ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 5 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 5

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር አምስት በዚህች ዕለት #የአቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ የልደታቸው መታሰቢያ የለውጥ በዓል ነው፣ በከሀዲው ዑልያኖስ ዘመን የከበረ #ቅዱስ_አውስግንዮስ_አረጋዊ ምስክር ሁኖ ሞተ፣ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #ቅዱስ_አባ_ማቴዎስ አረፈ፡፡


ጥር አምስት በዚህች ዕለት የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የልደታቸው መታሰቢያ የለውጥ በዓል ነው፡፡ ትውልድ አገራቸው ደቡባዊ ግብፅ ከቆላው ልዩ ስሙ ከንሒሳ አካባቢ ነው፡፡አባታቸው ስም ቅዱስ ስምዖን እናታቸው ስም ቅድስት አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ወላጆቻቸው በእግዚአብሔር ፊት ደጋጎች የነበሩ ቢሆኑም አቅሌስያ መካን ሆና ልጅ በማጣቷ እያለቀሰች 30 ዘመን ኖራለች፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሥዕል ካለበት ፊት ለፊት በመቆም እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣት ዘንድ አልቅሳ ስትለምን ያንጊዜ ከሥዕሉ ቃል ወጥቶ "ክቡሩ ከሰማይ ከምድር ከፍ ከፍ የሚል፣ከሚካኤል ከገብርኤል ጋር በክብር የሚተካከል ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ ንጽሕናው እንደ እንደ ነቢይ ኤልያስ፣እንደ መጥምቁ ዮሐንስ የሆነ በክብር ከነቢያትና ከሐዋርያት ጋር የሚተካከል ልጅ ትወልጃለሽ አሏት።ይኸውም ለአንቺ ብቻ አይደለም ለዓለሙ ሁሉ ነው እንጂ።ያን ጊዜ ከሦስቱ አንዱ ተነሥቶ በእጁ ባርኮ በሰላም ወደ ቤትሽ ግቢ አሏት"።እርሷም ደስ እያላት ወደ ቤቷ ገባች፡፡
ቅድስት አቅሌስያም በመጋቢት 29 ቀን ፀንሳ በታኅሣሥ 29 ቀን ደም ግባቱ እጅግ የሚያምር ወንድ ልጅ እንደወለደች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል መጥቶ "የዚህ ልጅሽ ስሙ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን"አላት፡፡ ወዲያውም ሕፃኑ ተነሥቶ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሦስት ጊዜ ሰገደ፡፡ ዳግመኛም ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን" አለ፡፡
የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓለ ልደት ታህሳስ 29 በጌታችን ልደት ነው:: ነገር ግን ዕለቱ ትልቅ ሚስጥር የያዘ ነውና አባቶቻችን የጌታ ልደት ዘምረው ጣዕሙ ሳያልቅ ቅዳሴ ይገባሉ:: ስለዚህ የአባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ከሚቀር ልደታቸው ጥር 5 እንዲከበር ስርዓት ሰርተዋልና በዓለ ልደታቸው በዚህች ቀን ተከብሮ ይውላል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን በከሀዲው ዑልያኖስ ዘመን የከበረ አውስግንዮስ ምስክር ሁኖ ሞተ።
ይህም ከንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ጭፍሮች ውስጥ ነው እርሱም እግዚአብሔርን የሚያመልከው ለድኆችና ለምስኪኖች የሚመጸውት ነው መስቀልም እንደ ክዋክብት በሰማይ እያበራ ለንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማመኑ በፊት በተገለጠለት ጊዜ ይህ ቅዱስ አውስግንዮስ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንዲህ አለው። ይህ ለክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምልክቱ ነው በዚህም ጠላቶችህን ታሸንፋለህ።
ያን ጊዜ ከቈስጠንጢኖስ ሠራዊት ውስጥ ከዚህ ቅዱስ ሰው በቀር የክርስቶስን ስም ይጠራ ዘንድ የደፈረ የለም። ቈስጠንጢኖስ በከበረ መስቀል ምልክት ጠላቶቹን ድል በአደረገ ጊዜ ዕውነተኛ ክርስቲያን ሆነ የሃይማኖትንም ሥልጣን አቁሞ ከፍ ከፍ አደረገ።
ይህም ቅዱስ አውስግንዮስ እድሜው መቶ ዐሥር ዐመት እስከ ሆነው ከቈስጠንጢኖስና ከልጆቹ ዘመነ መንግሥት በኋላ እስከ ከሀዲው ዑልያኖስ ዘመን ኖረ።
በአንዲት ዕለትም በአንጾኪያ ከተማ በአደባባይ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲመላለስ ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አግኝቷቸው ሊያስታርቃቸውና በመካከላቸው ሰላም ሊያደርግ ወዶ አስታረቃቸው በመታረቃቸውም ደስታ አደረጉ እርሱ የከበረ አረጋዊ ሰው ነውና።
ከዚያም አንድ ክፉ ሰው ወደ ንጉሥ ዑልያኖስ ሒዶ ነገር ሠራበት እንዲህም አለው አውስግንዮስ በራሱ ፈቃድ ገዥና ፈራጅ ዳኛ ሆነ። ንጉሥም ይህን ቅዱስ ወደርሱ አቅርቦ ገሠጸው ገዥና ፈራጅ ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማነው አለው።
የከበረ አውስግንዮስ መልሶ ነፍስህ በእጁ የተያዘች የእግዚአብሔርን አምልኮት ትተህ አንተ ለረከሱ ጣዖታት ለምን ሰገድክ ከአንተ በፊት የነበሩ ነገሥታትን ለምን አልተከተልካቸውም እኔም እንዳንተ ወታደር ሁኜ ከቈስጠንጢኖስ ጋር ሃያ ዓመት ኖርኩ ከልጆቹም ጋር ነበርኩ ከእነርሱ ውስጥ እንዳንተ ያለ ጠባየ ክፉ የለም አለው።
ዑልያኖስም በቅዱስ አውስግንዮስ ላይ እጅግ ተቆጣ ይሰቅሉት ዘንድ በጐኖቹም ውስጥ መብራቶችን አስገብተው እንዲለበልቡት አዘዘ እርሱም ስለ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህን ሁሉ ታገሠ።
ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ወታደሮችም ሊቆርጡት በመጡ ጊዜ እስኪጸልይ ይታገሡት ዘንድ ለመናቸው ጸሎቱንም ሲፈጽም የከበረች ራሱን ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አባ ማቴዎስ አረፈ፡፡ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰማንያ ሰባተኛው ነው። የዚህም የአባ ማቴዎስ ወላጆቹ ከእስራኤል ነገድ የሆኑ ክርስቶስን የሚያምኑ በበጎ ሥራዎችም ፍጹማን የሆኑ ናቸው የአባቱም ስም ስምዖን የእናቱም በርባራ ይባላል እግዚአብሔርም ሁለት ዘርን ሰጣቸው የታላቁም ስም ያዕቆብ የታናሹም ማቴዎስ ነው።
እነሆ ማቴዎስም በእናቱ ሆድ ሳለ የአቡፌስ አገር ኤጲስቆጶስ አባ ጴጥሮስ እናቱን አገኛት በአያትም ጊዜ ከበቅሎው ላይ ወርዶ ሆድዋን ሳመ አንቺ ሴት የተባረክሽ ነሽ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው እነሆ እንደ ወንጌላዊ ማርቆስ በትምህርቱ ለሰው ሁሉ የሚያበራ ብሩህ ኮከብ ካንቺ ይወጣልና አላት።
አባ ማቴዎስም ከተወለደ ዐሥራ አምስት ዓመት ሲሆነው ወላጆቹ አረፉ ከዚህም በኋላ በቅዱስ አቡፋና ገዳም ወደአለ ቆሞስ ወደ አባ አብርሃም ሒዶ የምንኵስና ልብስ እንዲአለብሰውም ለመነው። እርሱም ከታላቅ ወንድምህ ተስማማ አለው አባ ማቴዎስም ሰምቶ በልቡ እየተከዘ ተመለሰ በጐዳናም የከበረ መልአክ ሚካኤል በመነኰስ አምሳል ተገናኘው እርሱ ሊቀ ጳጳሳት እንደሚሆን በእጆቹም ድንቆች ተአምራቶች እንደሚደረጉ ነገረው።
ወደ ወንድሙ ወደ ያዕቆብም ደርሶ እንዲመነኵስ ያሰናብተው ዘንድ ለመነው አባበለውም እምቢ ባለውም ጊዜ የአባ አሞኒ ወደ ሆነ ወደቶና ገዳም ሒዶ በቤተ ክርስቲያኒቱ ተማጸነ። መነኰሳቱም ወንድሙን በለመኑለት ጊዜ የወደደውን ያደርግ ዘንድ ተወው በዚያንም ጊዜ ወደ ቅዱስ አቡፋና ገዳም ሒዶ አባ አብርሃም አመነኰሰው ከመነኰሳት ሁሉ እስከ አየለ ድረስ በጾምና በጸሎት ተጋደለ።
አንድ ዓመትም ከሆነው በኋላ ኤጲስቆጶሱ አባ ጴጥሮስ ወደ አባ አብርሃም መጣ የአባ ማቴዎስንም ትዕግሥቱንና ብልህነቱን አይቶ ለርሱ ረዳት ይሆነው ዘንድ እንዲሰጠው አባ አብርሃምን ለመነው ኤጲስቆጶሱም ያለ ውዴታው ከርሱ ጋር ወሰደው ፀሐይ ስትገባ ጀምሮ እስከምትወጣ ድረስ መላ ሌሊቱን እየተጋ በኤጲስቆጶሱ ዘንድ ኖረ።
ዕድሜውም ዐሥራ ስምንት ዓመት ሲሆን ሳይወድ በግድ ኤጲስቆጶሱ ቅስና ሾመው። ሰይጣንም ቀናበት ፊቷንም እስካሳየችውና ለክፉ ፍትወት ሥራ እስከተናገረችው ድረስ በአንዲት ደም ግባት ባላት ሴት ልብ አድሮ አነሣሣት እርሱ ግን ሞትን እስከተመኘ ድረስ በማልቀስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ከዚህም በኋላ ወደ ገዳሙ ያሰናብተው ዘንድ ወደ ኤጲስቆጶሱ ገብቶ ማለደው።
ኤጲስቆጶስም መሔድን በከለከለው ጊዜ ወደ ዕቃ ቤት ገብቶ ዋጋው ብዙ የሆነ የኤጲስቆጶሱን መቀደሻ ልብስ ተክህኖ አንሥቶ በየጥቂቱ በምላጭ ቆረጠውና መልሶ ከቦታው አኖረው።
በማግሥቱም ኤጲስቆጶሱ አባ ማቴዎስን መቀደሻዬን ልብሰ ተክህኖ አምጣልኝ ዛሬ እቀድስ ዘንድ አለው። በአቀረበለትም ጊዜ እንደ ዕንጨት ጥራቢ ሁኖ በፊቱ ወደቀ ኤጲስቆጶሱም ተቆጥቶ ይህን የሠራ ማነው አለ አባ ማቴዎስም እኔ ነኝ አሁንም ወደ ቦታዬ ካላሰናበትከኝ በዚህ ቦታ በዝሙት ከምወድቅ ከዚህ የበለጠ እሠራለሁ አለ።
ከዚህም በኋላ በየቀኑ ሦስት ሦስት መቶ እንዲሰግድ በሌሊትም በቤትና በዋሻ ውስጥ ገብቶ እንዳያድር በቤተ ክርስቲያንም ከጸሎት ጊዜ በቀር እንዳይገባ ለገዳሙ ሰዎች ስለርሱ የውግዘት ደብዳቤ ጽፎ በቁጣ አሰናበተው። አባ ማቴዎስም ይህን ቅጣት ተቀብሎ ሁለት ዓመት ያህል ተጋደለ ኤጲስቆጶሱም ትዕግሥቱንና ቅንነቱን ሰምቶ የፍትሐትና የቡራኬ ቃል ላከለት።
ከዚህም በኋላ ወንድሙ ያዕቆብ ወደ ገዳም ወጥቶ መነኰሰ ሰይጣንንም እስከ አሸነፈው ድረስ ተጋደለ። አባ ማቴዎስም ወደ አባ እንጦንዮስ ገዳም ሒዶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዘመን ኖረ ከዚያም ስሙ ያዕቆብ የሚባል ጻድቅ መነኰስ ነበረ ብርሃናዊ መልአክ ወደ አባ ማቴዎስ መጥቶ እጅ ሲነሣው በራሱም ላይ ወንጌልን ሲያኖር በእጁም መክፈቻን ሲሰጠው ራእይን አየ አባ ያዕቆብም በነቃ ጊዜ ይህን ራእይ ለአባ ማቴዎስ ነገረው። ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ከንቱ ውዳሴን በመጥላት ከሀገር ወደ ሀገር የሚዘዋወር ሆነ።
በአንዲት ዕለትም በቊርባን ቅዳሴ ላይ ሲያገለግል ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሠዊያው ላይ ተቀምጦ አየው በታናሽ ሕፃን አምሳል በፃሕል ውስጥ ተኝቶ ነበር ኅብስቱንም በሚፈትትበት ጊዜ እጆቹን ዘርግቶ ከታላቅ ልቅሶ ጋር ፈጽሞ እያደነቀ በመፍራትም ለረጅም ጊዜ ይቆማል ይህንንም ራእይ ለማንም ለማን አይናገርም።
መምህሩም ለረጅም ሰዓት ሲቆም በአየ ጊዜ ያደንቅ ነበር ይህንንም ይገልጽለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በአንዲትም ዕለት አባ ማቴዎስ እንደልማዱ ሊቀድስ ገባ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በሕፃን አምሳል በጻሕሉ ውስጥ ተኝቶ ኅብስትንም መስሎ በአባ ማቴዎስ እጅ ሲቈረስ ለመምህሩ ለአበምኔቱ ታየው አበ ምኔቱም አደነቀ ለእኛ ለሰው ልጆች ይህን ታላቅ ጸጋ የሰጠኸን አቤቱ ለአንተ ምስጋና ይገባል አለ።
አባ ማቴዎስም ይህን በአየ ጊዜ የብረት ችንካር አመጣ ተልቶ ከእርሱ ትል እስቲወጣ ድረስ በጉልበቱ ውስጥ በዓርብ ቀን ቀረቀረው። ከዚህም በኋላ ወደ ደብረ ቊስቋም ሒዶ አብዝቶ እየተጋደለ በዚያ ኖረ ወደ ላይ ቀና ብሎ ሲመለከት ጌታችንን የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስን በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ የሚያየው ሆነ ወደታችም ሲመለከት በውቅያኖስ ጥልቅ ውስጥ በጌትነቱ ክብር የሚያየው ሆነ።
ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብርኤል በአረፈ ጊዜ ያለ ውዴታው ይህን አባት ሾሙት እምቢ በአላቸውም ጊዜ ጠባቂዎችን በላዩ አደረጉ በማግሥቱም ሊቀ ጵጵስና እንደሚገባው ያዩትን ራእይ ኤጲስቆጶሳቱ ሁሉም ነገሩት አባ ማቴዎስም እንደማይተዉት አውቆ በሥውር ምላጭ ወስዶ ምላሱን ጐትቶ ቆረጣት በዚያችም ሌሊት እመቤታችን የከበረች ድንግል ማርያም ወደርሱ መጥታ የሚያድን ቅባትን ቀብታ ምላሱን እንደ ቀድሞዋ አድርጋ መለሰችለት።
ወደ እስክንድርያም ወሰዱት በነሐሴ ዐሥራ ስድስት አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም በበዓልዋ ቀን ሊቀ ጵጵስና በሾሙት ጊዜ ሦስት ጊዜ ይገባዋል የሚል ቃል ከሰማይ ተሰማ በክንዱ ላይም ያደርጉ ዘንድ የወንጌላዊ ማርቆስን ራስ አመጡ እርሷም ወደ ላይ በረረችና አፉን ሳመች።
ከዚያንም ጊዜ ወዲህ በቊርባን ጊዜ በወንበር ላይ አልተቀመጠም በዓርብና በረቡዕ ቀን ከሰው ማንም ወደርሱ ቤት የሚገባ የለም። ወንድሙ ውድም አስፈሬ ንግሦ ሳለ የኢትዮጵያ ንጉሥ ዳዊት እንደሚነግሥ ትንቢት ተናገረ። ይህም አባት ከራሱ ላይ በሚያደርገው ቀጸላ በሽተኞችን በመፈወስ ሙታንን በማስነሣት በዘመኑ ብዙ ድንቅ ተአምራትን አደረገ።
በዘመኑም ከምስር ሥልጣን በታች ክፉ ሹም ተሾመ ሊቀ ጳጳሳት ማቴዎስን አስቀድሞ የሌለ ግብርን ሊቀበለው ሽቶ ግድ አምጣ አለው በከለከለውም ጊዜ ታላቅ የሆነ ድብደባን ደበደበው ተሸክመውም ወደ ቤቱ ወሰዱት። በዚያችም ቀን ከዚህ ዓለም ፃዕር ታሳርፈው ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለመናት እርሷም ተገልጻ አትዘን ከስምንት ቀን በኋላ ታርፋለህ ብላ ተናገረችው።
በማግሥቱም አባ ማቴዎስ ኤጲስቆጶሳቱን ቀሳውስቱንና ዲያቆናቱን ሕዝቡንም ሁሉ አስጠራቸውና የዕረፍቱን ቀን ነገራቸው የሃይማኖትንም ነገር መከራቸው ባረካቸውም።
ከዚህም በኋላ ጊዜው ደርሶ ሕማሙ በጸናበት ጊዜ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል አንሥቶ ይዞ ለረጅም ጊዜ ጸለየ ሥዕሊቱንም ተሳልሞ ሳማት ፊቱንም በመስቀል ምልክት አማተበ ክርስቶስን የሚያምኑ ምእመናን ያሉበትን ሀገር ሁሉ ባረከ በዕሑድ ቀንም በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages