አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር ስምንት በዚች ዕለት በአስቄጥስ ገዳም #የአባ_መቃርስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_እንድራኒቆስ አረፈ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ብንያሚን አረፈ፣ #የነቢይ_ሚክያስ መታሰቢያው ሆነ።
ጥር ስምንት በዚች ዕለት በአስቄጥስ ገዳም የአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን በከበረና በተመሰገነ በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ብንያሚን እጅ የከበረችበት ሆነ።
ከዚህም በኋላ መቆቅዝ ከሚባል ዐላዊ መለካዊ በአባ ብንያሚን ላይ መከራ ደረሰበት አባ ብንያሚንም ሸሽቶ ወደ ላይኛው ግብጽ ሔደ ዐሥር ዓመትም እስኪፈጸም በዚያ ኖረ ከዚህም በኋላ ያን ዓላዊ መቆቅዝን እግዚአብሔር አጠፋው ለአብያተ ክርስቲያን ሁሉ ጸጥታ ሰላም ሁኖ አባ ብንያሚንም ወደ መንበረ ሢመቱ ተመለሰ የአስቄጥስ ገዳም ሽማግሎችና መምህራን ወደርሱ መጡ ወደርሳቸውም ሒዶ አዲስ ቤተ ክርስቲያን እንዲ አከብርላቸው ለመኑት እርሷም የከበረ የአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ናት። በታላቅ ደስታም ተነሥቶ ከእሳቸው ጋር ሔደ የቤተ ክርስቲያኒቱንም መባረኪያ ጸሎት ጀመረ።
መሠዊያውንም በሜሮን ሊቀባ በጀመረ ጊዜ የክብር ባለቤት የጌታችን እጅ ከእርሱ ጋር ስትቀባ አየ ከታላቅ ፍርሀት የተነሣ በግምባሩ ፍግም ብሎ ወደቀ። ከኪሩቤልም አንዱ አነሣው እንዲህም አለው ተነሣ አትፍራ ልዩ የሆነውን ሥርዓት ለዚህ ቦታ ጻፍ ይህ የእግዚአብሔር ምሥጢር የሚፈጸምበት ነውና ማንም በትዕቢት ወይም መማለጃ በመስጠት እንዳይገባ በውስጡ በሚገባ ከሚሾም በቀር የሚደፍርና በውስጡ ከንቱ ነገርን የሚናገር አይኑር የእግዚአብሔር መመሰገኛ ቤቱ ነውና ይህም ሥርዓት በዚህ ቦታ እስከ ዘላለሙ የተሠራ ይሆናል።
እነሆ ዘመን ይመጣል የአባቶችንም ትእዛዝና ሥርዓት ያፈርሳሉ ይህም የከበረ ቦታ እንደ መሣለቂያ ቦታ ይሆናል። አባ ብንያሚንም ይህች የእግዚአብሔር ቤት የሰማይ ደጅ ናት አለ ይህንንም ከኪሩብ ጋር ሲናገር ከቤተ ክርስቲያኒቱ በስተምሥራቅ ተመለከተ አንድ መልኩ የሚያምር ጽሕሙ የረዘመ ፊቱም እንደ መልአክ ፊት የሚያበራ ሽማግሌ አየ። ለአባ ብንያሚንም ደስ አሰኘውና በልቡ እንዲህ አለ ከኤጲስቆጶሳት አንዱ ቢሞት በርሱ ፈንታ ይህን ሽማግሌ እሾመዋለሁ። ኪሩብም እንዲህ አለው ብንያሚን ሆይ ይህን አባት መቃርዮስን ኤጲስቆጵስን ታደርገዋለህን። እርሱ የሊቃነ ጳጳሳት አባታቸው ነውና ዛሬ ከልጆቹ ጋር ደስ ይለው ዘንድ መጥቷልና ከልጆቹም መንፈሳዊ ሹመት የሚሾም ወይም አለቃ የሚሆን አይታጣም ከገዳማቱም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ አይታጣም።
አባ ብንያሚንም ልጆቹ ብፁዓን ናቸው አለ ኪሩብም እንዲህ አለ ብፁዓንስ የሚባሉ ትእዛዞቹን ጠብቀው ፍለጋውን ቢከተሉ እነርሱ ከእርሱ ጋር አሁን በአለበት ክብር ውስጥ ይሆናሉ ትእዛዞቹን ቢተላለፉ ግን ከእርሱ ጋር ዕድል ፈንታ አይኖራቸውም ።
አባ ብንያሚንም ኪሩብን እንዲህ አለው ጌታዬ ሆይ በዚህ ነገር በልጆቼ ላይ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አትናገር ነገር ግን በሰብል ውስጥ አንዲት ቅንጣት የተረፈች እንደሆነ እግዚአብሔር በውስጥዋ በረከቱን ያደርጋል። እንዲሁም የፍቅር ቅንጣት በውስጣቸው የተገኘ እንደሆነ እግዚአብሔር ከመንግሥቱ እንደማያርቃቸው እኔ አምናለሁ።
ከአረጋዊው አባ መቃርስ ርኃራኄ የተነሣ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን አደነቀ መልአኩ ኪሩብ እንዳዘዘውም ያንን ሥርዓት ጽፎ ለዘወትር መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖረው።
ዕድሜው በደረሰ ጊዜ ዕረፍቱ በዚች ቀን ይሆን ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው እንዲሁም ሆነለት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሰባተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ እንድራኒቆስ አረፈ። ይህ አባት የሚራራ አዋቂ ሆነ እርሱ የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ተምሮአልና እርሱም ለእስክንድርያው ገዥ የአጎቱ ልጅ ነው ከእርሱ በፊት የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳት በገዳማት እንደሚኖሩ ስለ ቤቱና ስለ ክብሩ ታላቅነት በዘመኑ ሁሉ በገዳም የሚኖር አልሆነም በእስክንድርያ ከተማ ባለው ቤቱ የሚኖር ሆነ እንጂ።
ይህ አባት ሕርቃል በነገሠ በዐሥር ዓመት ከእስክንድር ዘመነ መንግሥት በዘጠኝ መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ተሾመ በዘመኑም ፀሐይን የሚያመልክ የፋርስ ነጉሥ ክስራን ተነሣ ብዙ የሆኑ ሠራዊቱንም ሰበሰበ የሶርያንና የፍልስጥኤምን አገሮች ከበባቸውና ዘረፋቸው። ከዚህም በኋላ ግብጽን ከበባት ወደ እስክንድርያም ከተማ ደረሰ በዙሪያዋም ሰባት መቶ ገዳማት አሉ በውስጣቸውም መነኰሳትን የተመሉ ነበሩ እነርሱም ገንዘብ ያላቸው በተድላ የሚኖሩ ናቸው ስለዚህም በነርሱ ላይ እግዚአብሔር ሥልጣንን ሰጥቶት ገዳማቱን አፈረሰ እነርሱንም ገደላቸው ከእርሱ ሸሽተው ከአመለጡ ከጥቂቶች በቀር የተረፈ የለም ገንዘባቸውንም ሁሉ ማረከ።
የእስክንድርያ ሰዎችም ንጉሥ ክስራ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ የከተማውን በር ከፈቱለት እርሱም ይቺን አገር በእጅህ አሳልፌ ሰጥቻታለሁ አታፍርሳት በውስጧ ያሉትን ብርቱዎች ግደላቸው ዓመፀኞች ናቸውና እንደሚለው በሕልሙ አየ ።በዚያንም ጊዜ የሀገሩን ንጉሥ አሠረው የሀገሩንም ሰዎች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው ሀገሪቱን ይጠብቋት ዘንድ በጦር ሠራዊት አደራጃቸዋለሁና ዕድሜያቸው ከዐሥራ ስምንት እስከ ሠላሳ ዓመት የሆኑትን ወጣቶች ብርታት ያላቸው የአርባና የሃምሳ ዓመት የሆኑትን እንድትሰበስቡልኝ እኔም ለየአንዳዱ ደመወዙን ሃያ ሃያ የወርቅ ዲናር እሰጠዋለሁ አላቸው።
እነርሱም እውነት መሰላቸወ ከእርሱም ዘንድ ስምንት ሺህ ሰዎች ወጥተው የሁሉንም ቁጥራቸውን ምዝገባ ጀመሩ እነርሱ ግን ወርቅ የሚቀበሉ ይመስላቸው ነበር ምዝገባቸውም በተፈጸመ ጊዜ ሁሉንም በሰይፍ ገደላቸው ።
ከዚህም በኋላ ወደ ላይኛው ግብጽ ወጥቶ ወደ ኒቅዮስ ደረሰ በዚያም ገዳማት በውስጣቸው ሰባት መቶ ሥራቸው ክፉ የሆነ መነኰሳት በዋሻዎችና በቦታዎች ሁሉ እንዳሉ ሰማ እነርሱን ሁሉንም በሰይፍ ገደላቸው።
የሮም ንጉሥ ህርቃልም የፋርስ ንጉሥ ክስራ ያደረገውን በሰማ ጊዜ ሠራዊቱን ሰብስቦ ወደርሱ ሔደ የክስራን ሠራዊት ሁሉንም ገደለ ሀገሩንም አጠፋ። የዚህ አባት እንድራኒቆስ ገድል ግን እጅግ ያማረ ነበረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ ከዓመተ ሰማዕታት ሦስት መቶ አርባ ሰባት እስላሞች በግብጽ ከመንገሣቸው በፊት በመንበረ ሢመቱም ሰባት ዓመት ኖረ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ስምንተኛ ነው። ይህም አባት ከእስክንድርያ ባርስጥ ከምትባል መንደር ከሀገሪቱ ከበርቴዎች ወገን ነው ከእስክንድርያ ምዕራብ ከምትገኝ ገዳም ውስጥ ስሙ ቴዎናስ ከሚባል ከአንድ ቅዱስ ሰው ዘንድ ከታናሽነቱ ጀምሮ መነኰሰና የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ተማረ ሁልጊዜ በበጎ ሥራ ያድግ ነበር።
በአንዲት ሌሊትም ብንያሚን ሆይ ደስ ይበልህ በሃይማኖት በትር የክርስቶስን በጎች ትጠብቃቸዋለህና የሚለውን ራእይ አይቶ ለመምህሩ ነገረው። መምህሩም ሰይጣናት በትዕቢት እንዳያስቱህ ተጠበቅ አለው እርሱም በትሩፋቱ ላይ ትሩፋትን ጨመረ።
ከዚህም በኋላ መምህሩ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ እንድራኒቆስ ወሰደውና ልጁ ብንያሚን ያየውን ራእይ ነገረው እርሱም ቅስና ሾመውና ለቤተ ክርስቲያንም አስተዳዳሪ አደረገው አባ እንድራኒቆስም እስከ አረፈ ድረስ በበጎ አስተዳደር ቤተ ክርስቲያንን እየአስተዳደረ ኖረ ከዚህም በኋላ ይህ አባ ብንያሚን ሊቀ ጵጵስና ተሾመ በተሾመ ጊዜም ታላቅ መከራ ደረሰበት።
በእርሱ ላይም ታላቅ መከራ ከመድረሱ በፊት የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ከእርሱ የሚሆነውን ሁሉ አስረዳው እርሱም እንዲሸሽ ኤጲስቆጶሳቱም ከእርሱ ጋር እንዲሸሹ አዘዘው። በዚያንም ጊዜ ቀድሶ ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አዘዛቸው እርሱ ከመልአኩ እንደተረዳ የሚሆነውን ሁሉ አስረዳቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ ኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ ወደ ገዳማት አለቆችም መልእክቶችን ላከ እንዲሸሹም አዘዛቸው እርሱም ወደ አባ መቃርስ ገዳም ወደ አስቄጥስ በረሀ ከዚያም ወደ ላይኛው ግብጽ ሔደ።
አባ ብንያሚንም ከእስክንድርያ አገር ከወጣ በኋላ ከሮም ንጉሥ ከሕርቃል ዘንድ የተሾመ መኰንን መጣ እርሱም ሊቀ ጵጵስና የደረበ በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ላይ የሠለጠነ ነው። ብዙዎች ምእመናንንም አሠቃያቸው ስሙ አባ ሚናስ የሚባል የአባ ብንያሚንንም ወንድም ይዞ አሠቃየው በጐኖቹም ውስጥ እሳት ጨምሮ አቃጠለው ከዚህም በኋላ በባሕር ውስጥ አሠጠመው።
በእነዚያም ወራቶች ንጉሥ ሕርቃል በሕልሙ እነሆ ግዙራን የሆኑ ብዙ ሕዝቦች በላይህ መጥተው በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣሉ የሚለውን ራእይ አየ ለንጉሡም አይሁድ እንደሆኑ መስሎት ነበር ለወዳጆቹ ይህን ራእይ አስረዳቸው ራእዩ ግን ስለ እስላሞች መንግሥት የሆነች ናት። በዚያንም ጊዜ ያትሮብ ከሚባል ምድር መጥተው በሶርያ ምድር ነገሡ።
በዚያንም ወቅት የአጽ ልጅ ኡመር መጥቶ በግብጽ ላይ ነግሦ ሦስት ዓመት ኖረ ወደ እስክንድርያም ሒዶ አፈረሳት ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትንም አቃጠለ ከታችኛው ምድር ከባሕር ዳር ያለች የታወቀች የወንጌላዊ የቅዱስ ማርቆስን ቤተ ክርስቲያንንም እንዲሁም በእስክንድርያ አገር ዙሪያ ያሉ ብዙ ገዳማትን አቃጠለ በውስጣቸው ያለ ገንዘባቸውን ሁሉ ማረከ።
ከዚህም በኋላ የጭፍራ አለቃው የቅዱስ ማርቆስን የቤተ ክርስቲያኒቱን መርከቦች ወሰደ እጁንም ወደ ሣጥን አስገብቶ ሲዳስስ የቅዱስ ማርቆስን ሥጋ አገኘ ታላቅ እንደሆነም አውቆ በመርከብ ውስጥ በክብር አስቀመጠው።
ወልደ አጽ ኡመር ግን የአባ ብንያሚንን ሥራ ስለምን እንደሸሸም በአወቀ ጊዜ መልእክትን ጻፈለት እንዲህም አለው ና አትፍራ ወገኖችህን አብያተ ክርስቲያናትንም አስተዳድራቸው። አባ ብንያሚንም ሕርቃል በነገሠ በዐሥር ዓመት እስላሞች በነገሡ በሰባት ዓመት ከሸሸበት ቦታ መጣ ወልደ አጽ ኡመርም አባ ብንያሚንን በታላቅ ክብር አከበረው አብያተ ክርስቲያናቱንም ገንዘባቸውንም የካህናቱንም ምድራቸውን እንዲሰጡት አዘዘለት።
በአምስቱ ሀገሮች ላይ እነግሥ ዘንድ ወደ ምዕራብ አገር እሔዳለሁና ሒደህ ስለእኔ ጸልይልኝ በተመለስኩም ጊዜ የምትሻውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው አባ ብንያሚንም እግዚአብሔር መንገድህን ያቀናልህ አለው በእርሱ ላይ የሚሆነውንም ሁሉ ነገረው።
በዚያን ጊዜም መርከቦቹን እንዲያቀርቡለትና እንዲሔድም ፈለገ በወደቡም ውስጥ መርከቦችን አዘጋጁለት ያቺንም የወንጌላዊ ማርቆስ ራስ በውስጧ ያለበትን መርከብ በገመድ አሥረው ጐተቷት ግን አልወጣችም መርከበኞችም ሁሉ ተሰበሰበው ቢስቧት ከቦታዋ አልተንቀሳቀሰችም።
የመርከቡም ሹም ፈራ በውስጧ የቅዱስ ማርቆስ ራስ ስለ አለባት ስለዚያች መርከብ ለኡመር ነገረው ኡመርም ለአባ ብንያሚን ይህን ነገረው ቅዱስ ማርቆስም ለአባ ብንያሚን በሕልም ተገለጠለትና ቦታ አዘጋጅልኝ አለው።
አባ ብንያሚንም በሰማ ጊዜ ተነሥቶ ወደ መኰንኑ ሔደ በመርከቡ ውስጥ ያለችው የከበረ የወንጌላዊው ማርቆስ ራስ እንደሆነች አስረዳው ከዚህም በኋላ አባ ብንያሚን የከበረ ማርቆስን ራስ ከመርከብ ውስጥ አውጥቶ ወሰዳት በዚያንም ጊዜ መርከቢቱ ከወደቡ ወጣች ገዥው መኰንን ኡመርም ይህን አይቶ እጅግ አደነቀ ብዙ ገንዘብም ሰጥቶ ለከበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራለት አዘዘው ያማረች ቤተ ክርስቲያንንም ሠራ የቅዱስ ማርቆስን ሥጋ ራሱንም በውስጧ አኖረ።
ይህ አባት ብንያሚንም አረማውያንን ስለማስተማር እጅግ ታጋይ ሆነ ከእነርሳቸውም ብዙዎቹን ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሳቸው አጸናቸውም። በዚህ አባት ዘመንም ከእርሱ አስቀድሞ እንደርሱ ያልሆነ እጅግ ታላቅ የሆነ ረሀብን እግዚአብሔር በሀገሩ ሁሉ አመጣ። ቊጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎችም ሞቱ በሀገሩ ሜዳዎችና ገበያዎች ውስጥ የወደቁ ሆኑ።
ከዚህም በኋላ አባ ብንያሚን ለሁለት ዓመት ያህል እግሩን ታመመና በሰላም አረፈ የሹመቱም ዘመን ሠላሳ ዘጠኝ ዓመት ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት የነቢይ ሚክያስ መታሰቢያው ሆነ። የዚህም ነቢይ ከታናሽነቱ ጀምሮ አካሔዱ መልካም ሆነ ስለ ሥራው ማማርና ስለ ጽድቁ ሕዝቡ ሁሉ ያደንቁታል ያከብሩታል ሚክያስም ይሉታል ትርጓሜውም መልአክ ማለት ነው መልኩ እጅግ ያማረ ነውና የሚናገረውም ትንቢት እንደተናገረው ይሆናል የእግዚአብሔር መልአክም ተገልጾለት ያነጋገረው ነበር ሕዝቡ ግን ያንን መልአክ አያዩትም ድምፁን ግን ይሰማሉ ከእርሳቸውም ያደላቸው የሚያዩት አሉ በመሳፍንት መጽሐፍ እንደተጻፈ። በጐልማሳነቱም አርፎ በአባቶቹ ቦታ ተቀበረ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment