ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, May 6, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 28

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ሃያ ስምንት በዚች ቀን በኮራሳት ተራራ በገድል ተጠምዶ የሚኖር ቅዱስ_ሜልዮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ መቅሱር ከሚባል አገር ቅዱስ_ብስጣውሮስ በሰማዕትነት አረፈ።


ሚያዝያ ሃያ ስምንት በዚች ቀን በኮራሳት ተራራ በገድል ተጠምዶ የሚኖር ቅዱስ ሜልዮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም አባት ኮራሳት በሚባል አገር በተራራ ባሉ ዋሻዎች ከሁለት አርድእቱ ጋራ ይኖር ነበር።
የኮራሳት ንጉሥ ሁለቱ ልጆቹ ወደዚያ ወጡ ከእርሳቸውም ጋራ አገልጋዮች አሉ አራዊትን አጥምደው በፍላፃዎች ይገሉ ዘንድ መረባቸውን ተክለው አርባ ምዕራፍ ያህል ሔዱ። መረቡን በጠቀለሉት ጊዜ ይህን ቅዱስ አባት ማቅ ለብሶ ጠጉሩም የረዘመ ሁኖ አገኙት።
የንጉሥ ልጆችም በአዩት ጊዜ ፈሩ አንተ ሰው ነህን ወይም መንፈስ ብለው ጠየቁት እርሱም በዚህ ተራራ ውስጥ የምኖር ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የምሰግድ ሰው ነኝ ብሎ መለሰላቸው።
እነርሱም ከእሳትና ከፀሐይ በቀር አምላክ የለም እንዳንገድልህ ሠዋላቸው አሉት። እርሱም እሳትና ፀሐይ የተፈጠሩ ናቸው እናንተም ተሳስታችኋል ፍጥረቶችን በፈጠረ በዕውነተኛ አምላክ ታምኑ ዘንድ እኔ እለምናችኋለሁ ብሎ መለሰላቸው።
በዚያን ጊዜ ይህን አባት ሁለቱን አርድእትም ይዘው ጽኑ ሥቃይ አሠቃዩአቸው በዚህ ወር በዐሥራ ሦስት የሁለቱን አርድእት ራሳቸውን ቆረጡአቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።
አረጋዊ ቅዱስ ሜልዮስን ግን ዐሥራ አምስት ቀን ያህል ሲአሠቃዩት ኖሩ ከዚህ በኋላ በመካከላቸው አቆሙት አንዱ በፊት አንዱ በኋላ ሁነው በፍላፃ ይነድፉት ጀመር። እርሱም በእናንተ ላይ ክፉ ያልሠራውን ለመግደል ሁለታችሁ ስለተስማማችሁ እንዲሁ እንደሥራችሁ በፍላፃችሁ ነገ ትሞታላችሁ አላቸው። ሰምተውም አልፈሩም ነፍሱን እስከሚአሳልፍና ምስክርም ሆኖ የሰማዕትነት አክሊልን እስከሚቀበል ነደፉት እንጂ።
በማግሥቱም እንደልማዳቸው ለአደን ወጡ የዱር አህያም አገኙ ተከትለውም ቀስታቸውን አስፈነጠሩ እግዚአብሔርም ፍላፃቸውን ወደልባቸው መለስ ቅዱስ ሜልዮስም እንደተናገረባቸው ሞቱ።
በዚህ ቅዱስም እጅ ጌታችን ተአምራትን ገለጠ በአንዲት ዕለትም አልፎ ሲሔድ በመንገድ ላይ የሞተ ሰው አገኘ የአገር ሰዎች ግን አንዱን መነኰስ አንተ ነህ የገደልከው ብለው ያዙት። ቅዱስ ሜልዮስም ጸለየ የሞተውንም በውኑ የገደለህ ይህ መነኵሴ ነውን አለው ያን ጊዜ የሞተው ተነሥቶ እርሱስ አልገደለኝም ነገር ግን ብዙ ገንዘቤን ከአንድ ቄስ ዘንድ አደራ አስጠበቅሁ ስለዚህ ገደለኝ ከዚህም ጣለኝ አለ ደግሞ እንዲህ ብሎ ለመነው ዕገሌ ወደሚባል ወደዚያ ቄስ ሒደህ ገንዘቤን ከርሱ ተቀብለህ ለልጆቼ ስጥ ቅዱስ ሜልዮስም እስከ ትንሣኤ ቀን በሰላም አርፈህ ተኛ እኔ ገንዘብ አከፋፋይ ዳኛ አይደለሁም አለው ያንጊዜም ተኛ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን መቅሱር ከሚባል አገር ቅዱስ ብስጣውሮስ በሰማዕትነት አረፈ። የዚህም ቅዱስ አባቱ ጻድቅ ሰው ነው እናቱን ግን ሰይጣን አስቷት ወደ እስልምና ገባች እርሱም ፈሪሀ እግዚአብሔርን እየተማረ እስከሚጐለምስ አደገ አካለ መጠንም አድርሶ ሚስት አገባ ከርሷም ልጆችን ወለደ።
ብዙ ዘመናትም በአለፉ ጊዜ አንገተ ደንዳና በቀለኛ ሰው በእርሱ ላይ ተነሥቶበት ወደ እስላሞች መኳንንት ሒዶ ሰው ወደ እኛ ሕግ ቢገባ ልጆቹም ሃይማኖቱን ይከተላሉ ይህ ብስጣውሮስ ግን ከሕጋችን የተለየ ነው ብሎ ነገር ሠራበት።
የእስላሞች ዳኞችም በሰሙ ጊዜ መልዕክተኞች ልከው ወደርሳቸው ወደ ሸንጎ አቀረቡት ስለ ሃይማኖቱም ጠየቁት ክርስቲያን እንደሆነ ያለ ፍርሀት ክርስቲያን ነኝ ብሎ ታመነ።
ዳኛው ግን ይሸነግለው ዘንድ በፍቅር ይናገረው ጀመረ ከከበረችና ከቀናች ሃይማኖቱ ይመልሰው ዘንድ ብዙ ስጦታዎችን እንደሚሰጠው ቃል ገባለት ቅዱሱ ግን ከቶ አልተመለሰም ወደ ስጦታውም ከቶ ልቡ አላዘነበለም።
ከዚህ በኋላ ወደ ግዞት ቤት ወስደው በእግረሙቅ እንዲአሥሩት በአንገቱም የተበሳ ታላቅ ግንድ አሥረው በግንባሩ ደፍተው በኲስ ላይ እንዲጥሉት መኰንኑ አዘዘ። እንዲሁም አደረጉበት እስከ ሦስት ቀን በእሥር ቤትም ሳለ ፀዐዳ ርግብ መጥቶ ጋረደው ስለዚህም የእሥር ቤቱ ጠባቂ ምስክር ሆነ።
ከዚህም በኋላ ዳኞች ወደ ሸንጎ አስቀርበው ከእንግዲህ አንታገሥህም ወደ ሃይማኖታችን ከምትገባና ወይም በእሳት ከምናቃጥልህ ምረጥ አሉት። እርሱም እኔ ከእናንተ ጋራ ለዘላለሙ ዕድል ፈንታ የለኝምና የወደዳችሁትን አድርጉ ብሎ መለሰላቸው።
በዚያን ጊዜም እጅግ ተቆጡ ያለ ርኀራኄ ይደበድቡት ዘንድ አዘዙ ያገር ሰዎችም በጫማቸው መቱት አንዲት ሴትም መጥታ በጫማዋ መታችው ወዲያውኑ እጆቿ ደረቁ።
ከዚህም በኋላ ባለ ሰይፍ ከመኰንኑ ታዝዞ ወጣ ሰይፉንም መዝዞ ሳያቋርጥ መላልሶ አንገቱን መታው። ምቱም ወደ ጐን ሒዶ ጆሮውን ቆረጠው አመታቱ ክፉ ስለ ሆነ ከሥሮቿ ብዙ ደም ፈሰሰ።
ከዚህም ደግሞ ተዉት ወደ እምነታቸው ሊአስገቡት እምቢ በአላቸውም ጊዜ ሁለተኛ ሰይፉን መዝዞ ሰያፊው የከበረች አንገቱን ቆረጠው በመንግሥተ ሰማያትም የምስክርነት አክሊልን ተቀበለ። ሥጋውንም ከእሳት ጨመሩ ግን አልተቃጠለም። ዘመዶቹም መጥተው በድኑን ወደአገሩ ወሰዱ። በቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ ጐን ቀበሩት። የክብር ባለቤት ጌታችንም ብዙ ድንቆች ተአምራትን ከሥጋው ገለጠ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም ቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages