ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 24 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 24

 #ቅዱስ_አጋቢጦስ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ሃያ አራት በዚች ቀን የከበረ አባት ኤጲስቆጶስ አጋቢጦስ አረፈ። ይህም አባት በከሀድያን ነገሥታት በዲዮቅልጥያኖስና በመክስምያኖስ ዘመን ነበር። ወላጆቹም ደጎች ምእመናን ነበሩ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተምረውት ዲቁና ተሾመ።


ከዚህም በኋላ እናትና አባቱን ትቶ ወደ አንድ ገዳም ሔዶ የሸመገሉ መነኰሳትን አገለገለ። ከእርሳቸውም በጎ አምልኮትን ተማረ አረጋውያኑንም እያገለገለ በገድል ተጠመደ ያለማቋረጥም በጾም በጸሎትና በስግደት ይተጋል ከጥዋትም እስከ ምሽት በመጾም የሽንብራ አሠር የሚመገብ ሆነ።
ከእንቅልፍም ጋር ሊታገል በወደደ ጊዜ ከሽምብራ አሠር ጋር አመድ እየተመገበ ሰማንያ ቀን ኖረ በዚህም ተጋድሎ ውስጥ እያለ ኃይሉ ግን ይጨመርለት ነበር። ለአረጋውያንም አገልግሎቱን አላስታጐለም ሲጠራቸውም ጌቶቼ ይላቸዋል የጽድቅንና የትሩፋትን ሥራ ሁሉ ፈጸመ።
እግዚአብሔርም የሚያስደንቁ ብዙዎች የሆኑ ታላላቅ ተአምራቶችን በእጆቹ ገለጠ። ከእርሳቸውም አንዲቷን ብላቴና አዳናት እርሷም እንደ ዕንጨት የደረቀች እስከምትሆን ብዙ ዘመን ጭንቅ በሆነ ደዌ ታማ የኖረች ናት። ዳግመኛም ብዙ ሰዎችን ያጠፋውን ታላቅ ከይሲ በጸሎቱ ገደለው። ከሰውና ከእንስሳም አስጨናቂ የሆኑ በሽታዎችን አሰወገደ።
የተጋድሎውና የኃይሉ ጽናት ወሬው በተሰማ ጊዜ ስሙ ሉክያኖስ የሚባል መኰንን ወደርሱ ልኮ አስመጥቶ ያለ ውዴታው በግድ የጭፍራ አለቃ አድርጎ ሾመው እርሱ ግን ተጋድሎውን አልተወም ጾምንም ጸሎትንም የትሩፋትን ሥራ የሚጨመር ሆነ እንጂ የቀደመ ሥራውን አልተወም በጥቂት ቀኖችም ዲዮቅልጥያኖስንና መክስምያኖስን እግዚአብሔር አጠፋቸው አምላክን የሚወድ ጻድቅ ሰው ቈስጠንጢኖስ ነገሠ ይህም ቅዱስ ከጭፍራ ውስጥ ይወጣ ዘንድ ምክንያት የሚሻ ሆነ።
ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እጅግ የሚወደው መልከ መልካም የሆነ ወጣት ብላቴና ነበር ክፉ ጋኔንም ተጫነበት በቀንም በሌሊትም ታላቅ ሥቃይን የሚያሠቃየው ሆነ ቅዱስ አጋቢጦስንም ከሚያውቁት ውስጥ አንድ ሰው በአየው ጊዜ የወታደር አለቃ አጋቢጦስ ቢመጣ በአዳነህ ነበር አለው የታመመውም እርሱ በንጉሥ ጭፍራ ሥርዓት ውስጥ ያለ በውኑ ይህን ሥራ መሥራት ይችላልን አለ ሰውዬውም ገድሉንና ሥራውን ሁሉ አስረዳው። ጋኔን ያደረበትም በእውነት ሊያድነኝ ይችላልና ከዚህ ከአስጨናቂ ደዌ ያድነኝ ዘንድ የወታደር አለቃ አጋቢጦስን ፈጥናችሁ አምጡልኝ አለ።
ንጉሥም ይህን በአወቀ ጊዜ ቅዱስ አጋቢጦስን እንዲአመጡለት አዘዘ በመጣ ጊዜም በወጣቱ ላይ ጸለየ በከበረ መስቀልም አማተበው በዚያንም ጊዜ በእግዚአብሔር ኃይል ዳነ ንጉሡም በዚህ ደስ ብሎት ቅዱስ አጋቢጦስን አከበረው ምን እንዳደርግልህ ትሻለህ አለው እርሱም ንጉሡን ከወታደርነት ውስጥ አሰናብተኝ አለውና አሰናበተው አስቀድሞ ወደ ነበረባትም ቦታው ተመለሰ ብዙ ዘመናትም እጅግ እየተጋደለ ኖረ።
ከዚህም በኋላ የዚያች አገር ኤጲስቆጶስ ይዞ ቅስና ሾመው ይህም ኤጲስቆጶስ በሞተ ጊዜ ቅዱስ አጋቢጦስን ይሾምላቸው ዘንድ ሕዝቡ ሊቀ ጳጳሳቱን ለመኑት እርሱም ሾመላቸው መልካም ተናጋሪዎች የሆኑትን የክርስቶስን መንጋዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው።
እግዚአብሔርም የትንቢትን ጸጋ የተሠወረውንም የማወቅ ድንቆች ተአምራቶችንም የማድረግ ሀብትን ሰጠው። በሥውር ኃጢአትን የሚሠሩትን ኃጢአተኞች የሚገሥጻቸው ሆነ በንስሐም እስኪመለሱ ከመቅደስ ያርቃቸዋል።
ዳግመኛም በገድሉ መጽሐፍ ተጽፎ የተገኘ የታላቅ ወንዝ ወራጅ ውኃን በመስቀሉ አቁሞ ወደ ሌላ መንገድ መለሰው የዕውር ዐይኖችንም ገለጠ ለምጻሞችንም አነጻ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳነ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለም አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages