ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት 30 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, March 9, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት 30






አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ሠላሳ በዚህች ዕለት የመጥምቁ ዮሐንስ የከበረች ራሱ ተገኘች። ይህም እንዲህ ነው ከሀዲ ኄሮድስ የከበረ ዮሐንስን ራሱን ይቆርጡት ዘንድ በአዘዘ ጊዜ በእሥር ቤት ራሱን ቆርጠው ወደ ኄሮድስ አቀረቧት እርሱም ለወገኖቹ በማሳየት በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ስለ አደረገው ሥራ እንደሚያዝን ገለጠላቸው የክቡር ዮሐንስንም ራስ በቤቱ ውስጥ አስቀራት።
የፊተኛዪቱ ሚስቱ የንጉሥ አርጣ ልጅ ግን በአበረራት ጊዜ ወደ አባቷ መጥታ በፊቱ አለቀሰች ኄሮድስ በእርሷ ላይ ያደረገውን ሁሉ እርሷን አሳዶ የወንድሙን ሚስት ኄሮድያዳን እንዳገባ ነገረችው። በዚያንም ጊዜ ንጉሥ አርጣ ተቆጥቶ ተነሣ ሠራዊቱንም ሰብስቦ ወደ ገሊላ ዘመተ የገሊላንም ሀገሮች ሁሉ አጠፋ በእሳትም አቃጠለ።
ንጉሥ ጢባርዮስ ቄሣር ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ኄሮድስ በአባረራት በልጁ ምክንያት ንጉሥ አርጣ ይህን እንዳደረገም በአስረዱት ጊዜ ስለዚህ ንጉሥ ጢባርዮስ ቄሣር ተቆጣ ኄሮድስንም ወደ ሮሜ ከተማ ወደርሱ አስቀረበው በእርሱም ምክንያት የሀገሮች ጥፋት በመደረጉና ታላቁን ነቢይም ስለ መግደሉ ከሹመቱ ሻረውና እንድልኩ ወደሚባል አገር አጋዘው በዚያም በክፉ አሟሟት ሞተ።
የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ግን በኄሮድስ ቤት ተቀብራ ትኖር ነበር ከዚህም በኋላ ንጉሥ ጢባርዮስ ጭፍሮቹን ልኮ የኄሮድስን ቤት አስፈረሰ ጥሪቱን ሁሉ ወሰደ ለሚያየውም ሁሉ አርአያና ተረት ሆነ ያለ ጣሪያና ያለ ደጃፍ ቀርቷልና ነጋዴዎችም መነሃሪያ አድርገው ያድሩበት ነበር።
በዚያንም ወራት በገንዘብ ድኆች በሃይማኖት ባለጸጎች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ እነርሱም ሊሰግዱ የከበረች የአርባ ቀን ጾምንም ሊጾሙ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ ይህም ከብዙ ዘመን በኋላ ነው።
ምሽትም በሆነ ጊዜ ምድረ በዳ በሆነ በኄሮድስ ቤት ውስጥ አደሩ ቅዱስ ዮሐንስም ከእርሳቸው ለአንዱ በሕልም ተገለጠለትና የከበረች ራሱ ያለችበትን ቦታ አስረዳው ወደቤቱም ተሸክሞ ይወስዳት ዘንድ አዘዘው በነቃም ጊዜ ራእይን እንዳየ ለባልንጀራው ነገረው።
ቅዱስ ዮሐንስም ወደአመለከተው ወደዚያ ቦታ ተነሥተው በአንድነት ሔዱ በቆፈሩም ጊዜ የሸክላ ዕቃ አግኝተው ከፈቷት ያን ጊዜ እጅግ የሚመስጥ በጎ መዓዛ ወጣ የቅዱስ ዮሐንስንም ራስ አገኙዋት ከእርሷም ተባረኩ ወደ ሸክላውም ዕቃ መለሱዋትና በፊት እንደ ነበረ አፉን ዘጉ ያም ሰው ከእርሱ ጋር ወደ ቤቱ ወሰዳት ታላቅ ክብርንም አከበራት ሁል ጊዜም የሚያበሩ መብራቶችን በፊቷ አኖረ።
የዚያም ሰው ዕረፍቱ በቀረበ ጊዜ ለእኅቱ ነገራት እርሷ ቅድስና ስለአላት እርሱ ሲሠራው እንደነበረ ትሠራ ዘንድ አዘዛት እርሷም የምታከብራትና ሁል ጊዜ መብራትንም የምታበራ ሆነች።
የቅዱስ ዮሐንስም ራስ ወደ አርዮሳዊ ሰው እስከ ደረሰች ድረስ ከአንዱ ሰው ወደ አንዱ ሰው የምትፋለስ ሆነች ይህም ሰው በከሀዲው አርዮስ እምነት ውስጥ እያለ የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ድንቆች ተአምራቶችን እንደምታደርግ ያስብ ነበር።
የከበረ ዮሐንስም ከእርሱ የሚበልጥ ሰው በላዩ አስነሣበትና ከዚያ ቦታ አሳደደው ያም ቦታ አባ ቄርሎስ በኢየሩሳሌም ሀገር አባ አንያኖስ በሀገረ ኀምዳ ኤጲስቆጶስነት እስከ ተሾሙ ድረስ ፈጽሞ ሰው የማይኖርበት ምድረ በዳ ሆነ።
ቅዱስ ዮሐንስም ለአባ አንያኖስ በሕልም ተገልጦ የከበረች ራሱ ያለችበትን ቦታ ነግሮ አመለከተው አባ አንያኖስም ሒዶ እንደ ዛሬው ግንቦት ሠላሳ ከዚያ አወጣት ይህም የካቲት ሠላሳ ቀን ከአገኙዋት በኋላ ዳግመኛ ያገኙበት ነው።
እንዲህም የሚል አለ የከበረ ዮሐንስ አፈወርቅ ተናገረ ይህም ኄሮድስ በአዘዘ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በእሥር ቤት ሳለ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው በጻሕል አድርገው ወደ ኄሮድስ አመጡለት እርሱም ለኄሮድያዳ ልጅ ሰጣት እርሷም ለእናቷ ወስዳ ሰጠች።
ይቺም የረከሰች አመንዝራ ልትዳስሣት በወደደች ጊዜ በወጭቱ ውስጥ ጠጒሩዋ ተዘርግቶ ወደ አየር በረረች በአየርም ሁና የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም እያለች የምትጮኽ ሆነች እንዲህም እያለች ዐሥራ አምስት ዓመት ኑራ በዓረቢያ ምድር ዐረፉ በዚያ ተቀበረች።
ነጋድያንም በዚያ ቦታ የሚያድሩ ሆነ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ሁለት አማንያን ነጋዴዎች ወደዚያ ቦታ ደርሰው አደሩ ቅዱስ ዮሐንስም በሕልም ተገለጠላቸውና የከበረች ራሱን ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው እነርሱም አወጡዋት ከእርሳቸውም ጋር ወደ ቤታቸው ወስደው ታላቅ ክብርን አከበሩዋት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም መለኮትን በአጠመቀ በከበረ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን፤ ልዩ የሆነች በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages