ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 21 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 21

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ሃያ አንድ በዚህችም ዕለት የከበረ የሐዋርያው የጳውሎስ ደቀ መዝሙር የሆነ #ቅዱስ_አናሲሞስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #አባ_ገብርኤል አረፈ፣ የሀገረ ስሐ ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት #አባ_ዘካርያስ አረፈ።


የካቲት ሃያ አንድ በዚህችም ዕለት የከበረ የሐዋርያው የጳውሎስ ደቀ መዝሙር የሆነ ቅዱስ አናሲሞስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ከሮሜ ሰዎች ወገን ለሚሆን ስሙ ፊልሞና ለሚባል ለሮሜ ሰው አገልጋይ ሆኖ ነበር ይህም ፊሊሞና በሮሜ በአስተማረ ጊዜ በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት በጌታችን አመነ ይህ ፊሊሞናም ከዚያ ከሮሜ አገር ወደ አስባንያ ሔደ።
ይህንንም አገልጋዩን አናሲሞስን ከእርሱ ጋር ወሰደው ሰይጣን ግን አናሲሞስን አሳተው ልቡንም ለወጠውና የጌታውን ገንዘብ ሰረቀ ጌታውም እንደሚቀጣው አውቆ ሸሽቶ ወደ ሮሜ ተመልሶ ሔደና በዚያ ተቀመጠ።
በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደ ከበረ ሐዋርያ ጳውሎስ ሔደ ትምህርቱንም ሰምቶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ለቅዱስ ጳውሎስም ደቀ መዝሙሩ ሆነ። ነገር ግን የጌታውን ገንዘብ በመስረቁ በአናሲሞስ ልብ ጽኑ ሀዘን አደረ ለሐዋርያ ጳውሎስም የሠራውን ሁሉ ነገረው ሐዋርያ ጳውሎስም አትፍራ ልብህም አይዘን አለው ወደ ጌታው ወደ ፊልሞናም መልእክትን ጻፈለት ይቺም ስለ አናሲሞስ የጻፋት ከመልእክቶቹ አንዲቱ ናት።
በመልእክቱም እንዲህ አለ እኔ በእሥራቴ ጊዜ ስለወለድኩት ልጄ እማልድሃለሁ ይኸውም አናሲሞስ ነው። የቀድሞው ሥራው አልጠቀመህም ነበር ዛሬ ግን ላንተም ለኔም እጅግ የሚጠቅም ሁኗል አሁንም ወዳንተ ልኬዋለሁና ልጄ እንድመሆንህ ተቀበለው። የበደለህ በደልም ቢኖር ወይም የሚከፍልህ ቢኖር በኔ ላይ አድርገው።
ይህ የከበረ አናሲሞስም ወደ ፊልሞና ወደ ጌታው በደረሰ ጊዜ በማመኑና በመጸጸቱ ደስ አለው ሐዋርያው እንዳዘዘውም አደረገለት እጅግም ወደደው ብዙ ገንዘብም ሰጠው እርሱ ግን ምንም ምን አልወሰደም እኔ በክርስትና ባለጸጋ ሁኜአለሁ አለ እንጂ።
ከዚህም በኋላ ሸኙትና ወደ ሮሜ አገር ተመለሰ በሰማዕትነት እስከ ሚሞትበት ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን የሚያገለግልው ሆነ። ይህም ቅዱስ ካህን ሆኖ ተሾመ ሐዋርያትም በሥርዓት መጽሐፋቸው በአንቀጽ ሰባ ሰባት ሰማንያ አንድ በኃምሳ ሦስትና በኃምሳ ሰባት በምስጋና አስታውሰውታል እንደ ታማኝ ካህንም ነው አሉ።
ከሐዋርያው ጳውሎስም የምስክርነት ሞት በኋላ የንጉሥ ጭፍራ አለቃ ይህን ቅዱስ ይዞ ወደ አንዲት ደሴት ሰደደው የዚያችን ደሴት ሰዎች ሃይማኖትን እያስተማራቸው ኖረ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው።
ከብዙ ቀኖችም በኋላ የንጉሥ የጭፍራ አለቃ ወደዚያች ደረሰ የከበረ አናሲሞስንም ሕያው ሁኖ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ለሰዎች ሲያስተምር አገኘው ጽኑ ግርፋትንም ገርፈው ጭኖቹን እንዲሰበሩ አዘዘ ምስክርነቱንም ፈጸመ። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አባ ገብርኤል አረፈ፡፡ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ኃምሳ ሰባተኛ ነው። ይህም አባት በታናሽነቱ በአስቄጥስ ገዳም መነኰሰ በጾም በጸሎት በስግደት እየተጋ ፍጹም ተጋድሎን በመጋደል ተጠምዶ ኖረ በውስጡም ትሕትና ፍቅር ቅንነት አለው።
በአንዲትም ዕለት ስሙ መክሲሞስ ወደሚባል አረጋዊ ቤት ገባ እርሱም ልጄ ከሰው ለምን ትሸሻለህ አንተ ግን በወንዶችና በብዙ ሴቶች መካከል ትኖር ዘንድ አለህ አለው እርሱ ግን የሽማግሌውን የቃሉን ትርጓሜ አላስተዋለም ከጠላትም ወጥመድ ያድነው ዘንድ ሁል ጊዜ በማልቀስ እግዚአብሔርን የሚለምን ሆነ።
ከእርሱም አስቀድሞ የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል በአረፈ ጊዜ ይህን አባት ይዘው ያለ ውዴታው ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት አረጋዊ አባ መክሲሞስ ትንቢት እንደ ተናገረለት በተሾመም ጊዜ በአስቄጥስ ገዳም ተቀምጦ የቀድሞውን ተጋድሎውንና አገልግሎቱን ቸለል አላለም።
ስለ አብያተ ክርስቲያንም ጉዳይ ወደ እስክንድርያ ወደ ምስር ይሔድ ዘንድ ግድ በአሉት ጊዜ ይሔዳል ፈጥኖም ወደ አስቄጥስ ገዳም ይመለሳል።
እርሱም በዕድሜው ጐልማሳ ስለሆነ እንስሳዊት ፍትወት ትነሣሣበት ነበር እርሱም ያጠፋት ዘንድ ለጾም ለጸሎት ለስግደትም መትጋትን ያበዛል ሊያበርዳትም ባልተቻለው ጊዜ ለአንድ አረጋዊ ተናዘዘለት እርሱም እንዲህ አለው፦ ይህች እንስሳዊት ፍትወት ከጾምና ከጸሎት ከስግደት ጋር ያለ ትሕትና ሥራ አትጠፋም በበለጠ ግን ትሕትና መድኃኒቷ ነውና።
ይህንንም በሰማ ጊዜ የጉድፍ መጐተቻ ከብረት ሠራ አጭር የሆነ የቆሸሸ ልብስ በመልበስ በሌሊት ተነሥቶ የመነኰሳቱን መንደር እይዞረ ቆሻሻውን ጠርጎ ተሸክሞ ወስዶ ከራቀ ቦታ ይጥለዋል። ይህንንም ሥራ እይሠራ ሁለት ዓመት ያህል ኖረ እግዚአብሔርም ንጽሕናውንና የልቡን ትሑትነት ተመልክቶ የባሕርይ የሆነውን ፍትወት አራቀለት።
ይህም አባት በገድል እንደተጠመደ ሁኖ መንጋዎቹ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ እያስተማራቸውና እየገሠጻቸው እየመከራቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የሀገረ ስሐ ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት አባ ዘካርያስ አረፈ። ይህም አባት የጸሐፊዎች ወገን ነው አባቱ ግን ጸሐፊነቱን ትቶ ቅስና ተሾመ ስሙም ዮሐንስ ነው።
ልጁ ዘካርያስም በአደገ ጊዜ ትምህርቶችን ሁሉ ጽሕፈትንም የጽርእና የሮማውያንን ጥበብ የቤተ ክርስቲያንንም ሕግ ተማረ የንጉሥም የጭፍራ አለቃ ወሰደውና በንጉሡ ቤት ጸሐፊነት ሾመው። በጽሕፈቱም የሀገረ ስሐ መኰንን የሆነው ስሙ አብጥልማዎስ የሚባል ወዳጅ ሆነው እነርሱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ሒደው ይመነኵሱ ዘንድ ተስማሙ።
በዚያንም ጊዜ በአስቄጥስ ገዳም ከአባ ዮሐንስ ደብር አንድ መነኰስ ወደነርሱ መጣ አብረውትም ይሔዱ ዘንድ ተስማሙ መኳንንቶችም ይህን በሰሙ ጊዜ መሔድን ከለከሉዋቸው።
ከጥቂት ቀኖች በኋላም ለእግዚአብሔር የተሳላችሁትን ስለት ለምን አትፈጽሙም የሚላቸውን ራእይ አዩ በዚያንም ጊዜ በሥውር ወጡ እነርሱ ግን መንገዱን አያውቁትም ነበር አንድ መነኰስም ተገለጠላቸውና ወደ አስቄጥስ ወደ አባ ዮሐንስ ገዳም መርቶ አደረሳቸው፡፡መኳንንቱም መሔዳቸውን በሰሙ ጊዜ ከንጉሥ ዘንድ ደብዳቤ ተቀብለው በመላክ ከገዳም ሊአስወጡአቸው ተስማሙ የክብር ባለቤት ጌታችንም ምክራቸውን በተነ።
በመነኰሱም ጊዜ በብዙ ተጋድሎ ተጠመዱ ይልቁንም አባ ዘካርያስ በዚያም ወራት አረጋውያን አባ አብርሃምና አባ ገዐርጊ ነበሩ ወደ እርሳቸው እየመጡ በሥራቸው ሁሉ ያረጋጉዋቸውና ያጸኑዋቸው ነበር።
የሀገረ ስሐ ኤጲስቆጶስም በአረፈ ጊዜ ሕዝቡ አባ ዘካርያስን አሰቡት እርሱንም ይሾምላቸው ዘንድ ስለ አባ ዘካርያስ እየለመኑ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ የመልእክት ደብዳቤ ጻፉ። ሊቀ ጳጳሳቱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ልኮ አባ ዘካርያስን ወደ እርሱ አስመጣው በሀገረ ስሐ ላይም ኤጲስቆጶስነት ሾመው ሊቀ ጳጳሳቱም እጁን በላዩ በጫነ ጊዜ የእግዚአብሔርን ኃይል አየ በላዩ ወርዷልና ፊቱም በብርሃን ተጋረደ።
ወደ መንበረ ሢመቱም በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ በታላቅ ደስታ ተቀበሉት በዕለተ ሆሣዕና የእስራኤል ሕዝብ መድኃኒታችንን እንደተቀበሉት። ከዚህም በኋላ በትምህርቱና በድርሰቶቹ ቤተ ክርስቲያን ብርሃን ሆነች ቃሉም እጅግ ጣዕም ያለው እርሱም የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የተመላ ነው። በመንበረ ሢመቱም አርባ ዘመን ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ትሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages