ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 9 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 9

 #አባ_አብርሃም_ገዳማዊ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር ዘጠኝ በዚህች ቀን የከበረ አባት አባ አብርሃም ዐረፈ፡፡ የዚህም ቅዱስ ሰው አባቱ ድኆችን የሚወዳቸውና የሚራራላቸው ነው። በዘመኑም በግብጽ አገር ታላቅ ረሀብ ሆነ እጅግ ባለጸጋ ነበርና ከደግነቱና ከታማኝነቱ ብዛት የተነሣ እርሱ በአለበት አገር ዙሪያ ያሉ አገሮች ሁሉም የምድራቸው ፍሬ በእርሱ ዘንድ አደራ ያስቀምጡ ነበር ረሀቡም በጸና ጊዜ በእርሱ ዘንድ በአደራ የተቀመጠውን እህል ሁሉንም ለድኆች ሰጠ እግዚአብሔርም ስለ ምድራቸው ፍሬ ሁሉንም ክፉ ቃልን እንዳይናገሩት አደረጋቸው። በእርሱ ዘንድ ያኖሩትን የምድራቸውን ፍሬ ሽተው ወደርሱ በሚልኩ ጊዜ ተነሥቶ ወደርሳቸው ይሔዳል እነርሱም በየራሳቸው ለያንዳንዱ የምድራቸው ፍሬ እንደደረሳቸው አድርገው ይጽፉለታል እንጂ ምንም ምን አይናገሩትም።


የዚህም ቅዱስ እናት እግዚአብሔርን የምትፈራ ምእመን ናት ሰይጣንም ቀናባት በአንድ ክፉ ሰው ልቡና አድሮ በፋርስ ሰዎች ዘንድ ነገር ሠራባት እነርሱም ማርከው ወደ አገራቸው ወሰድዋት በአንዲት ሌሊትም ራዕይን አየች ያ ነገር የሠራባት ሰው በሲኦል ውስጥ በእሳት ሰንሰለት ታሥሮ "እግዚአብሔር ያደረገልሽን ተመለከትሽን ነገር የሠራብሽን ያንን ሰው ተበቅሎታልና" ይላታል እርሷ ግን "ጌታዬ ሆይ መከራና ሥቃይ በርሱ ላይ እንዲደርስ አልሻም" ትላለች ያ የሚያሳያትም "አንቺ ግን ወደ አገርሽ ተመልሰሽ በቤትሽ ትኖሪ ዘንድ አለሽ" ይላታል እንዲሁም ሆነ።
ባሏም በሞተ ጊዜ አብርሃም ድኃ አደግ ሆነ እርሷም እናቱ ሚስት ልታጋባው አሰበች እርሱ ግን ይህን አልወደደም እናቱም እጅግ ደስ ተሰኘችበት። ወደ ገዳም ሒዶ ሊመነኵስ በፈለገ ጊዜ እናቱ ልትሸኘው ወጣች እጆቿንም ወደ ሰማይ አንሥታ በመጸለይ ልጇን ወደ እግዚአብሔር አደራ አስጠበቀች። "አቤቱ ጌታዬ ይህን ቊርባንን አድርገህ ተቀበለኝ" አለች።
በዚያንም ጊዜ አባ አብርሃም ሔደ በአስቄጥስ በረሀ ውስጥ ተጒዞ በአባ ዮሐንስ አበ ምኔትነት ዘመን ወደ አባ መቃርስ ገዳም ደረሰ ወደርሱም ወደ አባ ዮሐንስ ገባ ተወዳጅ ልጅንም ሆነለት። በጎ ተጋድሎንም ጀመረ በአንዲት ሌሊትም ራዕይን አየ የበዓቱ ጣሪያ ተሰነጠቀ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጦ ወደርሱ ሲወርድ አየው ኪሩቤልም ያመሰግኑት ነበር እርሱም ፈርቶ ተንቀጠቀጠ ፈጥኖም ሰገደ ጌታችንም ባረከውና በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ ዐረገ። ጌታችንም የወረደባት በቤቱ ጣሪያ የተሠነጠቀችው ምልክት ሁና እስከ ዛሬ በመታሰቢያነት አለች እርሷም ለመንፈሳዊ አባቱ ለአበ ምኔቱ አባ ዮሐንስ መኖሪያ ቅርብ ናት እርሷም በግቢግ ትባላለች። የእግዚአብሔርም መልአክ ሁል ጊዜ ይጐበኘዋል ብዙ ምሥጢራትንም ይገልጥለታል ያስገነዝበዋልም።
ከዚህም በኋላ አባ አብርሃም ወደ ደብረ ኀርዮን ሔደ በዚያም አባ ገዐርጊን አግኝቶት ወደ አስቄጥስ ገዳም ከእርሱ ጋር ወሰደውና እስከ ዕረፍታቸው ጊዜ በዚያች በዓት ኖሩ።
አበ ምኔቱ አባ ዮሐንስም በዐረፈ ጊዜ በአባ አብርሃም ላይ ሰይጣን ታላቅ ደዌ አምጥቶበት ዐሥራ ስምንት ዓመት በዚያ ደዌ ውስጥ ኖረ ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ የጌታችንን ሥጋና ደም ያቀብሉት ዘንድ ወንድሞችን ለመናቸው ከተቀበለም በኋላ መንፈሳዊ አባቱ አባ ዮሐንስ ወደርሱ መጥቶ "እነሆ ወደ ታላቅ ሠርግ እግዚአብሔር ጠርቶሃል" አለው። ከዚህም በኋላ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት ሁኖት በሰላም ዐረፈ፡፡ በዓታቸውም እስከ ዛሬ የታወቀች ሁና ትኖራለች።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages