ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 19

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ዐስራ ዘጠኝ በዚች እለት #የአባ_መርትያኖስ ስጋው የፈለሰበት ሆነ፣ ታላቁ ጻድቅ #አቡነ_አባለ_ክርስቶስም ልደታቸው ነው።


የካቲት ዐስራ ዘጠኝ በዚች እለት የተጋዳይ መነኰስ የአባ መርትያኖስ ስጋው ከአቴና አገር ወደ አንፆኪያ የፈለሰበት ሆነ። እርሱም ሽንግላ በኃጢአት ልትጥለው በወደደች ጊዜ ከአመንዝራ ሴት ከተፈተነ በኃላ እርሱ ግን መንኲሳ በገድል እስከ ተፀመደች ድረስ ስቦ ወደ ንስሀ የመለሰ ነው።
ይህም አባት በልጅነቱ ከአንድ ቅዱስ የሆነ አረጋዊ አባት ዘንድ መንኵሶ ታላቅ ገድልን ተጋደለ። ከዚህም በኋላ ሐመረ ኖኅ ወደምትባል በቂሣርያ ወደአለች ገዳም ሔደ በዚያም እጅግ በጣም የበዛ ገድልን ተጋደለ።
በጸሎት በጾም በስግደትም በሌሊትና በመዓልት በመትጋት እየተጋደለ ስድሳ ሰባት ዓመት በኖረ ጊዜ የገድሉና የትሩፋቱ ወሬ በቦታው ሁሉ ተሰማ። እነሆ አንዲት በክፉ ሥራዋና በዝሙቷ የታወቀች ኃጢአተኛ አመንዝራ ሴት ሰማች። ጽድቁንና ቅድስናውን በመናገር የሚያመሰግኑትን እንዲህ አለቻቸው። እናንተ ታመሰግኑታላችሁ እርሱ የሚኖረው በዱር ነው የሴት ገጽ ከቶ አያይም እኔን ቢያይ ድንግልናውን አጥፍቼ ቅዱስናውን በአረከስኩት ትኀርምቱንም ባፈረስኩት ነበር። እነርሱ ግን ጥንክርናውን ስለ ሚያውቁ ተከራከሩዋት። ስለዚህም በመካከላቸው ክርክር ሆነ ሔጄ ከእኔ ጋራ በኃጢአት ብጥለው ምን ትሰጡኛላችሁ አለቻቸውና ገንዘብ ሊሰጡአት ተስማሙ።
ያን ጊዜም ተነሥታ ጌጦቿን ልብሶቿንና ሽቱዎቿን ያዘች መልኳም እጅግ ውብ ነበረች ፊቷንም ተከናንባ ጨርቅ ለብሳ ወደ በዓቱ ሔደች። ልብሷንና ጌጦቿንም ለብቻቸው በከረጢት አሥራ ያዘች። ከበዓቱም ቅርብ በሆነ ቦታ ተሠውራ እስከ ሚመሽ ቆይታ የበዓቱን ደጃፍ አንኳኳች። አራዊት እንዲበሉኝ በውጭ አትተወኝ እኔ መጻተኛ ነኝና መንገድንም ተሳስቼ ወደዚህ ደረስኩ አለችው። እርሱም በልቡ አሰበ በውጭ ብተዋት አራዊት ይበሏታል ባስገባትም ስለርስዋ ጦር በኔ ላይ ይነሣብኛል አለ።
ከዚህም በኋላ ከፈተላት በዚያችም በዓት ውስጥ ትቷት ወደ ሌላ ቦታ ፈቀቅ አለ። እርሷ ግን ልብሶቿን ለብሳ ጌጦቿንም ተሸልማ ሽቱዎቿን ተቀብታ ወደርሱ ገባች ከርሷ ጋርም እንዲተኛ ፈልጋ ከዚህ ማንም የሚያየን የለም አለችው።
ቅዱሱም የሰይጣን ማጥመጃው እንደሆነች አውቆ ጥቂት ታገሺኝ መንገድን እስታይ እግዚአብሔርን የማንፈራው ከሆነ እንደእኛ ያሉ ሰዎችን ላንፈራቸው ይገባናል አላት። ይህንንም ብሎ ከእርሷ ዘንድ ወጣ ታላቅ እሳትም እንድዶ እግሩን ከውስጡ ጨመረ ነፍሱንም የሲኦልን እሳት የምትችዪ ከሆንሽ ኃጢአትን ሥሪያ አላት።
በዘገየ ጊዜ ወደርሱ ሔደች በእሳት ውስጥም እግሩን ሲያቃጥል አይታው እጅግ ደነገጠች። ከእሳትም ውስጥ ጐትታ አወጣችው ልቧም ወደ ንስሓ ተመለሰ። ልብሷንና ጌጦቿን ከላይዋ አውጥታ ጣለች ከእግሩ በታች ሰገደች ስለነፍሷ ድኅነትም እንዲረዳት ለመነችው። እርሱም ይህ ዓለም ፍላጎቱ ሁሉ ኀላፊ እንደ ሆነ ያስተምራትና ይመክራት ልብ ያስደርጋትም ጀመር እርሷም በጨከነ ልብ ንስሓ ገባች። ከዚህም በኋላ በአንድነት መኖር አግባብ አይደለም ብሎ ወደ ደናግል ገዳም ወሰዳት ትጠብቃትም ዘንድ እመ ምኔቷን አደራ አላት። በቀረው ዕድሜዋም በገድል ተጠምዳ እግዚአብሔርን አገለገለችው ወደ በጎ ሽምግልናም ደረሰች የመፈወስ ሀብትም አድሮባት ብዙዎች በሽተኞችን አዳነች።
የከበረ አባ መርትያኖስ ግን ሌላ ሴት እንዳያመጣበት ፈርቶ በባሕር መካከል ወዳለች ደሴት ገብቶ በዚያ የሚኖር ሆነ። አንድ ባለ ታንኳም የእጅ ሥራውን እየሸጠ ምግቡን ያመጣለት ነበር። ከብዙ ዘመናትም በኋላ መርከብ ተሰብራ ሰጠመች አንዲት ሴትም በመርከብ ስባሪ ተጣብቃ አባ መርትያኖስ ወደ አለበት ደሴት የባሕሩ ማዕበል አደረሳት በአያትም ጊዜ ደነገጠ አደነቀም። ከእርሷ ጋር በአንድነት ስለ መኖሩም አዘነ የእግዚአብሔርንም ቃል አስተምሮ የምንኲስና ልብስ አለበሳት ምግቧንም አዘጋጀላትና ለእኛ በአንድነት መኖር አግባብ አይደለም አላት። ያንንም ደሴት ትቶላት ወደ ባሕሩ ተወርውሮ ገባ አንበሪም ተሸክሞ ወደ የብስ አወጣው።
መቶ ስምንት አገሮችንም እስቲአዳርስ በአገሮች በአሉ ገዳማት ሁሉ ከዚያች ቀን ጀምሮ የሚዞር ሆነ በአንድ ቦታ እንዳይቀመጥ አስቦ ነው። ከዚህ በኋላም የዕረፍቱ ጊዜ እንደ ቀረበ አውቆ በበዓት ውስጥ ራሱን እሥረኛ አደረገ። ኤጲስቆጶሱንም ጠርቶ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ገድሉን ሁሉ ነገረው ኤጲስቆጶሱም ከጸጋው ገናናነት የተነሣ አደነቀ።
ከዚህም አስቀድሞ የእግዚአብሔር መልአክ ለኤጲስቆጶሱ ስለአባ መርትያኖስ ሥጋ እንዲአስብ ነግሮት ነበር። ከዚህም በኋላ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ኤጲስቆጶሱም በታላቅ ክብር ገንዞ ቀበረው።
ያቺን ሴት ግን እስከ ዕረፍቷ ቀን ባለ መርከብ የሚጎበኛት ሆነ በአረፈችም ጊዜ ሥጋዋ እንደ በረዶ ነጥቶ አገኛት ሥጋዋንም ወደ ሀገሩ ተሸክሞ ወስዶ ቀበራት።
የከበረ ቴዎድሮስም ለአንፆኪያ ሀገር በከሀዲው የፋርስ ንጉስ ዘመን ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህ አባት የካህናት አለቆችንና ምእመናንን ልኮ ስጋውን ከአቴና አፍልሰው ወደ አንፆኪያ ከተማ አመጡት በምስጋናም እየዘመሩ አክብረው ተቀበሉት ሊቀ ጳጳሳቱም ተሳለመው በሳጥን አድርጎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖረው። በዚችም እለት በአልን አደረጉለት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ አባለ ክርስቶስም ልደታቸው ነው። እርሳቸውም ገና ሲወለዱ ከሰውነታቸው ህቡዕ የሆኑ የእግዚአብሔር የምሥጢር ስሞች በሰውነታቸው ላይ ይዘው (ተጽፎባቸው) የተወለዱ ናቸው፡፡
አባታቸው ቅዱስ አቃርዮስ እናታቸው ቅድስት ታውክልያ የተባሉ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ቅዱሳን ናቸው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ነገሥታት መዲና በሆነችው በአክሱም ከተማ በንጉሥ አንበሳ ውድም በ910 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ሕግ በቅዱስ ጋብቻ ተጋቡ፡፡ ንጉሥ አንበሳ ውድም በነገሠ በመጀመሪያ ዓመት እነርሱም በጾም በጸሎት ተወስነው ሲኖሩ እግዚአብሔር የተባረከ ልጅ ቅዱስ አባለ ክርስቶስን ሰጣቸው፡፡ በዚኽም መሠረት አቡነ አባለ ክርስቶስ የካቲት 19 ቀን በአክሱም ከተማ ተወለዱ፡፡ እንደ ነቢዩ ቅዱስ ኤርምያስ በእናታቸው ማሕፀን ሳሉ የተመረጡ ብፁዓት ናቸውና ብፁዕ አባታችን አባለ ክርስቶስ ከሰውነታቸው ህቡዕ የሆኑ የእግዚአብሔር የምሥጢር ስሞች በእብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ዲካባ፣ ማርትያስ፣ ክስብኤል›› የተባሉ ህቡዓን የምሥጢር ስሞችን በሰውነታቸው ላይ ይዘው (ተጽፎውባቸው) ተወለዱ፡፡
እናታቸውና አባታቸው ይኽንን ተኣምር በማየት እየተደነቁና እየተገረሙ ትርጉሙ ምን ይሆናል እያሉ ሲደነቁ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በድንገት መጥቶ ‹‹የእግዚአብሔር አገልጋዮች ጻድቃን ሆይ! ሰላም ለእናንተ ይሁን›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹እኔ የመጣሁት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ነውና እነዚህን የእግዚአብሔር ህቡዓን ስሞች ልተረጉምላችሁ መጥቻለሁ፤ ይህ ታላቅ ስም አባለ ክርስቶስ ተብሎ ይጠራል አላቸው፤ ትርጉሙም አጋንንትን የሚያሥር፣ ጠላትን የሚያርቅ ማለት ነው ›› ብሎ ትርጒሙን ከነገራቸው በኋላ እንዲያጠምቁት አዘዛቸውና ከእነርሱ ተሰወረ፡፡
ከዚኽም በኋላ ወላጆቻቸው ቅዱስ አቃርዮስ እና ቅድስት ታውክልያ በመልአኩ ትእዛዝ መሠረት ወደ አክሱሙ ሊቀ ጳጳስ ወደ አባ ሉቃስ ዘንድ ወሰዷቸው፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ሊያጠምቋቸው ሲቀርቡ ህቡዓን የምስጢር ስሞቹ የመለኮት ቃል ስለሆኑ ወዲያውኑ ደንግጠው ወደቁ፡፡ በዚህም ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በፍጥነት አነሣቸውና ‹‹…በዚህ በምታየው ተኣምር ይህንን ሕፃን አጥምቀው፣ ስሙንም በህቡዓን ስሞች ትርጉም መሠረት አባለ ክርስቶስ ብለህ ጥራው›› በማለት ነገራቸው፡፡ ዳግመኛም መልአኩ ስለ አቡነ አባለ ክርስቶስ ‹‹..እንደ ፋኑኤል መልአክና እንደ አምላኩ መድኀኒዓለም ክርስቶስ የሕሙማን መድኀኒት ይሆናል›› ብሎ ከነገራቸው በኋላ ተሰወረ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages