ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 3 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, October 12, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 3

 ጥቅምት_3

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሦስት በዚህች ቀን የኢትዮጵያዊው ቄርሎስ #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ በዓለ ፅንሰቱ ነው፣ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 51ኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባ_ስምዖን አረፈ፣ #የቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሐዲስ የምስክርነቱ መታሰቢያ ነው፡፡
ጥቅምት ሦስት በዚህች ዕለት ከመጽሐፈ ሰዓታት ውጭ እጅግ ብዙ ድርሰቶችን የደረሰ ፈላስፋም ጻዲቅም ደራሲም መናኝ ባሕታዊም የሆነ ድርሰቶቹንም ለቅዱሳን በነፋስ ጭኖ ይልክላቸው የነበረ የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ኩራት ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በዓለ ፅንሰቱ ነው፡፡
አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ አሁንም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡
ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ “ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ” ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- “እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ 'አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?” ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣ እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?” ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡
በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ ሊቃውንቱም “እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ” ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደረገ፡፡ በአልጋ ላይ ሆኖም በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ነገሩት፡፡ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ ገድሉ በሚከተለው መንገድ ይገልጥልናል “እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?” በዚህ ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱ “በምጽአት ጊዜ የሚመጣው ወልድ ብቻውን እንጂ አብና መንፈስ ቅዱስ አይመጡም” የሚል ኑፋ*ቄ ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ቢቱ ከዚህ ኑፋ*ቄው በተጨማሪ የጥንቆላ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ቢቱ በጥንቆላ ሥራው የተነሣ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት የነበረው ሰው እንደ ነበረ ገድሉ ይናገራል፡፡ ይህን መሰሉን ተግባር አጥብቆ የተዋጋው ዘርዐ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ ነገሥታቱ ምንም ክርስቲያኖች ቢሆኑ በዚህ መሰሉ ስንኩል ሕፀፅ ይዋጡ ነበር፡፡
ቢቱና አባ ጊዮርጊስ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ጳጳሱና ሊቃውንቱ ባሉበት እንዲነጋገሩ ስለ ወሰነ ጳጳሱ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ተንኮለኛው ቢቱ ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ከተከራከረ እንደሚረታ ስላወቀ “ንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ክዷ*ልና አትምጣ” የሚል ደብዳቤ በአባ ጊዮርጊስ ስም ጽፎ ጳጳሱን ሊጠሩ በሄዱት መልእክተኞች እጅ ላከ፡፡ ወድያውም ለዐፄ ዳዊት ይህንን ነገር አሳበቀ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ፈጣን መልእክተኞች ልኮ የፊተኞቹ መልእክተኞች እንዲመለሱ አደረገና ደብዳቤው ተነበበ፡፡ የቢቱ ተንኮል ያልገባው ንጉሥ ዳዊት ይህን ደብዳቤ ሲመለከት አባ ጊዮርጊስን በደም አበላ እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡

ዳግመኛም በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ኃምሣ አንደኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን አረፈ።
ይህም አባት ከእስክንድርያ ከታላላቆች ተወላጅ የሆነ ወላጆቹም ሃይማኖታቸው የቀና ነው እርሱም ከታናሽነቱ የሃይማኖት ወተትን ጠጥቶ አደገ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተማረ።
የምንኵስናንም ልብስ ሊለብስ በልቡ አስቦ ወደ አስቄጥስ ገዳም በመሔድ ከእርሱ አስቀድሞ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በአባ ያዕቆብ ገዳም መነኰሰ በየጊዜው በሚጨመር ተጋድሎም ሥጋውን እያደከመ አብዝቶ በመጋደል በእርሱ ዘንድ ኖረ።
ዳግማዊ አባ ማርቆስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህን አባ ስምዖንን ስለ በጎተጋድሎውና ስለ አገልግሎቱ ከአባ ያዕቆብ ዘንድ ወሰደው እያገለገለውም ከእርሱ ጋር ኖረ።
አባ ማርቆስም በአረፈ ጊዜ አባ ያዕቆብ ተሾመ ያን ጊዜም እያገለገለው ከአባ ያዕቆብ ጋር ኖረ። ከዚህም በኋላ አባ ያዕቆብ በአረፈ ጊዜ ብዙዎች ካህናትና ኤጲስቆጶሳት የሀገር ታላላቆች ሁሉም ይህን አባት አባ ስምዖንን መረጡት። ትሩፋቱንና የአማረ ሥራውን በእነዚህ በሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ በነበረበት ጊዜ ስለተመለከቱ አምላካዊ ፍቅር አነሣሥቷቸዋልና በወንጌላዊ ማርቆስ መንበር ላይ ይዘው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።
ከዚህም በኋላ በሹመቱ ጸንቶ መልካምን ጉዞ ተጓዘ እግዚአብሔርንም አገለገለው የሃይማኖትንም ሕግ በማስጠበቅ የክርስቶስን መንጋዎች ጠበቀ።
በሹመቱ ወራትም ቤተ ክርስቲያን በጸጥታና በሰላም ኖረች። ከዚህም በኋላ እግሮቹን በጽኑዕ ደዌ ታመመ ፈጣሪ እግዚአብሔርንም ከዚህ ደዌ ያሳርፈው ዘንድ ለመነው። ክብር ይግባውና ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ በሰላም በፍቅር አንድነት አሳረፈው የሹመቱ ወራትም አምስት ወር ከዐሥራ አምስት ቀን ነው።

ሰማዕቱ የተወለደው በምድረ ግብጽ አሕዛብ (ተንባላት) በሰለጠኑበት የመጀመሪያው ዘመን ነበር። በተለይ ተንባላቱ ግብፅና ሶርያን ከያዙ በኋላ ባልተጠበቀ ፍጥነት በኃይልም በሰውም ተደራጅተው ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሊቀ ሰማዕታት አይደለም) የተወለደው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር።
እናቱ የተመሠከረላት ክርስቲያን ብትሆንም እንዳለመታደል አባቱ ተንባላታዊ (አሕዛብ) ነበር። ስሙንም መዛሕዝም ይሉታል። ሕጻኑ እንደተወለደ ያወጡለት ስም አሕዛባዊ ከመሆኑ ባለፈ በሰዓቱ መጠመቅ አልቻለም። የወቅቱ ሕግ ከወላጆቹ አንዱ አሕዛባዊ ከሆነና አጠምቃለሁ ቢባል የሚከተለው ሰይፍ ነበር። በዚሕ ምክንያት ሳይጠመቅ 7 ዓመት ሞላው።
እናቱ ግን ሕጻን ቢሆንም ፍቅረ ክርስትናን ታስተምረው ነበር። ባይጠመቅም ጸበሉን እመነቱን ትቀባው ነበር። ደብቃ ቅዳሴ ታሰማውም ነበር። አንድ ቀን ግን ሕጻናት ሲቆርቡ አይቶ ካልቆረብኩ ብሎ አለቀሰ። ምን ታድርገው? ወደ ውጪ አውጥታ ከአውሎግያ (የሰንበት በረከት) አበላችው። "ጌታዬ ልጄን እርዳው" አለች።
ልክ በአፉ ሲቀምሳት መዓዛ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና ፍጹም ተደሰተ። ትንሽ ከፍ ሲል ለምን እንደማይጠመቅና እንደማይቆርብ እናቱን ጠየቃት። "ልጄ ሆይ! ይገድሉሃል" አለችው። ከዚህች ቀን ጀምሮ የሚጠመቅበትን ዘዴ ይፈልግ ጀመር።
አስቀድሞ ትምሕርተ ክርስትናን ተማረ። ለአካለ መጠን ሲደርስ አፈላልጐ ጠንካራ ክርስቲያን የሆነች ሴት አገባ። ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ሚስቱን ስለ መጠመቅ አማከራት። "ሌላ ሃገር ሒደህ ተጠመቅ" አለችው። ከግብፅ ተነስቶ ሶርያ ገባ። አባቶችን አፈላልጎ ተጠመቀ። ቀጥሎም መንገዱን ወደ ልዳ አደረገ።
ወደ ደብሩ ተጠግቶ አባቶችን "ስም አውጡልኝ" ቢላቸው መንፈስ ቅዱስ አናግሯቸው "ጊዮርጊስ" አሉት። እሱም ደስ እያለው ባጭር ታጥቆ የልዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገለግለው ገባ። ትንሽ ቆይቶ ሁከት መንፈሳዊ ተሰማው። ማለትም ስለ ሃይማኖቱ ደሙን ማፍሰስ ፈለገና ወደ ግብፅ ተመለሰ።
በዚያ ያሉ አሕዛብ በክርስትና ስም ልብስና ሞገስ ሲመለከቱት ተበሳጩ። ዕለቱኑ አሠሩት። ሌሊት እናቱና ሚስቱ መጥተው አሉት "አደራ! ፍቅረ ዓለም እንዳያታልልህ። ሰማዕት ብትሆን ላንተም ክብር ለእኛም ሞገስ ነው" ብለውም አጽናኑት። እንዲህ ያሉ እናትና ሚስት ማግኘትም ታላቅ እድል ነው::
ሐዲስ ጊዮርጊስም ጸና። ከዚያች ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ደበደቡት አካሉን ቆራረጡት ደሙንም መሬት ላይ አንጠፈጠፉት። በየመንገዱ እየጎተቱ ተሳለቁበት። እርሱ ግን ክርስቶስን ወዷልና ሁሉን ታገሰ። ሌሊት በሆነ ጊዜም ጌታችን ተገልጦ "ከሰማዕታት ተቆጠርህ" አለው።
በማግስቱ በአደባባይ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት። ክፋታቸው የጸና ነውና ሥጋውን በእሳት አቃጠሉት። ወደ ባሕርም ጣሉት። እናቱ ከባሕር ስታወጣው ግን ምንም አላገኘውም ነበር። በዚሕች ቀን እናቱና ሚስቱ በክብር ቀብረውታል።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages