አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ ሁለት በዚች ቀን የመጥምቁ የቅዱስ ዮሐንስ ሥጋ የቀናተኛው ኤልያስ ደቀ መዝሙር ከሆነው ከነቢዩ ኤልሳዕ ሥጋ ጋር በአንድነት ተገኘ፣ የኢትዮጵያ መነኰስ የቅዱስ ቀዎስጦ ዘመሀግሉ መታሰቢያቸው ነው።
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት (ፍልሠቱ)
ሰኔ ሁለት በዚች ቀን የመጥምቁ የቅዱስ ዮሐንስ ሥጋ የቀናተኛው ኤልያስ ደቀ መዝሙር ከሆነው ከነቢዩ ኤልሳዕ ሥጋ ጋር በአንድነት ተገኘ።
ከሀዲው ንጉሥ ዑልያኖስ የጥጦስ ልጅ አስባስያኖስ ከአፈረሰው በኋላ በዘመኑ በኢየሩሳሌም የአይሁድ ምኵራባቸውን ሊሠራ በወደደ ጊዜ እርሱ በቅዱስ ወንጌል ደንጊያ በደንጊያ ላይ ተቀምጦ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም የተባለውን የእግዚአብሔርን ቃል ሊሽር ፈልጎ መሥራት በጀመረ ጊዜ ሦስት ጊዜ ፈረሰበት።
አይሁድም እንዲህ አሉት የደጋግ ክርስቲያኖች ዐፅሞቻቸው በዚህ ቦታ ስለሚኖሩ ከዚህ ካላወጣሃቸውና ካላቃጠልኻቸው በዚህ ቦታ ምኵራብ አይሠራም። በዚያንም ጊዜ የቅዱሳንን ዐፅሞቻቸውን አውጥተው በእሳት እንዲአቃጥሉት አዘዘ በአፈለሱም ጊዜ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስንና የነቢዩ ኤልሳዕን ሥጋቸውን አግኝተው በእሳት ሊአቃጥሉ ፈለጉ ምእመናንም መጥተው ለወታደሮች ብዙ ገንዘብ ሰጡ ንጉሡም ሰምቶ እንዳያጠፋቸው በዚያች አገር እንዳያስቀሩ ከአማሏቸው በኋላ የቅዱሳንን ሥጋ ወሰዱ።
የዑልያኖስም ዜናው እንዲህ ሆነ የጳጳሳት አለቆች ባስልዮስንና ጎርጎርዮስን በአሠራቸው ጊዜ እነርሱ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ዘንድ እያለቀሱ ጸለዩ። የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችንን የከበረ ስሙን ሰድቧልና ያን ጊዜ እግዚአብሔር ቅዱስ መርቆሬዎስን በአካለ ነፍስ ላከው ዑልያኖስንም በጦር ወጋው ከደሙም ዘግኖ ኢየሱስ የሰጠኸኝን ነፍስ ተቀበል እያለ ወደ አየር ረጨ ወዲያውኑም በክፉ አሟሟት ሞተ።
የከበሩ የዮሐንስንና የኤልሳዕን ሥጋ ግን እሊያ ሰዎች በእስክንድርያ ከተማ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ አባ አትናቴዎስ አደረሱ። እርሱም በእርሳቸው ታላቅ ደስታ ደስ አለው ቤተ ክርስቲያንም እስኪሠራላቸው ድረስ በርሱ ዘንድ አኖራቸው።
በአንዲት ዕለትም አባ አትናቴዎስ በአባቶቹ ቦታዎች ላይ ስለ ጸሐፊው ቴዎፍሎስም አብሮት ሳለ እግዚአብሔር መልካም ዘመን ቢሰጠኝ ሥጋቸውን በውስጧ አኖር ዘንድ ለቅዱሳን መጥምቁ ዮሐንስና ለነቢዩ ኤልሳዕ በስማቸው በዚህ ቦታ ቤተ ክርስቲያን እሠራለሁ አለ ቴዎፍሎስም ሰማው።
አባ ቴዎፍሎስም በተሾመ ጊዜ አባ አትናቴዎስ የተናገረውን ያንን ቃል አስቦ ቤተ ክርስቲያን ሠራ። ከርሱ ጋራም ብዙዎች ካህናትንና የክርስቲያን ወገኖችን ይዞ የቅዱሳን የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልሳዕ ሥጋቸው ወዳለበት ሔደ በታላቅ ክብርም ተሸክመው አምጥተው ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገቡ።
ሥጋቸውንም ይዘው በሚጓዙበት ጊዜ በጐዳናቸው አቅራቢያ ቤት ካለበት ቦታ ደረሱ በውስጡም በምጥ ተይዛ አራት ቀናት እየጮኸች ለሞት የተቃረበች ሴት ነበረች። እርሷም አረማዊት ነበረች በቅዱሳኑም ሥጋ ዘንድ ካህናቱ የሚያመሰግኑትን ሰምታ በቤቷ መስኮት ተመለከተች ይህ ምንድን ነው ብላ ጠየቀች። የቅዱሳን የመጥምቁ ዮሐንስና የነቢዩ ኤልሳዕ ሥጋቸው ነው አሏት እርሷም ከዚህ ሥቃይ ከዳንኩ ክርስቲያን እሆናለሁ አለች ገና ቃሏ ከአፉዋ ሳይፈጸም ያን ጊዜ መልካም ሕፃን ወለደች ስሙንም ዮሐንስ ብላ ጠራችው። ከዚህም በኋላ ከቤተሰቦቿ ሁሉ ጋራ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀች።
የቅዱሳኑንም ሥጋቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከእርሳቸውም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ። በቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑም ጊዜ ከሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ ጋራ ብዙዎች ሰዎች ቅዱሳን መጥምቁ ዮሐንስንና ነቢዩ ኤልሳዕን ሲዞሩ አዩአቸው በቀድሞ መልካቸው ያውቋቸዋልና የመጥምቁ ዮሐንስ መልክ ሁለመናው ጸጉር ሲሆን ኤልሳዕም ቁመቱ ረጅም ራሱ በራ ነበር።
ከዚህም በኋላ ኤጲስቆጶሱ አባ መቃርስ በሰማዕትነት በሞተ ጊዜ ሥጋውን ከቅዱሳን ዮሐንስና ኤልሳዕ ሥጋ ጋራ አደረጉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ቀውስጦስ ኢትዮጵያዊ
በዚችም ዕለት የኢትዮጵያ መነኰስ የቀውስጦስ ዘመሐግሉ መታሰቢያቸው ነው። ይኸውም ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሾሙአቸው ከ12ቱ ንብረ ዕድ ወስጥ አንዱ ሲሆኑ ደብረ ሊባኖስንም የሚያጥኑበትም ወር በመጋቢት ወር ነበር። ሕዝቡ አጥብቆ የሚወዳቸውና የሚያከበራቸው አባት ናቸው፡፡ ግብፃዊው አቡነ ያዕቆብ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የደብረ ሊባኖሱን እጨጌ አቡነ ፊልጶስን አስጠርተው፤ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት “ኢትዮጵያ በአንድ ጳጳስ መወሰን የለባትም፡፡ ስለዚህ ዐሥራ ሁለት አበው መርጠን ክርስትና ይስፋፋ” ብለው ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት፤ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ /ኤጲስ ቆጶስ/፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፣ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያን መርጠው ሀገረ ስብከት ተሰጥቷቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮ ተሠማሩ፡፡ ዐሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ለስብከተ ወንጌል በመላዋ አገሪቱ ሲሠማሩ፡፡
ጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ አርሲ ፈንታሌ ተራራ ላይ ሠሪቲ ለምትባል ጠንቋይ እየተላላኩ ሕዝቡን የሚያስቱና የሚያሰቃዩ 470300 (አራት መቶ ሰባ ሺህ ሦስት መቶ) አጋንንትን በጸሎታቸው እሳት ከሰማይ አውርደው ተራውንን ደምስሰው አጋንንቱን ያቃጠሉ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ የታናሽ ወንድማቸው የዐፄ ይኩኖ አምላክ ልጅ ዐፄ አምደ ጽዮን በክፉዎች ምክር የአባቱን እቁባት በማግባቱ አቡነ ቀውስጦስ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ሄደው ንጉሡን ስለገሠፁት በግዞት ወስዶ ጎናቸው በጦር ወግቶ ገድሏቸዋል፡፡ ጻድቁ ልደታቸውም ሆነ ዕረፍታቸው ከእመቤታችን ልደትና ዕረፍት ጋር የተባበረላቸው
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ
No comments:
Post a Comment