በጻፈው ደብዳቤም ቤተ ክርስቲያን አስቀድማ የጀመረችውን ስልታዊ እቅድ፣ የመዋቅር እና የአስተዳደራዊ ማሻሻያ ሰነዶችን ተመልክቶ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቋል።
ከማንኛውም ሹመት በፊት የእጩ ኤጲስ ቆጶሳት የምርጫና የመመዘኛ ሥርዓት ሁሉን በአሳተፈ መንገድ ለውይይት ቀርቦ እንዲጸድቅም ሃሳብ ሰጥቷል ።
1ኛ. ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ቤተ ክርስቲያን የሚያጋጥሟት ፈተናዎች ዋነኛ ምክንያት የቤተ ክህነት አስተዳደር ዘመኑን የዋጀ አለመሆን ነው፡፡ ይህንንም ብፁዓን አባቶቻችን ከፍተኛ የመንግሥት ባላሥልጣናት እና የሚመለከታቸው አካላት ባሉበት ባደረጋችሁት ስምምነት አንቀጽ 8 እና 9 ላይ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን “ለትውልድ አርአያ የሚሆን ቤተ ክህነት እንዲኖር ለማድረግ አሠራራችንን በጥናት አሻሽለን ቤተ ክርስቲያንን ለትውልድ እናሻግራለን፡፡” በማለት ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሠረት ቤተ ክርስቲያን አስቀድማ የጀመረችውን የመሪ እቅድ እና የዘላቂ አስተዳደራዊ መፍትሔ ጥናቶች ውጤት መሠረት የተዘጋጁትን ስልታዊ እቅድ፣ የመዋቅር እና የአስተዳደራዊ ማሻሻያ ሰነዶችን ተመልክቶ ውሳኔ ቢሰጥ፡፡
2ኛ. ቤተ ክርስቲያናችን በ2009 ዓ.ም ኤጲስ ቆጶሳትን ከሾመች በኋላ በልዩ ልዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ ክፍተቶች የተነሣ በብፁዓን አባቶች ተደርበው የተያዙ ሀገረ ስብከቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ባደረጋችሁት ውይይትና ሰምምነት አንቀጽ 4 ላይ #… በቀጣይ የግንቦት ርክበ ካህናት ተወስኖ እንዲሾም በማለት መስማማታችሁ ይታዋሳል፡፡ በዚሁ መሠረት ተደርበው ለተያዙ ሀገረ ስብከቶች የኤጲስ ቆጶሳትን መሾም አስፈላጊነትን በመወሰን አፈጻጸሙ በቤተ ክርሰቲያን ቀኖና መሠረት በጥንቃቄ ለማከናወን በዐቢይ ኮሚቴው ተጠንቶ የቀረበውን ወቅቱ የሚጠይቀውን የእጩ ኤጲስ ቆጶሳት የምርጫና የመመዘኛ ሥርዓት ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ እና ሁሉን አካታች የሆነ ግልጽና ተጠያቂነት ባለው አሠራር የሚመራ አስመራጭ ኮሚቴ በመሰየም፣ የሢመቱ ሂደትም ግልጽ፣ ምእመናንና ካህናት በንቃት ተሳታፊ የሚሆኑበት ለማድረግ በጥንቃቄ እንዲታይና በሚጸድቀው መሥፈርትና ስምምነት መሠረት ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በአባትነት በሙሉ ልባቸው የሚቀበሏቸው ኤጲስ ቆጶሳት ለመሾም የምርጫ ሂደቱ ቢጀምር፡፡
3ኛ. ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር ያላቸው አስተዳደራዊ ግንኙነት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሁኔታ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ቢከናወን በቀጣይ የቤተ ክርስቲያን ጎዞ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ በመሆኑም ይህ ችግር ተወግዶ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አንድነት እንዲጠናከር ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን በትኩረት ተመልክቶ አስፈላጊውን ውሳኔና አቅጣጫ ቢሰጥ፡፡
4ኛ. ቤተ ክርሰቲያን ያጋጠማትን ወቅታዊ ችግር ምክንያት በማድረግና እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም አብያተ ክርሰቲያናትን በኃይል ሰብሮ በመግባት፣ ታሪካዊ ቅርሶችን በመዝረፍና በማውደም፣ ምእመናን ላይ የአካልና የሕይወት ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኙ ሕገወጥ አካላትን መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገርና በመመካከር የቤተ ክርስቲያን መብትና ሕልውና እንደያስከብር ቢያደርግ፡፡
በመጨረሻም ወደ ፊት ቤተ ክርስቲያን ፈተና እንዳይገጥማት ማድረግ ባትችልም እንኳ ለትውልድ መሻገር የምትችለው የውስጥ አስተዳደራዊ አቅሟን ማሳደግ ስትችል ነው፡፡ ይህንን አስተዳደራዊ ጥንካሬ እና ተቋማዊ ልዕልና መፍጠር የሚቻለው ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና በየዘርፉ ባሉ ባለሙያዎች የሚቀርቡ ጥናቶችንና ምክረ ሐሳቦችን በበጎ ሕሊናና በሠለጠነ አስተሳሰብ በመቀበል ጥናቶቹ በውይይት እንዲበለጽጉ አድርጎ ለታለመው ዓላማ መጠቀም ሲቻል ነው፡፡
በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን ሊቃውንትና የየዘርፉ ባለሙያዎች የሆኑ የቤተ ክርስቲያንን ልጆች በተናጠልና በጋራ በበጎ ፈቃድ የሚያቀርቡትን አስተዳደራዊ ማሻሻያዎች ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ መሳካትና ተቋማዊ ልዕልና ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ አቅጣጫ እንዲሰጥበት እየጠየቅን ማኅበረ ቅዱሳንም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚወስነው ውሳኔ መሠረት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣትና በልጅነት ለመታዘዝ ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
Source:- Mahibere Kidusan Broadcast Service - ማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት
No comments:
Post a Comment