ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 9 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, July 25, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 9

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ ዘጠኝ በዚህች እለት ለአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ጌታችን ቃልኪዳኑን የሰጠበት ዕለት ነው፣ የአምስቱ አህጉር ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ቴዎድሮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ ቅዱስ ታውድሮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ መስተጋድል አባ ኅልያን አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ለአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
ሐምሌ ዘጠኝ በዚህች እለት ለአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ጌታችን ቃልኪዳኑን የሰጠበት ዕለት ነው፡፡ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ አባታቸው መልአከ ምክሩ እናቱ ወለተ ማርያም ይባላሉ፡፡ የተወለዱበት ልዩ ቦታው ወሎ ክፍለ ሀገር ዳውንት ነው፡፡ በተወለዱ ዕለት ተነሥተው በእግራቸው ቆመው ሦስት ጊዜ ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ብለው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል፡፡ የስማቸው ትርጓሜ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ አንድም የክርስቶስ እስትንፋስ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃቸውና በመንገዳቸው ሁሉ እየመራቸው ነው ያደጉት፡፡
መንፈስ ቅዱስ ልቡናቸውን ብሩህ አድርጎላቸው በ5 ዓመታቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃላትን፣ ብሉያትንና ሐዲሳትን፣ድርሳናትንም ጠንቅቀው ዐውቀዋል፡፡ በተወለዱ በ14 ዓመታቸው ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ደብረ ሐይቅ ገዳም ሄደው ከባሕር ዳር ቆመው የሙሴን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ባሕሩን አሻግሯቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተዋል፡፡
ለ3 ዓመታት ያህል በኃይቅ ገዳም ለመነኮሳት እንጨት በመልቀምና ውሃን በመቅዳት ለአባቶች መነኮሳት ምግብ የሚሆናቸው ዓሣ ከባህር ውስጥ በማውጣት አገልግለዋል፡፡
አባታችን እስትንፋሰ ክርስቶስ 40 መዓልትና 40 ሌሊት ከጾሙ በኋላ ምንም እህል ሳይቀምሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ለሙሴ በደብረ ሲና እንደሰጠው ለአባታችንም ወደ እርሳቸው መጥቶ ዓሥሩን ቃላተ ኦሪትና ስድስቱን ቃላተ ወንጌል በውስጣቸው የተጻፈባቸው ሁለት ጽላቶችን ሰጥቷቸዋል፡፡
አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከሠሩ በኋላ ዕለቱን ስንዴ ዘርተው፣ ወይን ተክለው፣ ጽድን ወይራንና ግራርን ተክለው በአንዲት ቀን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ዕለቱን አድርሰዋል፡፡ ስንዴውን ለመሥዋዕት ወይኑን ለቍርባን በተአምራት አድርሰዋል፡፡
አባታችን በጸሎት ላይ እንዳሉ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተልኮ መጥቶ አባታችንን በደመና ጭኖ ወስዶ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ፊት አቆማቸው፡፡ ጌታንም በቅዱሳኑ ሁሉ እንዲባረኩ ካደረጋቸው በኋላ መልአኩን "ወደ ተወለድኩባትና ወደ ኖርኩባት ቦታ ወደ ኢየሩሳሌም አድርሰው" ብሎት ኢየሩሳሌምን አሳልሞ ሀገራችን መልሶ አምጥቷቸዋል።
አባታችን ሁሉንም የኢትዮጵያን ቅዱሳት ገዳማትን ተዘዋውሮ ሲጎበኙ በሕይወተ ሥጋ የሌሉት የየገዳማቱ ቅዱሳን ሁሉ በአካል ይገለጡላቸው ነበር፡፡ ጎጃም ውስጥ እያስተማሩ፣ እያጠመቁ፣ የታመሙትን እየፈወሱ፣ የዕውራንን ዐይን እያበሩና ሙታንን እያሥነሱ ብዙ ካገለገሉ በኋላ ለዘጠኝ ዓመታት በባሕር ውስጥ ገብተው ቁልቁል ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ጸልየው የምሕረት ቃልኪዳን በዚህች ዕለት ተቀብለዋል፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ጌታችን መጥቶ "ከመነኮሳት ሁሉ ብልጫ ያለህ ወዳጄ ሆይ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ምሬልሃለሁ ከዚህች ባሕር ውጣ" በማለት በሞት የሚያርፉበትን ቦታ ነግሯቸዋል፡፡
ጻድቁ ወደ ደብረ አሰጋጅ በሚሄዱበት ጊዜ ጸሐይ ልትገባ ስትል "በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አውግዤሻለሁ ለመስፍን ኢያሱ በገባኦን እንደቆምሽ አሁንም ቀጥ ብለሽ ቁሚ" ብለው ገዝተው ፀሐይን አቁመዋል፡፡ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስም ደብረ አሰጋጅ ሲደርሱ ፀሐይ አፍ አውጥታ "አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ እገባ ዘንድ ፍታኝ" ስትላቸው "እግዚአብሔር ይፍታሽ" ባሏት ጊዜ ጠልቃለች፡፡
ጻድቁ ሌላው በእጅጉ የሚታወቁበት አንድ ትልቅ ቃል ኪዳን አላቸው፡፡ በአምላክ ልቡና የሚገኝ፣ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ልቡና የሚገኝ፣ በቅዱስ ሚካኤልና በቅዱስ ገብርኤል ልቡና የሚገኝ እንደ መልክአ መድኃኔዓለም ያለች እጅግ አስገራሚ ጸሎት አለቻቸው፤ እርሷን ጸሎት በጸለዩ ጊዜ እልፍ ነፍሳትን ከሲኦል ያወጣሉ፡፡ ጸሎቷም የመድኃኔዓለምን የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እየጠቀሰች እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሎቹ የተቀበሉትን ጸዋትዎ መከራዎች ሁሉ ታዘክራለች፡፡ በእያንዳንዱ ክፍልም የጸሎት ማሳረጊያ አቡነ ዘበሰማያት ይደግማሉ፡፡ ንስሓ የገባ ኃጢአተኛ ሰው እንኳን ቢሆን ይህችን የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስን ጸሎት በጸለየ ጊዜ ሺህ ነፍሳትን ከሲኦል እንደሚያወጣ ጌታችን በማይታበል ቃሉ ለአባታችን ነግሯቸዋል፡፡ እያንዳንዱን የመድኃኔዓለምን የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እየጠቀሰች መከራዎቹን የምታዘክረውን ይህቺን በአምላክ ልቡና ያለች ግሩም የሆነች ጸሎት ነፍሳትን ከሲኦል አታወጣም ብሎ የሚጠራጠር ቢኖር መንግስተ ሰማያትን አያያትም፡፡ (ይህንን የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስን ጸሎት የምናገኘው ከገድላቸው ላይ ነው፡፡) ጻድቁ ታኅሣሥ 8 ቀን ተወልው ሚያዝያ 9 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ቴዎድሮስ (ዘሐምስቱ አሕጉር)
ሐምሌ ዘጠኝ በዚህች ቀን የአምስቱ አህጉር ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ቴዎድሮስ በሰማዕትነት አረፈ። ዲዮቅልጥያኖስም በካደና ጣዖትን በአመለከ ጊዜ ምእመናንን ያሠቃዩአቸው ዘንድ መኳንንቱን ወደ ሀገሮች ሁሉ ላከ። ለጣዖትም እንዲሰግዱ ያስገድዷቸው ነበር።
ስሙ ፍላጦስ የሚባል አንድ መኰንንም ወደ አፍራቅያ አገር መጣ። በዚህም ቅዱስ ለክርስቲያን ወገን መምህር እንደ ሆነ ነገር ሠሩበት መኰንኑም ወደርሱ አስቀርቦ ለአማልክት እንዲሠዋ አዘዘው።
ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት ሰማይና ምድርን የፈጠረ አምላክን ትተን ጣዖት ማምለክ አይግባንም። መኰንኑም በውኑ አርጤምስንና አጵሎንን አርዳሚስንም ሌሎች አማልክትንም ያይላቸዋልን ሌላ ነውን አንተ ይምትናገርለት አምላክ ካለ እነዚህስ አማልክት አይደሉምን አለው። ቅዱስ ቴዎድሮስም መልሶ አዎን አማልክት አይደሉም ክብር ይግባውና ከአንድ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አምላክ የለም እርሱም ለፍጥረቶች ሁሉ ፈጣሪያቸው ነው አለው።
መኰንኑም ኃይለ ቃል ስለመመለሱ ተቆጥቶ አርባ ቀን በግርፋትና በስቅላት በእሥራትና በመንኰራኲራት እንዲአሠቃዩት አዘዘ። እርሱ ግን ትእዛዙን አልሰማም ከሥቃዩም የተነሣ አልፈራም። ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጀ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ታውድሮስ
በዚህችም ቀን ከቆጵሮስ አገር ቅዱስ ታኦድሮስ በሰማዕትነት አረፈ፡፡ ከእርሱም ጋራ ሦስት ሴቶችና ያሠቃዩት የነበሩ ሁለቱ መኳንንት ሉክያኖስና ድግናንዮስ አረፉ።
ይህም እንዲህ ነው ይህን ቅዱስ ወደእነዚህ መኰንኖች በከሰሱት ጊዜ እርሱ ክርስቲያንና የቆጵሮስ ኤጲስቆጶስ እንደሆነ ሰምተው ወደ እነርሱ አቀረቡት ስለሃይማኖቱም ጠየቁት። እርሱም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ታመነ በበትሮችም እየደበደቡና እየገረፉ ቀጡት እርሱም እየዳኸ ሒዶ ጣዖቱን ረገጠው ከመንበሩም ላይ ገልብጦ ጣለው። እሊህ ሁለቱ መኳንንትም ተቆጥተው ጽኑ ሥቃይን አሠቃዩት ሥጋውንም በማቅ ጨርቅ ጨውና ኮምጣጣ ነክረው ፋቁት እርሱም ጣዖታቱን ይረግም ነበረ። ሁለተኛም ምላሱን ቆረጡት። ያን ጊዜም በዚያ ከነበሩ ሴቶች አንዲቱ ምላሱን አንሥታ ወሰደች።
ከዚህም በኋላ ቅዱሱን በአሠሩት ጊዜ ከሴትዮዋ እጅ ምላሱን ተቀብሎ በሆዱ ላይ አኖራት ወዲያውኑም ምላሱ ተዘርግታ ወደ አፉ ገባች አንዲት ነጭ ርግብም መጥታ በቅዱሱ ላይ ዞረች ሁለተኛም ሶሪት ዎፍ መጥታ በላዩ ተቀመጠች እሊህ ሁለቱ መኳንንትም አይተው አደነቁ። ሉክዮስም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ያን ጊዜም መኰንኑ ድግናንዮስ ተቆጥቶ ከቅዱስ ታኦድሮስ ኋላ ይከተሉ የነበሩ ሦስት ሴቶችን ገደላቸው።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ታኦድሮስ ነፍሱን በሰጠ ጊዜ ርግቧና ሶሪት ዎፍ በርረው ሔዱ ድግናንዮስም አደነቀ ሉክዮስም የክርስቲያን ሃይማኖት የቀናች እንደሆነች አስረዳው ክብር ይግባውና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አመነ።
ከዚህም በኋላ ሁለቱ መኰንኖች ከቆሮንቶስ አገር በመርከብ እስከ ቆጵሮስ ሔዱ በዚያም ክርስቲያኖችን ሲአሠቃያቸው ሌላውን መኰንን አገኙ ሉክዮስም ከድግናንዮስ ተሠውሮ በመኰንኑ ፊት ቆመ የጣዖታቱንም መንበር ገለበጠ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ። ድግናንዮስም ሥጋውን ወስዶ ገንዞ ቀበረው።
ከዚህም በኋላ ድግናንዮስ በመኰንኑ ፊት ቁሞ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ይህንንም በሰይፍ ራሱን ቆርጠው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ኅልያን
በዚህችም ቀን መስተጋድል አባ ኅልያን አረፈ። የዚህ ቅዱስ የአባቱ ስም ዲስጣ የእናቱ ስም ካልሞና ነው የአገሩም ስም ዐይነ ፀሐይ ይባላል። እርሱም ቀድሞ በወጣትነቱ ጊዜ የወርቅና የብር አንጥረኛ ነበር በሥራውም የተመሰገነ ነው።
በአንዲት ቀንም ከዐረብ አገልጋዮች አንዲት ሴት መጥታ ለጆሮዎቿ ጉትቻ እንዲሠራላት ለመነችው ከሠራላትም በኋላ የሠራበትን ዋጋ ከእርሷ ፈለገ። በፊቱም ራሷን ዘንበል አድርጋ ወንዶች ከሴቶች የሚሹትን ብትሻ እነሆኝ አለሁ ሌላ ገንዘብ ግን የለኝም አለችው። ይህንም በሰማ ጊዜም አንቺ የጨለማው አበጋዝ ልጅ ከእኔ ራቂ ፊትሽንም አታሳይኝ አላት።
ከዚህም በኋላ ሞትና ፍርድ መኖሩን ለነፍሱ እያሳሰባት በማደሪያው ውስጥ ጥቂት ቆየ። ተነሥቶም ለድኆችና ለችግረኞች ገንዘቡን መጸወተ ከገንዘቡም ከፍሎ ለእናቱ ሰጥቷት ተሰናበታት። ለሦስት ቀን የሚበቃውንም ስንቅ ይዞ ወደ ገዳም ሔደ እግዚአብሔርም የልቡናውን ንጽሕና ስለ አየ መራው የራቀውን ቦታ ወደ እርሱ አቀረበለት ወደ ኤርትራ ባሕር ዳርቻም በአንዲት ቀን ደረሰ።
ቆሞ ሳለም ነጭ ልብስ የለበሱና እንደ ፀሐይ የሚያበራ መስቀልን የተመረኰዙ ሦስት ሰዎች ተገለጡለት አነቁትና ከእሳቸው ጋራ ወሰዱት ወደ አትክልት ቦታም በደረሱ ጊዜ በትርና የዕንቁ መስቀል ሰጡት። በዚያም በአንድነት ጸለዩና ሰገዱ ከሰገደበትም ራሱን ቀና ባደረገ ጊዜ ከእርሳቸው ያገኘው አልነበረም በመለየቱም አዘነ አለቀሰም።
ከዚህም በኋላ ከአትክልቱ ቦታ ቅጠል እየበላ ውኃም ከርሷ እየጠጣ ኑሮውን በብሕትውና አደረገ። ወደ ቦታዎችና ወደ ዋሻዎች ለመሔድ የፈለገ እንደሆነም በትረ መስቀሉ ታበራለት ነበር። የረዘመውንም መንገድ ትጠቀልልለት ነበር ልብሱም ከእነዚያ ዛፎች ቅጠል ነበር።
የተረገመ ሰይጣንም ተጋድሎውን በአየ ጊዜ ሰው ተመስሎ ወደ ክፉዎች ሰዎች ሔደ እንዲህም ብሎ ነገራቸው በእገሌ በረሀ የተሠወረ ገንዘብ አለ የሚጠብቀውን ከያዛችሁት ታገኛላችሁ ወደዚያ ወንዝ ማዶም መርቶ አደረሳቸው በደረሱም ጊዜ መሻገሪያ መንገድ አጡ። እጅግም ተጠምተው ነበርና ውኃውን እያዩ ወደ ውኃው መድረስ ተሳናቸው።
ሁለተኛም በሚያስፈራ ዘንዶ ተመስሎ ቅዱስ ኅልያንን ውኃ ሲጠማቸው አንተ ለባልንጀሮችህ እንዴት አትራራም እንዴትስ ውኃ አታጠጣቸውም አለው በዚህ የሚይዙት መስሎት ነበርና። ለቅዱስ ኅልያንም በአውሬ አንደበት እግዚአብሔር የዘለፈው መስሎት ውኃ ቀዳላቸው ያጠጣቸውም ዘንድ ተሻገረ። እነርሱም ድኃነቱን አይተው ራሩለት ልብስ ሊሰጡትም ወደዱ እርሱ ግን አልተቀበላቸውም ወደ በዓቱም ተመለሰ።
ሰይጣንም ተንኰሉ በከሸፈበት ጊዜ በደጋጎች መነኰሳት ተመሰለ ሊአስቱትም ወደርሱ ሔዱ በመስቀል ምልክትም በማተበ ጊዜ አፍረው ተበተኑ ። የዕረፍቱም ሰዓት በቀረበ ጊዜ ቀድሞ ተገልጸውለት የነበሩ እነዚያ ሦስት ሰዎች መጥተው ገድሉን ጻፉ ባረፈ ጊዜም ቀበሩት።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages