እንኳን ለአምላካችንና ለመድኀኒታችን፤ ለፈጣሪያችንና ለአዳኛችን መድኀኔ ዓለም ጥንተ ስቅለት ክብረ በዓል አደረሳችሁ፥ አደረሰን፡፡
የጥንተ ስቅለቱ የመታሰቢያ በዓል በሚከበርበት በመጋቢት ፳፯ ቀን ሰማያዊ አምላክ ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራዎችን የተቀበለበትና በሞቱ ሞትን ሽሮ የአዳምን ዘር ሁሉ ከሞት ሞት ያዳነበት፣ ለዓለሙ ሁሉ ፍቅሩን የገለጠበት፣ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙም ዓለምን ነፃ ያወጣበት፣ ሕማማተ መስቀልን በትዕግሥት ተቀብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው #በገዛ_ፈቃዱ የለየበት የስቅለቱና የሞቱ መታሰቢያ የሚከበርበት ቀን በመሆኑ ጥንተ ስቅለት ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓሉም በዓለ መድኃኔዓለም እየተባለ በየዓመቱ #በመድኃኔዓለም ስም በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ታቦተ ሕጉ ወጥቶ ይከበራል ፡፡ የመጋቢት ጽንሰት ( ብሥራት ) ታሕሣስ 22 እንደሚከብረሁ ሁሉ ማለት ነው ፡፡
፠#ክርስቶስ የተሰቀለው መጋቢት ፳፯ ቀን ከሆነ እንደገና በሌላ ጊዜ በዓለ ስቅለትን ማክበር ለምን አስፈለገ?
ክርስቶስ የተሰቀለው በዕለተ ዓርብ ሲሆን ከመቃብር የተነሣውም በዕለተ እሑድ በመሆኑ #ስቅለት ከዕለተ ዓርብ፣ #ትንሣኤም ከዕለተ እሑድ፣ #ዕርገት ደግሞ ከዕለተ ሐሙስ እንዳይወጡ፤ ሌሎቹም በዓላትና አጽዋማት በተወሰነላቸው ቀን እንዲውሉ ማድረግ ይቻል ዘንድ የቀድሞ አባቶችና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሰባት አዕዋዳት አዘጋጅተው እና ቀምረው ሁሉም ሥርዓቱን ጠብቆ ድርጊቱ በተፈጸመበት ቀን እንዲከበር የወሰኑ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም በዲሜጥሮስ ቀመር መሠረት ጥንተ ስቅለቱ መጋቢት ፳፯ ቀን በየዓመቱ እየታሰበ በዓለ ስቅለቱ ደግሞ ከሰሙነ ሕማማቱ ጋር በዓመት አንድ ጊዜ በዕለተ ዓርብ በጾምና በጸሎት እንዲሁም በአክፍሎትና በስግደት እንዲከበር በማድረግ ሕግና ሥርዓት ስለሠሩ በዚሁ መሠረት ይፈጻማል::
#ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ የሆነው የጌታችን #የጽንሰቱ_በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበርበት ቀን ከመሆኑ የተነሣ በዓሉን በዓል ተጭኖት ነው እንጂ ፫ኛው ቀን መጋቢት ፳፱ኝም ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣበት ጥንተ_ትንሣኤ በመሆኑ እንደ ጥንተ ስቅለቱ ሁሉ ጥንተ ትንሣኤውም ከበዓለ ጽንሰቱ ጋር አብሮ የሚታሰብ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባንም፡፡
142 ዓመታትን ያስቈጠረው ጥንታዊው የጮቢ ደብረ መድኀኒት መድኀኔ ዓለም፡፡ በ1868ዓ.ም. የተመሠረተ፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን በጀልዱ ወረዳ በጮቢ የሚገኝ፡፡
በሃገራችን ከሚገኙ የመድኀኔዓለም ገዳማትና አድባራት ጥቂቶቹ፤
፤ ዋልድባ አበረንታት መድኀኔዓለም ገዳምና
ኤልሻማ ደብረ ማኅቶት መድኀኔዓለም ቤ.ክ.
፠ አንድ ላይ ያሉት፤
✤1. ዋልድባ አበረንታት መድኀኔዓለም ገዳም፤
✤2.ላሊበላ መድኀኔዓለም
✤3. ጎንደር መንበረ መንግሥት መድኀኔዓለም
✤4. መንዳባ አቡነ ያሳይ መድኀኔዓለም፤ ጣና
✤5. ሽረ እንዳሥላሴ መድኀኔዓለም ወመስቀል ክብራ
✤6. ቆላድባ መድኀኔዓለም፤ ጎንደር ከተማ አጠገብ
✤7.ቦሌ ደብረ ሳሌም መጥምቁ ዮሐንስ፤ (ቦሌ የመድኀኔዓለም ታቦት )
✤ 8.ድሬዳዋ መድኀኔዓለም
✤9.#ቀጨኔ_ደብረ_ሰላም_መድኀኔዓለም ✤ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፤ ፤ የ 110 ዓመታት ዕድሜ ያለው ጥንታዊ የኢያሱ ደብር፡፡ ‹‹በወርቅ ወበዕንቊ ሥርጉት ደብረ ሰላም፤ ወነገሥት ይትቀነዩ ለኪ›› ይህችን ደብረ ሰላምን በመጀመሪያ አቤቶ ኢያሱ /አልጋ ወራሽ ልጅ ኢያሱ/ (ክፍለ ያዕቆብ) በሐምሌ 26 ቀን 1903 ዓ.ም. መሠረታት፤ ንግሥት ዘውዲቱ አሁን ያለውን ሕንፃው ቤ.ክ ጥቅምት 27 ቀን 1913 ዓ.ም አስፈጸመች፡፡)
የብዙ ሊቃውንት መፍለቂያ፤ የላይ ቤት አቋቋም፣ የተክሌ ዝማሜና የሸዋና የራሱ የደብሩ ቀለም እንደ ወንዝ የሚፈስባት፤ ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘ ቤተ መዘክር (Museum)ና ቤተ መጻሕፍት የሚገኙበት፤ ስዕለት ሰሚ ታቦታት ያሉበት፤ 4ት የሚጠጉ ፈዋሽ ጠበሎች የሚገኙበት፡፡ ጽዶቹ ሳይቀሩ በ72 አርድዕት ቅዱሳን አምሳያ የተተከሉበት፤ በቀድሞ ዘመን መዐዛ ቅዳሴ የተሰኘው የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ቅዳሴ በወርኃ ጽጌ የሚቀድስበት፤ 3 ጳጳሳትን ያፈራ፣ ……. ደብር ነው፡፡
✣ ለደብረ ሰላም ይደልዋ ስብሐት፤ እስመ በውስቴታ ኀደረ መድኀኔዓለም (በደብረ ሰላም በውስጧ መድኀኔዓለም ስላደረ ምስጋና ይገባታል፡፡)
10 #መናገሻ_ጋራ_መድኀኔዓለም፤ ግማደ መስቀሉ ያረፈበት፤ ቀድሞ የቅዳሴ ቤቱን ታላቁ አባት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቀድሞ የልደታ ቤ.ክ) በአካል በመገኘት በመስቀሉ የባረከው፤ በድርሳነ ራጕኤል ላይ የተገለጸና ቅዱስ ራጕኤል የማይለየው፤ በአረማዊው ግራኝ ወረራ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑ ካህናቱን መነኮሳቱንና ምዕመናኑን እንደያዘ በምድር ውስጥ ገብቶ የተሰወረበት በሥጋ ዕረፍተ ሞት ያልተገቱ ሥውራን ግሩማን አበው የሚኖሩበት "ዛቲ ይእቲ አምባ ማርያም መካነ ክብሮሙ ወጸሎቶሙ ለቅዱሳን ወለነገሥታተ ኢትዮጵያ በሐ በልዋ ተሳለምዋ ጊሱ ሐቤሃ ኢትርሐቁ እምኔሐ" ብለው አበው ያወደሷት የጸሎት የአርምሞና የትኅርምት ቦታ፡፡
11. #ገዳመ_አባ_ጽጌ_ድንግል (መድኀኔዓለም ቤ.ክ)፤ ማኅሌተ ጽጌ የተደረሰበት ወሎ፤ ወግዲ፤ ወለቃ ወንዝ አጠገብ፤ የበረሃው ዕንቊ ገዳም፤ አባ ጽጌ ድንግል የፈለፈሉት ባለ 3 መቅደስ እጅግ ሰፊ ዋሻ ቤ.ክ፡፡
12. #ደብረ_ቀራንዮ_መድኀኔዓለም ቤ.ክ፥ አዲስ አበባ፤ በአዲስ አበባ ከተመሠረተ ከ1826 ዓ.ም ጀምሮ ፍልሰት ሳያጋጥመው በመቆየቱ፤ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ቤ.ክ፡፡ (ነገር ግን በመሃል ፍልሰት እያጋጠማቸው እንጂ በአዲስ አበባ ከ1600 ዓመታት በፊት ደብረ ኤረር፣ የካ ዋሻ ተክለሃይማኖትና /ኋላ የካ ሚካኤል/ በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመን፤ እንዲሁም እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት በአልአሜዳ ዘመነ መንግሥት መመሥረታቸውን ልብ ይሏል)
#በዓለም አቀፍ ደረጃ በዋነኛነትና በግንባር ቀደምትነት የስቅለት በዓል የሚከበርባችው ፪ቱ ታላላቅ ገዳማት
፩ኛ. ኢየሩሳሌም ዴር ሡልጣን
፪ኛ. #ዋልድባ (ዋሊ)፡፡
/በቀጨኔ ደ.ሰላም መድኀኔዓለምና ደ.ት.ቅ.ገብርኤል ቤ.ክ ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሕትመት እና ሚዲያ ንዑስ ክፍል የተዘጋጀ ::/
No comments:
Post a Comment