አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር ሀያ አንድ በዚች ቀን ለእመቤታችን ለከበረች #ድንግል_ማርያም የእረፍቷ መታሰቢያ ነው፣ የከበረች #ቅድስት_ኢላርያ አረፈች፣ የባስልዮስ ወንድም የከበረ #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ የእረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ የካህኑ ኬልቅዩ ልጅ ታላቁ #ነቢይ_ኤርምያስ መታሰቢያው ነው።
ጥር ሀያ አንድ በዚች ቀን አምላክን ለወለድች ለእመቤታችን ለከበረች ድንግል ማርያም የእረፍቷ በአል መታሰቢያ ነው።ያን ጊዜ እመቤታችን በልጅዋ በጌታችን በፈጣሪያችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ መቃበሩ ቦታ ትፀልይ ነበረ ከዚህም አለም እንደምትለይ መንፈስ ቅዱስ ነገራት ከዚህም በኃላ ከደብረ ዘይት ደናግል መጡ ጌታችን ነግሮዋቸዋልና እርሷም ነገረቻቸው።
በዚያንም ጊዜ እመቤታችን እንዲህ ብላ ፀለየች፦ "ልጄ ወዳጄ ጌታዬና ፈጣሩዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናዬን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሀንስን በዚች ሰአት አምጣው።እንዲሁም ህያዋን እንደሆኑ ሀዋርያትን ሁሉንም ነፍሳቸውንም የለየሀቸውን አምጣቸው አንተ የህያዋንና የሙታን አምላክ ነህና ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
በዚያንም ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ ከኤፌሶን አገር ዮሀንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን ማርያም አደረሰችው ሰገደላትና በፊቷ ቁሞ እንዲህ አላት ሰላምታ ይገባሻል ጌታችንን ፈጣሪያችንንና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለድሺው ፀጋን የተመላሽ ደስ ይበልሽ አንቺ ከዚህ አለም ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘላለም ህይወት ትሄጂአለሽና። ይህም ስሙ ክብር ምስጉን የሆነ ጌታችንና ፈጣሪያችን ድንቆች ተአምራቶችን በአንቺ ላይ ከገለጠ በኃላ ነው።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላትእግዚአብሄርንም እንዲህ ብላ አመሰገነችው ፈጣሪዬ ጌታዬ ላንተ ምስጋና ይሁን አንተ የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና አሁንም ነፍሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊአሳርጓት ከሚመጡ መላእከቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ።
በዚያንም ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል መጣ እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ ሀዋርያትም ሁሉ ከምድር ዳርቻ በደመና ተጭነው ለሰማይና ለምድር ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወደ ሆነች ወደ ቅድስት ድንግል ይደርሳሉ።
ወዲያውኑ ሁሉም ሀዋርያት የሞቱትም ከመቃብራቸው ተነስተው ወደ እመቤታችን ደርሰው ሰገዱላት አምላከችን ከአንቺ የተወለደ ፀጋን የተመላሽ ሆን ደስ ይበልሽ እርሱ ከዚህ አለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከርሱ ጋር ያሳርግሻልና አሏት።
በዚያንም ጊዜ እመቤታችን በአልጋዋ ላይ ተቀመጠች ሀዋርያትንም እንዲህ አለቻቸው ፈጣሪዬ ፈጣሪያቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኃችሁ እንደማየው አሁን አውቅሁ ከዚህ ከስጋዬም ወጥቼ ወደዘላለም ህይወት እሄዳለሁ ነገር ግን ትነግሩኝ ዘንድ እሻለሁ ከዚህም አለም እንደምለይ ከወዴት አወቃችሁ ።
ጴጥሮስና ሐዋርያት ሁሉም ወዳንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን በደመና ላይም በተጫን ጊዜ ወዳንቺ እንደ አይን ጥቅሻ ፈጥነን ደረስን አሏት።
እመቤታችንም ማርያምም ይህን ነገር ከሀዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ክቡር ምስጉን የሆነ ስምህን ፈፅሜ አመሰግናለሁ።የእኔን የአገልጋይህን መከራ ተመልክተህ ድንቅ ኃይልህን አድርገህልኛልና ከእንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል።
ፀሎቷንና ምስጋናዋን ስትጨርስ ሀዋርያትን እንዲህ አለቻቸው እጣን አምጥታችሁ በማጠን የጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ጥሩት እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ ።በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፍት መላእክት አጅበው እያመሰገኑት መጣና አረጋጋት ያዘጋጀላትንም ተድላ ደስታ ነገራት በዚያንም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተደረገ እውሮች አይተዋልና፣አንካሶች ቀንተው ሄደዋልና ደንቆሮዎች ሰምተዋልና ለምፃሞች ነፁ አጋንንትም ከሰዎች ወጥተው ሄዱ ዲዳዎች ተናገሩ በሽታና ደዌ ያለበት ሁሉ ዳነ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወዳለቸወበት ቤት በቀረብ ጊዜ ከደዌያቸው ይፈወሳሉና።
ከዚህም በኃላ እመቤታችን ተወዳጅ ልጅዋን እንዲህ አለችው በአየር ውስጥ ተበትነው ከሚኖሩ ከሚያስደነግጡ ግሩማን መላእክት የተነሳ ከእሳት ባህርም እፈራለሁ ጌታችንም ከእናንተ ለማንም በአለሁ ላይ ስልጣን የለውም አላት።
ከስጋዋም የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሀወሰርያትና ደናግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኑዋት እጃዋን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው በዚያንም ጊዜ ጌታችን ንፅህት ነፍሷን ከስጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሀን ልብስ አጎናፅፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት ስጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው ወደ ጌቴሴማኒ ተሸክመው እንዲወስዷት ሀዋርያትን አዘዛቸው።
ነፍሷ ከስጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሀንን እያየች ነበር የክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስም እንግዲህ ስጋሽን ተድላ ወዳለበት ገነት አፈልሳለሁ ዳግመኛም ስጋሽን ከነፍስሽ ጋር አዋህጄ አስነስቼ መላእክት በውስጡ በፊትሽ ሆነው በሚያመሰግኑበት ተመሳሳይ በሌለው ተድላ ደስታ በአለበት ማደሪያ አኖርሻለሁ አላት።
እመቤታችንም እንዲህ አለች አቤቱ በረቀቀ ጥበብህ ይህን ሁሉ የሰራህ አመሰግንሀለሁ ሁለተኛም ልመናዬን ትሰማ ዘንድ እለምንሀለሁ በስሜ ወደ አንተ የሚለምነውን ሁሉ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሆኖ ስሜን ጠርቶ ወዳንተ የሚለምነውን ከመከራው ሁሉ አድነው በሰማይም በምድርም በስራው ላይ ሁሉ አንተ ከሀሊ ነህና መታሰቢያዬን በውስጧ የሚያደርጉትን ቦታ ሁሉ ባርክ በእኔ ስም የሚያቀርቡትን የሁሉንም መስዋእታቸውን ተቀበል።
ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላት የለመንሽኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ ደስ ይበልሽ ከእኔ ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ፀጋ ክብር ባለሟልነት ተሰጥቶሻልና ስምሽንም ጠርቶ የሚለምን ሁሉ በዚህም አለም በሚመጣውም አለም አይጠፋም።
እመቤታችንም ከአረፈች በኃላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴሴማኒ ሊወስዷት ሀዋርያት ገንዘው ተሸከሟት። አይሁድም በሰሙ ጊዜ ስጋዋን ሊአቃጥሉ ወጡ ከእነርሱም አንዱ ከምድር ላይ ይጥላት ዘንድ የእመቤታችንን አልጋዋን ያዘ ያን ጊዜ ከእግዚአብሄር የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በአልጋዋ ላይ ተንጠለጠሉ።
ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመነ የእውነተኛ አምላክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት አንቺ በእውነት ድንግል የሆንሽ በእኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ እለምንሻለሁ በሀዋርያትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደኅነኞች ሆኑ።
በቀበሩዋትም ጊዜ ከዚያ ሶስት ቀን ኖሩ እረፍቷም የሆነው እሁድ ቀን በጥር ወር በሀያ አንድ በዚች ቀን ነበረ ጌታችንም ብርሀናውያን መላእክትን ላከ እነርሱም ስጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በእፀ ህይወት ስር አኖሩዋት።
ሀዋርያ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲአሳርጓት እመቤታችንን አገኛት መላእክትም ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ና እጅ ንሳ አሉት እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከእርሷም ተባረከ ከዚህም በኃላ ወደ ሀዋርያት ደረሰ ። እነርሱም እመቤታችንን ማርያምን እንደ አረፈችና እንደ ቀበርዋትም ነገሩት ቶማስም ስጋዋን እስከማይ አላምንም አላቸው።
ስጋዋንም ያሳዪት ዘንድ ወደ መቃብርዋ በአደረሱት ጊዜ በመቃብር ውስጥ ስጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችንን እንዳገኛት ቶማስ ነገራቸው። ሀዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የእመቤታችንን እርገቷን ስለ አላዩ እጅግ አዘኑ ስጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው። ከዚህም በኃላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ስጣቸው እነርሱም እስከ ነሀሴ አስራ ስድስት በረስፋ ኖሩ።
የእመቤታችንም የእድሜዋ ዘመን ስልሳ አራት አመት ነው በአባትና እናቷ ቤት ሶስት አመት ከሰባት ወር በቤተ መቅደስም አስራ ሁለት አመት በዮሴፍም ቤት ሰላሳ አራት አመት ከሶስት ወር ከጌታ እርገት በኃላ በወንጌላዊ ዮሀንስ ቤት አስራ አራት አመት ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም እለት የሮሜ አገር ንጉስ የዘይኑን ልጅ የከበረች ኢላርያ አረፈች። የዚችም ቅድስት አባቷ እግዚአብሔርን የሚውድ ሀይማኖቱ የቀና ነው ይቺን ቅድስት ኢላርያንና ሁለተኛዋን እኃቷን ወለደ ከእንርሱም በቀር ወንድ ልጅ የለውም። ይቺም ቅድስት ኢላርያ የምንኮስና ልብስን የመላእክትንም አስኬማ ትለብስ ዘንድ የምትመኝ ሆነች ከቤተመንግስትም ወጥታ ልብሷን ለውጣ የወንድ ልብስ ለብሳ ወደ ግብፅ ሀገር ሄድች።
ከዚያም ወደ አስቄጠስ ገዳም ደረሰች በዚያም ስሙ አበሰ ባውሚን የሚባለውን ፍፁም ሽማግሌ ፃድቅ ሰውን አግኝታ ሀሳቧን ሁሉ ነገረችው እርሷ ሴት እንደ ሆነችም አስረዳችው እርሱም ምስጢሯን ሰውሮ ለብቻዋ በዋሻ ውስጥ አስገባት ይጎበኛትና ልትሰራው የሚገባትን ያስተምራት ነበር። እንዲህም ሆና አስራ ሁለት አመት ኖረች ፅህም ስለሌላትም ለአረጋውያን መነኰሳት ጃንደረባ ትመስላቸው ነበር።በወንድ ስም አጠራርም አባ ኢላርዮን ብለው ይጠሩዋታል።
ከአባቷ ዘንድ በቀረችው በሁለተኛዋ ግን ርኩስ ሰይጣን አደረባትና ያሰቃያት ጀመር ያድኗትም ዘንድ ለባለ መድሀኒቶች አባቷ ብዙ ገንዘብ ሰጠ ግን አልተቻላቸውም። ከዚህም በኃላ የከበሩ አረጋውያን መነኮሳት ወዳሉበት አስቄጥስ ገዳም ይልካት ዘንድ መኳንንቶቹ መከሩት የቅድስናቸው ወሬ በሮም ሀገሮች ሁሉ ተሰምቷልና በዚያንም ጊዜ ወደ ቅዱሳኑ ከብዙ ሰራዊት ጋር ላካት ለቅዱሳኑም መልእክትን ፃፈላቸው እንዲህ ሲል የተከበራችሁ አባቶቼ ሆይ የደረሰብኝን ኃዘን አስረዳችኃለሁ እግዚአብሔር ሁለት ሴቶቸ ልጆችን ሰጥቶኝ ነበር።
አንዲቱ ከአለም ሸሸች ወደየት ቦታ እንደምትኖር አላውቅም በሁለተኛዪቱም በላይዋ ርኩስ መንፈስ ተጫነበት እኔ መፅናኛ ትሆነኛለች ብዬ እየሰብኩ ነበር አሁንም በፀሎታቸሁ እግዚአብሔር ያድናት ዘንድ በላይዋ እንድትፀልዩ አኔ ቅድስናችሁን እለምናሉ።
ቅዱሳን መነኮሳትም የንጉሱን ደብዳቤ በአነበቡ ጊዜ በላይዋ ሊፀልዩ ጀመሩ በላይዋ ያደረ ሰይጣንም ከኢላርዮን በቀር ከማደሪያዬ የሚያሰጠኝ የለም ብሎ ጮኸ። አርጋውያኑም ጃንደረባ የሚሏትን ኢላርያን ጠርተው እግዚአብሄር እስከ አዳናት ድረስ የንጉሱን ልጅ ወስደህ በላይዋ ፀልይ አሏት ቅድስት ኢለርያም እኔ በደለኛ ሰው ነኝ ይህን ጭንቅ የሆነ ስራን መስራት አልችልም አለቻቸው።
በአሰገደድዋትም ጊዜ ወደ በአትዋ ወሰዳ በላይዋ ፀለየች ሰይጣነም ትቷት ሸሸ እህቷ እንደሆነች ታውቃለች ስለዚህ አቅፋ ትስማት ነበር ስለ ናፍቆቷና ስለ ፍቅርዋ ወደ ውጭ ወጥታ ታለቅሳለች።
ከዚህም በኃላ ወደ ከበሩ አረጋውያን አደረሰቻችና እነሆ በፀሎታችሁ እግዚአብሔር አድኗታል ወደ አባቷ መልሷት አለቻቸው። እነርሱም እጅግ ደስ ብሏቸው ወደ አባቷ መለሱዋት ለእግዚአብሔርም ምስጋና አቀረቡ።
ወደ ሮሜ አገርም ወደ አባቷ በደረሰች ጊዜ አባትና እናቷ ስለ መዳንዋ በእርሷ እጅግ ደስ አላቸው የቤተ መንግስትም ሰዎችም ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
አባቷም በገዳም ከቅዱሳን አባቶች ጋር አኗኗርሽ እንዴት ነበር ብሎ ጠየቃት እርሷም እንዲህ ብላ ነገረችው ያ ያዳነኝ አባ ኢላርዮን የሚባል አባት አብዝቶ ይወደኛል አቅፎም ይስመኛል ንጉሱም ይህን ሰምቶ በልቡ ታወከ ለመነኩሴ ሴቶችን መሳም ይገባዋልን አለ። በዚያንም ጊዜ በእኔ ላይ ይፀልይ ዘንድ አገሬንም ይባርክ ዘንድ ልጄን ያዳናትን አባ ኢላርዮንን ወደኔ ላኩት የሚል ደብዳቤ ፅፎ ወደ ቅዲሳን አረጋውያን ላከ።
አረጋውያንም ቅድስት ኢላርያን ጠርተው ወደ ንጉስ እንድትሄድ አዘዙዋት እርሷም ይተዋት ዘንድ አረጋውያን አባቶችን አልቅሳ ለመነቻቸው። እንርሱም እንዲህ አሉዋት ይህ ንጉስ ክርስቲያኖችን የሚወድ ፃድቅ ነው ቅዱሳት መፃህፍትም እንደሚያዙን ትእዛዙን መተላለፍ አይቻለንም ይህንንም ብለው አስገድደው ላኩዋት።
ወደ ንጉሱም በደረሰች ጊዜ ንጉሱና የቤተ መንግስት ሰዎች ሁሉም በክብር ተቀብለው ተሳለሟት ከዚህም በኃላ ንጉሱና ንግስቲቱ ለብቻቸው ሆነው ወደ ውስጠኛው አዳራሽ አስገለሉዋትና ንጉሱ እነዲህ ብሎ ጠየቃት አንተ ልጄን እንደምትስማት በሰማሁ ጊዜ በሀሳቤ ታውኬ አለሁ መነኩሴ ሴትን መሳም አይገባውምና ይህን ነገር ትገልጥልኝ ዘንድ እሻለሁ።
የከበረች ኢላርያም በነገርኳችሁ ጊዜ ወደ አስቄጥስ ገዳም መሄድን ላትከለክሉኝ የከበረ ወንጌልን አምጥታችሁ ማሉልኝ አለቻቸው እነርሱም እንዳለችው ማሉላት። በዚያንም ጊዜ ልጃቸው ኢላርያ እንደሆነች ነገረቻቸው። አወጣጧም እንዴት እንደሆነ ልብሶቿንም ለውጣ የወንድ ልብስ እንደለበሰች አስረዳቻቸው በአካሏም ውስጥ ያለ ምልክትን አሳየቻቸው።
በዚያንም ጊዜ ታላቅ ጩኸትን ጮኹ አቅፈው እየሳሟት አለቀሱ ከእኛ ዘንድ እንድትሄጂ ከቶ አንተውሽም አሏት እርሷም በከበረ ወንጌል የማላችሁትን መሀላ አስቡ አለቻቸው። እነርሱም ከእርሱ ጋር አርባ ቀን ያህል እንድትኖር ለመኑዋትና አርባ ቀን አብራቸው ኖረች ከዚህም በኃላ ወደ ቦታዋ ሄደች።
ከዚያችም እለት ወዲህ በአስቄጥስ ገዳም ለሚኖሩ ቅዱሳን የከበሩ አረጋውያን መነኮሳት ለፍላጊታቸው ይሆን ዘንድ የግብፅን ምድር ሁሉ ግብር እንዲሰጧቸው ንጉስ ዘይኑን አዘዘ በዚያንም ወራት በአባ መቃርስ ገዳም አራት መቶ የመነኮሳትን ቤቶች ሰሩ በአባ ዮሀንስም ገዳም ሰባት መቶ በአባ ሙሴ ገዳም ሶስት መቶ ቤቶችን ሰሩ። ከዚህም በኃላ ቅድስት ኢላርያ አምስት አመት ከኖረች በኃላ አረፈች ከእረፍቷም አስቀድሞ እርሷ ሴት እንደሆነች ያወቀ የለም።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም እለት የኑሲስ ኤጲስቆጶስ የባስልዮስ ወንድም የከበረ ጎርጎርዮስ የእፍቱ መታሰቢያ ነው እነሆ የአባቱንና የወንድሙን መታሰቢያቸውን በዚህ ወር ጥር ስድስት ቀን ፅፈናል።
ይህም ቅዱስ ጎርጎርዮስ እጅግ የተማረ አዋቂ ነበረ በደሴቶችም ላይ ኤጲስቆጶስነት ተሾመ እነሆ በዚህ ወር በአስራ አምስት ቀን የሆነውን ከገድሉ ጥቂት እንፅፋለን። ስለርሱም እንዲህ ተባለ እርሱ መስዋእቱን ለማክበር በሚቀድስ ጊዜ በመሰዊያው ላይ ሲወርድ መንፈስ ቅዱስን የሚያየው ሆነ ከዚህም በኃላ ኪሩብን አየው በደረቱም ውስጥ አቀፈው በመሰዊያውም ላይ ሳለ ወደ ዝምታና ተደሞ አደረሰው ሰዎችም ሁሉ ስጋዊ እንቅልፍ የሚያንቀላፋ ይመስላቸው ነበር።
በኤጲስቆጶስነት ሹመት ሰላሳ ሶስት ዘመናት በተፈፀመለት ጊዜ ወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ ሊጠይቀው መጣ እርሱ ከተጋድሎ ብዛት የተነሳ በፅኑ ደዌ የሚታመም ሆኖ ነበርና በቅዱስ ባስልዮስ መምጣት ደስ አለው።
ቅዱስ ጎርጎርዮስም እንደ ልማዱ ሊቀድስ ወደ መሰዊያው በወጣ ጊዜ የከበረች ድንግል እመቤታችን ማርያም ተገለፀችለትና ዛሬ ወደኔ ትመጣለህ አለችው የቁርባኑንም ቅዳሴ ሲጨርስ ህዝቡ በቀናች ሀይማኖት ፀንተው እንዲኖሩ ይመክራቸውና ያስተምራቸው ዘንድ ወንድሙን ባስልዮስን ለመነው እርሱም እንደሚያንቀላፋ ሆነ በቀሰቀሱትም ጊዜ ሞቶ አገኙት ቅዱስ ባስልዮስም ሳጥን እንዲሰሩለት አዘዛቸው። ፀሎታትንም በመፀለይ መዝሙራትንም በመዘመር በማመስገንም እንደሚገባ ገንዞ በመቃብር ውስጥ አኖሩት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የካህኑ ኬልቅዩ ልጅ ታላቁ ነቢይ ኤርምያስ መታሰቢያው ነው። ይህም እውነተኛ ነቢይ የአሞጽ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ሦስት ዓመቱ ማስተማር ጀመረ።
ከዚያም በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ዐሠራ አንዱ የሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥቱ እስከሚፈጸም በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት ጊዜ ያስተምር ነበር።
ስለ ራሱ እንዲህ ሲል ራሱ ተናገረ የእግዚአብሔር ቃል ወደኔ መጣ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ "በእናትህ ማሕፀን ሳልፈጥርህ ወደድኩህ ከእናትህም ማሕፀን ሳትወጣ መረጥኩህ ለአሕዛብም መምህር አደረግሁህ አለኝ።" ይህም ነቢይ የእግዚአብሔርን አምልኮና ሕጉን በመተዋቸው እንዲህ ሲል የእስራኤልን ልጆች ገሠጻቸው። ተጠበቁ ንስሐም ግቡ የእግዚአብሔር ቁጣው በላያችሁ እንዳይመጣ።
ሁለተኛም እንዲህ ብሎ አስረዳቸው ወደ ፈጣሪያችሁ እግዚአብሔር ካልተመለሳችሁ ያለዚያ የከላውዴዎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን በላያችሁ እርሱ ያሥነሣዋል ይማርካችኋልም እንደቃሉም ሆነ። ሁለተኛም ሕዝቡ ተማርከው ሰባ ዘመን እንደሚኖሩ ትንቢት ተናገረ።
ደግሞ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ለኩነተ ሥጋ እንደሚመጣና መከራ እንደሚቀበል የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደሚሸጠውና ሠላሳ ብር እንደሚወስድ ተናገረ። ስለ ብዙ ሥራዎችም ተናገረ አይሁድ ግን ሊገድሉት ወደው ገርፈው አሥረው በጒድጓድ ውሰጥ ጣሉት እግዚአብሔርም አዳነው። እርሱ ግን ስለእነርሱ ይለምንና ይማልድ ነበር እግዚአብሔርም ስለ እርሳቸው ወደእኔ አትማልድ እነርሱ ከክፋታቸው አይመለሱምና አለው።
ናቡከደነጾርም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ በማረከ ጊዜ ከእሳቸው ጋራ አልማረከውም። ነገር ግን ከምርኮ የቀሩት ወደ ግብጽ አገር ወሰዱት የግብጽን ሰዎች ሲያጠፉአቸው የነበሩ በግብጽ ወንዞች የሚኖሩ አራዊትን በእርሱ ጸሎት እግዚአብሔር አጠፋቸው።
ከዚያም ወደ ባቢሎን አገር ወሰዱት በዚያም የእስራኤል ልጆች ከምርኮ እስኪመለሱ ትንቢት እየተናገረ ሕዝቡን ሲአስተምር ኖረ። የትንቢቱ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ አይሁድ በደንጊያዎች ወገሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
የህይወት የድኅነት አለኝታ የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በፀሎቷም ከክፉ ነገር ይጠብቀን አሜን።
No comments:
Post a Comment