ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 20 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 20

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ሃያ በዚህች ዕለት ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የከበረ #ሐዋርያ_አብሮኮሮስ አረፈ፣ የከበረ #ቀሲስ_አክሎግ በሰማዕትነት ሞተ፣ #አባ_ዮሐንስ_ወንጌሉ_ዘወርቅ ሥጋው ወደ ሮሜ አገር የፈለሰበት እና ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው፣ የታላቁ ሰማዕት #የቅዱስ_መርምሕናም ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበትና ተአምራቱ የተገለጠበት ዕለት ነው፡፡


ጥር ሃያ በዚህች ዕለት ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ በሽተኞችንም ይፈውሱ ዘንድ ጌታችን መርጦ ከላካቸው ከሰብዓ ሁለቱ አርድእት አንዱ የከበረ ሐዋርያ አብሮኮሮስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ በጽርሐ ጽዮን ከሐዋርያት ጋር ሁኖ ሳለ የአጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተሞላ። እርሱንም ሐዋርያት መርጠውት ከሰባቱ ዲያቆናት ጋር የተቆጠረ ሆነ እነርሱ መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው ዕውቀትም ያላቸው እንደሆኑ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስለርሳቸው ምስክር ሆነ።
ከዚህም በኋላ ለወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙሩ ሆነ ከእርሱም ጋር ወደ ብዙ አገሮች ሔደ በቢታንያ አገር በኒቆምድያ ከተማ ላይ በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሾመው። እርሱም የክብር ባለቤት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት አስተማረ ከዮናናውያንም ብዙዎችን መልሶ ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው የወንጌልንም ትእዛዞች እንዲጠብቁ አስተማራቸው ቤተ ክርስቲያንንም ሠርቶ ቀሳውስትን ዲያቆናትን ሾመላቸው።
ከዚህም በኋላ ያቺን አገር ወደሚከቧት አገሮች ወጣ በውስጣቸውም የከበረ ወንጌልን ሰበከ ብዙዎችንም ከስሕተት መለሳቸው አይሁድንም የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ነገር ግን ብዙ መከራና ስደት ደርሶበታል ስለ ክርስቶስ ስም ተጋድሎውንም ሲፈጽም ጌታችንንም አገልግሎ በመልካም ሽምግልና አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን በግብጽ አገር እልፈንት ከሚባል ከተማ የከበረ ቀሲስ አክሎግ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ዲዮስቆርስ የናቱ ስም አፎምያ ነው እነርሱም ከከበሩ ወገኖች ውስጥ ናቸው በወርቅ በብር በላሞችና በበጎች በፈረሶችና በግመሎች እጅግ የበለጸጉ ናቸው ነገር ግን ልጅ የላቸውም ስለዚህም ያዝኑ ነበር። ልጅንም ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ሲለምኑ ኖሩ ልመናቸውንም ተቀብሎ ይህን የተባረከ ልጅ ሰጣቸው ስሙንም አክሎግ ብለው ጠሩት ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ጣዕም ያለው ይሆናል ማለት ነው።
ስምንት ዓመትም በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕግ ይማር ዘንድ ለመምህር ሰጡት የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ሁሉ ተማረ ሁል ጊዜም ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ምስጋናዎችንና ጸሎቶችን ይሰማል ይህንንም የሚያደርግ ወደ መምህር ከመሔዱ አስቀድም ነው።
በአንዲትም ዕለት ከመምህሩ ዘንድ ወጣ ወደ ቤቱም ሊሔድ በፈረስ ተቀምጦ ሁለት አገልጋዮችም ተከትለውት ሲጓዙ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ተሰብስበው ሲጮሁ አያቸው የሆነውንም ሊያይ ወደ ርሳቸው ቀረበ። እባብ የነከሰውና ለሞትም የቀረበ አንድ ሕፃን በመካከላቸው ወድቆ አገኘ። የከበረ አክሎግም ይቺ ምልክት በስሜ የሚያምኑትን ትከተላቸዋለች በስሜም አጋንትን ያስወጣሉ አዳዲስ ቋንቋን ይናገራሉ የምድር አራዊቶችን በእጃቸው ይይዛሉ የሚጐዳቸውም ነገር የለም ያለውን የከበረ የወንጌልን ቃል አሰበ።
በዚያንም ጊዜ የሕፃኑን እጅ ይዞ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ብሎ በላዩ በመስቀል ምልክት አማተበና ሕፃን ሆይ ከዚህ ክፉ እባብ መርዝ ትድን ዘንድ እናገርሃለሁ ጌታችን ንጹሕና እውነት በሆነ ቃሉ እባቡን ጊንጡን የጠላትን ኃይል ሁሉ ትረግጡ ዘንድ እነሆ ሥልጣን ሰጠኋችሁ ምንም የሚጎዳችሁ ነገር የለም ብሏልና አለ ወዲያውኑ ያ ልጅ ዳነ ከክፉ ነገርም ምንም ምን እንዳልደረሰበት ሆነ።
ሕዝቡም ይህን ተአምር በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ በቅዱሳኑ አድሮ ድንቅ ሥራ የሚሠራ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት የዚችም ተአምር ወሬዋ በሀገሩ ሁሉ ተሰማ። ከመምህሩም ዘንድ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ አራቱን ወንጌሎች፣ የሐዋርያትን ሥራ፣ ዐስራ አራቱን የጳውሎስን መልእክቶች፣ ሰባቱን የሐዋርያት መልእክታት፣ የዮሐንስንም ራእይ፣ መቶ ሃምሳውን የዳዊት መዝሙራት፣ የነቢያትንና የሰሎሞንን መኅልይ ጠንቅቆ አጠና። ሁል ጊዜ በቀንና በሌሊት ያነባል በእሑድ ሌሊትም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያገለገለ ያድራል ሁል ጊዜም አዘውትሮ ይጾማል ይጸልያል።
ወላጆቹም ከአረፉ በኋላ ሰዎች መልካም ተጋድሎውን በአዩ ጊዜ ስለ እነርሱ ይጸልይ ዘንድ ቅስና እንዲሾምላቸው ኤጲስቆጶሱን ለመኑት እርሱ በዘመኑ ሁሉ በየሁለት ቀን በየሦስት ቀን በየሱባዔው ይጾማልና በልብሱም ውስጥ ማቅ ይለብሳልና። ቅስና ይሾም ዘንድ የእግዚአብሔር ጸጋ ጠራችውና ኤጲስቆጶሱም ወስዶ ሳይወድ በግድ ቅስና ሾመው በተሾመ ጊዜም ለአባ አክሎግ የክህነት ሹመት ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል እያለ ሲጮህ ሕዝቡ ቃልን ሰሙ ኤጲስቆጶሱና ሕዝቡም እጅግ አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
ከእነዚያ ወራቶችም በኋላ በሀገሩ ሁሉ በክርስቲያን ወገኖች ላይ ከከሀዲዉ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ ታልቅ መከራና ስደት ሆነ አብያተ ክርስቲያናትንም አፈረሰ ብዙዎችም በሰማዕትነት ሞቱ።
ምስክርም ይሆን ዘንድ አባ አክሎግን እግዚአብሔር ጠራው እርሱም ቆመ ወደሰማይም ቀና በማለት እንዲህ ብሎ ጸለየ ዓለሙን ሁሉ የያዝክ ጌታዬ ፈጣሪዬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በሀገርህ በሁለመናዋ ላሉ ሕዝብ ቸርነትህን ይቅርታህንና ሰላምህን አድርግ። ትባርካቸውም ዘንድ ከሰይጣናትም ስሕተት ታድናቸው ዘንድ ለእኔም ስለ ከበረው ስምህ ተጋድሎዬን እስከምፈጽም ያጸናኝ ዘንድ ቸር መልአክህን እንድትልክልኝ እለምንሃለሁ ኃይል ክብር ገንዘብህ የሆነ ለዘላለሙ አሜን።
ከዚህም በኋላ በዙሪያው ወዳሉ ሰዎች ተመልሶ የሚሻ ይምጣ ከእኔ ጋር ይሒድ አለ የእርሱ ሰዎችና የሀገሩ ሰዎች ሦስት መቶ አርባ ተከተሉት በከፍታ ቦታ ላይም ቁመው እኛ በግልጥ ክርስቲያን ነን ብለው ጮኹ። የንጉሡም የሠራዊት አለቃ ሰምቶ አዘነ አባ አክሎግንም አሥሮ ለመኰንኑ ለአርያኖስ ሰጠው እርሱም ለአማልክት ስገድ አለው አባ አክሎግም ለክብር ባለቤት ለጌታዬና ለፈጣሪዬ ለኢየሱስ ክርስቶስ እሰግዳለሁ እንጂ እኔ ለረከሱ አማልክት አልሰግድም አለ።
ቢዚያንም ጊዜ መኰንኑ አርያኖስ ተቆጣ አባ አክሎግንም ጽኑ ሥቃይን አሠቃይቶ ከእሳት ማንደጃ ውስጥ ጨመረው ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ወርዶ እሳቱን እንደ ጠል ቀዝቃዛ አደረገው አባ አክሎግም በእቶኑ መካከል ቁሞ ጸለየ።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ አርያኖስ ሦስት መቶ አርባውን ሰዎች እናንተ ኑ ለአማልክት ስገዱ አላቸው እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱለት። እኛስ ከእግዚአብሔር በቀር ለረከሱ አማልክት አንሰግድም አሉት ራሶቻቸውንም በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘና ቆረጧቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።
በዚያንም ጊዜ የመኰንኑ የአርያኖስ ልጁ ሞተበትና እጅግ አዘነ የከበረ አባ አክሎግም በአንተ ላይ በጎ ሥራ ብሠራ ፈጣሪዬ እግዚአብሔርን ብለምነው ልጅህን ቢያስነሣልህ ምን ትሰጠኛለህ አለው አርያኖስም የመቶ አለቃ አድርጌ ሹሜ በታላቅ ክብር ወደ ሀገርህ እልክሃሁ አለው።
የከበረ አክሎግም ይህን አልሻም ነገር ግን እንድታሠቃየኝና እንድትገድለኝ ሥጋዬንም ወደ ሀገሬ እንድትልክ ማልልኝ አለው እርሱም ማለለት። በዚያንም ጊዜ የከበረ አክሎግ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ለመነ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ ዛሬ ይህን የሞተውን ሕፃን ታስነሣው ዘንድ የከበረ ስምህም ይመሰገን ዘንድ እለምንሃለሁ ምስጋና ክብር ያንተ ነውና ለዘላለሙ አሜን።
ይህንንም ሲል በመስቀል ምልክት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በሕፃኑ ላይ አማተበ ወዲያውኑ ሕፃኑ ተነሣ አሕዛብም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው ሁሉም በአንድ ቃል በቅዱስ አክሎግ አምላክ እናምናለን ብለው ጮኹ።
መኰንኑም ተቆጣ ከከተማም እንዲአወጧቸውና ሰፊ ጒድጓድ ቆፍረው እሳትንም አንድደው በውስጡ እንዲጨምሩዋቸው አዘዘ እንዲሁም አደረጉባቸውና ምስክርነታቸውን ፈጸሙ ቊጥራቸውም ስምንት መቶ ዘጠኝ ሆነ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ከዚህም በኋላ አባ አክሎግን ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃይተው ወደ ሀገሩ ወስደው በዚያ በሰይፍ ራሱን ይቆርጡ ዘንድ አርያኖስ አዘዘ አባ አክሎግም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው እንዲህ እያለ ቁሞ ጸለየ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እኔ ባሪያህ እለምንሃለሁ ቸርነትህን በሀገሬ ላይ በውስጧም በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ ታደርግ ዘንድ የእጃቸውንም ሥራ ባርክ ሴቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውን፣ እንስሶቻቸውን፣ እርሻዎቻቸውንም ባርክ ከመከራም ሁሉ አድናቸው ለሥጋዬም ጸጋህን ስጠው የታመመ ሁሉ ሥጋዬ ወዳለበት መጥቶ የከበረ ስምህን ጠርቶ ወዳንተ በሚጸልይ ጊዜ ከደዌው ይዳን።
የተጋድሎዬን መጽሐፍ የሚጽፈውን ሁሉ መታሰቢያዬንም ለሚያደርግ ለቊርባንም ሥንዴን የሚሰጥ ወይም ዕጣንን ወይም ዘይትን ወይም ወይንን ለሚሰጥ ለሁሉም በመንግሥተ ሰማያት ዋጋቸውን ስጣቸው ስሞቻቸውንም በሕይወት መጽሐፍ ጻፍላቸው ሥጋዬንም በንጹሕ ልብስ የሚገንዘውን ነፍሱን የብርሃን ልብስን ሸፍናት ለአንተም ምስጋና ክብር ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
አባ አክሎግም ይህን በአለ ጊዜ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጸለትና እንዲህ አለው። ወዳጄ የምወድህ የአባቴና የመንፈስ ቅዱስ ወዳጅ ሰላም ላንተ ይሁን ዋጋህን ልሰጥህ በመንግሥቴም ውስጥ ላሳርፍህ መጣሁ ሦስት አክሊላትንም አዘጋጀሁልህ አንዱ ስለ ድንግልናህ ሁለተኛው ስለ ሥቃይህ ሦስተኛው የዚህን ዓለም ክብር ንቀህ ስለተውህ ነው።
በዚች ቀን ከእኔ የምትሻውን ሁሉ አደርግልሃለሁ ስለ ስሜ ስለአሠቃዩህ የማያልቅ ተድላን እሰጥሃለሁ የመላእክት ሠራዊትም እንዲአገለግሉህ አደርጋለሁ ዘላለማዊ ሕይወት ባለው በማዕዴ ውስጥም ከሁሉ ቅዱሳን ጋር ደስ ይልሃል። የመረጥኩህ አክሎግ ሆይ አንተን እነግርሃለሁ ሥጋህ ባለበት የሚማልደውን ሁሉ ርዳታ የሚሻውንም በችግር ውስጥም ወይም በደዌ ውስጥ በኀዘንም ላይ ሁሉንም እኔ አድናቸዋለሁ ልጁንም በስምህ የሚሰይመውን ሁሉ እኔ እባርከዋለሁ በበጎ አስተዳደግም አሳድገዋለሁ ከክፉ ነገር ሁሉ እጠብቀዋለሁ በስምህም መባ የሚአገባና ለችግረኞችም እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ምጽዋት የሚሰጠውን እኔ ለሁሉም ኃጢአቱን ይቅር ብዬ የዘላለም ሕይወትን አወርሰዋለሁ ተክል ተክሎ ዘር ዘርቶ በስምህ የሚለምነኝም እባርክለታለሁ ፍሬውንም አበዛለታለሁ።
ከአባ አክሎግ ጋር መነጋገርን ጌታችን ሲፈጽም ባረከው ሥጋውንም ጤነኛ አደረገውና ሳመው አባ አክሎግም እየተመለከተ በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ ወጣ። ከዚህም በኋላ የከበረ አባ አክሎግ ወደ ወታደሮች መለስ ብሎ የታዘዛችሁትን ፈጽሙ አላቸው ወታደሮችም ፊቱ እንደ ፀሐይ እጅግ ሲያበራ በአዩት ጊዜ ከፊቱ ብርሃን ግርማ ገናናነት የተነሣ ወደርሱ መቅረብ ፈሩ ከእርሳቸውም ርኅራኄ የጎደለው ልቡ የደነደነ አንድ ሰው እጁን ዘርግቶ አንገቱን በሰይፍ መታውና በዚች ቀን ተጋድሎውን ፈጸመ መላእክትም ነፍሱን ተቀበሏት በፊቷም እየዘመሩ ወደሰማይ አሳረጓት።
ወታደሮችም የአባ አክሎግን ሥጋ ከባሕሩ ዳር ትተው በመርከብ ተሳፍረው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ ከዚያም ጐልማሶች ነበሩ ስለ ከበረ አባ አክሎግ በሰማዕትነት መሞት ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ለሕዝቡ ነገሩዋቸው።ሕዝቡም በሰሙ ጊዜ ተሰብስበው ከካህናቱ ጋር ሔዱ አንሥተውም በክብር ገነዙት ተሸክመውም ወደ ሀገር ውስጥ አድርሰው በአማረ ቦታ አኖሩት ከእርሱም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች እለት የከበረ አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ሥጋው ወደ ሮሜ አገር የፈለሰበት እና ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው፡፡ ይህም ቅዱስ ከሮሜ አገር ነበር አባቱም አጥራብዮስ የሚባል ባለጠጋ ነው።የእናቱም ስም ብዱራ ይባላል። እንዲማርም ለመምህር ሰጡት ቅዱሳት መጻሕፍትንም ተማረ።
ከዚህም በኃላ ገበታው የወርቅ የሆነ ወንጌልን ያሠራለት ዘንድ አባቱን ለመነው አባቱም እንደፈለገው አሠራለት ሁል ጊዜም ያነበው ነበር።በሚያነብ ጊዜም አባቱና እናቱ ደስ ይላቸው ነበር።
በዚያም ወራት ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዝ መነኩሴ ወደ እነርሱ መጣ በእነርሱም ዘንድ አደረ ከቅዱስ ዮሐንስም ጋራ ተነጋግሮ የምንኩስናን ሥራ አመሰገነለት ይህን ዓለም እስከ ናቀና እንደ እርሱ መነኰስ ይሆን ዘንድ እስከ ወደደ ድረስ ልቡን ማረከው።
ያን ጊዜም ያ መነኰስ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ ሁለተኛም ተመልሶ እንደ ልማዱ በእነርሱ ዘንድ አደረ።ቅዱስ ዮሐንስም መነኰሴው ወደ ገዳሙ ይወስደው ዘንድ ፈለገ መነኰሴውም አባትህን እፈራዋለሁ ልወስድህ አይቻለኝም አለው።ቅዱስ ዮሐንስም ከእርሱ ጋራ እንዲወስደውና ነፍሱን እንዲያድን አማለው።
ከዚህም በኃላ በስውር ወሰደው በመርከብም ተጭነው ያ መነኮስ ወደሚኖርበት ገደም ደረሱ የገዳሙም አበ ምኔት የወጣቱን ዮሐንስን መልኩን አይቶ አደነቀ።ቅዱስ ዮሐንስም የምንኩስናን ልብስ ያለበሰው ዘንድ አበ ምኔቱን ለመነው አበ ምኔቱም ልጄ ሆይ የምንኵስና ሕግ እጅግ ጭንቅ ናት እኮ አለው።አብዝቶም በለመነውና ግድ ባለው ጊዜ ራሱን ላጭቶ አመነኰሰው።
ከዚህም በኃላ ከጾም ከትጋትና ከኀዘን የተነሣ ሥጋው ደርቆ አጥንቶቹ እስከ ሚታዩ ድረስ በብዙ ተጋድሎ ተጸመደ።አበ ምኔቱም ልጄ ሆይ ለሰውነትህ እዘን ድካምህንም ቀንስ መነኰሳቱም ሁሉ እንደሚሠሩት ሥራ እያለ ያጽናናውና ይመክረው ነበር።
በዚህ ተጋድለም ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜ ከእነርሱ በረከትን ትቀበል ዘንድ ከመሞትህ በፊት ወደ አባትህና እናትህ ሒድ የሚል ራእይ አየ።ይህንንም ራእይ በሦስት ሌሊቶች ውስጥ አየ ለአበምኔቱም እንዴት እንዳየ ነገረው አበምኔቱም ይህ ራእይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ሆነ ልትሔድ ይገባሃል አለው።ከገዳሙም በወጣ ጊዜ አንድ ምስኪን ሰው ጨርቅ ለብሶ አገኘ።የእርሱንም ልብስ ሰጥቶት ጨርቁን ወሰደ።
ወደ አባቱ ቤትም በደረሰ ጊዜ በትንሽ ጎጆ ውስጥ በአባቱ ደጅ በጾም በጸሎትና በስግደት እየተጋደለ ባሮች ከአባቱ ማዕድ የሚጥሉለትን ፍርፋሪ እየተመገበ ሰባት ዓመት ኖረ።እናቱም በአንጻሩ ስታልፍ የሚከረፋ ሽታው ያስጨንቃት ነበር።ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰባት ቀን በኃላ ከዚህ ዓለም ትወጣለህ ብሎ ነገረው።
ያን ጊዜም ወደ እናቱ ልኮ ልምናውን ልትሰማ ወደ እርሱ መጣች ልጅዋም እንደሆነ ፈጥኖ አልነገራትም ነገር ግን በዚያች በታናሽ ማደሪያ ውስጥ በላዩ ባለ ጨርቅ እንድትቀብረው የለበሰውንም ጨርቅ እንዳትለውጥ አማላት።ከዚህም በኃላ ያንን የወርቅ ወንጌል ሰጣት።እንዲህም አላት ይህን መጽሐፍ አንብቡ እኔንም አስቡኝ።
አባቱም በመጣ ገዜ ያንን የወርቅ ወንጌል አሳየችው እርሱም ለልጁ ያሠራለት ወንጌል እንደሆነ አወቀ።አባቱና እናቱም ወደ እርሱ ሔደው ስለ ልጃቸው ጠየቁት እርሱም ከዚህ ጨርቅና ከዚህ ትንሽ ማደሪያዬ ውስጥ በቀር በሌላ እንዳትቀብሩኝ ማሉልኝ አላቸው።
በአማላቸውም ጊዜ እርሱ ልጃቸው እንደሆነ ነገራቸው ያን ጊዜም ጮኹ መሪር ልቅሶንም አለቀሱ የሮሜ ከተማ ሽማግሌዎችና ሕዝቡ ሁሉ ተሰበሰቡ ሰባቱ ቀንም ሲፈጸም ቅዱስ ዮሐንስ አረፈ።
እናቱም መሐላዋን ረስታ አስቀድማ ለሠርጉ ያዘጋጀቻቸውን ያማሩ ልብሶች አውጥታ ገነዘችው።በዚያችም ጊዜ ታመመች አባቱ ግን መሐላውን አስታውሶ እነዚያን ያማሩ ልብሶች አስወገደ በጨርቆቹም ገነዙት በዚያ በትንሹ ማድሪያም ውስጥ ቀበሩት ከሥጋውም በሽተኞች የሚፈወሱበት ታላቅ ድኅነት ተገኘ።
ከዚህም በኃላ በስሙ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ሥጋውን በውስጧ አኖሩ። ከእርሱም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የታላቁ ሰማዕት የቅዱስ መርምሕናም ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበትና ተአምራቱ የተገለጠበት ዕለት ነው፡፡ ቅድስት ሣራና ወንድሟ መርምህናም አባታቸው የአቶር ንጉሥ ሲሆን እርሱም የተቀረጹ ጣዖታን ያመልክ ነበር፡፡ እናታቸው ግን አማኝ ክርስቲያን ነበረች፡፡ ቅዱስ መርምህናም አባቱን ለምኖና አስፈቅዶ ወደ ዱር ሄዶ አራዊትን ለማደን በወጣ ጊዜ እናቱ የሰማይና የምድር አምላክ እግዚአብሔር በላዩ በረከትን ያሳድርበት ዘንድ ከጸለየችለት በኋላ ሸኘችው፡፡ መርምህናም ከ40 ፈረሰኛ አገልጋዮቹ ጋር ወጥቶ ሄደ፡፡ ወደ አንድ ተራራም ወጥቶ በዚያ አደረ፡፡ በሌሊትም የታዘዘ መልአክ ጠራውና ‹‹መርምህናም ሆይ ተነሥተህ ወደዚህ ተራራ ጫፍ ላይ ውጣ፣ ስሙ ማቴዎስ የሚባል ቅዱስ ሰው ታገኛለህ፡፡ እርሱም የሕይወትን ነገር ይነግርሃል›› አለው፡፡ ቅዱስ መርምህናም ሲነጋ ወደ ተራራው ጫፍ ላይ ወጣና የበግ ጠጉር ለብሶ አባ ማቴዎስን ባገኘው ጊዜ እጅግ ፈራ፡፡ አባ ማቴዎስም ‹‹አይዞህ አትራ እኔም የእግዚአብሔር ፍጥረት ነኝና አትፍራ›› ብለው አበረቱት፡፡ መርምህናም የእግዚአብሔርን ስም ሲጠሩ ሲሰማ ‹‹አባቴ ከአማልክቶች በቀር አምላክ አለን?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን የሃይማኖትን ነገር ሁሉንም አስተማሩት፡፡ መርምህናምም ‹‹ከራስ ጠጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ በለምጽ የተመታች እኅት አለችኝና እርሷን የአምላክህን ስም ጠርተህ ካዳንክልኝ በእውነት በአምላክህ አምናለሁ›› አላቸው፡፡ ሁለቱም ተያይዘው ከተራራው ወርደው ወደ ንጉሡ ቤት ሄደው መርምህናም ለእናቱ ያጋጠመውን ነገር ነገራትና በለምጽ የተመታችውን እኅቱን ሣራን በሥውር ወደ አባ ማቴዎስ ዘንድ ወሰዳት፡፡ አባታችንም መሬቱን ባርከው ውኃ አፍልቀው አጠመቋትና ከለምጹዋ ፈወሷት፡፡ አርባው ጭፍራዎችም አምነው ተጠመቁ፡፡ አባታችንም ሰማዕትነትን እንደሚቀበሉ ትንቢት ነግረዋቸው ባርከው መርቀው አሰናበቷቸው፡፡
መርምህናምም ወደ አባቱ ቤት በተለመሰ ጊዜ ጣዖቱ ቤት መግባትን እምቢ አለ፡፡ ከዚህም በኋላ አርባውን ጭፍራዎችና እኅቱን ሣራን ይዞ ወደ አንዲት ተራራ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፡፡ የአቶሩን ንጉሥ የሆነው አባቱ ‹‹ና መንግሥቴን ውረስ›› ብሎ ለቅዱስ መርምህናም ላከበት፡፡ ነገር ግን ቅዱስ መርምህናም ‹‹የጌታዬን ፈጽሞ የማይጠፋውን መንግሥት እሻለሁ›› ብሎ ለንጉሥ አባቱ ላከበት፡፡ ንጉሡም በቅድሚያ 40ውን አገልጋዮቹን ጭፍራዎች እንዲገድሏቸው አዘዘና ራስ ራሶቻቸውን እየቆረጡ ከጉድጓድ ውስጥ ጨመሯቸው፡፡ መርምህናምም ሲጸልይ ከሰማይ ‹‹መርምህናም ሆይ! ጸሎትህን ሰምቻለሁ…›› የሚል ድምፅ መጣለት፡፡ ወዲያውም በንጉሡ ወላጅ አባታቸው ትእዛዝ ቅዱስ መርምህናምና እኅቱ ቅድስት ሣራ አንገታቸውን ተሰየፉና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጁ፡፡ ሥጋቸውንም በጉድጓድ ጨምረው ሊያቃጥሏቸው ሲሉ ሥጋቸውን እግዚአብሔር ሰወረባቸው፡፡ ወዲያውም ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ፣ ፀሐይም ጨለመች፡፡ የሰየፏቸውም ፈርተው ሸሹ፡፡ ከዚህም በኋላ ሰይጣን በአባታቸው በአቶሩ ንጉሥ ላይ አድሮበት አሳበደው፡፡ እንደ እሪያም መጮህ ጀመረ፡፡ ክርስቲያን የሆነችው የቅዱስ መርምህናምና የቅደስት ሣራ እናታቸው ወደ አባ ማቴዎስ ሄዳ ንጉሡ በልጆቹ ላይ ያደረገውንና በእርሱም ላይ የተፈጸመበትን ነገር ነገረቻቸው፡፡ አባ ማቴዎስም ንጉሡን ዘይት ቀብተው ጸልየው ፈወሱት፡፡ በውስጡ አድሮበት የነበረውንም ሰይጣን በእሪያ መልክ ከንጉሡ ውስጥ አስወጡት፡፡
ንጉሡም ወደ ልቡ ሲመለስ በአባ ማቴዎስ ትምህርት በጌታችን አመነ፡፡ በሚገዛቸው አገሮች ሁሉ ያሉትን ሰዎች ይዞ ከነቤተሰቡ ተጠመቀ፡፡ ንጉሡም በእመቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያን አሠራ፡፡ ንግሥቲቱ ሚስቱም የሰማዕታቱን ልጆቿን ሥጋ በሳጥን አድርጋ በውስጧ አኖረች፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ ተአምራት ተገለጡ፡፡ አባታቸው የአቶሩ ንጉሥም ለችግረኞችና ለጦም አዳሪዎች እየመጸወተ በተጋድሎ ኖረ፡፡ የቅዱስ መርምህናምና የእኅቱ የቅድስት ሣራ እረፍታቸው ታኅሣሥ 14 ቀን ነው፡፡
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የቅዱስ መርምህናም አባት ንጉሡ አቶርና የመርምህናም ማኅበርተኞች የሆኑ ቁጥራቸው 170 ሺህ የሆኑ ሰማዕታት የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ይህም የአቶሩ ንጉሥ ሰማክሬም ከሞተ በኋላ መንግሥቱን መጠበቅና ማዘዝ የማይችል ታናሽ ብላቴና ልጅ በአባቱ ፋንታ ነገሠ፡፡ እናቱም ስለ እርሱ ሹሞቹን ታዛቸው ነበር፡፡ ከለዳዊ ንጉሥም ይህን ሲሰማ የአቶርን መንግሥት ለመውሰድ መጣ፡፡ የንጉሡም ወታደሮችና የቅዱስ መርምህናምን መቃብር ይጠብቁ የነበሩ ሁሉ ለመዋጋት መጡ፡፡ የከለዳውያንም ንጉሥ አሸንፎ ከተማይቱን ወረራትና ብላቴናውን ንጉሥ ከእናቱ ጋር ገደላቸው፡፡ የአቶርም ሰዎች ተገዙለትና በላያቸው ነግሦ መንግሥትን ያዘ፡፡ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ የአቶርን ሰዎች ሰብስቦ ስለ ሃይማኖታቸው ጠየቃቸው፡፡ ሕዝቡም በቅዱስ መርምህናም አምላክ አምነው በአባ ማቴዎስ ጥምቀት ክርስቲያን መሆናቸውን በነገሩት ጊዜ ለጣዖት እንዲሰግዱ አዘዛቸው፡፡ እሺ ብለው ለጣዖት የሰገዱ አሉ፡፡ የቅዱስ መርምህናምና የአባቱ አግልጋዮች ግን ንጉሡን ‹‹በሰውነታችን ላይ የፈለከውን አድርግ እንጂ ሃይማኖታችንን አንክድም›› አሉት፡፡ ነገሡም ቁጥራቸው 170 ሺህ የሆኑ ክርስቲያኖችን በሰይፍ ፈጃቸውና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጁ፡፡ እነርሱም የቅዱስ መርምህናም ማኅበርተኞች ተባሉ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages