባታችን ሆይ ከአንተ በኋላ ሊቀ ጵጵስና የሚሾም ማን ነው አሉት። እርሱም ረዳቴ ቀሲስ ማርቆስ ነው የክብር ባለቤት ጌታችን ለዚች ሹመት መርጦታልና አላቸው። በሹመቱ ሃያ ሦስት ዓመት ከኖረ በኋላ ጥር ዐሥራ ስድስት ቀን አረፈ።
በዘመኑም በእስክንድርያ ሊቀ ጵጵስና በግፍ የተሾመው ዳዊት ሞተ ዳግመኛም ከእርሱ አስቀድሞ የነበረ በእሥር ቤት ዐሥር ዓመት ከኖረ በኋላ ሌላ ጊዮርጊስ የተባለ ተሾመ። ይህም አባት አባ ዮሐንስ በተሾመ ጊዜ ስለ ቀናች ሃይማኖት መልእክትን ጻፈ ጊዮርጊስም በአረፈ ጊዜ በእርሱ ፈንታ ስሙ ኪራኮስ የሚባል ጻድቅ ሰው ተሾመ መልእክትንም ጽፎ ወደ አባ ዮሐንስ ላከ እርሱም ደስ ተሰኘበት የመልእክቱንም መልስ ጽፎ ላከለት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ዓምድ ከሚባል አገር የሶሪያ ሰው ሊቅ ዳንኤል አረፈ የዚህም ቅዱስ አባቱ በወርቅና በብር ባለጸጋ የሆነ ነው። አባቱም በሞተ ጊዜ የሀገረ ዓምድ ጳጳስ አባ ዲዮናስዮስ ይህን ቅዱስ አሳደገው የቤተ ክርስቲያንንም ትምርት አስተማረው ከዚህም በኋላ ዲቁና ቅስና ሾመው የምንኲስና ልብስንም አለበሰው ሀብተ ፈውስም እስከተሰጠው ድረስ ከሰንበት እስከ ሰንበት ሳይበላ በጾም በጸሎት ጸንቶ ኖረ።
ከዚህም በኋላ የሴቶችን ፊት እንዳያይ ፈጽሞ ስዕለት አደረገ እናቱም ወሬውን በሰማች ጊዜ ወደርሱ መጣች ታየውም ዘንድ ላከችበት እርሱም የሴቶችን ፊት እንዳላይ ስዕለትን ተስያለሁ አላት። እርሷም እኔ እናትህ አይደለሁምን እንዴት እንደ ሌሎች ሴቶች ታስመስለኛለህ አለችው እምቢ በአላትም ጊዜ ክንብንቧን ገልጣ ሁለት ሴቶች አንድ ልብስ ለብሰው እያዩህ ሲጠቃቀሱብህ እግዚአብሔር ያሳየኝ ብላ ረገመችው።
ከጥቂት ቀንም በኋላ አንድ ምእመን ሰው ለሊቅ ዳንኤል ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር ወሰደለት በማታም ጊዜ ከሊቅ ዳንኤል ደጃፍ ሲደርስ ከእርሱ ጋር ያለ ወዳጁ ስለ ገንዘብ ፍቅር በላዩ ተነሥቶ ገደለው። ስለ ሟቹም የዓምድ ንጉሥ በሰማ ጊዜ አባ ዳንኤልን ያቀርቡት ዘንድ አዘዘ በውሽባ ቤት ያሉ ሁለት ሴቶች የአባ ዳንኤልን መምጣት ወሬ በሰሙ ጊዜ ከችኮላቸው ብዛት የተነሣ ያዩት ዘንድ አንድ ልብስ ለብሰው ወጡ አባ ዳንኤልም እናቱ የተናገረችው ስለደረሰበት ፈገግ ብሎ ሣቀ።
ንጉሡም ስለ ሞተው ሰው አባ ዳንኤልን በመረመረው ጊዜ እኔ አልገደልሁትም ነገር ግን የገደለውን ራሱ ይናገር አለ። በዚያንም ጊዜ ሟቹ በአባ ዳንኤል ጸሎት ተነስቶ ገዳዩን ተናገረ ይህንንም ድንቅ ተአምር ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ አይተው በአባ ዳንኤል ፊት ሰገዱ። በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ሥራ የሚሠራ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
ከዚህም በኋላ ለአባ ዳንኤል እጅ መንሻ ንጉሡ ብዙ ወርቅን አመጣ አባ ዳንኤልም ከርሱ መቀበልን እምቢ ባለ ጊዜ ንጉሥ ገዳምን ሠራለትና ብዙ መነኰሳት ተሰበሰቡ። ወደ መልካም ሽምግልናም በደረሰ ጊዜ ጥቂት ታመመና በሰላም አረፈ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages