አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አርስጦቡሎስ ነው እርሱም ከአምስቱ አገሮች የሆነ የእናቱም ስም ማርያም ነው እርሷም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ተጽፋለች እርሱም አስቀድሞ ስሙ ዮሐንስ ነው። በግብረ ሐዋርያት ማርቆስ በተባለ በዮሐንስ እናት ቤት ሐዋርያት ይጸልዩ ነበር ተብሎ እንደ ተጻፈ። እርሷም ባለጸጋ ነበረችና የዮናናውያንን የሮማይስጥን የዕብራይስጥን ትምህርት ለልጅዋ ለማርቆስ አስተማረችው።
በአደገም ጊዜ በርናባስ ወንጌልን ለመስበክ ከጳውሎስ ጋራ ሲሔድ ይዞት ሔደ በእነርሱም ላይ የሚደርስባቸውን መከራ አይቶ በጵንፍልያ ከተማ ሳሉ ትቷቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
ሐዋርያትም በተመለሱ ጊዜ የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን አሕዛብ እንደ ተመለሱ እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ላይ ድንቅ ተአምራትን እንዳደረገ ተናገሩ። ይህ ብላቴና ማርቆስም ከእርሳቸው ስለ መለየቱ አዘነ ተጸጸተ።
ከዚያም አብሮአቸው ሊሔድ ፈለገ አስቀድሞ ትቷቸው ስለተመለሰ ጳውሎስ ሊአስከትለው አልወደደም በርናባስ ግን ወሰደው አጎቱ ነውና። በርናባስም ከአረፈ በኋላ ወደ ሮሜ አገር ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ሒዶ ለእርሱ ደቀ መዝሙሩ ሆነ በዚያም ቅዱስ ጴጥሮስ የተረጐመለትን ወንጌልን ጻፈ በሮሜ አገርም አስተማረበት። ከዚያም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝና በሐዋርያትም ትእዛዝ ወደ እስክንድርያ አገር ሔደ። በውስጥዋም የከበረ ወንጌልን አስተማረ ደግሞም በአፍራቅያና በአምስቱ አገሮች በርቃ በሚባልም አገር ወደ እስክንድርያ ከተማ በገባ ጊዜ ጫማው ተቆረጠ።
በዚያም በከተማው መግቢያ ጫማ ሰፊ ነበረ። ቅዱስ ማርቆስም እንዲሰፋለት ለርሱ ሰጠው ሲሰፋም ጣቱን ወግቶ ሰነጠቀው ከእርሱም ደም ፈሰሰ በዮናኒም ቋንቋ ኢታስታዖስ አለ ትርጓሜውም አንድ እግዚአብሔር ማለት ነው። ቅዱስ ማርቆስም ስሙን የምትጠራው አውቀኸው ነውን አለው እንጠራዋለን እንጂ አናውቀውም አለ።
እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ አባታችን አዳም ትእዛዙን እንደተላለፈ የጥፋት ውኃም እንደ መጣ ሙሴንም እንደላከውና እስራኤልን ከግብጽ እንዳወጣቸው ሕግንም እንደ ሠራላቸው ናቡከደነጾርም ወደ ባቢሎን ማርኮ እንደወሰዳቸውና ከሰባ ዓመት በኋላ ወደ አገራቸው ኢየሩሳሌም እንደ ተመለሱ ክርስቶስ ሥጋ በመልበስ ወደ ዓለም ስለ መምጣቱ ነቢያት ትንቢት እንደ ተናገሩ ያስተምረው ዘንድ ጀመረ።
ከዚያም በኋላ ወደ ምድር ምራቁን ትፍ ብሎ ጭቃ አድርጎ ጣቱን ቀባው ወዲያው ዳነ በጌታችንም አመነ። ያም ሰፊ ስሙ አንያኖስ ነው። ቅዱስ ማርቆስንም ወደ ቤቱ ወስዶ ልጆቹን ዘመዶቹንም ወደ ርሱ አቀረበ እርሱም አስተምሮ አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው።
በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሰዎች በበዙ ጊዜ የቅዱስ ማርቆስን ዜና ሰምተው የአገር ሰዎች ሊገድሉት ተሰበሰቡ እርሱም አንያኖስን ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሹሞ ልጆቹን ቄሶችና ዲያቆኖች አድርጎ ከዚያም ወደ በርቃ ወደ አምስቱ አገሮችም ወጥቶ አስተማረ። በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው በእርሳቸውም ዘንድ ሁለት ዓመት ኖረ ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ተመለሰ ምእመናንም ተጨምረው በዝተው በታወቁ ቦታዎች ሁሉ በባሕሩም ዳር በላሞች መካበቢያ በሚባለውም አብያተ ክርስቲያን ሠርተው አገኛቸው።
ከሀድያንም የከበረ ሐዋርያን ይገድሉት ዘንድ በብዙ ድካም ፈለጉት እርሱም አምስቱን አገሮች ሲጐበኝ በሥውር ወደ እስክንድርያ ከተማ ይገባ ይወጣ ነበር። በአንዲትም ዓመትም ከአምስቱ አገሮች ተመልሶ ሚያዝያ ዐሥራ ሰባት ቀን በመድኃኒታችን የትንሣኤ በዓል ወደ ቤተክርስቲያን ገባ ሕዝቡም ሁሉ በዙሪያው አሉ። ከሀድያንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው በአንገቱ ውስጥ ገመዶችን አድርገው በከተማው ሁሉ ጎተቱት። እነርሱም ገና እንደፍየል ሙክት እንጎትተዋለን እያሉ ይጮኹ ነበር። በላሞች መካበቢያና በሀገሪቱ አደባባይ በከተማውም ዙሪያ በየቀኑ ሲጎትቱት ኖሩ።
ሌሊትም በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት ጋራ በነበረበት አርአያ ሁኖ ተገለጠለት ሰላምታም ሰጥቶ አጽናናው ቃል ኪዳንም ሰጠው። እነሆ አንተ ከወንድሞችህ ሐዋርያት ጋር ተካከልህ አለው። እርሱም በልቡናው ፈጽሞ ደስ አለው። በማግሥቱም ሁለተኛ ገመዶችን በአንገቱ አድርገው በአገሮች ሁሉ ጎተቱት በቀኑም መጨረሻ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።
ከሀዲዎችም ታላቅ እሳትን አንድደው የቅዱስ ማርቆስን ሥጋ ከውስጡ ጨመሩ። በክብር ባለቤት ጌታችን ፈቃድም ንውጽውጽታ ጨለማ ቀዝቃዛ ነፋስ መብረቅና ነጐድጓድ ሆነ። ፀሐይም ጨለመ ከሀዲዎችም ሸሹ ምእመናንም መጥተው የሐዋርያ ቅዱስ ማርቆስን ሥጋ ወሰዱ ምንም ጥፋት ሳይደርስበት ደኀና ሆኖ አገኙት በመልካም ልብስም ገንዘው በጥሩ ቦታ አኖሩት መታሰቢያውንም አደረጉ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ማርቆስ ጸሎት ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።
No comments:
Post a Comment