ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 17 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 17

 ቅዱስ_ሉቃስ_ዘዓምድ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስራ ሰባት በዚች ቀን ጻድቁ አቡነ ሉቃስ ዘዓምድ ፍልሠተ ሥጋው ሆነ፡፡ እርሱም ከፋርስ አገር ነው በመጀመሪያ በመቶ ጭፍራ ላይ መኰንን ሁኖ ተሹሞ ነበር ከዚህም በኋላ ሹመቱን ትቶ የምንኵስና ልብስን ለበሰ። በምሥራቅ አገር ከአሉ ገዳማትም በአንዱ ገዳም እየተጋደለ ብዙ ወራት ኖረ የምንኵስናንም ሥራ ተጋድሎንና ትሩፋትንም በፈጸመ ጊዜ በዚያ ገዳም ውስጥ ቅስና ተሾመ። በተሾመም ጊዜ በዚያ በኖረበት መጠን የብረት ልብስ ለበሰ ከዚያቺም ወዲህ ስድስት ቀን የሚጾም ሆነ በክርስቲያን ሰንበት ቀንም ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን ይቀበላል ከዚህም በኋላ ከጐመን ጋር አንድ የዳቦ ለከት ይመገባል።


ከዚህም በኋላ ከዓምድ ላይ ወጥቶ በላዩ ሦስት ዓመት ቆመ በስሙም ሲጠራውና ከዚያም ዓምድ ላይ እንዲወርድ ሲያዝዘው የመልአክን ቃል ሰማ የብርሃን መስቀል ተከተለው ከገዳማት ወደ አንዱ ገዳም እስከ አደረሰውም ድረስ መራው በዚያም የሚኖር ሆነ ሰዎችም ሁሉ ወደርሱ እየመጡ በትምህርቱ ይረጋጉ ነበር።
ከዚህም በኋላ የማይናገር ሆነ ከሰው ጋር ከቶ እንዳይናገር ከአፉ ውስጥ ደንጊያ ጐረሰ ዳግመኛም ወደ የቊስጥንጥንያ አገር ዳርቻ ይሔድ ዘንድ መልአክ አዘዘው ለእርሷም አቅራቢያ ወደ ሆነች ወደ አንዲት ቦታ ሔደ ከምሰሶ ላይም ወጥቶ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ በላዩ አርባ አምስት ዓመት ኖረ እግዚአብሔርም የመፈወስን ሀብት ሰጠው አስደናቂዎች ተአምራትን በማድረግ ወደርሱ የሚመጡትን ከብዙዎች በሽተኞችን ፈወሳቸው።
እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው በፈቀደ ጊዜ በዚህ ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን ዐረፈ የሚያገለግለውም ረድ ለጳጳሳት አለቆችና ለካህናት አለቆች ስለ ዕረፍቱ ነገራቸው እነርሱም መስቀሎችን፣ ጽንሐዎችን፣ መብራቶችን፣ ከመያዝ ጋር በዚያን ጊዜ ተነሠሰተው ወደመኖሪያው ሔዱ በላዩም ጸልየው ተሸክመው ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ ወሰዱት በዐረፈ በሦስተኛው ቀን ታኅሣሥ ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን አደረሱት ወደ ቤተ መቅደስም አስገብተው የከበረ ሥጋው በአለበት እንደሚገባ ጸሎትን ፈጸሙ። ከእርሱም ተባረኩ የተሰበሰቡትም ሁሉ ተባረኩ ከዚህም በኋላ ከርሱ አስቀድሞ የቅዱሳን ሥጋቸው ወዳለበት ሣጥን ውስጥ ጨመሩት እግዚአብሔርም እጅግ ጠቃመመ የሆኑ አስደናቂዎች ተአምራትን አብዝቶ ገለጠ አምነው በሚመጡ በብዙዎች በሽተኞች ላይ ታላቅ ፈውስ ሁኗልና።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages