ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 17 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, October 27, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 17

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አስራ ሰባት በዚችም ዕለት የዲያቆናት አለቃ #ቅዱስ_እስጢፋኖስ ለተሾመባት ቀን መታሰቢያ ነው፣ የታላቁ ነቢይና ካህን ሳሙኤል እናት #ቅድስት_ነቢይት_ሐና የተወለደችበት ነው፣ ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_ፊልያስ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው፣ የከበረ #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ_ካልዕ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።


ጥቅምት አስራ ሰባት በዚችም ዕለት የዲያቆናት አለቃ የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነ የከበረ እስጢፋኖስ ለተሾመባት ቀን መታሰቢያ ናት።
ለዚህም ለከበረ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ኃይልና ጸጋ የተመላ ሰው እንደነበረና በሕዝቡም መካከል ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራ እንደነበረ የሐዋርያት ሥራ የተባለ መጽሐፍ ስለርሱ ምስክር ሆነ።
ከዚህም በኋላ አይሁድ ቀኑበት የሐሰት ምስክሮች የሚሆኑ ሰዎችንም አስነሡበት ይህን ሰው በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃልን ሲናገር ሰምተነዋል እንዲሉ ሐሰትን አስተማሩአቸው። ሕዝቡንና ሽማግሌዎችን ጸሐፊዎችንም አነሣሡአቸው አዳርሱን ብለው ከበው እየጐተቱ ወደ ሸንጎ ወሰዱት።
የሐሰት ምስክሮችንም አቆሙበት እነርሱም ይህ ሰው በቤተ መቅደስ ላይ በኦሪትም ላይ ስድብን ሲናገር ተው ብንለው እምቢ አለ። የናዝሬቱ ኢየሱስ ቤተ መቅደሳችሁን ያፈርሰዋል ሙሴ የሰጣችሁን ኦሪታችሁንም ይሽራል ሲል ሰምተነዋል አሉ።
በአደባባይ ተቀምጠው የነበሩት ሁሉ ተመለከቱት ፊቱንም የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ሁኖ አዩት። ሊቀ ካህናቱም እውነት ነውን እንዲህ አልክ አለው። እርሱም እንዲህ አለ ወንድሞቻችንና አባቶቻችን ስሙ ወደ ካራን ከመምጣቱ አስቀድሞ በሶርያ ወንዞች መካከል ሳለ ለአባታችን ለአብርሃም የክብር ባለቤት እግዚአብሔር ተገለጠለት። ካገርህ ውጣ ከዘመዶችህም ተለይ እኔ ወደማሳይህ ሀገርም ና አለው።
ከዚህም በኋላ ከከላውዴዎን ወጥቶ በካራን ተቀመጠ አባቱም ከሞተ በኋላ ዛሬ እናንተ ወደ አላችሁባት ወደዚች አገር አመጣው። ከዚህም በኋላ የግዝረትን ሥርዓት ሰጠው ይስሐቅንም በወለደው ጊዜ በስምንተኛው ቀን ገዘረው እንዲሁ ይስሐቅም ያዕቆብን ገዘረው ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን ነገድ አባቶችን ገዘረ።
የቀደሙ አባቶቻችንም በዮሴፍ ላይ ቀንተው ወደ ግብጽ አገር ሸጡት እግዚአብሔር ግን አብሮት ነበር። ከመከራው ሁሉ አዳነው በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ዕውቀትን መወደድን ሰጠው በግብጽ አገር ሁሉና በቤቱ ሁሉ ላይ ሾመው። ነገርም በማስረዘም በሰሎሞን እጅ እስከተሠራችው ቤተ መቅደስ ያለውን ተረከላቸው።
ከዚህም በኋላ ድምፁን ከፍ ከፍ አድርጎ እናንተም እንደ አባቶቻችሁ ዘወትር መንፈስ ቅዱስን የምታሳዝኑት ዐይነ ልቡናችሁ የታወረ ዕዝነ ልቡናችሁ የደነቈረ አንገተ ደንዳኖች አላቸው። አባቶቻችሁ ከነቢያት ያላሳደዱት ያልገደሉት ማን አለ እናንተ ክዳችሁ የገደላችሁትን የአምላክን መምጣት አስቀድመው የነገሩዋችሁን ገደላችኋቸው።
በመላእክት ሥርዓት ኦሪትን ተቀብላችሁ አልጠበቃችሁም። ይህንንም ሰምተው ተበሳጩ ልባቸውም ተናደደ ተነሣሣ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። በእስጢፋኖስም መንፈስ ቅዱስ አደረበት ሰማይም ተከፍቶ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ የእግዚአብሔርን ክብር አየ። እነሆ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ አያለሁ አለ።
ጆሮአቸውን ይዘው በታላቅ ድምፅ ጮኹ በአንድነትም ከበው ጐተቱት። እየጐተቱም ከከተማ ወደ ውጭ አውጥተው በደንጊያ ወግረው ገደሉት የገደሉትም ሰዎች ልብሳቸውን ሳውል ለሚባል ጐልማሳ ልጅ ያስጠብቁ ነበር። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል እያለ ሲጸልይ እስጢፋኖስን በደንጊያ ወገሩት።
ዘለፍለፍ ባለ ጊዜም ድምፁን ከፍ አድርጎ አቤቱ ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው በደልም አታድርግባቸው ይህንንም ብሎ አረፈ። ደጋግ ሰዎችም መጥተው የእስጢፋኖስን ሥጋ ወስደው ቀበሩት ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት።

ዳግመኛም በዚህች ቀን የታላቁ ነቢይና ካህን ሳሙኤል እናት ቅድስት ነቢይት ሐና ተወለጀች።
ይችም ቅድስት ከሌዊ ነገድ ናት የታኅርም ልጅ ሕልቃና አገባት ፍናና የምትባልም ሌላ ሚስት አለችው እርሷም ወላድ በመሆኗ ሐና ልጅ ስለሌላት መካንም ስለሆነች ሁልጊዜ ትገዳደራት ነበር።
ሐና ግን ፈጽማ በማዘን አትበላም አትጠጣም ባሏ ሕልቃናም ያረጋጋታል ማረጋጋቱንም አልተቀበለችውም በሊቀ ካህናቱ በኤሊ ዘመንም ወደቤተ እግዚአብሔር ወጣች እያለቀሰችና እያዘነች በእግዚአብሔር ፊት ጸለየች እንዲህም ብላ ስለትን ተሳለች አቤቱ ልጅ የሰጠኸኝ እንደሆነ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለአንተ የሚያገለግል አደርገዋለሁ።
ካህኑ ኤሊም አያትና እርሷ የወይን ጠጅ ጠጥታ እንደ ሰከረች አሰበ እርሷ በዝምታ በልቧ ትጸልይ ነበርና በቊጣና በግሣጼ የወይን ጠጅ ጠጥተሽ ወደዚህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለምን መጣሽ አሁን ሒጂ ስካርሺን በእንቅልፍ አስወግጂ አላት።
እርሷም እንዲህ አለችው የወይን ጠጅ ከቶ አልጠጣሁም ልጅ ያጣሁ በመሆኔ በልቤ አዝናለሁ እንጂ ካህን ኤሊም አጽናናት እንዲሁም ብሎ ባረካት የእስራኤል ፈጣሪ የለመንሽውን ይስጥሽ በሰላም ሒጂ በቃሉም አምና ወደ ቤቷ ገባች።
ከዚህም በኋላ ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ስሙንም ሳሙኤል ብላ ጠራችው። ጡትንም በአስጣለችው ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዛው ወጣች ወደ ካህን ኤሊም አቀረበችውና እንዲህ ብላ አስረዳችው ከአሁን በፊት ልጅን ይሰጠኝ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ስጸልይና ስለምን ያየኸኝ ሴት ነኝ ልመናዬንም ሰምቶ ይህን ልጅ ሰጠኝ አሁንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልጋይ ይሆን ዘንድ አመጣሁት።
ከዚህም በኋላ ሐና እግዚአብሔርን አመሰገነችው። ልቤ በእግዚአብሔር አምኖ ጸና የሚለውን ጸሎትና ትንቢት እስከ መጨረሻው ተናገረች። ይቺም በዳዊት መዝሙር መጨረሻ ከሙሴ መኀልይ ቀጥላ ተጽፋለች።
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔርን አገልግላ በሰላም ጥቅምት 6 አርፋለች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚች ቀን የሀገረ ቀምስ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ፊልያስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህንንም ቅዱስ በመኰንኑ ቊልቊልያኖስ ዘመን ወደ ፍርድ አደባባይ አቀረቡት ቊልቊልያኖስም ለአማልክት ሠዋ አለው። ፊልያስም እኔ ከብቻው እግዚአብሔር በቀር ለአማልክት አልሠዋም አለ። ቊልቊልያኖስም እግዚአብሔር ምን አይነት መሥዋዕት ይሻል አለ ፊልያስም ቅን ትሑት የሆነ ንጹሕ ልቡናን ዕውነተኛ ፍርድን ቁም ነገርን እንዲህ ያለ መሥዋዕትን እግዚአብሔር ይወዳል አለው።
ቊልቊልያኖስም የምትጋደል ስለ ነፍስ ነው ወይስ ስለ ሥጋ አለ ፊልያስም ስለ ነፍስና ስለ ሥጋ ነው እነርሱ በአንድነት ይነሣሉና አለ። ቊልቊልያኖስም የምትወዳት ሚስት የምትወዳቸው ልጆች ወይም ወንድምና ዘመድ አለህን አለው ፊልያስም ከሁሉም የእግዚአብሔር ፍቅር ይበልጣል አለ።
ቊልቊልያኖስም እግዚአብሔር ከበጎ ሥራ የሠራው ምንድን ነው አለ ፊልያስም እግዚአብሔር ያደረገልን ይህ ነው ሰማይና ምድርን በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ ፈጠረልን። ዳግመኛም ከጠላታችን ከሰይጣን እጅ ያድነን ዘንድ ከሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሁኖ ተወለደ የሕይወት መንገድንም በዓለም ውስጥ ተመላልሶ አስተማረ መከራንም በሥጋው ተቀብሎ ተሰቅሎ ሞተ በሦስተኛውም ቀን ተነሥቶ በአርባ ቀን ዐረገ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል ይህን ሁሉ ስለ እኛ አደረገ።
ቊልቊልያኖስም አምላክ ይሰቀላልን ይሞታልን አለ ፊልያስም አዎን የዘላለም ሕይወትን ይሰጠን ዘንድ ስለ እኛ ፍቅር ሞተ አለው።
ቊልቊልያኖስም እንዲህ አለው እኔ እንዳከበርኩህ ልጣላህም እንዳልፈለግሁ አላወቅህምን አንተ በወገን የከበርክ እንደሆንክ አውቃለሁና አሁንም ለአማልክት ሠዋ በክፉ አሟሟት እንዳትሞት አለው። ፊልያስም እኔን ደስ ማሰኘት ከወደድክ እንዲያሰቃዩኝና እንዲገድሉኝ እዘዝ አለው በዚያንም ጊዜ በሰይፍ ራሱን እንዲቆርጡት አዘዘ።
ሊገድሉት ሲወስዱትም ዘመዶቹና የሀገር ታላላቆች ወደርሱ መጡ ለመኰንኑም በመታዘዝ ለአማልክት እንዲሠዋ እጆቹን እግሮቹን እየሳሙ ለመኑት። እርሱ ግን የጌታዬ ክርስቶስን መከራ መስቀልን ልሸከም እሔዳለሁና እናንተ አሳሳቾች ከእኔ ወግዱ ብሎ ገሠጻቸው።
ከሚገድሉበትም ሲደርስ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ እጆቹን ዘርግቶ ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየ ሕዝቡን አደራ ወደ ጌታ አስጠበቀና ተሰናበተ ከዚህም በኋላ ራሱን ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ።

በዚችም ዕለት የኑሲስ ኤጲስቆጶስ የባስልዮስ ወንድም የከበረ ጎርጎርዮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
ይህም ቅዱስ ጎርጎርዮስ እጅግ የተማረ አዋቂ ነበረ በደሴቶችም ላይ ኤጲስቆጶስነት ተሾመ እነሆ በዚህ ወር በአሥራ አምስት ቀን የሆነውን ከገድሉ ጥቂት እንጽፋለን። ስለርሱም እንዲህ ተባለ እርሱ መሥዋዕቱን ለማክበር በሚቀድስ ጊዜ በመሠዊያው ላይ ሲወርድ መንፈስ ቅዱስን የሚያየው ሆነ ከዚህም በኋላ ኪሩብን አየው በደረቱም ውስጥ አቀፈው በመሠዊያውም ላይ ሳለ ወደ ዝምታና ተደሞ አደረሰው ሰዎችም ሁሉ ሥጋዊ እንቅልፍ የሚያንቀላፋ ይመስላቸው ነበር።
በኤጲስቆጶስነት ሹመት ሠላሳ ሦስት ዘመናት በተፈጸሙለት ጊዜ ወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ ሊጠይቀው መጣ እርሱ ከተጋድሎ ብዛት የተነሣ በጽኑ ደዌ የሚታመም ሁኖ ነበርና በቅዱስ ባስልዮስ መምጣት ደስ አለው።
ቅዱስ ጎርጎርዮስም እንደ ልማዱ ሊቀድስ ወደ መሠዊያው በወጣ ጊዜ የከበረች ድንግል እመቤታችን ማርያም ተገለጸችለትና ዛሬ ወደኔ ትመጣለህ አለችው የቊርባኑንም ቅዳሴ ሲጨርስ ሕዝቡ በቀናች ሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ይመክራቸውና ያስተምራቸው ዘንድ ወንድሙን ባስልዮስን ለመነው እርሱም እንደሚያንቀላፋ ሆነ በቀሰቀሱትም ጊዜ ሙቶ አገኙት ቅዱስ ባስልዮስም ሣጥን እንዲሠሩለት አዘዛቸው። ጸሎታትንም በመጸለይ መዝሙራትንም በመዘመር በማመስገንም እንደሚገባ ገንዞ በመቃብር ውስጥ አኖሩት።

በዚችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ አንደኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዲዮስቆሮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ። ይህም አባት በዘመኑ ካሉ ትውልድ እርሱን የሚመስል ያልተገኘ በጠባዩ ቅን የዋህ በእውቀቱ አስተዋይ በበጎ ሥራው ፍጹም የሆነ ነው።
በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ መልእክትን ጽፎ ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጰሳት ቅዱስ ሳዊሮስ ላካት ። እርሱም ልዩ ሦስት የሆኑ ሥላሴ በመለኮት አንድ እንደሆኑ እየገለጠና እያሳሰበ ነው። ስለ ወልደ እግዚአብሔርም ሰው መሆን እርሱ ፍጹም ሥጋን ነባቢትና ለባዊት ነፍስን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ነሣ በመለኮቱና በትስብእቱም አካል ያለው አንድ ልጅ እንደሆነ ከተዋሕዶውም በኋላ በሥራው ሁሉ የማይለያይ ጭማሪ ወይም ጉድለት የሌለው ነው።
መልእክቱም ወደ ቅዱስ አባት ሳዊሮስ በደረሰች ጊዜ አነበባትና ፈጽሞ ደስ ተሰኘባት ለአንጾኪያም ሕዝብ አስተማረባት ሁሉም ደስ አለቸው።
ከዚህም በኋላ አባ ሳዊሮስ ለአባ ዲዮስቆሮስ የመልእክቱን መልስ እንዲህ ብሎ ጻፈ ። በኒቅያ ከተማ ተሰብስበው ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ቅዱሳን አባቶቻችን በቀናች ሃይማኖት አጽንተው የሠሩዋትን ቤተ ክርስቲያኑን እንድትጠብቅ ለዚች ለከበረች አገልግሎት የመረጠህ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። ዳግመኛም በዚሁ እንዲጸና ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ እንዳይል አስገነዘበው ደግሞም በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ ሕዝቡን ሁል ጊዜ አስተምራቸው አለው።
የአባ ሳዊሮስም መልእክት ወደ አባ ዲዮስቆሮስ በደረሰች ጊዜ ደስ ተሰኘባት በሁሉ ቦታም እንዲአስተምሩባት አዘዘ ይህም አባት ሕዝቡን ሁል ጊዜ የሚያስተምራቸው ሆነ። ሁል ጊዜም ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ያስተምራቸዋል ኤጲስቆጶሳቱንና ካህናቱንም መንጋዎቻቸውን ስለ መጠበቅ ያዛቸዋል መልካም አገልግሎቱንም አድርሶ እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages