ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 20 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 20

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ሃያ በዚህች እለት #አቡነ_ክፍለ_ማርያም_ዘዲባጋ የተሰወሩበት ነው፣ የእስክንድርያ 21ኛ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ጴጥሮስ አረፈ፣ አዝማሪው #ቅዱስ_ፊልሞን በሰማዕትነት ሞተ፡፡


የካቲት ሃያ በዚህች እለት አቡነ ክፍለ ማርያም ዘዲባጋ የተሰወረበት ነው፡፡ እኚኽም ቅዱስ ትውልዳቸው እንደርታ ሲሆን በ14 ዓመታቸው መንኩሰው መንነው በቅተው ሲኖሩ በአንድ ወቅት ወደ አክሱም ሄዱና ወላጆቻቸው ካሉበት ደረሱ፡፡ ከቅዳሴ በኋላ መበለት ቆርሰው ሲያድሉ ወላጅ እናታቸው ከስተውና ጠቁረው ስላዩአቸው ለእናታቸው አዳልተው በብዙ ሰጧቸው፡፡ እናትየው ግን ጻድቁ የሠሩትን አያውቁም ነበር፡፡
ጻድቁ ከብቃታቸው የተነሳ መና ከሰማይ እየወረደላቸው ከዓለትም ላይ ውኃ እያፈለቁ ይጠጡ ነበር፡፡ አድሎ ስላደረጉ ግን በዚህ ድርጊታቸው እግዚአብሔር ተቆጥቷቸው የሰጣቸውን ይህን ጸጋቸውን ነሳቸው፡፡ አቡነ ክፍለ ማርያምም ይህን ባወቁ ጊዜ ‹‹ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ›› ብለው ከሰው ሳይገናኙ ዋሻ ገብተው ድፍን 11 ዓመት በለቅሶና በዋይታ እግዚአብሔርን ለመኑት፡፡ በኋላም እግዚአብሔር ይቅር እንዳላቸው ነገራቸውና የቀደመ ጸጋቸውና ክብራቸው መለሰላቸው፡፡ ስለ ዘረኝነት አስከፊነትም በብዛት አስተማሩ፡፡
ከዛ በኋላ ውኃ ከደረቅ ጭንጫ ላይ እያፈለቁ አሕዛብን ሁሉ እያስተማሩ ያጠምቁ ጀመር፡፡ ኅብስትም ከሰማይ እየወረደላቸው ሕዝቡን ያቆርቡ ጀመር፡፡ ጻድቁ በመጨረሻ በዚህች ቀን እንደነ ሄኖክና ኤልያስ ዐርገዋል እንጂ በምድር ሞትን አልቀመሱም፡፡ ትልቅና አስደናቂ ገዳማቸው አክሱም ይገኛል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስ አረፈ፡፡ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ አንደኛ ነው። ይህንንም ቅዱስ ከሐዋርያዊ አትናቴዎስ በኋላ በሹመቱ ወንበር በተቀመጠ ጊዜ ከንጉሥ ዳርዮስና ከከሀዲ አርዮስ ወገኖች ብዙ መከራ ደርሶበታል።
ሊገድሉትም በፈለጉ ጊዜ ሸሽቶ ሁለት ዓመት ያህል ተሠወረ አርዮሳውያንም ሉቅዮስ የተባለ ከሀዲውን ሰው በእርሱ ፈንታ በወንበሩ ላይ አስቀምጠው ሁለት ዓመት ኖረ።
ከዚህም በኋላ ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናን ሁሉም ተነሥተው አርዮሳዊ ሉቅዮስን አሳደዱትና ይህን አባት ጴጥሮስን ወደ መንበረ ሢመቱ መለሱት አርዮሳውያንንም በመጣላት እያወገዛቸውና እያሳደዳቸው ሰባት ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም አርፎ ወደ ዘላለም ዕረፍት ሔደ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት መኰንን አርያኖስን የሚያጫውተው አዝማሪው ፊልሞን በሰማዕትነት ሞተ። በአንዲትም ዕለት አርያኖስ አናጉንስጢስ አስቃሎንን ጠርቶ ለአጵሎን ሠዋ አለው አስቃሎንም ወደ ፊልሞን ሒዶ በእኔ ፈንታ ብትሠዋ አራት የወርቅ ዲናር እሰጥሃለሁ አለው ፊልሞንም ልብስህን ስጠኝና ተሸፋፍኜ በአንተ ፈንታ እሠዋለሁ አለው።
በገባም ጊዜ አውቀውት ምን ሆንክ አሉት ፊልሞንም በክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ አላቸው አርያኖስም በሕይወት እንድትኖር ለአማልክት ሰዋ አለው ፊልሞንም በክርስቶስ ስም ከመሞት በቀር ሕይወት የለም አለው።
አርያኖስም ጥምቀትን ሳታገኝ ፈጥኜ እገድልሃለሁ ተስፋህን ታጣለህ አለው ፊልሞንም ሰምቶ የክርስትና ጥምቀትን ያድለው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በዚያንም ጊዜ ከሰማይ ብሩህ ደመና መጥቶ አጠመቀው።
አርያኖስም አፍሮ ቢመለስ ብሎ ሦስት ወታደሮች እንዲጸፉት አዘዘ ፊልሞንም የእግዚአብሔር መላእክት ስለ እኔ ደስ ሲላቸው አያለሁና ከዚህ የከፋ ቢጸፉኝም እኔ አላፍርም አለ። አርያኖስም ባላ ባለው ግንድ ላይ ሰቅለው በፍላፃዎች ይነድፉት ዘንድ አዘዘ ግን ምንም የነካው የለም ፍላፃውም እንዳልነካው ለአርያኖስ ነገሩት ዳግመኛም እርሱ እንደ ቆመ ይነድፉት ዘንድ አዘዘ አንዲቱም ፍላፃ ተመልሳ የአርያኖስን ዐይን ነድፋ ዐሳወረችው በዚያንም ጊዜ ከተሰቀለበት አውርደው ከአናጉንስጢስ አስቃሎን ጋር ራሱን እንዲቆርጡ አዘዘ ገድላቸውንም ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።
መኰንኑም በፍላፃው ሕመም በተሠቃየ ጊዜ ከቅዱሳን ደም ወስዶ ከዐይኑ ውስጥ እንዲጨምር ሰዎች መከሩት ይህንንም ሲያደርግ ዳነ በክብር ባለቤት በጌታችን ክርስቶስም አመነ እስረኞችንም ሁሉ ፈታቸው እርሱም መጋቢት ስምንት ቀን በዲዮቅልጥያኖስ እጅ በሰማዕትነት ሞተ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ትሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages