አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ አንድ ቀን በዚች ቀን ከእርሱ ተአምራት የተገለጡ የሶርያ ሰው የሆነ የቅዱስ ሊውንቲዎስ የቤተ ክርስቲያኑ ቅዳሴ ነው፣ እስራኤል የተባለው የያዕቆብ ልጅ የጻድቁ ዮሴፍና የሚስቱ የአሰኔት የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው፣ የመስተጋድል የሰማዕት ቢፋሞን የዕረፍቱ መታሰቢያና በስሙ ከታነፁ አብያተ ክርስቲያናት የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ነው፡፡
ቅዱስ ሊውንቲዎስ ክቡር ሰማዕት
ሰኔ አንድ ቀን በዚች ቀን ከእርሱ ተአምራት የተገለጡ የሶርያ ሰው የሆነ የቅዱስ ለውንትዮስ የቤተ ክርስቲያኑ ቅዳሴ ነው።
ይኸውም ቅዱስ ለውንትዮስ በሐምሌ ወር በሃያ ሁለተኛው ቀን በሰማዕትነት በሞተ ጊዜ ከታላላቅ መኳንንቶች የአንዱ መኰንን ሚስት መጣች ለወታደሮችም ብዙ ገንዘብ ሰጠች የቅዱሱንም ሥጋ ወሰደች በባሏም ልብስ ገነዘችው በሣጥንም አድርጋ በቤቷ ውስጥ አስቀመጠችው በቀንና በሌሊትም የሚያበራ መብራት በፊቱ አኖረች።
እነሆም ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በመኰንኑ ባሏ ላይ በሆነ የሥራ ምክንያት ተቈጣ። በአንጾኪያም ከተማ በወህኒ ቤት አሠረው። ቅዱስ ለውንትዮስም ለሥጋው መልካም ለሠራች ለመስፍኑ ሚስት መልካም ዋጋዋን ሊከፍላት ሽቶ በዚያች ሌሊት በወህኒ ቤት ለባልዋ ተገለጠለት በወህኒ ቤቱም ብርሃን ወጣ ለመኰንኑም የራሱ የሆነውን በቤቱ ያለውን የሚያውቀውን የወርቅ ልብስ ለብሶ በጐልማሳ ፈረሰኛ አምሳል ተገለጠለት።
ከዚህም በኋላ እንዲህ አለው አትዘን አታልቅስም ዛሬ ከዚህ ወጥተህ ከንጉሥ ጋር በማዕዱ ትቀመጣለህና ከዚያም ወደቤትህ በሰላም ትሔዳለህና። የታሠረው መስፍንም ይህን ጐልማሳ ፈረሰኛ ስለ አየው በላዩም ስለ ወጣው ብረሃን የወህኒ ቤቱም ደጅ እንደ ተዘጋና እንደ ተቆለፈ ወደ ርሱ ስለ መግባቱ ደግሞም የራሱ የሆነውን በቤቱ ውስጥ የተወውን የወርቅ ልብስ ለብሶ ስለ ማየቱ በዚህ ሁሉ ሥራ ያደንቅ ነበር።
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ለውንትዮስ በዚያች ሰዓት ወደ ንጉሡ ሔደ በመኝታውም ተኝቶ ሳለ ረገጠው እጅግም ደነገጠ ለንጉሡም እንዲህ አለው ንጋት በሆነ ጊዜ መስፍን ዕገሌን ከወህኒ ቤት አውጣው አክብረውም በክፉ አሟሟትም ሙተህ እንዳትጠፋ ወደ ቤቱ ይሔድ ዘንድ ተወው። ንጉሡም ከግርማው የተነሣ እየተንቀጠቀጠ እሺ ጌታዬ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ ብሎ መለሰለት። በነጋ ጊዜም ንጉሡ ወደ ወህኒ ቤት ልኮ መስፍኑን አወጣው ታላቅ ክብርንም አከበረው መልካም ልብሶችንም አልብሶ ከእርሱ ጋራ በማዕዱ አስቀመጠው። ፈረሰኛም እንደ ተገለጠለትና ይፈታው ዘንድ እንዳዘዘው ነገረው መስፍኑም አደነቀ።
ንጉሡም የሥራይ ሥራ እንደሆነ አድርጎ አሰበ መስፍኑም እኔ መጠበብንና ሥራይን አላውቅም ከእሊህ ከምትለኝም ነገሮች ማን እንደተገለጠልህ ምንም አላውቅም። ንጉሡም ከተገለጠለት ራእይ ፍርሀት የተነሣ ክፉ ነገርን ሊናገረው አልደፈረም ነገር ግን ወደ ሀገሩ በታላቅ ክብር ሰደደው።
መስፍኑም በጎዳና ሲጓዝ ሁለተኛ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት ወደ ሀገሩ ጠራብሎስም እስኪደርስ እያነጋገረው ያጽናናው ነበር ከዚህም በኋላ ተሠወረው። ወደ ቤቱም በገባ ጊዜ ቤተ ሰቦቹን ሰላም አላቸው የእርሱን የወርቅ ልብስ የሚመስል ልብስ ለብሶ ፈረሰኛ ጐልማሳ እንደ ተገለጠለትም ነገራቸው ከወህኒ ቤትም እሥራት ያድነው ዘንድ ቃል እንደገባለት ነገራቸው። ሚስቱም ያዳነው ቅዱስ ለውንትዮስ እንደሆነ አውቃ ብታየው ታውቀዋለህን አለችው። አዎን አላት ከዚያም የቅዱስ ለውንትዮስ ሥዕል ወደ አለበት ቦታ አስገባችው አይቶም የተገለጠልኝ በእውነት ይህ ነው አለ።
ሁለተኛም የቅዱስ ለውንትዮስ ሥጋ ያለበትን ሣጥን ከፈተች ያንንም የርሱን የወርቅ ልብስ እንደለበሰ አየው። የፊቱንም መሸፈኛ ገለጠ የተገለጠለትና ከእሥራት ያዳነውም እርሱ እንደ ሆነ ተረዳ።
መስፍኑም ማን እንደሆነ ስለ እርሱ ሚስቱን ጠየቃት እርሷም የቅዱስ ለውንትዮስን ገድል ነገረችው መስፍኑም ይህን መልካም ሥራ ስለ ሠራች ሚስቱን አመሰገናት መረቃትም የተመሰገነ እግዚአብሔርንም በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ድንቅ ሥራ ስለሚሠራ አመሰገነው። መብራትና ማዕጠንትም እንዳይለየው ሚስቱን አዘዛት ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስን ጌታችን እስከ አጠፋው ድረስ እንዲሁ የምትሠራ ሆነች።
ከዚህም በኋላ መልካም ቤተ ክርስቲያን አንፀው ሥጋውን በውስጧ አኖሩ በዚች ዕለትም አከበሩዋት ከሥጋውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ
በዚችም ዕለት እስራኤል የተባለው የያዕቆብ ልጅ የጻድቁ ዮሴፍና የሚስቱ የአሰኔት የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው። አባቱ ያዕቆብ እናቱ ራሄል ይባላሉ፡፡ ለአባቱ 11ኛ ልጅ ነው፡፡ አባቱ ያዕቆብ የወንድሙን የኤሳውን በረከት ከአባቱ ከወሰደ በኋላ ከኤሳው ሸሽቶ ወደ አጎቱ ላባ ዘንድ ተሰዶ 14 ዓመት ለላባ ተገዝቶ ራሄልንና ርብቃን አግብቶ ብዙ ልጆችን ወለደ፡፡ ሀብት ንብረትም ካፈራ ከ21 ዓመት በኋላ ወደ አባቱ አገር ተመልሶ ከወንድሙ ጋር ታረቀ፡፡ ያዕቆብም በምድረ በዳ አቅራቢያ ባለች አብርሃም ይቀመጥባት ከነበረ አገር ከአባቱ ከይስሐቅ ዘንድ ደረሰ፡፡ ይህችውም በከነዓን ያለችው ኬብሮን ናት፡፡ አባቱ ይስሐቅ አብርሃም ይቀመጥባት በነበረችው የወይራ ዛፍ ሥር ተቀምጦ አገኘው፡፡ ከዚህም በኋላ ይስሐቅ አርጅቶ ዘመኑን ጨርሶ ሞተ፡፡ ያዕቆብም አባቱ ይስሐቅ ይኖርባት በነበረች አገር ኖረ፡፡ ያንጊዜም ልጁ ዮሴፍ 17 ዓመት ሆኖት ነበር፡፡ እርሱም ከአባቱ ከያዕቆብ ሚስቶች ከዘለፋ ልጆችና ከባላ ልጆች ጋር የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር፡፡ ያዕቆብም በእርጅናው ዘመን ወልዶታልና አብልጦ ይወደው ነበር፡፡
ወንድሞቹም በዚህ ምክንያት ጠሉት፡፡ ዮሴፍም ሕልም አልሞ ሕልሙን ለወንድሞቹ ነገራቸው፡፡ ዮሴፍም ያየው ሕልም 11ዱ ወንድሞቹና አባቱም ጭምር ለዮሴፍ እንደሚገዙለትና እንደሚሰግዱለት የሚያሳይ ነበር፡፡ ይህንንም ሕልሙን ሲሰሙ ወንድሞቹ ይበልጥ ጠሉት፡፡
የዮሴፍም ወንድሞች የአባታቸውን በጎች ይዘው ወደ ሴኬም ጎዳና ሄዱ፡፡ አባቱም ዮሴፍን ‹‹ወንድሞችህን አይተሃቸው ና›› ብሎ ስንቃቸውን ቋጥሮ ወደ ቆላው ላከው፡፡ ሴኬምም እንደደረሰ አንድ ሰው ወንድሞቹ ያሉበትን አሳይቶት ወደ ዶታይን ወረደ፤ በዶታይንም አገኛቸው፡፡ እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩትና ወደ እነርሱ ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ፡፡ ‹‹እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው፡፡ ክፉ አውሬም በላው እንላለን›› ብለው ሲመካከሩ ከእነርሱ ውስጥ ሮቤል ይህን ሲሰማ ‹‹ሕይወቱን አናጥፋ፣ ደም አታፍስሱ፤ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፣ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት›› አላቸው፡፡ ሮቤልም እንዲህ ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው፡፡ ዮሴፍንም ቀሚሱን ገፈው ወስደው ወደ ቀበሮ ጕድጓድ ጣሉት፡፡ ጉድጓዱንም በድንጋይ ገጥመው በላይ ተቀምጠው ዮሴፍ ያመጣላቸውን እንጀራ እየተመገቡ ሳለ የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ ሲመጡ አይተው በይሁዳ ምክር ወንድማቸውን ከጕድጓድ አውጥተው ለእስማኤላውያን በሀያ ብር ሸጡት፤ እስማኤላውያንም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት፡፡ የፈርዖን ጃንደረባ የዘበኞቹም አለቃ የሚሆን የግብፅ ሰው ጲጥፋራ ዮሴፍን ወደ ግብፅ ካወረዱት ከእስማኤላውያን እጅ ገዛው፡፡ እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ፣ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ፡፡ ጌታውም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ፣ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ፡፡ ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን ስላገኘ በቤቱ ላይ ሾመው፣ ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው፡፡ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኋላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት ስለ ዮሴፍ ባረከው፤ የእግዚአብሔር በረከት በውጪም በግቢም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ፡፡ ጲጥፋራም ያለውን ሁሉ ለዮሴፍ አስረከበ። የዮሴፍም ፊቱ መልከ መልካምና ውብ ነበረ፡፡ ይኸውም ምሳሌ ነው፡፡ ዮሴፍ የጌታችን፣ ወንድሞቹ ደግሞ የአይሁድ ምሳሌ ናቸው፡፡ ዮሴፍ ምግባቸውን ይዞላቸው ቢሄድ ከበው እንደደበደቡት ሁሉ ጌታችንም ‹‹እኔ ግን እላችኋለሁ…›› እያለ የነፍሳቸውን ምግብ ቢያስተምራቸው አይሁድ ጠልተውት ገድለውታል፡፡ ዮሴፍ እንዲሸጥ ሀሳብ ያመጣው ይሁዳም ጌታችንን የሸጠው የይሁዳ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሴፍ በግብፅ ሕያው በከነዓን ግን ምውት እንደሆነ ሁሉ ጌታችንም በመለኮቱ ሕያው ሲሆን በትስብእቱ ግን ምውት ሆኗል፡፡
ወንድሞቹም የዮሴፍን ቀሚስ ወስደው የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነክረው ወደ አባታቸው ሄደው ‹‹ይህንን አገኘን፣ ይህ የልጅህ ልብስ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው›› አሉት፡፡ ያቆዕብም ‹‹ይህ የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል›› ካለ በኋላ ልብሱን ቀዶ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ጊዜ አምርሮ ስላለቀሰ ዐይኑ ጠፋ፡፡
ዮሴፍም ጌታውን በቅንነት እያገለገለ ሲኖር የጌታው ሚስት ባሏ በሌለበት ጠብቃ በዮሴፍ ላይ የዝሙት ዐይኗን ጣለችበትና ‹‹ከእኔ ጋር ተኛ›› አለችው፡፡ ዮሴፍም ‹‹እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፣ ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤ ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?›› አላት፡፡ እርሷ ግን ስለዚህ ነገር በየጊዜው ትጨቀጭቀው ነበር፡፡ አንድ ቀን ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ በቤት ውስጥ ከቤት ሰዎች ማንም ስላልነበረ ወደ እርሱ ገብታ ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች፤ እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሽቶ ወደ ውጭ ወጥቶ ሄደ፡፡ የጲጥፋራ ሚስት ግን የቤቷን ሰዎች ጠርታ ‹‹እዩ ዕብራዊው ሰው ከእኔ ጋር ሊተኛ ወደ እኔ ገባ፣ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ቢሰማ ልብሱን በእኔ ዘንድ ጥሎ ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ›› ብላ በሐሰት ከሰሰችው፡፡ ባሏም ሲመጣ እንዲሁ ብላ ነገረችው፡፡ ባሏም የእርሷን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፡፡ ዮሴፍን ይዞ እስር ቤት ጣለው፡፡ እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ፣ ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው፡፡ የሚያደርገውንም ሁሉ እግዚአብሔር ያቀናለት ነበር፡፡
የጲጥፋራ ሚስት የኃጢአት ምሳሌ ስትሆን ዮሴፍ የንጽሕና ምሳሌ ነው፡፡ ኃጢአት ደርሳ ሥሩኝ ሥሩኝ ስትላችሁ የንጽሕናን የቅድስናን ነገር አስባችሁ ፈጥናችሁ ከእርሷ ተለዩ ሲል ነው፡፡ ንጽሕናችሁን በኃጢአት አታቆሽሹ አለ፡፡ አንድም የጲጥፋራ ሚስት የዚህ ዓለም ዮሴፍ የመናንያን ምሳሌ ነው፡፡ ዮሴፍን የጲጥፋራ ሚስት ሽንገላ ሳያታልለው ጥሏት እንደሸሸ ሁሉ መናንያንም የዚህ ዓለም ሀብት፣ ንብረት፣ ቤት፣ ልጅ፣ ባል፣ ሚስት… ሳያታልላቸው የዓለምን ጣዕም ሸሽተው ገዳም ይገባሉና ነው፡፡
ዮሴፍ ከታሰረ ከሁለት ዓመት በኋላ ንጉሡ ፈርዖን ሕልም አየ፡፡ በነጋም ጊዜ ነፍሱ ታውካ የግብፅን ሕልም ተርጓሚዎችና ጠቢባንን ሁሉ ሰብስቦ እንዲተረጉሙለት ሕልሙን በዝርዝር ነገራቸው፡፡ ነገር ግን ሊተረጉሙለት አልቻሉም ነበር፡፡ የንጉሡም የጠጅ አሳላፊ አስቀድም ከዮሴፍ ጋር ታስሮ ሳለ እርሱ ያየውን ሕልም ዮሴፍ ተርጉሞለት እንደነገረው ሆኖለት ስለነበር በዚህ ጊዜ የጠጅ አሳላፈው ለንጉሡ ስለ የሴፍ ነገረው፡፡ ፈርዖንም ዮሴፍን አስመጥቶ ሕልሙን ነግሮት ተረጎመለት፡፡ በፈርዖንም ሕልም መሠረት ሰባት ዓመታት ጥጋብ እንደሚሆንና ከዚያም በኋላ ሰባት የርኃብ ዓመታት እንደሚመጡ ነገረው፡፡ ፈርዖንም ዮሴፍን ‹‹እኔ በዙፋኔ ብቻ ከአንተ እበልጣለሁ›› ብሎ በቤቱና በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው፡፡ ቀለበቱንም አውጥቶ አሰረለት፡፡ ይህም የሆነው በ30 ዘመኑ ነው፡፡ ዮሴፍ በእናት በባቱ ቤት 17 ዓመት፣ በጲጥፋራ ቤት 10 ዓመት፣ በእስር ቤት ሁለት ዓመት ተቀምጦ ባጠቃላይ ልክ 30 ዓመት ሲሆነው በፈርዖን ፊት ለሹመት ቆመ፡፡ ይኸውም ምሳሌ ነው፡፡ ዮሴፍ በ30 ዘመኑ ለሹመት በፈርዖን ፊት እንደቆመ ሁሉ ጌታችን መድኃኔዓም ክርስቶስም በጲላጦስ ፊት ለፍርድ የቆመው በ30 ዘመኑ ነው፡፡
ዮሴፍም በግብፅ ምድር ዞሮ የሰባቱን ዓመት እጅግ ብዙ እህል ሰበሰበ፡፡ ሰባቱም የጥጋብ ዘመን ሲያልፍ ሰባቱ የርኃብ ዘመን በጀመረ ጊዜ በሀገሩ ሁሉ ታላቅ ርኃብ ሆነ ነገር ግን በግብፅ ምድር ብቻ እህል ነበር፡፡ ንጉሡም ከየሀገሩ ሁሉ ወደ እርሱ የሚመጡትን ወደ ዮሴፍ እየላካቸው ዮሴፍም እህል ከጎተራ እያወጣ ይሸጥላቸው ነበር፡፡ የዮሴፍ አባት ያዕቆብ በግብፅ እህል እንዳለ በሰማ ጊዜ ልጆቹን እህል እንዲሸምቱ ወደ ግብፅ ላካቸው፡፡ ነገር ግን ክፉ እንዳያገኘው ብሎ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን ከእነርሱ ጋር አላከውም ነበር፡፡ ዮሴፍም ዐሥሩ ወንድሞቹ ከሕዝቡ ጋር ገብተው ሲሰግዱለት አይቶ ዐወቃቸው፣ እነርሱ ግን የሰገዱለት የሀገሩ ገዥ ስለነበረ ነው እንጂ ወንድማቸው እንደሆነ ዐላወቁትም ነበር፡፡ ዮሴፍም በልጅነቱ ከእነርሱ ጋር ሳለ ያየውን ሕልም አሰበ፡፡ እነርሱም ስለራሳቸው በነገሩት ጊዜ ‹‹እቤት የቀረውን ወንድማችሁን አምጡ›› ብሎ ለርኃባቸው እህሉን ሰጥቶ አንዱን (ስምዖንን) ለይቶ አስቀርቶ ዘጠኙን ስንቃቸውን ጭኑ ወደ አባታቸው ቤት ወደ ከነዓን ላካቸው፡፡ ሄደውም የሆነውን ለያዕቆብ ነገሩት፡፡
እርሱም ከወንድማቸው ጋር ድጋሚ ወደ ግብፅ ላካቸውና ድጋሚ በዮሴፍ ፊት ሰግደው ሰላምታ አቅርበው እጅ መንሻን አመጡለት፡፡ ዮሴፍም የእናቱን ልጅ ብንያምን ባየው ጊዜ ወደ ውስጥ ገብቶ አለቀሰ፡፡ ዮሴፍ ቆይቶ ራሱን ገለጠላቸው፡፡ ያደረጉበትንም ነገራቸው፡፡ የርኃቡም ዘመን ገና 5 ዓመት ይቀረው ነበርና ዮሴፍ ወንድሞቹን ‹‹ስለሸጣችሁኝ አትዘኑ እነሆ ሕይወታችሁን ለማዳን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከእናንተ በፊት ወደ ግብፅ ልኮኛል›› አላቸው፡፡ አባቱንም ወደ እርሱ እንዲያመጡት ላካቸው፡፡ ያዕቆብም ከነቤተሰቡ ንብረቱንም ሁሉ ሰብስቦ ወደ ግብፅ ወረደ፡፡ ልጁን ዮሴፍንም ባየው ጊዜ እያለቀሰ አቅፎ ከሳመው በኋላ ሞቱን ተመኘ፡፡
በግብፅ የያዕቆብ የልጅ ልጆቹ ቁጥር 66 ሆነ፡፡ ከዮሴፍም ልጆች ጋር አንድ ላይ 70 ሆኑ፡፡ ያዕቆብም ፈርዖንን ገብቶ ከባረከው በኋላ በግብፅ ጌሤም ምድር 17 ዓመት ተቀመጠ፡፡ ዘመኑም 140 በሆነ ጊዜ በሞት ማረፉን ዐውቆ ልጁን ዮሴፍን ጠርቶ በአባቶቹ መቃብር ቤት ውስዶ እንዲቀብረው ነገረው፡፡ የዮሴፍንም ሁለቱን ልጆች ምናሴንና ኤፍሬምን ባረካቸው፡፡ ‹‹አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፣ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፣ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅ ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድርም መካከል ይብዙ›› ብሎ ባረካቸው፡፡ ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ ይልቁንም የጌታችንን የመወለዱን ነገር በምሳሌ እያደረገ ነገራቸው፡፡ እያንዳንዳቸውንም እንደ በረከታቸው ባረካቸውና በአብርሃምና በይስሐቅ ሣራም በተቀበረችበት መቃብር ወስደው እንዲቀብሩት ከነገራቸው በኋላ በ137 ዕድሜው እግሮቹን በአልጋው ላይ ሰብስቦ በሰላም ዐረፈ፡፡ የግብፅ ሰዎችም 70 ቀን አለቀሱለት፡፡ ዮሴፍም አባቱን ባዘዘው ቦታ በእነ አብርሃም መቃብር ከቀበረው በኋላ ወደ ግብፅ ተመለሰ፡፡
የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ‹‹ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፣ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል›› ብለው ፈርተው ወደ ዮሴፍ መልዕክት ልከው ‹‹አባትህ ገና ሳይሞት ‹ዮሴፍን እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፣ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፤ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል› ብሎሃል›› ብለው ላኩለት፡፡ ወንድሞቹም መጥው በፊቱም ሰግደው ‹‹እነሆ እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን፣ በአባቶችህ አምላክ ባሮችህን ኃጢአታችንን ይቅር በለን›› አሉት፡፡ ዮሴፍም እንዲህ ሲሉት አለቀሰ፡፡ እርሱም ‹‹ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ ስለሆነ አይዟችሁ አትፍሩ›› እያለ እንዳይፈሩ አጽናናቸው፤ደስም አሰኛቸው፡፡ ዮሴፍም በግብፅ ተቀምጦ 110 ዓመት ኖረ፡፡
የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ ካየ በኋላ ወንድሞቹን ጠርቶ ‹‹እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፣ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል፡፡ እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ እንጂ ከዚህ አትተውት›› ብሎ አማላቸው፡፡ ዮሴፍም በ110 ዕድሜው በሰላም ዐረፈ፡፡ በሽቱ አሽተው በግብፅ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት፡፡ ዮሴፍም ‹‹እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ እንጂ ከዚህ አትተውት›› ማለቱ አንድም ከግብፅ ምድር እንደሚወጡና የአባቶቻቸውን ርስት ከነዓንን እንደሚወርሱ ሲነግራቸው ነው፡፡ ፍጻሜው ግን ግብፅ የመቃብር ከነዓን የትንሣኤ ምሳሌ ናቸው፡፡ አንድም ግብፅ የገሃነም ከነዓን የመንግሥተ ሰማይ ምሳሌ ናቸው፡፡ ያዕቆብም እንዲሁ ብሏልና ዮሴፍም እንዲህ ያለ ስለምን ነው ቢሉ አባቶቻችን እንዲህ ማለታቸው መውጣታችንን ቢያውቁ ነው ብለው እንዲነቁ፣ እንዲተጉ፣ አንድም ለማጸየፍ ነው፣ ‹‹አባቶቻችን አጥንታችን እንኳን ከዚህ አይቅር›› ብለዋል ብለው እንውጣ እንዲሉ ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አባ ቢፋሞን ሰማዕት
በዚህችም ቀን የመስተጋድል የሰማዕት ቢፋሞን የዕረፍቱ መታሰቢያና በስሙ ከታነፁ አብያተ ክርስቲያናት የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ነው፡፡ ይህም ከታናሽነቱ ድንግል የሆነ እግዚአብሔርን የሚወድ ለድኆችና ለችግረኞች የሚመጸውት ይህንንም ዓለም ንቆ የተወ ነው። አባቱም ከከበሩ ወገኖች የሆነ ስሙ አንስጣስዮስ የእናቱም ስም ሶስና ነው። እነርሱም መመጽወትን የሚወዱ ክርስቲያኖች ናቸው የጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን የከበሩ ሰማዕታትንም ሁሉ በዓላት ለድኆችና ለምስኪኖች ምጽዋትን በመስጠት ያከብራሉ የሚኖሩትም በምስር አውራጃ አውሲም በሚባል አገር ውስጥ ነው።
እግዚአብሔርም መልኩ እጅግ ያማረ ይህን የተባረከ ልጅ ቢፋሞንን ሰጣቸው በእርሱም ደስ ብሏቸው በጎ መሥራትንና ትሩፋትን አበዙ አድጎ ወደ ዘጠኝ ዓመትም ሲደርስ ያሰተምረው ዘንድ እግዚአብሔርን ለሚፈራ አንድ ቄስ ሰጡት እርሱም ተቀብሎ ወስዶ ጥበብን ጽሕፈትን ተግሣጽን አስተማረው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም መጻሕፍት አጠና በቤተ ክርስቲያንም ሁል ጊዜ ያገለግላል እጅግ በመትጋትም በጾም በጸሎት በመስገድ ይጋደል ነበር።
እግዚአብሔርም በእጆቹ ብዙዎች የሆኑ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ ከእሊህ በቊስል ደዌ እጆቹንና እግሮቹን የታመመ አንድ ድኃ ነበረ የከበረ ቢፋሞንን ምጽዋትን ለመነው ሊሰጠውም እጁን ሲዘረጋ በዚያን ጊዜ ከደዌው ድኖ ጤነኛ ሆነ ሕዋሳቱም ሁሉ ጠነከሩ።
ሁለተኛም በሌላ ጊዜ በዳዊት መዝሙር ሲያመሰግን ከዚያ አንድ ጋኔን የሚጥለው ሰው ነበረ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ ተወኝ ከዚህ ቦታ ልጥፋ በሎ ጮኸ የከበረ ቢፋሞንም ወደ ጌታችን ጸልዮ ያንን ጋኔን ያደረበትን ሰው አዳነው መምህሩም አይቶ አክብሮትን ለቢፋሞን ጨመረ። እርሱ ያለ ማቋረጥ በመንፈሳዊ ትሩፋት ሥራ የሚያድግ ሁኗልና የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማደሪያው ውስጥ የሚገለጥለት ሆነ ቅዱሳን መላእክቶቹም ከርሱ ጋር አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያምም በአንድነት ያጽናኑት ነበር በመምህሩም ዘንድ ስምንት ዓመት ኖረ።
ከዚህም በኋላ እየተጋደለ ኖረ በየሰባት ቀንም በመጾም ከሰንበት ቀን በቀር አይበላም ወላጆቹ ሚስት እንዲአገባ ጠየቁት እርሱም በዚህ በሚአልፍ ዓለም ከሴት ጋር መኖር ለእኔ ምኔ ነው ፍላጎቱ ሁሉ ያልፋልና አላቸው። ወላጆቹም በርሱ ደስ አላቸው በጎ መሥራትንም ጨመሩ። ከዚህም ነገር በኋላ በሰባተኛው ወር አባቱ አረፈ የከበረ ቢፋሞንም ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ምጻዋትን አብዝቶ ሰጠ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም የተጠመደ ሆኖ የከበረ የወንጌልን ትእዛዞች ለመፈጸም ይጋደል ነበር።
በዚያንም ወራት የፋርስ ሰዎች በሮም ሰዎች ላይ ጦርነት አስነሥተው ነበር የሮም ንጉሥም በጦርነት ሙቶ መንግሥት ያለ ንጉሥ ተቀመጠች መኳንንቱ እና የመንግሥት ታላላቆች ተሰብስበው ተማከሩ ከሁሉ አገሮችም ተዋጊዎች የሆኑ አርበኞችን ይሰበስቧቸው ዘንድ አዘዙ። ከላይኛውም ግብጽ ልበ ደንዳና የሆነ አንድ ሰው ተገኘ እርሱም ስሙ አግሪጳዳ የሚባል የሰይጣን ማደሪያ የሆነ ፍየሎችን የሚያረባ ነው ወደ አንጾኪያ ከተማም ወስደው ለመንግሥት ፈረሶች ባልደራስ አድርገው ሾሙት።
በአንዲትም ዕለት ሁለት ሸምበቆ አንሥቶ በአንድነት አሥሮ ዋሽንት ነፋባቸው በፈረሶች ሰይጣን አደረባቸውና ፈረሶችም እየጨፈሩ ያሽካኩ ጀመር የሞተውም ንጉሥ ሴት ልጅ በቤተ መንግሥት አዳራሽ ሁና በመስኮት ሲዘፍንና ዋሽንት ሲነፋ አግሪጳዳን አይታው እጅግ አማራት ሰይጣንም በልቧ የዝሙትን ፍላጎት ጨመረ ወደርሷም አስጠራችውና አገባችው ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ አሰኝታ አነገሠችው። ታናሽ እኅቷም ታላቂቱ እኅቷ ያደረገችውን በአየች ጊዜ ቀናች እርሷም መክስምያኖስ የሚባል አንድ መኰንን መልምላ አገባች ልብሰ መንግሥትም አልብሳ ንጉሥ አደረገችው መክስምያኖስና ዲዮቅልጥያኖስም በአንጾኪያና በሮም ተስተካክለው ነገሡ።
ከዚህም በኋላ ሰይጣን ተገለጠላቸውና እንዲህ አላቸው ነገሥታት እስከአደረግኋችሁ ድረስ በንጉሡ ሴቶች ልጆች የዝሙትን ፍቅር በልባቸው የጨመርኩ እኔ ነኝ። አሁንም ትእዛዜን ከሰማችሁ በምድር የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉንም በእጆቻችሁ ውስጥ አደርጋቸዋለሁ እናንተም ስገዱልኝ የወርቅና የብር ምስሎችንም ሠርታችሁ አማልክት በሏቸው ስማቸውንም አጵሎን፡ አርዳሚስ ብላችሁ ጥሩአቸው ሰዎችንም ሁሉ ዕጣን እንዲአሳርጉላቸው እንዲሰግዱላቸውም እዘዟቸው አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ ዝጉ የአማልክትንም ቤቶች ክፈቱ ትእዛዛችሁን ሰምተው ለአማልክት የማይሰግዱትን ግን በየአይነቱ በሆነ በጽኑዕ ሥቃይ አሠቃዩአቸው ራሶቻቸውንም በሰይፍ ቊረጡ።
እሊህም ሰነፎች ዲዮቅልጥያኖስና መክስምያኖስ በሰሙ ጊዜ ሰገዱለትና እኛ የአዘዝከንን ሁሉ እናደርጋለን አሉት። በዚያንም ጊዜ በግብጽ አገር ሄሬኔዎስንና አርያኖስን ሁለቱን መኳንንቶች ሾሙ ለጣዖት የማይሰግዱትን ሁሉ እንዲአሠቃዩ አዘዙአቸው። የከበረ አባ ቢፋሞንም ይህን ዜና በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ የሆነውንም እስቲረዳ ድረስ ተሠወረ ወዳጁን ቴዎድሮስንም ጠራውና በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ደማቸውን ያፈሱ ዘንድ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ ከክፉ ነገርም ሁሉ ያድናቸው ዘንድ በአንድነት ጸለዩ።
የከበረ ቢፋሞንም በጎ ሥራን አብዝቶ ይሠራ ነበር ወሬውም በንጉሥ መክስሚያኖስ ዘንድ ተሰማ እንዲህ ብለው ከሀዲዎች ነግረውታልና በምስር አውራጃ በአውሲም ከተማ ስሙ ቢፋሞን የሚባል አንድ ሰው አለ እርሱም የነገሥታትን ትእዛዝ የሚተላለፍ አማላክትን የሚረግምና የሚያቃልል ነው።
በዚያንም ጊዜ የከበረ ቢፋሞንን ለአማልክት እስከሚዐጥን ድረስ እንዲአሠቃየው ያለዚያም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጥ ንጉሥ ወደ አርያኖስ ደብዳቤ ጽፎ ላከ የእግዚአብሔርም መልአክ የሆነውን ይነግረው ዘንድ ለአባ ቢፋሞን ተገለጠለት በሰማዕትነትም እንደሚሞት እናቱም እንደምትሞት አስረዳው እግዚአብሔርም ያዘጋጀላቸውን አክሊላት አሳየው አገልጋዩን ዲዮጋኖስን ከእርሱ ጋር እንዲወስደው አዘዘው።
ያን ጊዜ ተነሣ ወደ እናቱም ገብቶ ያየውን ሁሉ ነገራት እርሷም ይህንኑ ራእይ እንዳየች ነገረችው በአንድነትም ደስ አላቸው ወደ ማደሪያውም ሒዶ እስቲነጋ ድረስ ሊጸልይ ቆመ በነጋ ጊዜ ወደ ወዳጁ ቲዎድሮስ ልኮ አስመጣው ራእይንም እንዳየ ነገረው ከዚህም በኋላ እንዲህ ብሎ አዘዘው የመከራው ወራት ካለፈ በኋላ በዚች አገር አንተ ኤጲስቆጶስነት ትሾማለህና ቤተ ክርስቲያን ሥራልኝ ይህንንም ነግሮት ሰላምታ ተለዋውጠው ተሳስመው ተለያዩ።
ከጥቂት ቀኖች በኋላ ወደ አውሲም ከተማ መኰንኑ አርያኖስ ደረሰ የሀገር ታላላቆችንም አቅርቦ ስለ ከበረ ቢፋሞን ጠየቃቸው እርሱ አማልክትን እንደሚረግም ሰምቷልና የሀገር ሽማግሌዎችም ስለ ቅዱስ ቢፋሞን አዘኑ እርሱ በእነርሱ ዘንድ ተወዳጅ ነውና። በዚያንም ጊዜ አባ ቢፋሞን ተነሥቶ ረጂም ጸሎትን ጸለየ ቤተ ሰቦቹንም ሁሉ ተሰናበታቸው ያማሩ ልብሶችንም ለብሶ በነጭ ፈረስ ተቀምጦ የአገር ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወዳሉበትም ሔደ እነርሱም በአዩት ጊዜ አክብረው ሰላምታ ሰጡት ተከትለውትም ወደ መኰንኑ ወደ አርያኖስ ሔደ አርያኖስም አባ ቢፋሞንን በአየው ጊዜ ደስ አለው ከወንበሩም ተነሥቶ ሰላም ላንተ ይሁን ብሎ ሰላምታ ሰጠው።
አባ ቢፋሞንም እንዲህ ብሎ መለሰለት ለምን ሰላም ትለኛለህ የሰላም ትርጓሜው ደስታ ነውና ለእኔ ግን በጌታዬ በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ አለኝ ለአንተና ለባልንጀሮችህ በሰማያት ደስታ የላችሁም ብሏል መጽሐፍ። አርያኖስም እኔ ክፉ ነገርን እንድትነግረኝ አልመጣሁም ለአማልክት እንድትሠዋ በንጉሡ ደብዳቤ ታዝዤ መጣሁ እንጂ አለው::
ቅዱሱም መልሶ ይህ አይገባም ትክክለኛውስ ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ ለእርሱም እንድንሰግድ ይገባል እሊህ አማልክቶቻችሁ አፍ አላቸው አይናገሩም ዓይን አላቸው አያዩም ጆሮ አላቸው አይሰሙም አፍንጫ አላቸው አያሸቱም እጅ አላቸው አይዳስሱም እግር አላቸው አይሔዱም በአንደበታቸውም አይናገሩም በአፋቸው ውስጥ ትንፋሽ የለምና የሠሩአቸውም እንደነርሱ ይሁኑ እኔ ግን ሰማይና ምድርን በውስጣቸው ያለውን ሁሉ ከፈጠረ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለሌላ አልሰግድም አለው።
አርያኖስም ከቅዱስ ቢፋሞን አፍ ይህን ነገር ሰምቶ እጅግ ተቆጣ በየዓይነቱም ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ዳግመኛም በፈረስ ጅራት አሥሮ መላ ከተማውን አስጎተተው እናቱና አገልጋዮቹም ሁሉ ወደርሱ መጡ እነርሱንም ከከበረ የወንጌል ቃል አስተማራቸው ገሠጻቸውም በዚያንም ጊዜ በግልጽ እኛ ክርስቲያን ነን ብለው ጮኹ የመኰንኑን ወንበር ገለበጡ መኰንኑም ጒድጓድ እንዲቆፍሩላቸውና እሳትንም አንድደው በውስጡ በሕይወት ሳሉ እንዲወረውሩአቸው አዘዘ እንዳዘዘውም አደረጉባቸው ቊጥራቸውም አምስት መቶ ነው።
ምስክርነታቸውንም እስኪፈጽሙ የከበረ ቢፋሞን ያጽናናቸውና ያስታግሣቸው ነበር እናቱም ልጅዋ ቢፋሞንን በላይዋ እንዲጸልይ ለመነችው እርሱም በመስቀል ምልክት በላይዋ አማተበና በሰላም ሒጂ አላት በዚያንም ጊዜ ሰውነቷን በእሳት ውስጥ ጣለች። ከእነሱ ጋርም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች።
የከበረ ቢፋሞንን ግን አርያኖስ ወደ ንጉሥ መክስምያኖስ ሰደደው ንጉሡም የነገሥታትን ትእዛዝ የምትተላለፍ ለአማልክት የማትሰግድ ሥራየኛው ቢፋሞን አንተ ነህን አለው። ቅዱሱም ሥራይን ግን አላውቅም ለረከሱ አማልክትም አልሰግድም አንተና አማልክቶችህ በአንድነት ወደ ገሀነም እሳት ትወርዳላችሁና አለው ንጉሡም ተቆጥቶ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ከማሠቃየትም በሰለቸ ጊዜ ወደ ኄሬኔዎስ ሰደደው እርሱም ወደ አርያኖስ ሰደደው በእነዚያ ቀኖችም ምንም አልበላም።
አርያኖስም ወስዶ በብረት ችንካሮች ቸነከረውና ለአማልክት ካልሰገድክ አጠፋሃለሁ አለው ቅዱሱም እርሱንና አማልክቶቹን ዘለፈ ረገማቸውም ከዚህም በኋላ በከተማዪቱ ሁሉ መንገድ እንዲጎትቱትና ከእንዴናው ከተማ ውጭ በእሳት እንዲአቃጥሉት መኰንኑ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት ጌታችንም ያለ ጥፋት በጤና ከእሳት ውስጥ አወጣው የከበረ ቢፋሞንም ከእሳት ውስጥ ቁሞ በነበረ ጊዜ ከእግሮቹ ብዙ ደም ፈሰሰ ከሕዝብ ጋር የቆመ አንድ ሰው ነበረ እርሱም ለምጻምና ዕውር ነበር ከደሙም ወስዶ ዓይኖቹን ቀባ ያን ጊዜ አየ ከለምጹም ነጻ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታመን ክርስቲያን ነኝ ብሎ ጮኸ ራሱንም እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘና ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
የከበረ አባ ቢፋሞንንም ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አርያኖስ አዘዘ ቢፋሞንም አገልጋዩን ዲዮጋኖስን እንዲህ ሲል ሥጋውን በሥውር እንዲጠብቅ ደሙንም በበፍታ ልብስ እንዲቀበል ገድሉንም በአውሲም አገር ላሉ ምእመናን እንዲነግር አዘዘው የመከራው ወራት ያልፍ ዘንድ አለውና ከዚህም በኋላ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ብሎ በመስቀል ምልክት አማተበ ወደ ጭፍሮችም ቀርቦ የታዘዛችሁትን ፈጽሙ አላቸው እነርሱም ወደ ሌላ ቦታ ብቻውን ወስደው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት ።
ከአንገቱም ብዙ ደም ፈሰሰ አገልጋዩ ዲዮጋኖስም ከእርሱ ዘንድ ያለውን በፍታ ዘርግቶ የቅዱስ ቢፋሞንን ደም ተቀበለበት። በዚያም ቦታ እጅግ ጣፋጭ የሆነ መዓዛ መላ ጭፍሮች እስኪያደንቁና እስኪደነግጡ ድረስ ታላቅ ፍርሀት ወረደባቸው ከዚያም ቦታ ሸሹ።
ከዚህም በኋላ ምእመናን መጥተው ሥጋውን ወሰዱ ብዙ ሽቱ አምጥተውም በመዘመር በክብር ገነዙት ከከተማም ውጭ ተሸክመው ወስደው ቀበሩት ከመቃብሩም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ አገልጋዩም ያቺን በፍታ ወስዶ ጠበቃት ወደ ሀገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የሚፈራ ሆነ ምን እንደሚያደርግም አሰበ የከበረ ቢፋሞንም ተገለጠለትና ለወዳጁ ለቴዎድሮስና ለሀገሩ ሰዎች ዜናውን እንዲነግር አዘዘው እግዚአብሔርም ምእመናን ሰዎችን ላከለት እነርሱም ከእርሳቸው ጋር በመርከብ አሳፍረው ወሰዱት በመርከብም ውስጥ ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን ከዚያች በፍታ በከበረ ቢፋሞን ደም ከታለለችው ተአምራትን ገለጠ አገልጋዩ ዲዮጋኖስም ገድሉን ነገራቸው አደነቁ ጌታችንንም አመሰገኑት እርሱንም ወደ አገሩ ወደ አውሲም አደረሱት ዲዮጋኖስም ለወዳጁ ለቴዎድሮስና ለሀገሩ ሰዎች ሁሉ የገድሉን ዜና ነገራቸው ያቺንም በደም የታለለች በፍታ ሰጣቸው ይህችም የመከራው ወራት አልፎ ደጉ ቈስጠንጢኖስ ነግሦ በሀገሮች ሁሉ በክርስቲያን ወገኖችም ላይ ሰላምና ጸጥታ እስከሆኑ ድረስ በእነርሱ ዘንድ ተጠብቃ ኖረች።
እግዚአብሔርም የከበረ የቢፋሞንን ሥጋ ለምእመናን አለኝታና መጽናኛ ለበሽተኞችም የሚፈውስ ኃይል እንዲሆን ሊገልጠው ወደደና በእርሱም በላይኛው ግብጽ በጥማ አውራጃ በቃው ከተማ በጥር ሃያ ሰባት በሰማዕትነት የሞተ ነው። በዚህችም ዕለት የዕረፍቱ መታሰቢያና በስሙ ከታነፁ አብያተ ክርስቲያናት የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ይከበራል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ
No comments:
Post a Comment