ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 1 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, March 9, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 1

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት አንድ በዚህች ቀን የኢየሩሳሌም አገር ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_በርኪሶስ አረፈ፣ የሰማዕቱ #የቅዱስ_እለእስክንድሮስ መታሰቢያው ነው፣ የሄኖክ ልጅ #ቅዱስ_ማቱሳላህ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡




መጋቢት አንድ በዚህች ቀን የኢየሩሳሌም አገር ኤጲስቆጶስ ቅዱስ በርኪሶስ አረፈ። ይህም አባት ክርስቲያኖችን በሚወዳቸው በቄሣር እለእስክንድሮስ ዘመነ መንግሥት ተሹሞ ሳለ ሐዋርያት ሲጠብቋቸው እንደነበረ በበጎ አጠባበቅ ሕዝቡን ጠበቃቸው።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ እለእስክንድሮስ ሞተ ከእርሱም በኋላ ቄሣር መክስሚያኖስ ነገሠ፡፡ ክርስቲያኖችንም በጽኑዕ መከራ አሠቃያቸው ከእርሳቸውም ብዙዎችን ገደላቸው። ሀገሮቻቸውን ትተው የተሰደዱም አሉ። ይህም አባት ሽሽቶ ወደ ገዳም ገባ ሕዝቡም ፈልገው አጡት።
ከዚህም በኋላ ስሙ ዲዮስ የተባለ ሌላ ኤጲስቆጶስ በላያቸው ሾሙ። እርሱም በጥቂት ቀን አረፈ። ከዚህ በኋላ ስሙ አግርንዲኖስ የሚባል ሌላ ኤጲስቆጶስ ሾሙ።
የስደቱም ወራት በአለፈ ጊዜ ይህ አባት በርኪሶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ተመለሰ። አግርንዲኖስ የሚባል ሌላ ኤጲስቆጶስ ሹመው አገኛቸው።
ወደርሳቸውም በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ በመምጣቱ ደስ አላቸው አግርንዲኖስም ተመልሶ በመንበረ ጵጵስናው ላይ እንዲቀመጥ ለመነው በታላቅ ድካምም በወንበሩ ላይ አስቀመጡት። ከአግርንዲኖስም ጋራ አንዲት ዓመት ኖረ አግርንዲኖስም አረፈ።
አባ በርኪሶስም እጅግ እስኪያረጅና እስኪደክም ድረስ ኖረ ወገኖቹንም ሌላ ኤጲስቆጶስ በላያቸው እንዲሾሙ ለመናቸው እነርሱም አይሆንም አሉ።
በዚያም ወራት የቀጰዶቅያ ኤጲስቆጶስ ስሙ እለእስክንድሮስ የሚባል አንድ ሰው ነበር። እርሱም በውስጥዋ ሊጸልይና ወዳገሩ ሊመለስ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። ሥራውንም በጨረሰ ጊዜ የበዓሉም ቀኖች በተፈጸሙ ጊዜ ወዳገሩ ሊመለስ ወደደ።
በመድኃኒታችን ትንሣኤ በዓል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መግቢያ ወደ ዕገሌ ደጃፍ ውጡ ወደ ደጃፉ መጀመሪያ የሚገባውን ያዙት በጵጵስና ሥራም ይረዳው ዘንድ ከበርኪሶስ ጋራ አድርጉት የሚል ቃል እነሆ ተሰማ።
ወጥተውም ወደ ደጃፉ በደረሱ ጊዜ እለእስክንድሮስን አገኙት ይረዳውም ዘንድ ያለ ፈቃዱ ከአባት በርኪሶስ ጋራ አደረጉት። እስከሚአርፍበትም ጊዜ አብሮት ኖረ።
መላ የሕይወቱ ዘመን አንድ መቶ አሥራ ሰባት ዓመት ሆነ ኤጲስቆጶስነት ሳይሾም ሰማንያ አንድ ዓመት ኖረ በሹመቱም ላይ ሠላሳ ስድስት ዓመታትን ኖረ። እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የሰማዕቱ የቅዱስ እለእስክንድሮስ መታሰቢያው ነው። ይህም ቅዱስ ሰማዕት የሮም ሀገር ሰው ነው ለእርሱ ባለመታዘዙና ለረከሱ ጣዖቶቹ ባለመሠዋቱ ከሀዲው መክስሚያኖስ ጽኑዕ ስቃይን አሠቃየው።
እጅግ ከባድና ታላቅ የሆነ ደንጊያ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ አሥሮ ሰቀለው። ብዙ ግርፋትንም ገረፈው ጐኖቹንም ቀደደ በፊቱም ላይ የእሳት መብራት ጨመሩ።
ሥቃዩንም ባልፈራ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕታትን አክሊል ተቀዳጀ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የሄኖክ ልጅ የማቱሳላህ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ እርሱም 969 ዓመት የኖረ ሲሆን የአዳም 7ኛ ትውልድ የሆነው የሄኖክ ልጅ ነው፡፡ አዳም ሴትን ወለደ፣ ሴት ሄኖስን፣ ሄኖስ ቃይናን፣ ቃይናን መላልኤልን፣ መላልኤል ያሬድን፣ ያሬድ ሄኖክንመ ሄኖክ ማቱሳላህን ወለደ፡፡ ማቱሳላህም ላሜሕን ወለደ፣ ላሜህም ኖኅን ወለደ፡፡ ማቱሳላህም 969 ዓመት ከኖረ በኋላ ዐረፈ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን ልዩ የሆነች በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages