ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 3 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, May 11, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 3

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምግንቦት ሦስት በዚች ቀን ጌታ ከመረጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን አረፈ። ይህም ቅዱስ ከሐዋርያት ጋራ ወንጌልን በሰበከ ጊዜ ብዙ መከራዎችን በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተቀበለ ድንቆች ተአምራትንም አደረገ በሃምሳኛው ቀን ከሐዋርያት ጋራ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሏልና።
ትውልዱም ከጠርሴስ አገር ነው ከጠርሴስም ሰዎች አስቀድሞ አመነ ሐዋርያ ጳውሎስም ከተጠራና ከአመነ በኋላ በብዙ አገሮች ተከትሎ በወንጌል ትምህርት አገለገለው በተሰሎንቄ ከተማም ከጳውሎስ ጋራ ይዘው በመጐተት ከተሰሎንቄ ገዢ ዘንድ አቀረቡአቸው።
ከዚህም በኋላ በጠርሴስ አገር ቅዱስ ጳውሎስ ኤጲስቆጶስነት ሾመው የወልደ እግዚአብሔርንም ቤተ ክርስቲያን በመልካም አጠባበቅ በቅንነት ጠበቀ። ምእመናንን በቀናች ሃይማኖት ከአጸናቸውና በጎ ምግባርን ከአስተማራቸው በኋላ ከዚያ ወደ ምዕራብ አገር ሒዶ በውስጥዋ የከበረ ወንጌልን አስተማረ። ስሟ ኮራኮራስ ወደምትባል ደሴትም ደርሶ በውስጧ ወንጌልን ሰበከ እግዚአብሔርንም ወደማወቅ መለሳቸው በዲያቆናት አለቃ በሰማዕታትም መጀመሪያ በከበረ ሐዋርያ እስጢፋኖስ ስም በውስጧ ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው።
የዚያች አገር ገዥም በአወቀ ጊዜ ይዞ ከእሥር ቤት አስገባው በዚያም ሰባት ወንበዴዎችን አግኝቶ ሃይማኖትን አስተማራቸው በክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው። ከዚያም በኋላ በመኮንኑ ፊት ቁመው እኛ ክርስቲያን ነን በክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን ብለው ጮኹ። መኰንኑም ዝፍትና ዲን በተመላ ምጣድ ውስጥ አግብቶ አቃጠላቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሶንን ከእሥር ቤት አውጥቶ ብዙ አሠቃየው ነገር ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰበትም። የንጉሡም ልጅ ከቤቷ መስኮት ሁና አይታ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነች ልብሶቿንና ጌጦቿን አውጥታ ለድኆችና ለምስኪኖች ሰጠችና ከዚያም በሐዋርያው በያሶን አምላክ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ታመነች አባቷም ሰምቶ እንዲአሥሩዋት አዘዘ እንዳዘዛቸውም አደረጉ። በጢስም አፍነው አሠቃዩዋት ደግመውም አራቈቷትና አባቷ በፍላፃ ነደፋት ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሶንን ወደ ደሴት ሰደደው በደሴትም ውስጥ ያሠቃየው ዘንድ መኰንኑ ከሠራዊቱ ጋራ አብሮ በመርከብ ተሳፈረ እግዚአብሔርም ከሠራዊቱ ጋራ በባሕር አሠጠመው።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሶን ወንጌልን እያስተማረ ብዙ ዘመናት ኖረ። ሁለተኛም ሌላ መኰንን ተሾመ ቅዱስ ያሶንንም ይዞ በምጣድም ውስጥ ድኝና ዝፍት ሰም መልቶ ነበልባሉ ወደ ላይ እስቲወጣ ድረስ ከበታቹ አነደደ ቅዱስ ያሶንንም በውስጡ ጨመረው። የክብር ባለቤት ጌታችንም አዳነው ምንም ምን ጉዳት አልደረሰበትም መኰንኑም ይህን ድንቅ ሥራ አይቶ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተሰቡ ሁሉ ከሀገር ሰዎች ሁሉ ጋራ አመነ። ሁሉንም አጥምቆ የከበረ የወንጌልን ሕግና ትእዛዝ አስተማራቸው አብያተ ክርስቲያንም ሠራላቸው በውስጣቸውም ብዙ ድንቆች ተአምራትን አደረገ ብሩህ በሆነ ገድሉ ጌታችንን ደስ ካሰኘውና ካገለገለው በኋላ በበጎ ሽምግልና አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages