ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲተት 23 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲተት 23

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ሀያ ሦስት በዚህች ቀን #ቅዱስ_ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት አባቶቻችንን አድዋ ላይ የረዳበት ነው፣ የክቡር ፋሲለደስ ልጅ የከበረ #ቅዱስ_አውሳብዮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የሰርምኔሱ ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያዊው ሰማዕት #ቅዱስ_ፖሊካርፐስ መታሰቢያው ነው፡፡


የካቲት ሀያ ሦስት በዚህች ቀን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት አባቶቻችንን አድዋ ላይ የረዳበት ነው፡፡ በዚያን ወራት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ አራት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በነገሡ በሃያ ስድስት ዓመት የምኒልክ የጦር አለቃ ገበየሁ ድል ከአደረጋቸው በኋላ እንደገና ምኒልክም ወግተው ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ሊገዙ የሮም ሰዎች መጡ።
ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት፡ ዳግማዊ አጤ (ዓፄ) ምኒልክ መስከረም ፯ ቀን ፲፰፻፹፰ (1888፡ዓ.ም ) ላይ "እግዚአብሔር በቸርነቱ፡ እስከ አሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስከ አሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለ እኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡ እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት፤ እግዚአብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷልና እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስከ አሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው፤ ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም አንተም እስከ አሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ስለዚህ ስንቅህን በአህያ አመልህን በጉያህ ይዘህ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፤ለሚስትህ፤ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን በኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም፡፡ ማርያምን! በዚህ አማላጅ የለኝም"፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ" ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡ ዳግኛም በፈረሶታቸው መጣብር ላይ በጦራቸው አንደበት ላይ የመስቀል ምልክት እንዲያደርጉ ጭፍሮችን አዘዛቸው መስቀል ጠላትን ድል አድራጊ እንደሆነ አስቀድሞ ያውቅ ነበርና።
አዋጁን ካስነገሩ በኋላ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ትግራይ ክፍለ አገር ዘመቱና ከትግራይ አውራጃ አንዷ የምትሆን አድዋ የምትባል አገር ደረሱ፡፡ የሣህለ ማርያም (ዳግማዊ ምኒልክ) ሚስት ወለተ ሚካኤል (እቴጌ ጣይቱም) በንጉሡ ትዕዛዝ ታቦተ ጊዮርጊስን አስይዘው ከሊቀ ጳጳሱ ከአባ ማቴዎስ እንዲሁም ከቀሳውስቱና ከመነኰሳቱ ጭምር ከንጉሡ ጋር ወደ ጦርነቱ ተጓዘች፡፡በዚያም ጊዜ የአክሱም ጽዮን መነኰሳትና ካህናት የእመቤታችንን ሥዕል ይዘው ወደ ንጉሡ ወደ ምኒልክ መጥተው ከሊቀ ጳጳሱ ከነአቡነ ማቴዎስ ጋር ተቀላቀሉ ከዚያም ሌሊቱን ሙሉ ጸሎት ምሕላ ሲያደርሱ አደሩ።
ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ የካቲት ሃያ ሁለት ቀን ነው ንጉሡ ሣህለ ማርያም (ምኒልክ) የጦር ልብሱን ለብሰው ከሠራዊቱ ጋር ወደ ጦር ግንባር ሄደ፡፡ ከዚያም ከሮማውያን የጠላት ጦር ጋር ተገናኝቶ ከሌሊቱ ዐሥራ አንድ ሰዓት ጦርነቱን ጀመረ፡፡ የንጉሡ የሣህለ ማርያም (የምኒልክ) ሚስት ወለተ ሚካኤል (እቴጌ ጣይቱም) ሌሊት በታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስና በእመቤታችን ሥዕል ፊት በጸሎትና በስግደት እያደረች ሲነጋ ወደጦርነቱ ቦታ በመሄድ እጅግ ለሚያስደንቅ የአነጋገሯ ኃይል ቃል በጦርነቱ መካከል እየተገኘች ለንጉሡ ወታደሮች የሞራልና የብርታት ድጋፍ ትሰጣቸው ነበር። በእውነትም ለተመለከታት ሁሉ እንደ ኃይለኛ ተጋዳይ አርበኛ ትመስል ነበር እንጂ የሴቶች የተፈጥሮ ባሕርይ በእርሷ ላይ አይታይባትም ነበር። የንጉሡም ወታደሮች የንግሥቲቱን የጀግንነት አነጋገር በሰሙ ጊዜ በእሳት ላይ እንደተጣደ የብረት ምጣድ ልባቸው ጋለ ይልቁንም ላም እንዳየ አንበሳና የፍየል መንጋ እንዳየ ነብር እየተወረወሩ በጦርነቱ መካከል በመግባት የጠላትን ጦር በሰይፍ ይጨፈጭፋት ነበር። መጽሐፍ ሹመትን ሽልማትን ያየ አርበኛ ከጦርነት ከሰልፍ ወደኋላ አያፈገፍግም ብሎ ተናግሯልና፡፡ በዚያም ጊዜ ንጉሡ ሣህለ ማርያም (ምኒልክ) በጦርነቱ መካከል ሳለ ሊቀ ጳጳሱ አባ ማቴዎስ እንዲሁም የአክሱም መነኰሳትና ሌሎቹ ካህናት በሙሉ ታቦተ ጊዮርጊስንና ሥዕለ ማርያምን ይዘው ከንጉሡ በስተኋላ በደጀንነት ቆመው ጸሎተ ምህላ ያደርሱ ነበር። ንግሥቲቱ ወለተ ሚካኤል (እቴጌ፡ጣይቱም) በጸሎት ጊዜ በመዓልትም በሌሊትም ከእነርሱ አትለይም ነበር። የጽዮን አገልጋዮችም በእግዚአብሔር የሕጉ ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር።
በዚህም ዕለት ይኸውም የካቲት ሃያ ሦስት ቀን በሮማውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሆነ በዚህም ጊዜ በሰማይ ታላቅ ተአምር ተደረገ። ማለትም የቀስተ ደመና ምልክት ታየ ከዚያም ከቀስተ ደመናው ውስጥ መልኩ አረንጓዴ የመሰለ ጢስ ይወጣ ነበር፡፡ ከዚህም ጢስ ውስጥ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ያለ ድምጽ ተሰማ፡፡ ከዚህም የነጐድጓድ ድምጽ የተነሳ በሮማውያን ወታደሮች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ሽብር ሆነ ለመዋጋት አልቻሉም፡፡ ይልቁኑ ኃያሉ ገባሬ ተአምር ማር ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምባ ላይ ፈረሱ ተቀምጦ ከነፋስ ሩጫ ይልቅ እየተፋጠነ በአየር ላይ በተገለጸ ጊዜ በግንባራቸው ፍግም እያሉ ወደቁ፡፡ "የኢትዮጵያ ህዝብ አምላካቸው ሊረዳቸው መጣ እንግዲህ ማን ያድኅነናል" አሉ ምድርም ጠበበቻቸው በዚህን ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሮምን የጦር ሠራዊት ፈጁዋቸው የተረፉትንም ማረኳቸው ፈጽመውም እስኪያጠፏቸው ድረስ በሮማውያን ላይ በእግዚአብሔር ሥልጣን የኢትዮጵያውያን እጅ እየበረታ ሄደ፡፡ ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሣህለ ማርያም (ምኒልክ) በእግዚአብሔር ኃይልና በተአምራት አድራጊው በቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳይነት የሮማውያንን የጦር ሠራዊት ድል አድርገው የድል አክሊል ተቀዳጅተው ተመለሱ፡፡
ስለዚህም በዳዊት የምስጋና ቃል የድል ዘውድ ያቀዳጀኝን እግዚአብሔር "ባለ ዘመኔ ሁሉ አመሰግነዋለሁ ለፈጣሪዬ እዘምራለሁ" አለ ሕዝቡም ሁሉ "በክብር ከፍ ከፍ ያለ እግዚአብሔርን በፍጹም ምስጋና እናመስግነውለን የሮማውያንን ኃይል ቀጥቅጦ አጥፍቷልና ሠረገሎቻቸውንም ሠባብሯልና ሠራዊቱንም ሁሉ በምድር ላይ በትኗልና" እያሉ አመሰገኑ። በፈጣሪው በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል በጦርነቱ መካከል የረዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስንም በፍጹም ማድነቅ አደነቁ። የሮማም የጦር ሠራዊት በኢትዮጵያውያን ፊት ተዋረዱ ዳግመኛም በኢትዮጵያ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። በምኒልክም ዘመነ መንግሥት ኢትዮጽያ ከጦርነት ለዓርባ ዓመት ያህል አረፈች።
የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ከአደዋ ጦርነት ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ በምትበል ከተማው መካከል በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ቤተክርስቲያን አሠራ። ስሟንም ገነተ ጽጌ ብለው ሰየሟት። ቅዱስ ጊዮርጊስ በጦርነት ቦታ ሁሉ ይረዳው ነበርና። ልመና ክብሩ በኛ ለዘላለሙ በዕውነት ይደረግል። በረከቱ ከእኛ ጋር ትሁን እኛንም በቅዱስ ጊዮርጊስ አማላጅነት ይማረን ለዘለዓለሙ አሜን!!! (ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተአምር 17)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የክቡር ፋሲለደስ ልጅ የከበረ አውሳብዮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም የከበረ ፋሲለደስ ለአንፆኪያ መንግስት የሰራዊት አለቃ ነው ለመንግስት ልጆችም አባታቸው ነው እርሱም ከፋርስ ሰዎች ጋር በጢርነት ውስጥ እያለ ዲዮቅልጥያኖስ የክብር ባለቤት ጌታችንን ክርስቶስን ክዶ ጣኦትን እንዳመለከ ሰማ።
እጅግ አዝኖ ወደ ልጁ ወደ አውሳብዮስ ልኮ ይህንን ነገረው የከበሩ የቤተ መንግስት ሰዎች ዘመዶቹን ዳግመኛ ጠራቸው እነርሱም የንጉስ ልጅ ዮስጦስ አባዲር ገላውዴዎስና ቴዎድሮስ ከእርሳቸውም ጋር ያሉትን ጠርቶ ስለ ከሀዲው ንጉስ ነገራቸው።
ሁሉም እጅግ አዘኑ ዳግመኛም እንዲህ አላቸው እኔ ስለ ፈጣሪዬ ስለ ክርስቶስ ስም ደሜን አፈሳለሁ ሁሉም በዚህ በጎ ምክር ተስማምተው እርስ በርሳቸው ተማማሉ።ጠላቶቻቸውንም ድል አድርገው ወደ ሀገራቸው በተመለሱጊዜ ንጉሱ ከሰራዊቱ ጋር ወጥቶ በደስታ ተቀበሏቸው።
ከዘህም በኃላ የቅዱስ ፊቅጦር አባት ህርማኖስ ለቅዱሳኑ ጣዖትን እንዲአቀርብላቸውና አንዲሰግዱለት ንጉሱን መከረው ንጉሱም ህርማኖስ እንደ መከረው አደረገ። በዚያንም ጊዜ ቅዱሳንን ጠርቶ እነዲህ አላቸው እኔ እጅግ እንደምወዳችሁ እናንተ ታውቃላችሁ አሁንም ለአጶሎን ሰግዳችሁ ልቤን ደስ ታሰኙ ዘንድ ከእናንተ እሻለሁ።
ቅዱሳንም ሰምተው እጅግ ተቆጡ አውሳብየስም ንጉሱን ሊገድል ሰይፉን መዘዘ ንጉሱም ሸሽቶ ተሸሸገ ከንጉስም ባለሟሎች ብዙዎችን ሰራዊቱንም ጭምር ገደለ የከበረ ፋሲለደስም ባይከለክላቸው ከንጉስ ቤት ምንም ሰው ባልቀራቸው ነበር።
ከዚህም በኃላ ደግሞ አውሳብዮስን ወደ ግብፅ አገር ወስደው በዚያ ይገድሉት ዘንድ ህርማኖስ ንጉሱን መከረው እርሱ በዚች ሀገር ከኖረ ያገር ሰዎችን በላይህ ያስነሳብሀልና ያሰብከውን ምንም ምን መስራት አትችልም አለው።
ንጉሱም ቅድስ አውሳብዮስን ፅኑዕ ስቃይን ያሰቃዩት ዘንድ ወደ ግብፅ አገር ወደ ቅፍጥ ገዥ ሉልያኖስ ዘንድ እንዲወስዱት ፃፈ ወደ መኮንን ሉልያኖስም በደረሰ ጊዜ በመንኮራኩር ሀዋሳቱን በመቁራረጥ በግርፋት አሰቃዩት። ደግመኛም በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት ጌታችንም መልአኩን ልኮ ከመከራው ሁሉ አዳነው አፅናንቶና አረጋግቶ ያለ ጉዳት አስነሳው።
ነፍሱንም ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ወሰዳት የፃድቃንና የሰማእታትንም መኖሪያ አየ ለርሱና ለአባቱ ለዘመዶቹም ያዘጋጀላቸውን ቦታዎች አይቶ ነፍሱ እጅግ ደስ አላት።
ከዚህም በኃላ ወደ እሳት ማንደጃ ውስጥ ይጨምሩት ዘንድ መኮንኑ አዘዘ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአከ ወርዶ እሳቱን እንደ ጠል አቀዝቅዞ ያለ ጥፋት የከበረ አውሳብዮስን አውጣው።
መኮንን ሆይ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ እዘዝ ከእርሱም ትግል ታርፋለህ እርሱም የአውሳብዮስን የከበረች ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጡት የሰማእትነት አክሊልንም በመንግስተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የሰርምኔሱ ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያዊው ሰማዕት ቅዱስ ፖሊካርፐስ መታሰቢያው ነው፡፡ ቅዱስ ፖሊካርፐስ የተወለደው ከክርስቲያን ቤተሰቦች በ70 ዓ.ም. በጥንታዊቷ ሰምርኔስ ከተማ (ቱርክ ውስጥ የአሁኗ እዝሚር) ነው፡፡ ቤተሰቦቹን በልጅነቱ ስላጣ ካሊቶስ/ካሊስታ የተባለች ደግ ክርስቲያን አሳድጋዋለች፡፡ ከእርሷም በኋላ የሰምርኔስ ከተማ ጳጳስ ቡኩሎስ ወስዶ ትምህርተ ሃይማኖትን በሚገባ እያስተማረ አሳድጎታል:: ይህ ቅዱስ ቡኩሎስ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙር ስለነበር ቅዱስ ፖሊካርፐስ ዮሐንስ ወንጌላዊን እና ሌሎችንም ሐዋርያት የማግኘት ዕድል ነበረው:: ቅዱስ ቡኩሎስ ቅንዓቱንና ትጋቱን አይቶ ዲቁና ሾመው፤ ቀጥሎም ቅስናን ሾመውና የቅርብ ረዳቱ አደረገው:: ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ሐዋርያዊ ጉዞ በሚያደርግበት ወቅት አስከትሎት ይሄድ ነበር፤ ከሌሎች ሐዋርያት ረዘም ላለ ጊዜ በምድር ላይ ስለነበር ለብዙ ዓመታት የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ቅዱስ ቡኩሎስ ካረፈ በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ የሰምርኔስ ከተማ ጳጳስ አድርጎ ሹሞታል::
ቅዱስ ፖሊካርፐስ ወንጌልን ከሐዋርያት በተለይም ከዮሐንስ በቀጥታ እየሰማ ያደገ፣ የሐዋርያትን ትውፊት በሚገባ የወረሰ፣ በሥራዎቹ በሙሉ እነርሱን መስሎ እነርሱን አክሎ የተነሣ አባት ነው፤ ቁጥሩም ከሐዋርያውያነ አበው መካከል ነው:: የሰምርኔስን ቤተ ክርስቲያን በሚገባ የጠበቀእና በካህናትና ምእመናን ዘንድም እጅግ ተወዳጅ የነበረ አባት ነው:: ብዙ ደቀ መዛሙርትን ያፈራ ሲሆን ከእነዚህም ታላላቆቹ ቅዱስ ሄሬኔዎስ እና ቅዱስ ፓፒያስ ይገኙበታል:: የአንጾኪያው ጳጳስ ቅዱስ አግናጥዮስ ቅዱስ ፖሊካርፐስን እጅግ ይወደውና ያከብረው ነበር:: ሁለቱ ቅዱሳን ሰፊ የሆነ የዕድሜ ልዩነት የነበራቸው ቢሆንም በሐዋርያት መካከል አዋቂውም ሕፃኑም ቃላቸውን ለመስማት ይሰበሰብ ስለነበር በዚያ ተዋወቁ:: ስለዚህም ሁለቱም የዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዛሙርት ናቸው:: ቅዱስ አግናጥዮስ ለሰማዕትነት ወደ ሮም ሲጓዝ ለመጨረሻ ጊዜ ተገናኝተው እንዲህ ብሎታል:- “የአንጾኪያን ቤተ ክርስቲያን አደራ፤ እኔ መልእክት ላልጻፍሁላቸው አብያተ ክርስቲያናት አንተ ጻፍላቸው::” በዚህም ምክንያት ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጽፎ ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የተጻፉ የአግናጥዮስ መልእክታትንም ጨምሮ ልኮላቸዋል:: በመጨረሻም ቅዱስ አግናጥዮስ ለግሉ በስሙ ደብዳቤ ጽፎለታል፤ ይህም ለግለሰብ የጻፈው ብቸኛው መልእክት ነው::
ቅዱስ ፖሊካርፐስ ጠንካራ የኦርቶዶክስ እምነት ጠበቃ ነበር:: ዘመኑ መናፍቃን ከቀናችው የሐዋርያት ትምህርት የወጣ ልዩ ልዩ ትምህርቶችን ያፈሉበትና ምእመናንን የሚያደናግሩበት ወቅት ስለነበር እነርሱን በመርታት ትክክለኛውን የሐዋርያት ወንጌል ያስተምር ነበር:: በምንፍቅና ትምህርት የተወሰዱ ብዙዎችንም ወደ ቀናችው ትምህርት መልሷል:: ደቀ መዛሙርቱንም “ልጆቼ እባካችሁ ከስህተት ራቁ” እያለ በተደጋጋሚ ይመክራቸው ነበር:: በአስተምህሮውም ሁሉ መምህሩን ወንጌላዊ ዮሐንስን ይመስል ነበር:: ለምሳሌ ወደ ፊልጵስዩስ ከጻፈው መልእክቱ ብንመለከት:- “ማንም ኢየሱስ በሥጋ እንደመጣ የማያምን ፀረ-ክርስቶስ ነው:: በመስቀል ላይ መከራ መቀበሉን የማያምንም ዲያብሎስ ነው:: ማንም የክርስቶስን ትምህርት ለራሱ እንደሚመቸው የሚያጣምም፤ ትንሣኤና የመጨረሻ ፍርድ የለም የሚል ይህም የሰይጣን የበኩር ልጅ ነው” ይህም ነገረ ሥጋዌን የካዱትን በሚመለከት የጻፈው ሲሆን ከሐዋርያው ቃል ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል:- “የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥” (1ዮሐ. 4፥2-3):: በእስያ ብቻ ሳይሆን ሮም ድረስ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በዚያ በነበሩ መናፍቃን የተወሰዱትን ምእመናን አስተምሮ መልሷል::
ቅዱስ ፖሊካርፐስ ከሐዋርያት ትምህርት የወጣ አስተምህሮ ሲሰማ ያለቅስ ነበር፤ እጅግም ስለሚዘገንነው ሥፍራውን ለቆ ይወጣ ነበር:: ይህንንም ከሐዋርያው ዮሐንስ እንደተማረው ያደርግ ነበር፤ በነገር ሁሉ እርሱን ይመስለው ነበርና:: ቅዱስ ሄሬኔዎስ ቅዱስ ፖሊካርፐስ እንዲህ ሲል ተሰማ በማለት ጽፏል: “ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በኤፌሶን ወደ አንድ መታጠቢያ ክፍል ሲገባ መናፍቁ ቀሪንጦስን አየውና ‘ከዚህ እንሽሽ የእውነት ጠላቷ ቀሪንጦስ በዚህ አለና’ እያለ ወዲያውኑ ክፍሉን ለቆ ወጣ::” እርሱም ቀንደኛ የሆኑ መናፍቃንን መንገድ ላይ በሚያገኝበት ጊዜ እንዲሁ ያደርግ ነበር:: ወደ ሮም በተጓዘበት ወቅት መርቅያን የተባለውን መናፈቅ አየውና ትኩር ብሎ በመመልከት ሲቃወመው መርቅያን “ታውቀኛለህን” አለው:: ፖሊካርፐስም “አዎን አውቅሃለሁ፤ አንተ የዲያብሎስ የበኩር ልጁ ነህ” ብሎ መልሶለታል:: ቅዱስ ሄሬኔዎስም ለመናፍቃን ምላሽ በጻፈው መጽሐፉ ውስጥ ፍሎሪነስ ለተባለው መናፍቅ መልስ በሰጠበት ክፍል ስለፖሊካርፐስ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “. . . ነግር ግን ይህ ቅዱስ [ፖሊካርፐስን ነው] እንዳንተ ትምህርት ያለ የተሳሳተ ትምህርት ሲሰማ እንደልማዱ ፈጥኖ ጆሮውን በመያዝ እንዲህ በማለት ይጮሃል ‘አቤቱ ቸር ፈጣሪዬ ሆይ እስከዚህ ዘመን ድረስ ያቆየኸኝ ይህን ነገር ልታሰማኝ ነውን?’ . . .ወዲያውም ይህን ዓይነት የክህደት ትምህርት የሰማበትን ሥፍራ ለቆ እያለቀሰ በፍጥነት ይወጣል::”
የቅዱስ ፖሊካርፐስ የሰማዕትነቱ ዜና የተገኘው የራሱ የሆነችው የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነቱን በአካል በተከታተሉ ወንድሞች አማካኝነት ጽፋ ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከበተነችው መልእክት ነው:: በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት የሰማዕትነታቸው ሁኔታ፣ ሳይፈሩ ሰውነታቸውን ለሰይፍ ለስለት እንዴት እንደሰጡ፣ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር እንዴት ይጨክኑ እንደነበር በሙሉ ዜና ገድላቸው እየተጻፈ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይሰራጭ ነበር:: እንደ አግናጥዮስ ሁሉ (በሮም) ፖሊካርፐስ ሰማዕት በሆነበት ጊዜም በሰምርኔስ ከተማ የሕዝብ በዓል ተደርጎ ነበር:: እንደልማዳቸው በዓሉ በሚከበርበት በእስታድየማቸው የአራዊት ትርኢት ነበር:: አሬኒከስ የተባለ አንድ ክርስቲያንም የአሕዛብ ጣዖታትን ካላመለክህ ለአራዊት እንሰጥሃለን ብለውት አሻፈረኝ ብሎ በመፅናቱ በዚያ በአራዊት ተበልቶ ሰማዕት ሆነ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ ክርስቲያኖች እንዲህ እንዲፀኑ የሚያስተምራቸው ዋነኛው ፖሊካርፐስ ነው እርሱ ተይዞ ይምጣ እያሉ ጮሁ::
ቅዱስ ፖሊካርፐስ የሞት ፍርድ ሲፈረድበት ፀንቶ በከተማዋ ቢቆይም ምእመናን እንዲሸሽ እያለቀሱ ስለለመኑት ባጠገብ ወዳለች መንደር ሸሸ::በዚያ ሳለ ሰማዕት እንደሚሆን በራእይ ተረድቶ እንደሚሞት ለወንድሞችና እህቶች ነገራቸው:: ወዲያው በጥቆማ ተይዞ ወደ ሰምርኔስ ከተማ እያንገላቱ ወስደው ሕዝብ በተሰበሰበበት በበዓሉ አደባባይ አቆሙት:: እርሱም ክርስቶስ በሕዝብ አደባባይ ቆሞ የተቀበለውን መከራ እያሰበ የመከራው ተካፋይ ስላደረገው በፍጹም ደስታ መከራውን ይቀበል ነበር:: በሕዝቡ ፊት አቁሞ የሚያናዝዘው ሹም ክርስቶስን እንዲክድ ብዙ ማግባቢያዎችንና ማስፈራሪያዎችን ቢያቀርብለትም ያለፍርሃት ፀንቶ ክርስቲያንነቱን ስለመሰከረ በእሳት እንዲቃጠል ተፈረደበት:: ወታደሮቹ እሳቱ ውስጥ ከገባ በኋላ የሚያመልጠን መስሏቸው ለማጠር ሲዘጋጁ አይቶ “ወደ እሳቱ እንድገባ ያበረታኝ ጌታዬ በእሳቱ ውስጥም ፀንቼ እንድቆይ ያስችለኛል” አላቸው:: ወታደሮቹ እጅና እግሩን አስረው ወደ እሳቱ ሲያቀርቡት አይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ በማለት የመጨረሻ ጸሎት አደረገ:- “አቤቱ ልዑል እግዚአብሔር የተወደደው ልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሆይ በልጅህ አንተን እንድናውቅ ሆነናል:: የመላእክትና የኀይላት እንዲሁም የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ አንተ ነህ፤ ፍጥረታትም ሁሉ የሚኖሩት ባንተ ነው:: በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ለዘላለማዊ ሕይወት ትንሣኤ ያለፍርሃት ከክርስቶስ መከራ ተካፋይ ከሆኑት ከሰማዕታት ወገን እንድቆጠር ስላደረግኸኝ እና በዚህች ቀንና ሰዓት በሚገባ ስላስተማርኸኝ አመሰግንሃለሁ:: እንደ እነርሱ ዛሬ በፊትህ ተቀብያለሁና እንደ መልካምና የተወደደ መሥዋዕት አድርገህ ተቀበልልኝ:: አንተ አስቀድመህ እንዳሳየኸኝ እና እንዳዘጋጀኸኝ : አንተ እውነተኛና ታማኝ አምላክ ነህና ስለሁሉ ነገር አመሰግንሃለሁ፣ አከብርሃለሁ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ:: ከሰማያዊው ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ከተወደደው ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ: ከእርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብርና ምስጋና ለአንተ ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን!”
የጸሎቱ ይዘት ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታስተምረው ምሥጢረ ሥላሴ ጋር አንድ አይነት ሲሆን ይህንኑም የመሰለ ጸሎት አላት:: በዚህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጥንታዊና ከምንጮቹ ከሐዋርያት የተረከበችው ለመሆኑ ታላቅ ማስረጃ ነው:: ቅዱሱ ጸሎቱን ሲጨርስ በእሳቱ ውስጥ ወረወሩት:: በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ተአምር የሚሠራ እግዚአብሔር ለምእመናን መጽናኛ የሚሆን ድንቅ ተአምርን አደረገ:: እሳቱ የቅዱሱን ሰውነት ዙሪያውን እንደግድግዳ ከቦ የማያቃጥለው ሆነ;: ሕዝቡም እሳቱ እንዳላቃጠለው ባዩ ጊዜ በጦር ተወግቶ ይሙት እያሉ ጮሁ፤ ወታደሮቹም በጦር ወጉትና በዚህ ሰማዕትነቱን ፈጸመ:: ክርስቲያኖች እንዳያመልኩት በሚል የከበረ ሥጋውን አቃጠሉ፤ በዚህ ጊዜ ደስ የሚያሰኝ የእጣንና የሽቶ መአዛ ሸተተ:: ክርስቲያኖችም ተረፈ አፅሙን በክብር ወሰደው ቀበሩት ቤተ ክርስቲያንም በስሙ ሠሩለት:: (ወ/ሮ ዘውዴ ገ/እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ሐዋርያዊ ጳጳስ ወሰማዕት፣ 2001 ዓ,ም.)
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለእኛም የሰማዕታት ጽናታቸውን አድሎ ከበረከታቸው ይክፈለን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages