ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 29 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, March 7, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 29

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን ታላቋ ሐዋርያዊት እናታችን የእመ ምኡዝ #ቅድስት_ፍቅርተ_ክርስቶስ ዕረፍቷ ነው፣ የአርሞኒ ሀገር ኤጲስቆጶስ የከበረ #ቅዱስ_ቢላካርዮስ በሰማዕትነት ሞተ።


የካቲት ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን ታላቋ ሐዋርያዊት እናታችን የእመ ምኡዝ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት ዕረፍቷ ነው፡፡
እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስ ወይም እመ-ምዑዝ በጎንደር ክፍለ ሀገር በደራ ፎገራ አንበሳሜ በሚባለው ቦታ የአብርሃምና የሣራ ምግባር ካላቸው ከአባቷ ከላባ ከእናቷ ከወንጌላዊት ጌታችን በተወለደበት ዕለት ታኅሣሥ 29 ቀን በታዘዘ መልአክ አብሳሪነት ተወለደች፡፡ በተወለደችም ጊዜ በእግሯ ቆማ ‹‹በማኅየዊ ቸርነትህ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላወጣኸኝ ለአብ ምስጋና ለወልድ ምስጋና ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል›› ብላ አምላኳን አመስግናለች፡፡ ቤተሰቦቿ ያገኙዋት በስዕለት ሲሆን ስመ ክርስትናዋም ማርያም ጸዳለ ተባለ፡፡ ፍቅርተ ክርስቶስ የሚለው የቆብ (የምንኩስና) ስሟ ነው፡፡ ዕድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ እግዚአብሔር የላከው አንድ ደገኛ መነኩሴ ወደ እርሷ በመሄድ የዳዊትን መዝሙር፣ የብሉያትና የሐዲሳት መጻሕፍትንና የቤተክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ በሚገባ አስተምሯታል፡፡
እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስ በነበረችበት ዘመን ዐፄ ሱስንዮስ ‹‹ሁለት ባሕርይ›› የሚለውን የረከሰ የሮማውያንን ሃይማኖት የአገራችን ሕዝዝ ሁሉ እንዲያምን በማወጁ ምክንያት በሀገራችን ከፍተኛ የሆነ የሃይማኖት ግጭት ስለተነሣና ከ8ሺህ በላይ ክርስቲያኖች በግፍ ተጨፍጭፈው ሲያልቁ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ከእነ አቡነ ስምዖንና ከሌሎችም ቅዱሳንና ቅዱሳት ጋር ተሰልፋ ሰማዕትነትን ተቀብላ ለሃይማኖቷ መስክር ሆናለች፡፡ ባለቤቷ ዘርዐ ክርስቶስም በሰማዕትነት ዐርፎ ሰባት አክሊላት ወርደውለታል፡፡
ዐፄ ሱስንዮስ ለፖለቲካዊ ጥቅም ብሎ የረከሰች የሮማውያንን ሃይማኖት በአገራችን ላይ እንዳወጀ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖን ካህናትንና ክርስቲያን ልጆቻቸውን አነሳስተው እያስተማሩና እያጠነከሩ እያለ በጦር ተወግተው በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖንም በሰማዕትነት ከማረፋቸው በፊት ግን እነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን፣ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስን፣ ቅድስት አካለ ክርስቶስን፣ ቅድስት እመ ወተትንና ሌሎቹንም ቅዱሳንና ቅዱሳት አነሳስተው ባራ ሄደው ንጉሡን መክረውታል፣ ገሥጸውታል፡፡ ንጉሡ ግን ከፍተኛ ፖሊቲካዊ ጥቅም እንደሚያገኝ ሮማውያን ቃል ገብተውለት ስለነበር ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶ አብዝተው ቢመክሩትም ከክህደቱ ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይልቁንም ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን የሃይማኖቷን ጽናት ስላየ ሥጋዋ እየተቆረሰ መሬት ላይ እስኪወድቅ ድረስ በብረት በትር አጥብቆ ያስገርፋት ጀመር፡፡ በመጨረሻም ምድር እየሰወረቻት ለመግረፍ የማይመቻቸው ቢሆን ከሌሎቹ ሰማዕታት ጋር አንገቷን በሰይፍ አስቆርጦታል፡፡ በዚህም ጊዜ ፍጹም ጨለማ ሆኖ ምድርም ተነዋወጠች፡፡ ስምንት ሺህ አሥር ቅዱሳንም በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን አንገቷን በሰይፍ ቢቆርጧትና በሞት ብታርፍም ነገር ግን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ገነትንና ሲኦልን አሳይቶ 14 ቀን በሰማያዊት ኢየሩሳሌም ከተቀመጠች በኋላ እንደገና እንደተኛ ወይም ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ከሞት አስነሥቶ ወደ ቦታዋ መለሳት፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልም ከሞት ካስነሣት በኋላ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ መናኒ ሆና በየገዳሙና በየአድባራቱ እየሔደች ዓለምን ስትዞር ያቀናቻቸው ብዙ ገዳማት አሉ፡፡ ለምሳሌ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ በሆኑት በአባ ጉባ ተመሥርታ በግራኝ ወረራ ጠፍታ የነበረችውን ራማ ኪዳነምሕረት አንድነት ገዳምን አቅንታ የወንድና የሴት ገዳም ብላ ሥርዓት ሠርታለች፡፡ ወደ ኢየሩሳሌምም በመሄድ ላይ ሳለች በመንገድ ሰውን የሚበሉ ፍጡሮች ወደሚኖሩበት አካባቢ ስትደርስ 60 የሚሆኑ አገልጋዮቿን ለመብላት ይዘው ሳር ቅጠል እንዲበሉ በማድረግ ዐይናቸውን በጉጠት በማውጣት 4 ወራት በጨለማ ቤት ውስጥ ዘጉባቸው፡፡ ሰይጣንንም ያመልኩ ነበርና ከ4 ወራት በኋላም በዓል አድርገው ለመብላት ከእሳት ውስጥ ጨመሯቸው፣ ነገር ግን ጌታችን በቸርነቱ ጠብቋቸዋልና እነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን ምንም አልሆኑም፡፡ ያንጊዜም ሰው በላዎቹ ‹‹እናንተ ሰዎች ምንድን ናችሁ?›› ብለው ጠየቋቸው። ቅድስት እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስም ክርስቲያን መሆናቸውንና እነርሱ የሥላሴ ሕንፃ የሆነውን የሰውን ልጅ መብላት እንደሌለባቸው ብታስተምራቸው ‹‹ምን እንበላለን?›› አሏት፡፡ እርሷም ከራማ ኪዳነ ምሕረት ስትነሳ የእህል ዘርን ለአገልጋዮቿ አሰይዛ ስለነበር ከዚያ ስንዴ ወስዳ ዘራችው፡፡ ስንዴውም በአንድ ቀን ብቻ ተዘርቶ በቅሎ፣ ታጭዶ፣ ደርቆ፣ ተፈጭቶ ለምግብነት በቅቷል፡፡ ቅድስት እናታችንም ቀምሳ ስታቀምሳቸው እንደማር እንደወተት የሚጣፍጥ ሆኖላቸው በደስታ ተመግበውታል፡፡ ከዚያም እንደዚህ እያደረጉ እየሠሩ እንዲበሉ አስተምራ አስጠምቃቸው ስድስት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርታላቸዋለች፡፡ ወንጌልን፣ ስንክሳርን፣ ሃይማኖተ አበውን፣ ግንዘትን፣ መዝሙረ ዳዊትን፣ አርጋኖንን ሁሉ በእጇ ጽፋ አስቀመጠችላቸው፡፡ እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስ ምን ያህል የከበረች ‹‹ሐዋሪያዊት›› እንደሆነች ከዚህ ልብ ይሏል፡፡
የብርሃን እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ተገልጣላት በልጇ ምክንያት ስለደረሱባት ሀዘኖች አውርታላታለች፡፡ የፈለገችውንም እንድታደርግበት በእጇ ያለውን መስቀል ለፍቅርተ ክርስቶስ ሰጥታታለች፡፡ በዚህም መስቀል እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስ ባሕር ከፍላ ደቀ መዛሙርቶቿን አሻግራለች፡፡ የአባታችን የቅዱስ ኤዎስጣቴዎስን ገድል በማንበብና በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እርዳታ ባህሩን በአጽፏ ተሻግራ ወደ ሀገረ ናግራን ሄዳለች፡፡ እንዲሁም በበትረ መስቀሏም እንደ ዘርዐ ቡሩክ ከባሕር ውስጥ የሠጠሙ የደቀ መዛሙርቶቿን መጻሕፍት ምንም ሳይሆኑ ማውጣት ችላለች፡፡ እናታችን በሁሉም ሀገር እየዞረች ቅዱሳት መካናትን ትሳለም ነበር፡፡ በደብረ ዳሞም ሄዳ ‹‹ሴቶች መውጣት አይችሉም›› ቢሏት በሀዘን ስታለቅስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በሥውር ወስዶ ከዓምባው ላይ አውጥቶ ከቤተ መቅደሱ አድርሷታል፣ አቡነ አረጋዊም ተገልጸውላት ባርከዋታል፡፡ በዚያም ሥጋ ወደሙን በእጃቸው ተቀብላለች፡፡ እናታችን ወደ ኢየሩሳሌምም ሄዳ ቅዱሳት መካናትን እየተሳለመች ለ7 ዓመታት ቆይታለች፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም በዓምደ ብርሃን እየመራት ተመልሳ ወደ ሀገራችን መጥታ በድጋሚ ከሱስንዮስ ጋር ተሟግታለች፡፡ ሙታንንም እያስነሳች እንዲመሰክሩለት ብታደርግም እርሱ ግን ከጥፋቱና ከክህደቱ ሊመለስ አልቻለም፡፡ ነገር ግን እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስ የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ መልእክቷንም በንስር አሞራ አድርጋ እየላከች ትመክረው ነበር፡፡
በአንድም ወቅት በሀገራችን የእህል መታጣት ሆነና ቅድስት እናታችን ዘወትር እንደምታደርገው የኪዳምሕረትን ዝክር ልታደርግ ብላ ዝክሩን የምታደርግበት እህል አጣች፡፡ ደናግል ልጆቿንም ጠርታ ትንሽ ዱቄት እንዲያመጡላት ነግራቸው አመጡላት፡፡ በዚያችም ትንሽ ዱቄት ላይ ጸሎት አድርጋ ከጨረሰች በኋላ ‹ወደ ቦታው መልሱት› አለቻቸው፡፡ በማግስቱም እንስራው ጋኑ ሁሉ በዱቄት ተሞልቶ አግኝተውታል፡፡ ቅድስት እናታችንና ልጆቿም የየካቲት ኪዳነ ምሕረትን በዓል በታላቅ ደስታ አክብረዋል፡፡
መልአኩም እናታችንን ከቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም መልሶ ወደ ኢትዮጵያ ካመጣት በኋላ ዛሬ ገዳሟ ካለበት ቦታ ስትደርስ ከቦታዋ ላይ ዓምደ ብርሃን ተተክሎ በቀስተ ደማና ተከቦ አይታ ‹‹ይህች ቦታ ምንታምር›› ብላ ጠራቻት፡፡ በመድኃኔዓለምም ትእዛዝ የቅድስት ኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያን በአንዲት ቀን ብቻ ሠርታለች፡፡ ቦታዋ ዛሬም ድረስ ‹ምንታምር› እየተባለች የምትጠራ ሲሆን ቅድስት እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስ የሠራቻት በስሚዛ (በሰንሰል) እንጨት፣ በአይጥ ሐረግ፣ በነጠላ ማገር አድርጋ የግድግዳ ቤተ መቅደስ በአንዲት ቀን ብቻ ሠርታ በታኅሣሥ 16 ቀን በዕለተ እሁድ ቅዳሴ ቤቷን አክብራለች፡፡ በዚህም ጊዜ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤልና ቅዱስ መሲፋይል በክንፋቸው አፈር ከኢየሩሳሌም አምጥተው በቦታዋ ላይ ቀላቅለውበታል፡፡ ጌታችንም ከብርሃን እናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ለፍቅርተ ክርስቶስ ተገልጦላት ቦታዋን ባርኮላት እስከዕለተ ምፅዓትም ድረስ እንደማትፈርስ ቃልኪዳን ገብቶላታል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ከባድ የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ጫካውን ሁሉ ሲያቃጥል ከቤተክርስያኗ ላይ ግን ለምልክት ያህል ጫፏ ላይ ያለችውን የሰጎን እንቁላል ብቻ አቃጥሎ ቤተ መቅደሷን አልፎ ሄዶ ጫካውን ሁሉ አቃጥሏል፡፡
እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስ በአንዲት ቀን ብቻ በተአምራት የሠራቻት ቤተ ክርስቲያኗ ተሠርታ ባለቀች ጊዜ ጌታችን ለእናታችን ተገልጦላታል፡፡ ጌታችንም በተገለጠላት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ በአራቱም አቅጣጫ ለጌታችን ሰግዳለች፡፡ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያኗ በአራቱም አቅጣጫ ሆነው ሲመለከቷት በተቃራኒው አቅጣጫ እየሰገደች ትታያለች፡፡ በምሥራቅ አቅጣጫ ሆነው ቢያዩዋት ወደ ምዕራብ ሰግዳ ትታያለች፤ በምዕራብም ሆነው ቢያዩዋት ወደ ምሥራቅ ሰግዳ ትያለች፡፡ በሰሜን አስራቅ አቅጣጫ ሆነው ቢያዩዋት ወደ ደቡብ ሰግዳ ትታያለች፤ በደቡብም ሆነው ቢያዩዋት ወደ ሰሜን ሰግዳ ትያለች፡፡
እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስ በተሰጣት ቃልኪዳን መሠረት በገዳሟም ውስጥ መርዘኛ እባብም ቢሆን ሰውን ወይም እንስሳትን ቢነድፍ መርዙ ምንም አይጎዳም፡፡ እንዲሁም ጌታችን ገዳሟን መናፍቃን ወይም ከሐዲያን እንደማይረግጧት ቃልኪዳን ሰጥቷታል፡፡ ለምሳሌ የጣሊያን ጦር በሀገራችን የተለያዩ ገዳማትን እያጠፋ መነኮሳትን እየገደለ ከፍተኛ ጥፋት ባደረሰበት ወቅት ይህችንም ገዳም ለማጥፋትና መነኮሳቶቹንም ለመግደል መጥቶ ነበር፡፡ መነኮሳቶቹም ይህን ሰምተው ለሰማዕትነት ተዘጋጅተው ጠበቁ ነገር ግን የጦር አዛዡና ሠራዊቱ የገዳሟን ክልል አልፈው መግባት አልቻሉም፣ የገዳሟ ክልል ላይ ሲደርሱ በተአምራት እግራቸው ተሳስሮ መቆም መቀመጥ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የጦር አዛዡም ‹‹ክርስቶስ ከዚች ገዳም አለ›› ብሎ ሃምሳ ጠገራ ብር ሰጥቶ ወደመጣበት ተመልሷል፡፡
መድኃኔዓለም ክርስቶስ በዚህች ገዳም ላይ ለቅድስት እናታችን ድንቅ ድንቅ ቃልኪዳን ከሰጣት በኋላ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በየካቲት 29 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፋለች፡፡ በሥጋዋም ላይ ታላቅ የብርሃን አምድ ተተክሎ የታየ ሲሆን እንደፀሐይም ከጠዋት እስከ ማታ ያበራ ነበር፡፡ በመካነ መቃብሯም ላይ እስከ አርባ ቀን ድረስ ብርሃን ተተክሎ ታይቷል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት የአርሞኒ ሀገር ኤጲስቆጶስ የከበረ ቢላካርዮስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም አባት ፈጽሞ እስከ አረጀ ድረስ በተሾመበት ወንበር ብዙ ዘመናት ኖረ ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትንም ደረሰ እሊህም ስለከበረች የልደት በዓልና ስለ እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስለ ሞትና ስለ መቃብር በኃጥአንም ላይ ስለ ሚደርስባቸው ሥቃይ ስለ መድኃኒታችንም የረቀቀ ጥበብ ስለ ከበሩ በዓላትም ናቸው ሕይወት በሆኑ ትምህርቶቹም ብዙ ነፍሳትን መሥዋዕትን አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ።
በክርስቲያንም ወገኖች ላይ የስደትና የመከራ ወራት በሆነ ጊዜ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደሙን ሊያፈስ ወደደ ሕዝቡንም ሰብስቦ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ አዘዛቸው። ስለ ጌታችን ኢየሱስ ደሙን ሊያፈስ ይሻልና እነርሱ እንግዲህ ፊቱን እንደማያዩት ነገራቸው። ሰምተውም አለቀሱ ስለ መለየታቸውም እጅግ አዘኑ የሙት ልጆች እንሆን ዘንድ ለምን ትተወናለህ አሉት ማስቀረትና ማስተውም ባልተቻላቸው ጊዜ ከእርሳቸው ዘንድ ወጥቶ ወደ መኰንኑ ሔደ በፊቱም ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ብዙ አሰቃየው። ሕዝቡም ብዙ ልመናን አብዝተው ለመኑት ራስህን አድን ከከተማም ውጣ አሉት እርሱም ልባቸውን ደስ ያሰኝ ዘንድ በሥውር እወጣለሁ አላቸው።
በዚያችም ሌሊት ሰማዕትን ትሆን ዘንድ የተመኘኸውን በጎ ምክር ለምን ረሳህ እንደሚለው ሰው ሁኖ ራእይን አየ። ከዚህም በኋላ ተመልሶ ለመኰንኑ ተገለጠለት በዚያንም ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ሥጋውንም ምእመናን አንሥተው ወሰዱት ለኤጲስቆጶሳትም እንደሚገባ አክብረው ገንዘው በመቃብር አኖሩት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages