ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 15 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, May 23, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 15

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምግንቦት ዐሥራ አምስት በዚች ቀን ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ሐዋርያ ስምዖን ምስክር ሆኖ አረፈ። እርሱም ናትናኤል ተብሎ ይጠራል በገሊላ አውራጃ የቃና ሰው ነው የኦሪትና የነቢያትንም መጻሕፍት ተምሮ ያወቀ ነው። መንፈሳዊ ቅንዓትም በውስጡ አለበት ስለዚህም ቀናዒ ተባለ እርሱም ንጹሕ ፊት አይቶ የማያደላ በሃይማኖቱ ዕውነተኛ ነው።
ስለዚህም ፊልጶስ ስለርሱ ሙሴ የጻፈለትን የዮሴፍ ልጅ የሚሉትን የናዝሬቱን ክርስቶስን አገኘነው ባለው ጊዜ ከናዝሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይቻላልን አለው እንጂ አላደላለትም ፊልጶስም ታይ ዘንድ ና አለው።
በመጣም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ይህ በልቡ ሽንገላ የሌለበት ዕውነተኛ እስራኤላዊ ነው አለው። አሁንም ምስጋና ወደመቀበል አልተመለሰም በየት ታውቀኛለህ አለው እንጂ ልብንና ኵላሊትን የሚመረምር ጌታችንም ፊልጶስ ሳይጠራህ በፊት በበለስ ዕንጨት ሥር አየሁህ አለው። ያን ጊዜም የተሠወረውን የሚያውቅ አምላክ መሆኑን ተረድቶ ጌታዬና ፈጣሪዬ በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ የእስራኤልም ንጉሥ ነህ አለው እንደ አይሁድ መምህራንም አልተቃወመም እነርሱ ከዚህ የሚበልጥ ድንቅ ተአምራትንና ኃይሎችን አይተው ለዕውነት አልተገዙምና።
ስለርሱ እንዲህ ተብሏል ጐልማሳ ሁኖ ሳለ ከአሕዛብ ወገን ከሆነ ጐልማሳ ጋራ ተጣልቶ አንዲት አመታትን መትቶ ገደለው በቤቱ ዐፀድም በአለ ዕፀ በለስ በሥሩ ቀበረው ይህንንም ማንም አላወቀበትም።
ሁለተኛም በሕፃናት ዕልቂት ጊዜ እናቱ በአገልግል ውስጥ አድርጋ በበለስ ዕንጨት ላይ ሰቅላ ትሸሽገው እንደ ነበር በጭልታም አውርዳ አጥብታ መልሳ ትሰቅለዋለች የከመራውም ጊዜ ጸጥ እስከ አለ ድረስ እንዲህ ታደርግ ነበር።
መድኃኒታችንም በምልክት ከእርሱ የሆነውን በገለጠለት ጊዜ የተሠወረውን የሚያወቅ ሁሉንም የሚመረምር በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተረዳ። ያንጊዜም ራሱን ዝቅ አድርጎ ለመድኃኒታችን ተገዛለት። ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ተከተለው ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያትም ጋራ ተቈጠረ።
አጽናኝ የሆነ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በተቀበለ ጊዜ የሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ተገለጠለት መለኮታዊ ምሥጢርንም አወቀ ወደ ኵርጅ አገርና ወደ እልብጅህ ከተማ ከሀድያን በድንቁርና ወደሚኖሩበት ሁሉ ገብቶ የሃይማኖትን ብርሃን አበራላቸው። ከተራቃቂዎችና ከሰነፎችም ብዙዎችን መልሶ በክብር ባለቤት ክርስቶስ ሃይማኖት ልባቸውን አበራላቸው። የክርስትና ጥምቀትንም አጥምቆ ነጣቂዎች ተኵላ የነበሩትን የዋሃን በጎች አደረጋቸው።
ሁለተኛም ወደሌሎች የከሀድያን አገሮች ወደ በራንጥያ ደሴትም ሒዶ በውስጣቸው ሰበከ። ይዘውም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃዩት እርሱ ግን ኃይልና ብርታትን ተጨመረ በእግዚአብሔርም ኃይል ሙታንን አስነሣ እንዲአጠምቃቸውም ለመኑት የክርሰትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ብዙ ዘመንም ኖረ።
ከዚህም በኋላ ከሀድያን ይዘው በዕንጨት ላይ ሰቀሉት በዚህም ምስክርነቱን ፈጽሞ ከወንድሞቹ ሐዋርያት ጋራ የማይጠፋ መንግሥትን ወረሰ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፡ ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages