ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 18 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 18

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ዐስራ ስምንት በዚህች ቀን #አቡነ_ሰላማ_ከሣቴ_ብርሃን ጵጵስና የተሾሙበት ዕለት ነው፣ #የሐዋርያው_ቅዱስ_ቶማስ እና የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር የሆነው #የቅዱስ_ቲቶ የሥጋቸው ፍልሰት ነው፡፡


#አቡነ_ሰላማ_ከሣቴ_ብርሃን (ቅዱስ ፍሬምናጦስ)
ታኅሣሥ ዐስራ ስምንት በዚህቸ ቀን አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ጵጵስና የተሾሙበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱስ አባታችን አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኋላ በ245 ዓ.ም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ህዳር 26 ቀን ሲወለዱ ታላቅ ብርሃን ከሰማይ ወርዶ ለ7 ቀናት አብርቷል፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ወደ ምድር ወርደው በመወለዳቸው ታላቅ ደስታን አድርገዋል፡፡ በተወለዱም ጊዜ ‹‹ለአብ ስግደት ለወልድ ስግደት ለመንፈስ ቅዱስ ስግደት ይገባል፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጡኝ ቅድመ ዓለም ለነበሩ ዛሬም ላሉ ዓለምን አሳልፈው ለሚኖሩ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል ብለው ዳግመኛም አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› ብለው ፈጣሪያቸውን በአንድነት በሦስትነት አመስግነዋል፡፡
ቅዱስ አባታችን በሌላኛው ስማቸው ፍሬምናጦስ እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ በ40 ቀናቸው ጌታ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ያጠመቋቸውና ስመ ክርስትና የሰጧቸው ሊቀ ጳጳስ ‹‹ይህ ሕፃን ለኢትዮጵያውን ሁሉ ብርሃን ይሆንላቸዋል›› በማለት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ በሊቀ ጳጳሱ በቅዱስ አትናቴዎስ በሚገባ ተምረው ካደጉ በኋላ በ257 ዓ.ም ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ስሙ ሜርጵዮስ ከሚባል ከአንድ ነጋዴ ጋር መጡ፡፡ ከእነሱም ጋር አድስዮስ የሚባል ልጅ ነበር፡፡ ወደ ሀገራችንም ሊመጡ የቻሉት እንዴት ነው? ቢሉ መጀመሪያ ለሰባት ወር በአንድ ሌላ አገር ኖረው ወደ ኢየሩሳሌም ሊመለሱ ሲሉ የበረሃ ሽፍቶች ሜርጵዮስንና ሌሎች መንገደኞችን ገደሏቸውና ሁለቱን ልጆች ማርከው ወስደው ስሙ አልአሜዳ ለሚባል ለአክሱም ንጉሥ ሰጡት፡፡ እርሱም አድስዮስን የቤተክርስቲያን የአልባሳትና የዕቃ ቤት ጠባቂ አድርጎ ሲሾመው ፍሬምናጦስን ደግሞ የቤተክርስቲያንና የሕግ ጠባቂ አደረገው የቤተክርስቲያንን ሥርዓቷንና አገልግሎቷን ጠንቅቆ ያውቅ ነበርና፡፡
በአክሱምም በተጋድሎና በትጋት ኖረ፡፡ ቅዳሜና እሁድ የዛፍ ቅጠሎችን ከመመገብ በቀር ሌላ ምግብ አይቀምስም ነበር፡፡ በየቀኑም አምስት ሺህ ስግደትን ይሰግድ ነበር፡፡ በእርሱም የተጋድሎ ዘመን ደጋግ የሆኑ ነገሥታት አብርሃና አጽብሓ ነገሡ፡፡ እነርሱም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍሬምናጦስን በጣም ይወዱት ነበር፡፡ አንድ ቀን ፍሬምናጦስ የአክሱሙን ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ሚናስን ‹‹ግዝረትና እምነት በእናንተ ዘንድ አለ ነገር ግን ጥምቀትና ሥጋ ወደሙ መቀበል በእናንተ ዘንድ የለም›› አለው፡፡ ቅዱስ ሚናስም ‹‹ግዝረትንስ አባቶቻችን ሌዋውያን አመጡ፣ በክርስቶስ ማመንን ሕንኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ጃንደረባ አመጣልን፡፡ ስለ ጥምቀትና ሥጋ ወደሙ ሐዋርያ ወደ እኛ አልተላከም ነገር ግን ያልከውን ሁሉ የሚያደርግልን የሚባርከንና የሚቀድሰን ጳጳስን ታመጣልን ዘንድ ሊቀ ጳጳሱ ወዳለበት ወደ እስክንድሪያ አገር አንተ ሂድ›› አለው፡፡ ጥምቀትስ በጃንደረባው በኩል አገራችን ገብቶ ነበር ነገር ግን ገና ስላልተጠናከና ብዙ ሕዝብም አልተጠመቀም ነበርና አባታችን ፍሬምናጦስ አጠናክሮ ያልተጠመቀውን ሁሉ አጥምቆአል፡፡
ፍሬምናጦስም ወደ እስክንድሪያ ለመሄድ አስቦ ሳለ እንደተኛ ድንግል ማርያም ተገልጣለት ‹‹ዲቁናና ቅስናን መቀበል ይገባሃል፣ ለጵጵስና ተዘጋጅ፣ እግዚአብሔር ይህችን ከፍ ያለችውን ማዕረግ ሰጥተሃልና የልጄ ወዳጅ ሆይ በጸሎትህና በልመናህ በስብከትህም የኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ ይድናሉ፣ በእጅህ ጥምቀትንና ሥጋ ወደሙን ይቀበላሉ›› አለችው፡፡ ጌታችንም እንዲሁ ተገልጦለት ‹‹ወደ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አትናቴዎስ ሄደህ ከፍ ያችውን ማዕረግ ተቀብለህ የኢትዮጵያን ሰዎች አጥምቅልኝ፣ ነቢዩ ዳዊት ስለ እነርሱ ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች› ብሎ ተናግሯልና›› አለው፡፡ እርሱም ቅዱሳኑን ነገሥታት አብርሃንና አጽብሓን አግኝቶ ከእነርሱም ጋር ተማክሮ ወደ እስክንድሪያ ሄዶ በቅዱስ አትናቴዎስ እጅ በአገራችን ላይ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ታኅሳስ 18 ቀን ተሾመ፡፡ ስሙንም ሰላማ ከሣቴ ብርሃን አለው፡፡ ሰላማ ማለት እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ ማለት ነው፡፡ ከሣቴ ብርሃን ማለትም ሃይማኖትን ገልጦ የሚያስተምር ማለት ነው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም ከሾመው በኋላ ታቦትና በጣም ብዙ ንዋያተ ቅድሳትንና መገልገያ ዕቃዎችን ሰጥቶ መርቆ በሰላም ወደ ኢትዮጵያ ላከው፡፡ ይህች ዕለት አባታቸን በ330 ዓ.ም በሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ እጅ ጵጵስና የተሾሙባት ዕለት ናት፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት የሐዋርያው የቅዱስ ቶማስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፡፡ ቶማስ ማለት ፀሐይ ማለት ሲሆን ቀዳሚ ስሙ ‘ዲዲሞስ’ ነው ‘ዲዲሞስ’ ማለት ጨለማ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከ12 ሐዋርያት አንዱ ነው ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ያየው በ8ኛው ቀን እሁድ ነው ያየውም በጦር የተወጋ ጐኑን ዳስሶ ነው እንዲሁም የእመ አምላክን ዕርገቷን አስቀድሞ ያየውም እርሱ ነው፡፡
ሀገረ ስብከቱ ሕንደኬ ሲሆን ለምክንያት ይሁነኝ ብሎ በ30 ብር ተሽጦ ከመስፍነ ብሔሩ ክሉክዮስ ቤት እያገለገለ ይኖር ነበር ምን ምን መሥራት ትችላለህ ቢለው ሕንፃ ማነጽ ሐውልት መቅረጽ እችላለሁ አለው እንኪያስ ሠርተህ ቆየኝ ብሎ ብዙ ወርቅ እና ብር ሰጥቶት አሕዛብ ምኩሀን ናቸውና እንዲህ ያለ ጠቢብ አገኘሁ ለማለት ወደ ንጉሥ ሄደ፡፡ እሱም ሕንጻ ማነጽ ሐውልት መቅረጽ ከዚህ የበለጠ አለን ብሎ ለነዳያን መጸወተው ከዚያውም ዘንድ አስተምሮ አሳምኗቸዋል የሉክዮስም ሚስት አርሶንዋ ከነልጆቿ ከአገልጋዮቿ አምና ተጠምቃለች፡፡ ሉክዮስ ከሄደበት ሲመለስ ያነጽከው ሕንጻ የቀረጽከው ሐውልት ወዴት ነው? አለው በወርቅና በብርህ ያነጽኳቸው ሕንጻዎች እኒህ ናቸው ብሎ ያመኑትን አገልጋዮች አሳየው ይህ ክፉ ባሪያ ተጫወተብኝ ብሎ እጅ እግሩን አሥሮ ቆዳውን አስገፍፎ ስልቻ አስፍቶ በአሸዋ መልቶ አሸክሞ ገበያ ለገበያ ሲያዞረው ሚስቱ አርሶንዋ አይታ በድንጋጤ ወድቃ ሞተች ሚስቴ የሞተችው ባንተ ምክንያት አይደለምን ካዳንካት እኔም በአምላክህ አምናለሁ ቢለው ጌታ ቁስሉን እንደ ውኃ አቀዝቅዞለት ካለችበት ሄዶ ስልቻውን ቢያስነካት ተነሥታለች በዚህም ሉክዮስ አምኖ ተጠምቋል፡፡
ከዚህም በኋላ ስልቻውን ተሸክሞ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረ ሙት እያነሣ ድውይ እየፈወሰ አሕዛብን አሳምኖ አጠመቀ፡፡ ቀንጦፍያ ሲደርስ አንድ ሽማግሌ ሰባት ልጆቹን ገድለውበት ሲያዝን አግኝቶ ስልቻውን እያስነካ ሰባቱን አስነሥቶለታል፡፡ በኢናስም የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት አይተው ከንጉሱ ሚስት ከንግሥቲቱ ጀምሮ እስከ ተራ ገባር ድረስ ያሉት ሁሉ አምነው ተጠመቁ ኋላ ግን ካህናተ ጣኦት ጥቅም የሚቀርባቸው ቢሆን በተንኮል ከንጉሥና መኳንንቱ አጣልተው በዚህ ዕለት አንገቱን በሰይፍ አስመትተውታል፡፡
ዛሬም ድረስ ሕንድ ውስጥ በመንበሩ ላይ የቅዱስ ቶማስ ቀኝ እጁ በሕይወት እንዳለች ሆና ትታያለች፡፡ መለኮትን (የጌታችንን የተወጋ ጎኑን) የዳሰሰች ቅድስት እጅ ናትና ዛሬም ድረስ ሕያው ናት፡፡ በሕንድ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ፓትርያርክ ሲሾሙም የቅዱስ ቶማስን ቀኝ እጅ በሚሾመው ፓትርያርክ ላይ ጭነው ነው፡፡ አንድ ወቅት አንድ ሰው ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገብቶ የቅዱስ ቶማስ ቀኝ እጅ እጨብጣለሁ ብሎ እጁን ቢዘረጋ የቶማስ እጅ ተሰወረችባቸው፡፡ እንደገና ብዙ እግዚኦታና ኪሪያላይሶን ካደረሱ በኋላ የቅዱስ ቶማስ እጅ በቦታዋ ተመልሳላቸዋለች፡፡
ይህች ዕለት የሥጋው ፍልሰት መታሰቢያ እንድትሆን አባቶች ሥርዓት ሠሩልን፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የሐዋርያው የቅዱስ ቲቶ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ ቀርጤስ ከሚባል አገር ሲሆን ለዮናናውያን ወገን ለሆነ ለአገረ ገዥው እኅት ልጇ ነው፡፡ ሐዋርያው ከታናሽነቱ ጀምሮ የዮናናውያንን ትምህርትና ፍልስፍና ተምሮ እጅግ አዋቂ ሆነ፡፡ በጠባዩም ቅን፣ ሥራው ያማረ፣ ለድኆችና ጦም አዳሪዎች መራራት የሚወድ ነው፡፡
ከዕለታትም በአንዲቱ ዕለት ‹‹ቲቶ ሆይ ስለነፍስህ ድኅነት ተጋደል፣ ይህ ዓለም አይጠቅምምና›› የሚለውን በራእይ ተመለከተ፡፡ ምን እንደሚሠራም አላወቀምና ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ደነገጠ፡፡ ከዚህም በኋላ የጌታችንን ተአምራት እያነሡ ሰዎች ሲነጋገሩ የአክራጥስ መኮንን ሰማ፡፡ መኮንኑም የሰማውቸው የጌታችን ተአምራቶች እውነት መሆናቸውን ወይም የሥራይ ሥራ እንደሆነ ያረጋግጥ ዘንድ የሚልከውን ብልህና አዋቂ ሰው ፈለገ፡፡ ከእርሱ የሚሻል አዋቂ የለምና መኮንኑ የእኅቱን ልጅ ቲቶን መርጦ ስለ ጌታችን ተአምራቶች ጥልቅ ምርምር ያደርግለት ዘንድ አዘዘው፡፡ ቅዱስ ቲቶም ከይሁዳ ምድር በደረሰ ጊዜ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ድንቅ ድንቅ ተአምራት በዐይኑ ተመለከተ፡፡ ትምህቶቹንም ሰማና የጌታንን ትምህርቶች ከዮናናውያን ትምህርትና ፍልስፍና ጋር አነጻጸረ፡፡ የዮናናውያንም ትምህርት የቀናች እንዳልሆነች ለይቶ ዐወቀ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቲቶ በጌታችን አመነ፣ ደቀ መዝሙሩም ሆኖ ተከተከለው፡፡
ቅዱስ ቲቶ ወደ እናቱ ወንድም ወደ አገረ ገዥው መልአክትና ላከና ጌታችን የሚያደርጋቸው ተአምራቶችና የሚያስተምራቸው ትምህርቶች እውነት እንደሆኑ ነገረው፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ቲቶን ቁጥሩን ከ72ቱ አርድእት ወገን አደረገው፡፡ ቅዱስ ቲቶም ከጌታችን ዕርገት በኋላ ከከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ በሀገሮች ሁሉ ዞሮ የከበረች ወንጌልን አስተማረ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በጌታችን ተጠርቶ ወንጌልን መስበክ ሲጀምር ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ተከትሎት በብዙ አገሮች ወንጌልን ሰበከ፡፡ የከበረ ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ ከተማ ሰማዕት ከሆነ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ወደ ሀገረ አክራጥስ ተመለሰ፡፡ በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው፡፡ በዙሪያቸው ባሉ ሀገሮችም እንዲሁ አደረገ፡፡ በመጨረሻም ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ሄደ፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ከ470,000 በላይ ክርስቲያኖችን በግፍ የገደለውን የሃዲውን ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስን መንግሥት ካጠፋ በኋላ የታሰሩትን ቅዱሳን አስፈትቶ በሚገዛቸው አገሮች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናትን አሳነጸ፡፡ ይልቁንም ቁስጥንጥንያ መናገሻ ከተማው ናትና ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ካሳነጸባት በኋላ የቅዱሳን ሐዋርያን እና የቅዱሳን ሰማዕታትን ሥጋቸውን ከየቦታው እየሰበሰበ በክብር በማምጣት በውስጣቸው አኖረ፡፡ የሐዋርያውም የቅዱስ ቲቶ ሥጋ አቅራጥስ በሚባል አገር መኖሩን ሲሰማ የካህናት አለቆችን ከብዙ ገንዘብና ሠራዊት ጋር ልኮ ወደ ቁስጥንጥንያ በክብር አስመጣው፡፡
ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የቅዱስ ቲቶ ሥጋ አቅራጥስ በሚባል አገር አፍልሶ ወደ ቁስጥንጥንያ ከተማ በክብር ካስመጣው በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠርቶለት የቅዱስ ቲቶን ሥጋ በውስጧ በክብር አኖረ፡፡ ከሥጋውም ብዙ አስገራሚ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ ይኸውም የሆነው ታኅሣሥ 18 ቀን ነው፡፡ የቅዱሱን ሥጋ ከከበረ እምነበረድ በተሠራው ሣጥን ውስጥ አድርገው ተሸክመው ሲወስዱ ከሰው ግፊያ የተነሣ ሣጥኑ ወድቆ የአንዱን ሰው እግር ሰበረው፡፡ እርሱም የቅዱስ ቲቶ ሥዕል ካለበት የመብራት ቅባት ላይ ወስዶ የተሰበረ እግሩን ቀባውና ሲያመው እየጮኸ አሰረው፡፡ ወደ ቤቱም መሄድ ባልቻለ ጊዜ የቅዱስ ቲቶ ሥጋ ሣጥን ባለበት በዚያው አደረ፡፡ በማግሥቱም አይቶ መድኃኒት ሊያደርግ ተሰብሮ የታሰረ እግሩን በፈታው ጊዜ ከቶ ምንም ምን ሕማም እንዳላገኘው ደህና ሆነ፡፡ ለምልክት ይሆን ዘንድ ግን ደም ነበረበት፡፡ ሰውየውም ተነሥቶ እየሮጠ በመሄድ የተደረገለትን ተአምር ለሰው ሁሉ ተናገረ፡፡ ያዩትም ሁሉ የቅዱስ ቲቶን አምላክ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages