ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 10 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, July 25, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 10

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሐምሌ ዐሥር በዚህች ቀን አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ልደታቸው ነው፣ ናትናኤል የተባለው ቅዱስ ስምዖን ቀለዮጳ በሰማዕትነት አረፈ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ከላድያኖስ አረፈ፣ ቅዱስ አባት ብስንዳ አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ
ሐምሌ ዐሥር በዚህች ቀን አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ልደታቸው ነው። ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል እንድርያስና አርሶንያ ከሚባሉ የበቁ ደጋግ አባትና እናታቸው የተወለዱት በሸዋ ሀገረ ስብከት ቀድሞ ጽላልሽ ዛሬ ቡልጋ በሚባለው አውራጃ ነው፡፡ የወላጆቻቸው በጎ ምግባርና ሃይማኖት ቅዱስ ተክለሃይማኖትን ከደብረ ሊባኖስ አነሣስቶ በቤታቸው ሄደው እንዲስተናገዱ አድርጓል፡፡ ልጅ ስላልነበራቸው ያዝኑ ነበርና አቡነ ተክለሃይማኖትም በጸጋ እግዚአብሔር ተገልጾላቸው ‹‹እግዚአብሔር ጣዖታትን የሚሰብር፣ አጋንንትን በጸሎቱ የሚያርቅ፣ ሕዝብን ከኃጢአት በሽታ የሚያድን፣ ፈጣሪውን የሚያስደስት ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ብለው ትንቢት ነግረዋቸዋል፡፡ በትንቢቱም መሠረት አቡነ ሳሙኤል ሐምሌ 10 ቀን 1248 ዓ.ም ሲወለዱ መልካቸው በአራት ልዩ ልዩ ሕብረ መልክ እየተለዋወጠ አንድ ጊዜ እንደ በረዶ፣ አንድ ጊዜ እንደ እሳት፣ አንድ ጊዜ እንደ ልምላሜና ቢጫ ሆነው ታይተዋል፡፡
አቡነ ተክለሃይማኖትም በአባቱ እንድሪያስ በኩል የሥጋ ዘመዱ ሲሆኑ የመንፈስ ቅዱስም አባት ሆኑትና በ40 ቀን ክርስትና አንስተው ስመ ክርስትናውን ‹‹ሳሙኤል›› አሉት፡፡ ትርጓሜውም ‹‹እግዚአብሔር ጸለቴን ሰማኝ›› ማለት ነው፡፡ ከሕፃንነትም ጀምረው በምግባር በሃይማኖት ኮትኩተው አሳድገው ለዲቁና አብቅተው በኋላም አመንኩሰውታል፡፡ ‹‹ደብረ ወገግ›› የሚለው ስያሜ የተገኘው ከመላእክት ነው፡፡ ድርሳነ ዑራኤል በሰፊው እንደሚያትተው ቅዱስ ዑራኤል የጌታችንን ደም በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ ዓለምን እየረጨ ሲቀድሳት የያዘውን ጽዋ በደብረ አስቦ ቆሞ ሳለ ነው ጨልጦ ያንጠፈጠፈው፡፡ ያንጊዜም ደብረ አስቦን የብርሃን ውጋጋን ሲያጥለቀልቀው መላእክትም ‹‹ቦታውን ደብረ ወገግ›› (የብርሃን ተራራ) ብለው ሰይመውታል፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ‹‹ወደፊት ፈጣሪውን የሚያገለግል ታላቅ ጻድቅ ይወጣባታልና ይህችን ቦታ ባርካት›› ብሎ ቅዱስ ዑራኤልን በነገረው መሠረት ባርኳት እንዳረገ ድርሳነ ዑራኤል ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡
በቦታው ላይ ብዙ ጊዜ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ መታየቱን የበቁ ገዳማውያን ብቻ ሳይሆኑ በከተማ ያሉና ለመሳለም ወደ ቦታው የሄዱ ደገኛ ሰዎችም በዐይናቸው ያዩትን ይናገራሉ፡፡ በገዳሙ ዙሪያ እጅግ በጣም ብዙ ስውራን ቅዱሳን እንዳሉ በግልጽ ይታወቃል፡፡
ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በክፉዎች ምክር የአባቱን ሚስት እንጀራ እናቱን በማግባቱ ምክንያት አቡነ ፊሊጶስ ጋር ሆነው ያወገዙትን የቅዱስ ተክለሃይማኖትን ወገኖች በየአውራጃው በተናቸው፡፡ አቡነ ፊሊጶስንም ደሙ በምድር ላይ እስከሚንጣለል ድረስ ገርፈው ወደነበረበት ቤቱ ወሰዱት፤ ፊሊጶስም በሚሄድበት ቦታ ላይ ሳይደርስ በመንገድ ሞተ፡፡
እንድርያስ፣ አኖሬዎስና ተክለ ጽዮን ሁላቸው ከተከታዮቻቸው ጋር በሰማዕትነት አርፈው እነስድስተይ በምትባል ምድር ተቀበሩ፡፡ ጳጳሱን አቡነ ያዕቆብንም ደሙ በምድር ላይ እንደውኃ እስኪወርድ ድረስ ገርፈው ወደ ሀገሩ እንዲሰደደ አደረጉት፡፡ ከዚያም በኋላ ሃይማኖቱ የቀና ደግ ጻድቅ ንጉሥ ዳዊት በነገሠ ጊዜ አባታችን ሳሙኤል ዘወገግን አገኘውና ‹‹መማጸኛ እንዲሆነኝ በእንድርያስ መቃብር ላይ ቤተክርስቲያን ሥራልኝ›› ብሎ ለመነውና የሩፋኤልን ቤተ ክርስቲያን ሠራለት፡፡ የእንድርያስንም አጽም ከመቅደሱ ስር አኖረው፡፡ ንጉሡም በዚያ በእንደግብጦን አውራጃ ሁሉ ላይ ፓትርያርክ አድርጎ ሾመው፡፡ በእነስድስታይ አገር ላሉ ሰዎችም ሁሉ አባት ሆናቸውና የመንፈስ ቅዱስ ልጁንም ታዲዮስን መምህርና አባት አድርጎ ሾመላቸውና ጽላልሽ ሄዶ እናቱን ይዞ ጽጋጋ ምድረ ወገግ ወስዶ አመነኮሳት፡፡
አቡነ ሳሙኤል ወደ ምድረ ርስቱ ደብረ ወገግ እየሄደ በዚያ ያሉ ልጆቹን እያጽናና ወደ እንደግብጦን አውራጃም እየተመለሰ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ፣ ወንጌልን እያስተማረ፣ ጣዖት አምላኪዎችን ወደ ክርስትና እየቀየረ፣ አጋንንትንና መመለኪያ ቦታዎቻቸውን እያጠፋ፣ አብያተ ክርስቲያናትን እያነጸ በብዙ ተጋድሎ ኖረ፡፡ በቅዱስ ገድሉ ውስጥ በጣም አስገራሚ በሆነ መልኩ እጅግ ብዙ ታሪኮች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም ታሪኮች ውስጥ አቡነ ሳሙኤል በሀገራችን በጣም ብዙ ጣዖታትንና መመለኪያ ቤቶቻቸውን እያጠፉ፣ በሰዎች (በጠንቋዮች) ላይ፣ በዛፍና በባሕር ውስጥ አድሮ ይመለኩ የነበሩ ሰይጣናት አጋንንትን በሚያመልኳቸው ሰዎች ፊት እያጋለጡና እያዋረዱ ሰዎቹን አስተምረው አጥምቀው ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እየመለሷቸው ቤተክርስቲያንም በመሥራት ሐዋርያትን መሰሉ፡፡
ሰይጣን አድሮባቸው የነበሩ ጠንቋዮች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ዕቃዎችን ጻድቁ እየባረኩና እየቀደሱ ለቤተክርስቲያን መሥሪያና መጠቀሚያነት ያውሉት ነበር፡፡ ይህም ገና ሳይወለዱ በአቡነ ተክለሃይማኖት ትንቢት ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖት ‹‹ጣዖታትን የሚሰብር፣ አጋንንትን በጸሎቱ የሚያርቅ፣ ሕዝብን ከኃጢአት በሽታ የሚያድን፣ ፈጣሪውን የሚያስደስት ደግ ልጅ ይሆናል›› ብሎው ትንቢት እንደተናገሩላቸው አቡነ ሳሙኤል በሰዎች፣ በባሕርና በዛፍ ላይ እያደሩ ይመለኩ የነበሩ በጣም ብዙ አጋንንትን አጠፏቸው፡፡ ጠንቋዮችንም በውስጣቸው ካደረባቸው ሰይጣን እያላቀቁ የእግዚአብሔር አገልጋይ ያደርጓቸውና ያመነኩሷቸው ነበር፡፡
ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል ወንጌልን ዞረው በማስተማር ሐዋርያትን መሰሉ፣ ከዓላውያን ጋር ለመዋጋት ሰውነታቸውን ለሞት በመስጠት ሰማዕታትን መሰሉ፣ በጾም በጸሎት በስግደት በተጋድሎ ቅዱሳን ጻድቃንን መሰሉ፣ ይህን ኃላፊና ጠፊ ዓለም ንቀው በመተው ባሕታውያንን መሰሉ፣ በደልንና ኃጢአትን በማስተሠረይ ካህናትን መሰሉ፣ በጽሕናና በቅድስና መላእክትን መሰሉ እንደዚሁም ሌሎች ብዙ አስደናቂ ተአምራትንም በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ በትእምርተ መስቀል አድርገው እንደሙሴ ባሕርን ለሁለት ከፍለዋል፣ እንደ ኢያሱ በጸሎታቸው ፀሐይን አቁመዋል፡፡ አቡነ ሳሙኤል ተጋድሎአቸውን ፈጽመው ከጌታችን ታላቅ ቃኪዳን ተቀብለው ጥቅምት ሃያ ዘጠኝ በሰላም ዐርፈዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ስምዖን ቀለዮጳ (ቀናተኛው ስምዖን)
በዚህች ቀን ናትናኤል የተባለው ቅዱስ ሐዋርያ ስምዖን ቀለዮጳ በሰማዕትነት አረፈ፡፡
ይህንንም ሐዋርያ አይሁድ የጌታችንን ወንድም ያዕቆብን ከገደሉት በኋላ ለኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አድርገው ሐዋርያት ሾሙት። እርሱም ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮ ከአይሁድ ብዙዎችን ጌታችንን ወደማመን መለሳቸው ተአምራትንም አድርጎአልና በሽተኞችንም አድኗልና።
ንጉሡ እንድርያስም ሴቶችን ከባሎቻቸው እንደሚለይ ንጽሕናቸውንም እንዲጠብቁ እንደሚአዝዛቸው ስለ እርሱ ሰማ ወደርሱም አስቀርቦ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ከእርሱም ጋር ቴዎና የምትባል አንዲት ድንግል ተገደለች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ከላድያኖስ
በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዘጠነኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ከላድያኖስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ በወንጌላዊው በማርቆስ መንበር ዐሥራ አራት ዓመት መንጋውን እየጠበቀ ከኖረ በኋላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አባት ብስንዳ
ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባት ብስንዳ አረፈ። ይህም ቅዱስ ጥልቅ በሆነ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ቆሞ ሲጋደል ኖረ መላእክትም ይጐበኙትና ዘጠኝ ክንድ ያህል በሠረገላ ከፍ ከፍ ያደርጉት ነበር። ከዚህም በኃላ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages