ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ትንሣኤው ሐዋርያት ተሰብስበው በነበረበት በዝግ ቤት ገብቶ ሲገለጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ ሐዋርያትም የጌታችንን ከሙታን ተለይቶ መነሣት ቢነግሩት ‹‹እኔ ሳላይ አላምንም›› አላቸው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንትም ጌታችን ቶማስ በተገኘበት በድጋሜ ተገለጠላቸው፡፡ ጌታችንም ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን›› ብሎ በጦር የተወጋ ጎኑን ፥ በችንካር የተቸነከረ እጁንና እግሩን እንዲዳስሰው በማድረግ ትንሣኤውን አረጋገጠለት፡፡ ቶማስም ሲዳስሰው እጅ ከእሳት እንደገባ ጅማት ስለተኮማተረ‹‹ጌታዬ አምላኬም›› ብሎ መሰከረ፡፡ በኋላ ግን ፈውሶታል፤ ኢየሱስም ‹‹ስለ አየኸኝ አምነሀል ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዐን ናቸው›› አለው፡፡ ምንም አንኳን ድርጊቱ የተፈጸመው በዳግም ትንሣኤ ቢሆንም የሐዋርያው መታሰቢያ ሆኖ ዕለተ ማክሰኞ ‹ቶማስ› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ (ዮሐ. ፳ ፥ ፳፬ -፴)
" ቶማስም አለ ለእኔ የእጆቹንና የእግሮቹን ችንካሮች የቅድስት ጎኑን መወጋትም አሳየኝ አስቀድሜ እጠራጠርና ትንሣኤውን ሳላምን ሳለው የቀኝ ጎኑን መወጋት ገልጦ አሳየኝ ደስም አለኝ "
መጽሐፈ ዲድስቅልያ
ቶማስ ማለት የስሙ ትርጉም ጸሐይ ማለት ነው ከአሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኃላ ትንሣኤውን ለቅዱሳን ሐዋርያት ሲገልጥላቸው ቅዱስ ቶማስ በቅርብ በአካባቢው አልነበረም ሲመለስ የጌታ ሞትን ድል አድርጎ መነሳት ከቅዱሳን ሐዋርያቱ ሲሰማ ትንሣኤውን ከራሱ ከክርስቶስ መስማት ሽቶ ነበርና ካላየው አላምንም አለ ሊቃውንቱ ለዚህ ሀሳቡ በትርጓሜ ላይ ሦስት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ
፩ የጌታን ትንሣኤ ሰምቶ ከመመስከር ይልቅ አይቶ ለማመስከር ስለፈለገ
፪ ሌሎቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ተነሳ እያሉ ሲያስተምሩ ከባልንጀሮቼ እንደ ሰማሁት ተነሳ እያለ ማስተማሩ ከእነርሱ የሚያሳንሰው ስለመሰለው
፫ ውልደቱ ትንሣኤ ሙታን የለም ከሚሉ ከሰዱቃውያን ወገን ስለነበር ከልጅነት ጀምሮ ስለትንሣኤ ሙታን ካለው የተሳሳት መረዳት ለመላቀቅ አይቶ በማመን እና በማረጋገጥ በፍጹም እምነት መመስከር ስለፈለገ ነው ይላሉ
በእነዚህ ምክንያቶች ጌታ ተነሣ ቢሉት የተወጋ ጎኑን የተቸነከረ እጁን ካለየው አላምንም አለ ጌታችንም ጣትህን ወደ እኔ አምጣና በጎኔ አግባው ያመንክ እንጂ ያለአመንክ አትሁን አለው ቶማስም እጆቹን ከጌታ ጎን ሲያስገባ እሳት እንደገባ ጅማት ተኮማተሩ በዚህ ጊዜ ጌታዬ አምላኬ ብሎ መሰከረለት ቅዱስ ያሬድም ይሄንን በዝማሬው ሲገልጽ እንዲህ ይላል
" ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ቶማስ እጄን ወደ ጎኑ ጣቶቼንም ወድ ቅንዋቱ ካላስገባው አላምንም አለ ኢየሱስም እኔ እንደሆንኩ እመንብኝ እንጂ እትጠራጠር አለው ቶማስም ጌታዬ አምላኬ አለ "
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ የሚለውን የጌታ ትዕዛዝ ለመፈጸም እጣ ወደ ደረሰችው ሀገር ወደ ህንድ ሄዶ በብዙ ተጋድሎ ወንጌልን የሰበከ ሰዎችን ካለማመን ወደ ማመን ከጨለማ ወደ ብርሃን ያመጣ በጥምቀት ብዙዎችን የእግዚአብሔር ልጆች ያደረገ ሐዋርያ ነው ዛሬ ላለችው የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም የወንጌልን መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ የጣለ አባት ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ግንቦት ሃያ ስድስት በሰማዕትነት ያረፈበትን ቀን ታከብራለች ጸሎት እና በረከቱ አይለየን።
No comments:
Post a Comment