ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 14 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, May 23, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 14

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምግንቦት ዐሥራ አራት በዚች ቀን ከመንፈሳውያን ሐዋርያት ጋራ አንድነት ያለው የከበረ አባት ቅዱስ ጳኩሚስ አረፈ፣ ከሀገረ ፈርማ ሰማዕት የሆነ አባ ሲማኮስ አረፈ፣ ድንጋዩን እንደ ጀልባ ተጠቅመው የጣናን ሐይቅ የተሻገሩት የአቡነ ያሳይ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፣ ሙሽራው ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ከጫጉላ ቤቱ ወጥቶ የመነነበት ዕለት ነው፡፡

ቅዱስ አባ ጳኩሚስ
ግንቦት ዐሥራ አራት በዚህች ቀን ከመንፈሳውያን ሐዋርያት ጋራ አንድነት ያለው የከበረ አባት ጳኩሚስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከአባ ጰላሞን ዘንድ መንኲሶ ሲያገለግለው የምንኵስናንም በጎ ሥራ እየሠራ ብዙ ዘመናት ኖረ።
ከዚህም በኋላ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገልጾለት እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት የአንድነትን ማኅበር ለመሥራት መነኰሳትን እንዲሰበስብ አዘዘው።
ከዚህም በኋላ ብዙዎች ሰዎችን ሰብስቦ በየቦታው ብዙ ገዳማትን ሠራላቸው። ለሁሉም በእጃቸው ሠርተው በሚአገኙትና በምግባቸው አንድነት እንዲሆኑ በጸሎት ጊዜ በመብልም የሚሠሩትን ሥርዓት ሠራላቸው እርሱ ከሁሉም በላይ አበ ምኔት ሁኖ ከበታቹ ከገዳማት ለየአንዳንዱ አበ ምኔት ሾመላቸው።
ከሀገረ እስዋን ወሰን ከአትፉ ከአክሚም ከተናዱስ እስከ ላዕላይ ግብጽ መጨረሻ ከደቡብም ከባሕራውያን የተመሳቀለ መንገድ ድረስ ሁሉንም ገዳማት በመዞር ይጐበኛቸዋል። ይህም አባት ስለዚህ ዓለም ከንቱ ውዳሴና በመካከላቸውም ጥል እንዳይኖር ከልጆቹ ክህነትን እንዲሾሙ አያሰናብትም ግን ለየአንዳንዱ ገዳም የሚቀድሱላቸውን ቀሳውስት ከዓለም አደረገ።
ሊቀ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ወደ ላዕላይ ግብጽ በወጣ ጊዜ ይህን አባት ጳኩሚስን ቅስና ሊሾመው ወደደ። ከእርሱም ሸሸ። የከበረ አትናቴዎስም ልጆቹን የማይናወጽ ቤትን የሠራህ ሆይ ከከንቱ ውዳሴ የራቅህ አንተ ብፁዕ ነህ ልጆችህም ብፁዓን ናቸው ብሎሃል በሉት አባታችሁን አላቸው።
አንድ ጊዜም ሲኦልን ያይ ዘንድ ወደደ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክም ነጥቆ አውጥቶ በገነት የጻድቃንን ማደሪያ እንዲሁም በሲኦል የሥቃይን ቦታ አሳየው። ይህም አባት በአንድነት ማኅበር ላይ እያጽናናቸውና ሥርዓትንም እየሠራላቸው አበምኔት ሆኖ አርባ ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ በእርሱ ፈንታ ደቀ መዝሙሩን ቴዎድሮስን ሹሞላቸው በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ሲማኮስ ሰማዕት
በዚህችም ቀን የምስር ገዢ በሆነ በቡላሚስ ዘመን ከሀገረ ፈርማ ሰማዕት የሆነ አባ ሲማኮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ቀጭን ልብሶችንና የከበሩ የሐር ልብሶችን የሚሠራ ነው።
ወዳጆችም አሉት እነርሱም ቴዎድሮስና ሲሲኮስ ናቸው ክርስቲያኖችን ሊአሠቃይ መኰንን ቡላሚስ እንደ መጣ በሰማ ጊዜ ይህ ቅዱስ የዚህን ዓለም ክብር ንቀው እስከተዉ ድረስ ባልንጀሮቹን ይመክርና ያስተምራቸው ጀመር።
ከዚህም በኋላ ወዳጆቹን ተሰናብቷቸው ለሀገረ ድሜራ ቅርብ ወደሆነ ወደ ሀገረ በክሩዝ ወጣ መኰንኑንም አንዲቷን ሴት ሲአሠቃያት አገኘው። ወደ እሳት ምድጃም ጨምሮዋት በሰማዕትነት ሞተች። በኋላ ግን እሳቱ ቀዝቃዛ ሆነ ይህ ቅዱስም ይኽንን ይመለከት ነበር።
ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ፊት ቀርቦ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው በዚያን ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበረ።
ሰቀሉት ከመንኰራኲርም ውስጥ ጨምረው አበራዩት ከእርሱም ብዙ ደም ፈሰሰ ወደ አንዲት ዕውርት ሴትም ደሙ ደርሶ ነካት ያን ጊዜም ድና አየች።
ከዚያም ደግመው በእንጨት ላይ ሰቀሉት እርሱም ይረዳው ዘንድ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ፈጽሞ ይማልድ ነበር። መኰንኑም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ሰያፊውም ይቆርጠው ዘንድ ሰይፉን መዘዘ ኃይል ተነሥቶት ማንቀሳቀስ አልተቻለውም። እንዲሁም ሁለተኛው ሦስተኛው እስከ ዐሥራ አራት ሰይፈኞች ኃይላቸው ደክሞ በምድር ላይ ወደቁ።
ከዚህ በኋላ በአንገቱ ገመድ አስገብተው እስከ ረዢም ተራራ አናት ድረስ ጐተቱት። ነፍሱንም በክብር ባለቤት ጌታችን እጅ ሰጥቶ የምስክርነት አክሊልን ተቀበለ። ከወታደሮች ውስጥ ዲዳና ደንቆሮ ነበረ የቅዱሱን ሥጋ በአየ ጊዜ ጆሮቹ ሰሙ አንደበቱም ተናገረ እድኩ ከተባለ ሀገርም ምእመናን መጥተው የቅዱስ ሲማኮስን ሥጋ ወሰዱ። የድሜራና የታይን የሁለቱ አገሮች ሰዎች ተሰበሰቡ መኰንኑ ቢላሞስም ፈርቶ ሸሸ ከሥጋውም ድንቆች ታላላቅ ተአምራት ለበሽተኞችም ፈውስ ሆነ።
አረማውያንም አይተው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ተጠመቁ። በሰማዕትነትም ሞቱ ቁጥራቸውም አንድ ሽህ ሰባት መቶ ኃምሳ ሆነ ወንዶችና ሴቶች ወጣቶችም።
ከዚህ በኋላ የቅዱስ ሲማኮስን ሥጋ ተሸክመው በርሙን ወደሚባል አገር በታላቅ ክብር ወሰዱ። የሀገሩ መኰንንም ከራሱ መልካም ልብሶችን አምጥቶ ገነዘው ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ሥጋውን በውስጧ አኖረ ከእርሱም ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ
ዳግመኛም በዚህች ቀን ድንጋዩን እንደ ጀልባ ተጠቅመው የጣናን ሐይቅ የተሻገሩት የአቡነ ያሳይ ዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ አቡነ ያሳይ ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› ከሚባሉት የሀገራችን ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ እነዚህም ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› የተባሉት አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘቆየፃ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልታርዋ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤ እና አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቄ ናቸው፡፡ እነዚህን የመላእክትን ሕይወት በምድር የኖሩ ታላላቅ የሀገራችንን ቅዱሳን በአንድ ጊዜ አስተምረውና አመንኩሰው ለጽድቅ ያበቋቸው አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፡፡ ‹‹ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን›› የተባሉት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ የኢትዮጵያ ብርሃኗ በሆኑት በአቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ ከመነኮሱ በኋላ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም በተራቸው ያስተማሯቸውና ያመነኮሷቸው መነኮሳት ቁጥራቸው በውል አይታወቅም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ለአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ‹‹ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት ቅዱሳንን›› በመንፈስ ቅዱስ እንደሚወልዱ ትንቢት ተናግረውላቸው ነበር፡፡ የተንቤኑን አቡነ ዐቢየ እግዚእን፣ የዞዝ አምባውን አቡነ አብሳዲን ጨምሮ አባታችን መድኃኒነ እግዚእ ብርሃን ሆነው በጣም ብዙ ቅዱሳንን የለኮሱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ‹‹ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን›› የተባሉት፡፡
አቡነ መድኃኒነ እነዚህንም ሰባቱን ቅዱሳን በአንድ ጊዜ ሲያመነኩሷቸው በዚያው ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን በብርሃን አጥለቅልቆት ታይቷል፡፡ ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰምቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ላይ የመነኮሱት እነዚህ ሰባቱ ቅዱሳን ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ እነዚህም ሰባቱ ከዋክብት የጣናን ባሕር በእግራቸው ጠቅጥቀው ተሻግረው ብዙዎቹን ደሴቱ ላይ ያሉ አስደናቂ የጣና ገዳማትን የመሠረቱት ናቸው፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ባሕሩን በእግራቸውም እየረገጡ ጠቅጥቀው የተሻገሩ አሉ፤ በሌላም ቦታ በየብስ የተሰማሩትም ቢሆኑ መጻሕፍቶቻቸውን በአንበሳ ጭነው የተጓዙ አሉ፤ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይን እንደጀልባ ተጠቅመው በእርሱ ላይ ሆነው ወደ ደሴት የገቡ አሉ፡፡ አንዱ ዛሬ በዓላታቸውን የምናከብራለቸው አቡነ ያሳይ ናቸው፡፡
ቅዱስ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው›› (መዝ 67፡35) ብሎ እንደተናገረ ጻድቁ አቡነ ያሳይ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ ጣና ሐይቅን የሚያቋርጡት በአንድ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ድንጋዩን እንደ ጀልባ ተጠቅመው ነበር፡፡ ያ ድንጋይ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ጻድቁ ከአቡነ ሳሙኤል ጋር አብረው ወደዚህ ቦታ መጡ፡፡ ከዚያም የቦታው አቀማመጥ የብስ መሬትና ደሴት መሆኑን አይተው ‹‹እግዚአብሔር ፈቅዶ ይችን ደሴት የጸሎት ቦታችን አድርጎ ቢሰጠን በጸሎት እንጠይቀው›› ተባብለው ሁሉቱም ቅዱሳን ሱባኤ ገቡ፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንም ለአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ተገሃድ ተልጦላቸው ‹‹ወዳጄ ሳሙኤል ሆይ ይህ ቦታ የአንተ አይደለም የወንድምህ የያሳይ ቦታ ነው፡፡ እኔ ወዳዘጋጀሁልህ ቦታ ወደ ዋሊ ሂድ›› ብሎ የዋልድባን ምድር አሳያቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም የጌታችንን ትእዛዝ ተቀብለው ወንድማቸውን አቡነ ያሳይን ተሰናብተው ወደ ዋልድባ ሄደው ገዳማቸውን አቅንተው ተጋድሎቸአውን በዚያ ፈጸሙ፡፡
ጌታችን ዳግመኛም ለአቡነ ያሳይ ተገለጠላቸውና ‹‹ወዳጄ ያሳይ ሆይ የአባትህን መንግሥትና የዓለሙን ክብር ከምኞቱ ጋር ለእኔ ብለህ ስለተውክ ይህንኑ ቦታ በዚህ ዓለም ሳለህ ለአንተ፣ ወደ ዘላለማዊ መንግሥቴ ከወሰድኩህ በኋላም ለልጆችህ ምንዳህ አድርጌ ሰጥቼሃለሁ፤ ምሕረቴንም በቦታህ አዘንባለሁ ቸርነቴም አይለያትም፣ ብዙ የመንፈስ ልጆችንም ታፈራለህ፤ ቦታህም እኔ ለፍርድ እስክመጣ ድረስ ትኖራለች›› በማለት ቃልኪዳኑን አቆመላቸውና ተሰወራቸው፡፡ ‹‹ምንዳህ›› ማለት ደመወዝ ማለት ነውና በዚህም ‹‹ማንዳባ›› ማለት ‹‹የአቡነ ያሳይ ምንዳ-ደመወዝ›› ማለት ነው ሲሉ አባቶች ገዳሙን ‹‹ማንዳባ-ምን እንደ አባ›› ብለው ሰየሙት፡፡
አቡነ ያሳይ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ተጉለት ነው፡፡ አባታቸው ንጉሡ ዓምደ ጽዮን ቀዳማዊ ነው፡፡ ይኸውም ከ1296-1326 ዓ.ም የነበረው ነው፡፡ አቡነ ያሳይ በልጅነታቸው በንጉሡ አባታቸው ቤት ሲኖሩ የገዳማ መነኮሳት ለመንፈሳዊ ሥራ ወደ ንጉሡ ዘንድ እየመጡ ደጅ ሲጠኑ ያዩአቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን ገና በልጅነታቸው የመነኮሳቱን እግር ያጥቡ ስለነበር በዚሁ አጋጣሚ መነኮሳቱን ስለምንኩስና ሕይወት ይጠይቋቸው ነበር፡፡ መነኮሳቱም ሕይወታቸውን ያስረዷቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይም ብሉያትንና ሐዲሳትን ከልጅነታቸው ጀምሮ የተማሩ ስለነበር የአባቶችን ትምህርትና የወንጌልን ቃል በማገናዘብ የፈጣሪያቸው ፍቅር በልቡናቸው እንደ እሳት ነደደ፡፡ ይልቁንም ‹‹ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል›› የሚለውን የጌታችንን ቃል አሰቡ፡፡ ማቴ 16፡26፡፡ ከዚህም በኋላ የንጉሡ አባታቸውን የአልጋ ወራሽነት ማለትም የንጉሥነትን ክብር ፈጽመው በመናቅ ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር እራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› (ማቴ 16፡27) ያለውን የጌታችንን ቃል አስበው ንጉሣውያን ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ለምነና ወጡ፡፡
ለምነና እንደወጡም ከሸዋ ተነሥተው ወደ ትግራይ ክፍለ ሀገር በአክሱም አቅራቢያ ከሚገኘው ገዳም ደብረ በንኮል ከሚባለው ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ደረሱ፡፡ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም አቡነ ያሳይ የእግዚአብሔር ጸጋ ያደረባቸው ሰው መሆናቸውንና ወደ እርሳቸውም እየመጡ መሆኑን በመንፈስ ዐውቀውት ስለነበር በደስታ ተቀበሏቸውና በረድእነት ከወንድሞቻቸው ጋር ጨመሯቸው፡፡ አቡነ ያሳይም የገዳም መነኮሳትን በማገልገል በመንፈሳዊ ተጋድሎ ብዙ ደከሙ፡፡ በደብረ በንኮል ገዳምም ብዙ እገራሚ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ወደ መካነ ገድላቸው በጣና አካባቢ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ‹‹ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን›› የተባሉ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም ቀደም ብለን የጠራናቸውን ‹‹ሰባቱን ከዋክብት›› ምግባር ሃይማኖታቸውን፣ ተጋድሎ ትሩፋታቸውንና ገቢረ ተአምራታቸውን አይተው ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቀው በአንድ ቢያመነኩሷቸው በዚያው ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን በብርሃን አጥለቅልቆት ታይቷል፡፡ ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰምቷል፡፡ ከዚህም በኋላ ከሰባቱ ቅዱሳን ውስጥ ሦስቱ ቅዱሳን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ያሳይ እና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ሆነው ከደብረ በንኮል ገዳም አባታቸውን አቡነ መድኃኒነ እግዚእን ተሰናብተው ወደ ጣና ደሴት መጥተዋል፡፡
አቡነ ያሳይ በ13ኛው መ/ክ/ዘመን በአባታቸው የዘመነ ንግሥና መጨረሻ ወደ አርባ ምንጭ ሄደው ከዚያው ሱባኤ ገብተው ፈጣሪያቸውንነ ቢማጸኑ እግዚአብሔርም ከዚያው አካባቢ የሚኖር አንድ ባሕታዊን የመድኃነዓለምን ጽላት እንዲወጣቸው አዘዘላቸው፡፡ እርሳቸውም ጽላቱን ተቀብለው በጎጃም በኩል አድርገው ወደ ጣና ተመልሰው በዘጌ አከባቢ ሲደረሱ ከጣና ባሕር ዳር ቆመው በየብስ ያለውን ርቀትና በባሕሩ ያለውን ቅርበት አይተው አሁንም ወደ ፈጣሪያቸው በጸሎት ተማጸኑ፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ተገልጦላቸው ‹‹ወዳጄ ያሳይ ሆይ አትጨነቅ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ ከጎንህ ያለውን ድንጋይ በባሕሩ ላይ ጫነው፤ ድንጋዩም ለልጅ ልጅ እኔ ዓለምን ለማሳለፍ እስከምመጣበት ሰዓት ድረስ መታሰቢያ ትሁንህ›› አላቸውና ተሰወረ፡፡ አቡነ ያሳይም የመድኃኔዓለምን ጽላት ይዘው በድንጋዩ ላይ እንደተቀመጡ ድንጋዩ እንደታንኳ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ፡፡ ባሕሩም ከማዕበሉ ብዛት የተነሣ ይታወክ ነበር፡፡ አባታችንም ያለ ምንም ቀዘፋ ልብሳቸውም ውኃ ሳይነካው ቁጭ እንዳሉ ማን እንደአባ ወደ ተባለው ቦታቸው ደረሱ፡፡
ከዚህም በኋላ አቡነ ያሳይ ገዳማቸውን ገድመው ወንድሞቻቸውን ሰብስበው በተጋድሎ በመኖር ብዙ ቅዱሳንን አፍርተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የጌታችንን እግር ያጠቡት አቡነ አብሳዲ፣ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ዝናብንና ነፋስን የከለከሉት አቡነ ያዕቆብ፣ እሬትን እንደ ማር ያጣፈጡት አቡነ ገብረ ኢየሱስ፣ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸጋንና ሞገስን የተሞሉት አቡነ ዳንኤል፣ እንደ ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብን የተሞሉት አቡነ ፊቅጦርና ሌሎችም ብዙዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በወቅቱም ብዙ የበቁ ቅዱሳን በአካባቢው ነበሩ፡፡ በአጽፋቸውና በእግራቸው በባሕሩ ላይ የሚሄዱ ነበሩ፣ በጸጋ ክንፍ ተሰጥቷቸውም የሚበሩ ነበሩ፡፡ የአቡነ ያሳይ ተአምራቶቻቸው ተነግረው አያልቁም፡፡ በወቅቱ የነበሩት ቅዱሳን ልጆቻቸው ‹‹ከቅዱሳን ማን እንደ አባ ያሳይ በከባድ ድንጋይ ላይ ተጭኖ በባሕር ላይ የተጓዘ አለና..›› ብለው ይገረሙባቸው ነበር፡፡ ቦታቸውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‹‹ማን እንደ አባ›› ተባለ፡፡ ይህም የአቡነ ያሳይ ገዳም በሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት በደንቢያ ወረዳ በጎርጎራ ጣና ሐይቅ አካባቢ ይገኛል፡፡
በጣና ደሴት ላይ ከሚገኙት ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ አንዱ ‹‹አትማረኝ ዋሻ›› ነው፡፡ ይህም ዋሻ ታሪኩ ከአቡነ ያሳይ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፡- አትማረኝ ዋሻ በጣና ሐይቅ ደሴቶች መካከል ከሚገኙ ገዳማት መካከል ከማን እንደ አቡነ ያሳይ መድኀኔዓለም አንድነት ገዳም በስተ ምእራብ አቅጣጫ የጣና ሐይቅን ጉዞ ከገታው አንድ ተራራ ሥር የሚገኝ ዋሻ ነው፡፡ ይህ ዋሻ ለብዙ ዘመናት አንድ ታላቅ አባት የጸሎት በዓት አድርገውት ‹‹አትማረኝ›› እያሉ የጸለዩበት ቦታ ነው፡፡ አቡነ ያሳይ ወደ ጣና ደሴት ከአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ እና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ጋር በመሆን በጸሎት ይተጉ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል፡፡ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ በጣና ሐይቅ ላይ እንደ ጀልባ የሚጓዙበት አንድ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይ በጣና ደሴት ላይ ለአገልግሎት በመፋጠን ላይ እያሉ ዛሬ አትማረኝ ዋሻ ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ አንድ አባት ዋሻው ውስጥ “አትማረኝ፣ አትማረኝ፣ አትማረኝ” እያሉ ሲጸልዩ ያገኟቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይም በሰውዬው ጸሎት በመገረም ቀርበዋቸው ‹‹አባቴ ምን ዓይነት ጸሎት ነው የሚጸልዩት?›› አሏቸው፡፡ ያም አባት ‹‹አባቴ እንደ እርስዎ ያሉ አባት መጥተው ‹አትማረኝ› እያልክ ጸልይ ብሎኝ ነው›› በማለት መለሱላቸው፡፡ አቡነ ያሳይም ‹‹እንዲህ ዓይነት ምክር የሚመክር ጠላት ዲያብሎስ ነው፡፡ ከዛሬ ጀምረው ‹ማረኝ› እያሉ ይጸልዩ በማለት አቡነ ዘበሰማያትን አሰተምረዋቸው ይሄዳሉ፡፡ ‹‹አትማረኝ›› እያሉ ይጸልዩ የነበሩት አባትም ‹‹ማረኝ›› እያሉ መጸለያቸውን ቢቀጥሉም ብዙ መግፋት ሳይችሉ ቀሩና ጸሎቱ ይጠፋባቸዋል፡፡ ወደ ሐይቁ ሲመለከቱም አቡነ ያሳይ ድንጋዩን እንደጀልባ ተጠቅመው እየሄዱ ነው፡፡ ጸሎቱን ያስጠኗቸው አቡነ ያሳይ ርቀው ሳይሄዱባቸው ያ አባት በውኃ ላይ በእግራቸው እየተራመዱ በመከተል ይደርሱባቸዋል፡፡ ከኋላቸውም ሆነው ‹‹አባታችን ያስጠኑኝ ጸሎት ጠፋብኝ፤ እባክዎን እንደገና ያስተምሩኝ›› አሏቸው፡፡ አቡነ ያሳይም ሐይቁን በእግራቸው እረገጡ እስኪሄዱ ድረስ ጽድቃቸው የተገለጠውን የእኚህን አባት መብቃት ተመልከተው ‹‹አባቴ እግዚአብሔር የልብ ነውና የሚመለከተው እንዳስለመዱት ይጸልዩ የእርስዎ ይበልጣል›› ብለዋቸው ሔዱ፡፡ በዚህም ምክንያት ቦታው ‹‹አትማረኝ ዋሻ›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ የአቡነ ያሳይ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት ሙሽራው ቅዱስ ገብረክርስቶስ ከጫጉላ ቤቱ ወጥቶ የመነነበት ዕለት ነው፡፡ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ ወላጅ አባቱ የቍስጥንጥንያው ንጉሥ ቴዎዶስዮስና እናቱ ንግሥት መርኬዛ በስለት ያገኙት ብቸኛ ልጃቸው ስለሆነ ሃይማኖትን እያስተማሩት በምግባር በእጅጉ ተንከባክበው አሳድገውታል፡፡ የአባቱን ንግሥና በመውረስ ቍስጥንጥንያን እንዲገዛላቸው በመፈለግ ወላጆቹ ለአካለ መጠን ሲደርስ የሮሙን ንጉሥ ሴት ልጅ አጋቡት፡፡ እርሱ ግን ዓለምን ፍጹም በመናቅ የክርስቶስን መስቀል ለመሸከም የተዘጋጀ ነበርና የሠርጉ ዕለት ሌሊት የእርሱንም ሆነ የሙሽይቱን ድንግልና እንደጠበቀ ከጫጉላ ቤት ወጥቶ በመርከብ ተሳፍሮ ሩቅ ሀገር በመሄድ በቤተክርስቲያን ተቀምጦ ከነዳያን ጋር ተደባልቆ በመለመን ለምኖ ያገኘውንም ለሌሎች እየመጸወተ በጾም በጸሎት ተጠምዶ 15 ዓመት ኖረ፡፡
እመቤታችን ተገልጻ ለአንድ የቤተክርስቲያኑ አገልጋይ የገብረ ክርስቶስን ጽድቅ ብትነግረው ምሥጢሩን ለሀገሩ ሁሉ አዳረሰበት፡፡ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስም ‹‹ግብሬ ታወቀ፣ ከዚህ ውዳሴ ከንቱ ልሽሽ›› በማለት ወደሌላ ሀገር በመርከብ ሲጓዝ ፈቃደ እግዚአብሔር መርከቢቱን ያለ አቅጣጫዋ ወስዶ አባቱ ደጅ አደረሰው፡፡ ማንነቱን እንደደበቀና ዓለምን ምን ያህል እንደናቃት ይረዳ ዘንድ በአባቱና በንጉሡ ደጅ የኔ ቢጤ ለማኝ ሆኖ ለአባቱ ውሾች የሚሰጠውን ፍርፋሪ እየተመገበ አሁንም 15 ዓመት ሙሉ በትዕግስት ተቀመጠ፡፡
የአባቱ አሽከሮች እንኳን እጣቢና ቆሻሻውን ሁሉ እየደፉበት ሲያሠቃዩት የአባቱ ውሾች ግን የእግሩን ቁስል ይልሱለት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ገብረ ክርስቶስ እጅግ የተከበረ የታላቅ ንጉሥ ልጅ ሲሆን ነገር ግን ዓለምን ፍጹም በመናቅ ስለ ጽድቅ ተሰዶ እየለመነ ያገኘውን እየመጸወተ በጾም በጸሎት እየተጋደለ 30 ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፡፡ በመጨረሻም ጌታችን እመቤታችንን፣ ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ፣ ከገብረ ክርስቶስ በፊት የነበሩ ነቢያትን ሁሉ፣ ሐዋርያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ቃልኪዳን ከገባለት በኋላ ከጌታችን ጋር አብረውት የመጡት ሁሉ በታላቅ ክብርና ምስጋና እያመሰገኑት ጌታችን ክብርት ነፍሱን በእቅፉ ተቀብሎ አሳርጓታል፡፡
የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ በቅዳሴ ላይ ሳሉ ከንጉሡ ቤት ሄደው የገብረ ክርስቶስን ሥጋ እንዲያመጡ የእግዚአብሔር ድምፅ ከሰማይ በትእዛዝ መጣላቸውና ሄደው ቢያዩ የገብረ ክርስቶስን ሥጋ በንጉሥ አባቱ ደጅ ወድቆ አገኙት፡፡ በገብረ ክርስቶስም እጅ ላይ በጥቅል ወረቀት የተጻፈ ደብዳቤ ነበርና ወስደው ሊያነቡት ሲሞክሩ ወረቀቱ አልላቀቅ ብሎ ፈጽሞ እምቢ አላቸው፡፡ ብዙ ምሕላና ጸሎት ከተደረገ በኋላ ወረቀቱ ከእጁ ላይ ተላቀቀና ሲነበብ ገብረ ክርስቶስ ስለ አምላኩ ፍቅር ብሎ ለ30 ዓመታት ያሳለፈውን እጅግ አሠቃቂ መከራ በተለይም በአባቱ ደጅ ማንም ሳያውቀው ያሳለፈውን እጅግ አሳዛኝ መከራና በኀዘን የሚያስለቅሰውን ታሪኩን በራሱ እጅ በዝርዝር ጽፎት ተገኝቷል፡፡ ንጉሡ አባቱና ንግሥት እናቱም ይህንን ልጃቸው የጻፈውን መልእክት ባነበቡ ጊዜ የሚሆኑት ጠፋቸው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ መጀመሪያ ላይ ወላጆቹ ሚስት አድርገው ያመጡለት የሮሙ ንጉሥ ሴት ልጅ ለባሏ ታማኝ ሆና 30 ዓመት ሙሉ በእናት አባቱ ቤት በትዕግስት ስትጠብቀው መኖሯ ነው፡፡ እርሷም ታሪኩ ሲነበብ ብትሰማ እንደ ዕብድ ሆነች፡፡ የቅዱስ ገብረ ክርስቶስን ሥጋውን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱ እጅግ አስገራሚ ተአምራት በድውያን ሕመምተኞች ላይ ተፈጽሟል፡፡ ከተአምራቱ የተነሣ መንገዱ በሕዝብ ተጨናንቆ አላሳልፍ ቢላቸው ነገሡ በመንገድ ዳር ወርቅ እየበተነ ሰው ወርቁን ለማንሳት ሲሄድ በፍጥነት ወደ ቤተ ክርስቲያን አድርሰውታል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages