በሰሜን ወሎ የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት ሊገነቡ እንደሆነ ተገለጸ!! - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, March 4, 2023

በሰሜን ወሎ የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት ሊገነቡ እንደሆነ ተገለጸ!!

 በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ አድባራትና ገዳማት በጥምረት ሆነው በሰሜን ወሎ የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያናት ሊገነቡ እንደሆነ ተገለጸ!!



(የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ/ም
(አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ)
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መመሪያ ሰጪነት በሥሩ የሚገኙት አድባራትና ገዳማት በጥምረት ሆነው በሰሜን ወሎ የፈረሱትን አብያተክርስቲያናት ሊገነቡ እንደሆነ ተገለጸ።
ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ እና የከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰሜን ወሎ በጦርነት ምክንያት ጉዳት ስለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት አስመልክተው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ለሚገኙ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሩን የሰጡት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመገኘት ነው።
ብፁዕነታቸው በጦርነቱ ምክንያት በሰሜን ወሎ በሚገኙ ምእመናን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ እና አስከፊ ችግር በሰፊው አንስተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በርካታ ንጹሐን ዜጎችና በአገልግሎት ላይ የነበሩ ካህናትና ዲያቆናት ለሞት መዳረጋቸውንም ጠቅሰዋል።
አሁንም ቢሆን አብዛኛው ማሕበረሰብ በከፋ የስነ ልቦና ጫና ስር እንደሚገኝ አሳስበዋል።
ከአብያተክርስቲያናቱ መፍረስ ጋር ተያይዞ ሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
አያይዘውም ሰባት ወረዳዎች የጥፋቱ ሰለባ መሆናቸውንና አንድ መቶ ዘጠኝ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳት ደርሶባቸው አገልግሎት እንማይሰጡ ጠቅሰዋል።
ሃያ አምስት ደቂቃ ገደማ የፈጀ የአብያተክርስቲያናቱን ጉዳት የሚያሳይ በቪድዮ የተደገፈ መረጃ እና ማስረጃም ታይቷል።
የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በምስል የተደገፈ ማስረጃ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ መሰጠቱ ትልቅ ሚና እንዳለውና ችግሩን ለመቅረፍ በእጅጉ የሚያነሣሣ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሰብአዊነት፣ እንደ ሃይማኖተኛ እና እንደ ዜጋ ሁላችንም የጠፋውን መልሰን የማልማት ግዴታ አለብን ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከዚህ በፊት ለተጎዱ ምእመናን የተለያዩ ዕርዳታዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው አሁንም አድባራቱንና ገዳማቱን በማስተባበር በሰሜን ወሎ የፈረሱትን አብያተክርስቲያናት እንደሚያስገነባ ገልጸዋል።
የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችም ስለ ተሰጣቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ አመስግነው ኮሚቴ ተዋቅሮ፤ ጥናት ተካሂዶ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ክረምት ሳይገባ እስከ ሰኔ ድረስ የፈረሱት አብያተክርስቲያናት ተገንብተው እንዲጠናቀቁ ሃሳብ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ጉባኤው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖትን ጨምሮ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴን መርጧል።
የተመረጠው ኮሚቴም ጥናቶችን አካሂዶ በፍጥነት ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጿል።
በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ:-

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages