ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 4 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, May 11, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 4

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት አራት በዚህች ቀን ኢትዮዽያዊ ጻድቅ አቡነ_መልከ_ጼዴቅ_ዘሚዳ ዕረፍታቸው ነው፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ_ዮሐንስ አረፈ።


ግንቦት አራት በዚህች ቀን ኢትዮዽያዊ ጻድቅ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ ዕረፍታቸው ነው፡፡ እኚህ ጻድቅ ከከበሩና ነገሥታት ከሆኑት ወገን በአገረ ጐጃም ኢናይ በምትባል ቦታ የካቲት አሥራ ስድስት ቀን ተወለዱ፡፡ ልደታቸውም እንዲህ ነበር፡፡
ንጉሥ አምደ ጽዮን ምስረነዓዳን ወለዱ፣ ምስረነዓዳም በዝራምበሳን ወለደች፣ በዝራምበሳም ፍሬጽዮንን ወለደ፣ ፍሬጽዮንም መልከ ጼዴቅን ወለደ የእናታቸውም ስም ቅድስት ዓመተ ማርያም ነው፡፡ በተወለዱም ጊዜም በአባትና በእናታቸው ቤት ታላቅ ደስታ ሆነ እግዚአብሔር ለብዙዎች አባት አድርጎ መርጦአቸዋልና፡፡
ለትምህርት በደረሱም ጊዜ መዝሙረ ዳዊት ይማሩ ዘንድ አባትና እናታቸው ለመምህር ሰጧቸው ፡፡ እርሳቸውም አምቢ ብለው ወደ አባትና እናታቸው ቤት ተመለሱ ፡፡ ፈረስ ጋላቢም ሆኑ፡፡ ደግሞ እኚህ ጻድቅ በጐለመሱ ጊዜ አባትና እናታቸው መልኳ የምታምር ሚስት አጩላቸው፡፡ የአባታቸውንም ሹመት የንጉሥ ሠራዊት አለቃ ሆነው ተሾሙ፡፡ በልባቸውም ሰሎሞን እንደተናገረው "ከፀሐይ በታች ያለው ሁሉ ከንቱ እንደሆነ አሰቡ" "በምድር ላይ ቋሚ የፀና ሕይወት የለምና" ይህንም ብለው ከአባትና ከእናታቸው ቤት ተሰደዱ፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ እየመራቸው ቅጽሮ ወደሚባል አገር ደረሱ የበሩም ጠባቂዎች አባታችን መልከ ጼዴቅን ከተሸከሟቸው ሁለት የወርቅ ልብሶች ጋር አቆሙአቸው "አትሻገር ተመለስ" አሏቸው፡፡ ያ የበር ጠባቂ የሆነ ሰውም "ለሌላው እስከምመለስ ጠብቀው" አላቸው ይህን ብሎም ይረዷቸው ዘንድ ጓደኞቹን ሊጠራ ሄደ የሚመራው መልአክም መልከ ጼዴቅ "ከወርቅህ ጋር ከዚህ ሂድ" አላቸው ልብሶቻቸውንም ተሸክመው ሄዱ፡፡ ይመራቸው የነበረ የእግዚአብሔር መልአክም እነዚህን የበርሃ ጠባቂዎች እንደ ድንጋይ የፈዘዙ እንደበድን የደነዘዙ አደረጋቸው፡፡ መናገርም ተሳናቸው፡፡
ከዚህ በኋላም የኢዮስያስ ቦታ ወደ ሆነችው ደጋዳሞት ደብረ ምዕራፍ ደረሱ፡፡ ከአባታችን ኢዮስያስ ቀጥሎ (በኋላ) በተሾሙት በአባታችን በአቡነ አሮን እጅ በዚያ መነኰሱ እርሳቸው አስቀድመው በስውር መንኩሰው ነበርና፡፡ አባታችን አቡነ አሮን ንዑድ ክቡር ለሚሆን መልከ ጼዴቅ የምንኩስናን ልብስ አለበሳቸው፡፡
ከዚህም በኋላ አባትና ወንድሞቹ ዘመዶቹም ኤናይ ከምትባል አገሩ እየፈለጉ መጡ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ተሰወራቸው አላገኙትም አባታችን አሮንንም ይዘው "ልጃችን አባት እናቱን እጮኛውንና ሹመቱን ትቶ ወደ አንተ መጥቷልና ስጠን" አሉት፡፡ አባታችን አሮንም ቅዱስ መልከ ጼዴቅ እንደመነኰሰ ነገራቸው፡፡ ያን ጊዜም አባትና እናቱ ወንድሞቹና ዘመዶቹ ታላቅ ለቅሶን አለቀሱ አዘኑ "ወዮልን ወዮልን ክብራችን ፈርሶአልና ኃይላችንም ተሽሮአልና ወልደን እንደ አልወለድንም ሆነናልና" አሉ፡፡ ከአባታችን ከአቡነ አሮን ጋር አስታረቋቸው አባቱም ያን ጊዜ "የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን" አለ አስቀድሞ ቅዱሳንን ሲጎበኝና ለነዳያን ሲራራላቸው ባየሁ ጊዜ ይህ ልጅ መነኩሴ እንደሚሆን በልቤ አስብ ነበር፡፡ ትተውትም ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላም የእግዚአብሔር መልአክ ክቡር መልከ ጼድቅን በዚያ ወስዶ ደብረ መድኃኒት አደረሳቸው፡፡ በዚያም ከቀሲስ አስጢፋኖስ የዳዊትን መዝሙርና የመጻሕፍትን ቃል እየተማሩ ተቀመጡ፡፡ ፈጥነውም ጨረሱ መንፈስ ቅዱስ በእርሳቸው ላይ ይናገራልና፡፡
ከዚህ በኋላ ከትንሽ ዋሻ ገቡ የአምላካቸውን የክርስቶስን መከራ በማሰብ በዚያ ገብተው ቀንና ሌሊት ዘግተው በረደኝ ፀሐይ ልሙቅ፣ ጨለመኝ ብርሃን ልይ ሳይሉ በጸሎት ብቻ ዘግተው በመኖር ራሳቸውን በችንካር እያቆሰሉና ጭንቅላታቸውን እያተሉ ትሉን ለሰማይ አእዋፍ ይመግቡ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የተገረፈውን ግርፋት እያሰቡ በየቀኑ እስከ ሦስት ሺህ ድረስ ይሰግዳሉ፡፡ ሰውነታቸውንም እንዲሁ ይገርፋሉ፡፡ የክርስቶስን መቸንከር እያሰቡ እጅና እግራቸውን፣ ወገብና ደረታቸውን በብረት ቸንክረው መከራውን ያስባሉ፡፡
ጎኑ በጦር መወጋቱን አስበው አጥንታቸው እስኪሰበር ድረስ ጎናቸውን ወጉ፤ ሐሞትና ከርቤ መጠጣቱን አስበው እርሳቸውም መራራ ይጠጡና እንክርዳድን ይመገባሉ፤ ሞቱን አስበው ደም እንባን ያነባሉ፤ ብፁዕ መልከ ጼዴቅ በቀንና በሌሊት በጾምና በጸሎት ይጋደሉ ዘንድ ጀመሩ፡፡ የዳዊትን መዝሙር በየቀኑ ሦስት ጊዜ ይጸልዩ፣ እየተጋደሉም አርባ መዓልትን ቆዩ፤ ሌሊትም ራቁታቸውን ማቅ ብቻ ለብሰው ከባህር ውስጥ ይቆማሉ፡፡ በነጋም ጊዜ ወደ በዓታቸው ይመለሳሉ፡፡ በየዓመቱም አራት ጊዜ እንዲህ ያደርጋሉ፡፡ በየዓመቱም አርባ ቀን እህል ሳይበሉ ወይን ሳይጠጡ፣ ከቅጠልና ከእንጨት ፍሬ ከሣርም ፍሬ የፅዋው ቁመት በትንሽ ጣት ልክ ከተሰፈረ ጥቂት ውኃ በስተቀር እንደዚህ እየተጋደሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በደብረ መድኃኒት ሰባት ዓመት ኖሩ፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ የክርስቶስን መከራ እያሰቡ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን ደናግል መነኰሳትን መስለው ሁሉን እያከናወኑ እያለ የወዳጆቹን መከራ የማይዘነጋ፣ የሰውን የድካሙን ዋጋ ፈጽሞ የማያስቀር አምላክ ሠራዊተ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ "መገረፍህ ስለ እኔ መገረፍ ይሁንልህ፤ የደምህ መፍሰስ ስለ እኔ ደም መፍሰስ ይሁንልህ፤ መቸንከርህም ስለ እኔ መቸንከር ይሁንልህ፤ ሞትህም ስለ እኔ ሞት ይሁንልህ" ብሎ ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡ "ከዚህ ቦታ መጥቶ የተሳለመውን እምርልሃለሁ ነፍሱ በአንተ ቃል ኪዳን የማይማር በአንተ ቦታ ለመሳለምም፣ ንሰሐ ለመግባትም ሆነ ለመቀበር አላቀርብብህም፣ መጥቶም የተቀበረውን ሥጋውን አፈር አይበላውም" የሚል እጅግ ድንቅ ቃል ኪዳን መድኃኒዓለም ሰጣቸው እስከ ዕለተ ምጽዓትም ሲታይ ይኖራል፡፡ በደጃቸው የተቀበረ ሰው አይበሰብስም፡፡
የእግዚአብሔር መልአክ አባታችን መልከ ጼጼቅን "በግራሪያ አገር ወደምትገኝ የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ደብር ወደሆነች ወደ ደብረ ሊባኖስ ሂድ" አለው፡፡ አባታችን መልከ ጼዴቅም በዚህ መልአክ ትዕዛዝ ሄዱ ደብረ ሊባኖስ ደረሱና በዚያ እያሉ ቅዱሳንን እጅ ነሷቸው ከንቡረ ዕድ እንድርያስ ጋርም ተቀመጡ፡፡ ትንሽ ዋሻ በዓትን ሰጡዋቸውና "ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ እግዚአብሔር ያጽናህ የገድልህንም ፍጻሜ ይሰጥህ" አላቸው፡፡ አባታችን እንድርያስ በእሱ ላይ በባረከ ጊዜም አባታችን መልከ ጼዴቅ ወደ በዓቱ ገብቶ ምስጋና ጸሎትና ስግደት ተግቶ ያዘ፡፡ እንደ መጀመሪያውም ታስሮ እያለ በየለቱ እስከ ሦስት ሺህ ስግደት ይሰግድ ነበር፡፡ ደሙም በምድር ላይ እስከሚፈስ ድረስ መንታ በሆነ የገመድ ጅራፍ ሰውነቱን ይገርፍ ነበር፡፡ እንባውም እንደክረምት ነጠብጣብ ይፈስ ነበር፤ የዓይኑ ብሌን እስኪገለበጥ ድረስ ያነባ ነበር፡፡ የሥጋውንም ቁስል እንደ መርፌ ሰርስሮ ወደ ውስጥ አካሉ እስኪገባ ድረስ በማቅ ፀጉር ይሰቀስቅና ይደመድም ነበር፡፡ እንዲህ ሆኖ መከራ ሲቀበልም ከእግዚአብሔር ምሥጋና ዝም አይልም ሥራውንም ፈጽሞ ያደንቅ ነበር፡፡ "ጌታ ሆይ የተኛሁትን አንቃኝ የደከምሁትን አበርታኝ የጨለምሁትን እኔን አብራልኝ" ይል ነበር፡፡ ይህንንም የሚለው ለራሱ ብቻ አይደለም ስለዓለም ሁሉ ነበር እንጅ እሱስ በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት ጋርና በዓርያም ካሉ ከሱራፌል ጋር በክህነት የሚያገለግል ፍጹም ንጹሕና ጻድቅ ሰው ነው፡፡
ከዚህ በኋላም አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሦስት የብርሃን አክሊሎችና የወርቅ ዘውድ ተቀዳጅቶ ተገለጠለት፡፡ የብርሃን ልብሶችን ለብሶ የመስቀል ምልክት ያለው በትርም ተመርኩዞ ፊቱም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ መጣና ወደ አባታችን መልከ ጼዴቅ ቀርቦም "ልጄ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን" አለው፡፡ አባታችን መልከ ጼዴቅም መልሶ "የእግዚአብሔር ሰላም ከአንተ ጋር ይሁን አንተ ማነህ አለው፡፡ "እኔ ከእናቴ ማኀፀን ጀምሮ መድኃኒዓለም የመረጠኝ ተክለ ሃይማኖት ብሎም የሰየመኝ ፍሰሐ ጽዮን ነኝ" አለው፡፡ ያንጊዜም ከእግሩ በታች ወደቅሁ ከኔ ጋር የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ አነሣኝ አቡነ ተክለ ሃይማኖት "የዳሞት ንጉሥ ሞተለሚ እንዴት እንዳደረገው የጣዖት ማምለኪያዎችን እንዴት እንዳጠፋ ብዙ ሰዎችን በክርስቶስ እንዴት እንደአሳመነ" ያን ጊዜ ነገረኝ፡፡
ስለዚህም "እግዚአብሔር አከበረኝ ከፍ ከፍ አደረገኝ፤ የብዙዎችም አባት አደረገኝ፤ ልጄ ሆይ አንተም ጸንተህ ተጋደል የብዙዎች አባት ትሆናለህ፤ እግዚአብሔር ለመጋደል ያበርታህ ሰላምንም ይስጥህ"፡፡ ይህንም ብሎ ከእርሱ ተሠወረ፡፡ ከርሱ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባታችን መልከ ጼዴቅ መጣና ወዳጄ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን" አለው፡፡ መልከ ጼዴቅም "አንተ ማነህ" አለው፡፡ "እኔ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ" አለው፡፡ ያን ጊዜም ከእግሩ በታች ወደቀ፡፡ ጌታችንም እጁን ይዞ፡፡ አነሣውና "ጽና አትፍራ" አለው፡፡ ያን ጊዜም እናቱ ድንግል ማርያም፣ ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል፣ ከሱራፌልና ከኪሩቤል ጋር ከነቢያት፣ ከሐዋርያት ጋር፣ ከጻድቃንና ከሰማዕታት ጋር መጣች መድኃኔዓለምም አባታችን መልከ ጼዴቅን "ከእናትህ ማኀፀን ጀምሮ በምስክር ሁሉ ፊት መረጥሁህ ካህንም አደረግሁህ ዛሬም የብዙዎቹ አባት አደርግሃለሁ፡፡ ኃጢአተኞችንም የምትመልስ ትሆናለህ፡፡ ያልጠቆረ ብሩህ አክሊልና በሰው እጅ ያልተሠሩ የብርሃን ልብሶችን እሰጥሃለሁ፡፡ ርስትህ ከአጥማቂዬ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ይሁን፤ ሹመትህም ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይና ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር ይሁን፣ ስምህም የኔ ምሳሌ በሆነው መልከ ጼዴቅ ይሁን" አለው፡፡
የመጀመሪያው በጥምቀት የተሰጠው ስሙ ኀሩየ ወልድ (በወልድ የተመረ) የሚል ነበርና ያን ጊዜም ቁመታቸው እስከ ሰማይ የሚደርስ ብርሃናቸው እንደ ፀሐይ የሚያበራ፤ ሦስት የወርቅ መስቀሎችን ሰጠው" በላያቸው ላይ ውጣ" አለኝ፤ እኔም በእያንዳንዳቸው ላይ ሦስት ጊዜ ወጣሁ እስከ አርያምም አገቡኝ፡፡ በዚያም የእግዚአብሔርን መንበር አየሁ፡፡ በአንድነት በሦስትነት የሚኖር የዘመናት ጌታም በላይ ተቀምጧል፡፡ ይህም ነገር እጅግ ድንቅ ነው ወልድ በምድር ላይ ከእርሱ ጋራ እየተነጋገረ ሳለ በአርያም ደግሞ በሦስትነቱ ተቀምጦ አየሁ፡፡ ጌታም ሥርዓትህ እንዲሁ እንዳየኸው ይሁን፤ እስከ ዕለት ዕረፍትህም ድረስ ስለ ገድልህ ጽናት የሚሆን ሰጥቼሃለሁ" አለው፡፡ በጸሎቱ የተማጸነውን እንደሚምርለትና ሌላም ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ "እኔም ከአንተ አልለይም፣ መላአክቶቼም ይጠብቁሃል" አለው፡፡ መልከ ጼዴቅም ይህንን በሰማ ጊዜ በፊቱ ሰገደ፡፡ "አቤቱ ለእኔ ለኃጢአተኛው አገልጋይህ ይህን ሁሉ ክብር የሰጠኸኝ ጌታ ሆይ መንግሥትህ ይባረክ" አለው፡፡ ጌታችንም ባርኮት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡
አባታች መልከ ጼዴቅ እንደዝህ በብዙ ተጋድሎ ሲኖሩ ዕረፍታቸው ሲደርስ ትንሽ በተቅማጥ በሽታ ታመሙ ያንጊዜም ጌታችን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክቶች ጋር መጣች፡፡ መላእክትንና ቀደምት አባቶችን፣ ነቢያትንና ሐዋርያትን፣ ጻደቃን ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናትን፣ ደናግልና መነኮሳትን፣ ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናትንም ምስክሮች አድርጎ አቆመ፡፡ ሄሮድስ ያስገደላቸው 144,000 ሕፃናት ከአለቃቸው ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር መጡ፡፡ "በእኔና በአንተ መካከል እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ይሁኑ፤ ስምህን የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ፣ በእጅህ የተጠመቀ፣ በቃልህ የተናዘዘና በእጅህ የተሳለመ ምሬልሃለሁ፤ የገድልህን መጽሐፍ የጻፈውና ያጻፈውን ምሬልሃለሁ ከአንተም ጋር ርስት እሰጠዋለሁ፤ የቤትህ ልጆች መንግሥተ ሰማያትን ከአንተ ጋር ይውረሱ" አለው፡፡ ዳግመኛም "ለምህረት ያልጠራኋትን ነፍስ ለመሳለምም ሆነ ለመባረክ ወይም ለመናዘዝ ወደ አንተ አላቀርብም፤ ከኃጥአንም ወገን አንተ ስለ እነርሱ ከለመንኸኝ እምርልሃለሁ" ብሎ ቃል ኪዳን ገባላቸው። አባታችንም በዚህች ቀን ነፍሳቸው ከስጋቸው ተለየች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሀያ ዘጠነኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ አረፈ። እርሱም ከእስክንድርያ አገር ነው ከታናሽነቱም በአስቄጥስ በአባ መቃርስ ገዳም መንኲሶ በተጋድሎ ኖረ።
ከእርሱ አስቀድሞ የነበረ አባ አትናቴዎስም በአረፈ ጊዜ አዋቂዎች ኤጲስቆጶሳት ሕዝቡም ሁሉ መረጡት። ወስደውም በግድ ተሾም አሉት እርሱ ግን አልፈለገም የክርስቶስን መንጋ እንዳይተው ሌላ ተሹሞ በክርስቶስ መንጋዎች ላይ ጥፋት እንዳያመጣ ብዙ ልመናዎችን ለመኑት አዋቂዎች ኤጲስቆጶሳትና መምህራን ሁሉ አጽንተው ሲለምኑት በአየ ጊዜ ፈራ ይህ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ይሆን ብሎ አሰበ።
ከዚህም በኋላ ሊቀ ጵጵስና ሾሙትና በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ ተቀመጠ። ስለ መንጋዎቹም ጥበቃ አሰበ ደግሞ ስለ ትምህርት መጻሕፍትንም ስለ ማንብበ በቀናች ሃይማኖትም የሚያጸናቸው ሆነ ምሁራን ካህናትንም ኤጲስቆጶሳትን አድርጎ ሾማቸው።
በዚያ ወራትም ስሙ ዘይኑን የሚባል እግዚአብሔርን የሚፈራ ደግ ንጉሥ ነበረ። ይህንንም ቅዱስ ስለረዳው ሥልጣኑ በሀገሮች ላይ ተዳረሰ የቀናች ሃይማኖትም በግብጽ አገሮች ሁሉ ላይ ተዘረጋች።
በዚያም ወራት ስንዴና ወይን ዘይትም የተመሉ ብዙ እንቅቦችን ለአብያተ ክርስቲያናትና ለገዳማት ለፍላጎታቸው ንጉሥ ዘይኑን ላከ። ለዚህም አባት ዘመኑ ሁሉ ጸጥታና ሰላም ሆነ። ጌታችንም በሥራው ሁሉ ተደሰተለት ከዚህም በኋላ በቸርነቱ ጐበኘውና ጥቂት ታመመ በሹመቱም ስምንት ዓመት ከኖረ በኋላ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages