ጥቅምት 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ ዮሴፍ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት
2.ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ኢላርዮስ
4.ቅድስት እለእስክንድርያ ሰማዕት
ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
6.አባ ሳሙኤል
7.አባ ስምዖን
8.አባ ገብርኤል
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት 23 በዚህች ቀን፣
1) የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ አረፈ፣
2) የከሀዲ ዱድያኖስ ንጉሥ ሚስት ቅድስት እለእስክንድርያ መታሰቢያዋ ነው፣
3) የቆሮንቶስ አገር ኤጲስቆጶስ በሰማዕትነት አረፈ፣
4) በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተተክለው በደብረ ሊባኖስ የተሾሙት
አቡነ ኤልሳ ዕረፍታቸው ነው፡፡
ጥቅምት ሃያ ሦስት በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ኀምሳ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ አረፈ ። ይህም አባት ከመኑፍ አገር ከታላላቆች ተወላጆች ወገን ነው ወላጆቹም ብዙ ገንዘብ ያላቸው ነበሩ ታናሽም ሁኖ ሳለ አባትና እናቱ ትተውት ሲሞቱ ድኃ አደግ ሆነ አንድ እግዚአብሔርንም የሚወድ ሰው አሳደገው።
አድጎ በጎለመሰም ጊዜ የወላጆቹን ገንዘብ ሁሉንም ወስዶ ለድኆችና ለምስኪኖች መጸወተ ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወጥቶ ከአንድ ፃድቅ ሽማግሌ ሰው አባት ዘንድ መነኰሰ በበጎ ገድል ሁሉ እየተጋደለ ኖረ ።
ዳግማዊ አባ ማርቆስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ የዚህን አባ ዮሴፍን በጎ ጠባዩንና የትሩፋቱን ዜና ሰምቶ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው በቤቱም አኖረው ።
ከብዙ ወራትም በኋላ አባ ዮሴፍ ሊቀ ጳጳሳቱን አባ ማርቆስን ወደ አስቄጥስ ገዳም እሔድ ዘንድ ተወኝ ብሎ ለመነው ያን ጊዜም ቅስና ሹሞ አሰናበተው ሊቀ ጳጳሳት አባ ስምዖንም እስከ አረፈ ድረስ በዚያ በእስቄጥስ ገዳም ኖረ ከዚህም በኋላ የግብጽ አገር ያለ ሊቀ ጳጳሳት ብዙ ወራት ኖረች ።
ከዚህም በኋላ ኤጲስቆጶሳቱ መማለጃ ስለተቀበሉ ከአንድ ሚስቱ ከሞተችበትና መዓስብ ከሆነ ጸሐፊ ጋር ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ ተስማሙ እኩሌቶቹ ግን ተቃወሟቸው እንዲህም አሏቸው የአባቶቻችን ቀኖና መማለጃ የሚቀበለውን ሁሉ ወይም ስለ ክህነት ሹመት መማለጃ የሚሰጠውን ያወግዛል ። ይልቁንም ይህ ሰው ሚስት አግብቷል እንዴት ሊሾም ይችላል በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ የሚሾም ንጹሕ ድንግልም ነውና።
ይህንንም በአሏቸው ጊዜ ፈሩ ተመልሰውም ተስማሙ ለዚች ለከበረች ሹመት የሚሻለውን ይገልጽላቸው ዘንድ ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን በአንድ ምክር ሁነው ጸለዩ እግዚአብሔርም ሰምቷቸው ለዚች የከበረች ሹመት የሚሻል አባ ዮሴፍ እንደሆነ አሳሰባቸው።
ከዚህም በኋላ አባ ዮሴፍን ያመጡት ዘንድ ወደ አስቄጥስ ገዳም መልእክተኞችን ላኩ መልክተኞችም ይህን አባት ዮሴፍን የመረጥከው ከሆነ ምልክትን ትገልጥልን ዘንድ አቤቱ እንለምንሃለን የቤቱም ደጃፍ ክፍት ሁኖ ካገኘን ምልክት ይሁንልን ብለው ወደ እግዚአብሔር ለመኑ።
በደረሱም ጊዜ አንዱን መነኰስ እየሸኘ የበዓቱም ደጃፍ ክፍት ሁኖ አባ ዮሴፍን አገኙት በአያቸውም ጊዜ መንፈሳዊ ሰላምታ በመስጠት እጅ ነሣቸውና በደስታ ተቀብሎ ወደ በዓቱ አስገባቸው በዚያንም ጊዜ ለአባ ዮሴፍ ሊቀ ጵጵስና ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል እያሉ ይዘው አሠሩት ። እርሱ ግን እኔ ብዙ ኃጢአትን ሠርቻለሁና ይህ የከበረ ሹመት አይገባኝም እያለ ይጮህ ነበር እነርሱም ወደ እስክንድርያ ከተማ ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት እንጂ ምንም ምክንያት አልተቀበሉትም።
በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም በተቀመጠ ጊዜ ለአብያተ ክርስቲያን እጅግ የሚያስብ ሆነ ለርሱ የሆነውን የግብሩን ገቢ ወስዶ ምድሮችን በመግዛት ለአብያተ ክርስተያን መተዳደሪያ ሊሆኑ ጉልቶች ያደርጋቸው ነበርና።
አዘውትሮም ሕዝቡን የሚያስተምራቸው ሆነ በምንም በምን ለየአንዳንዱ ቸለል አይልም ነገር ግን ሰይጣን ስለቀናበት ያለ ኀዘን አልተወውም ። ይህም እንዲህ ነው በምስር አገር የተሾሙ ሁለት ኤጲስቆጶሳት በሕዝቡ ላይ ክፉ ነገር በማድረግ በማይገባ ሥራ አስጨነቋቸው እርሱም በርኅራኄና በፍቅር መንጎቻቸውን እንዲጠብቁ አዘዛቸው ለመናቸውም እነርሱ ግን ሰምተው ከክፋታቸው አልተመለሱም።
በሕዝቡም ላይ ችግርን በአበዙ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉም በጠቅላላ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ መጡ በፊቱም እንዲህ ብለው ጮኹ እሊህን ኤጲስቆጶሳት ከላያችን ካላነሣሃቸው እኛ ወደሌላ ሃይማኖት እንገባለን አባ ዮሴፍም በመካከላቸው ሰላምን ለማድረግ ብዙ ትግልን ታገለ ግን አልተቻለውም።
ከዚህም በኋላ በግብጽ አገር ያሉትን ኤጲስቆጶሳት ለጉባኤ ሰበሰባቸውና ስለ እሊህ ሁለት ኤጲስቆጶሳት ነገራቸው አሁንም ከመንጋዎቻቸው ጋር ሊአስታርቅ ሽቶ እሊህን ኤጲስቆጶሳት ወደ ጉባኤው አስቀረባቸው እነርሱ ግን የጉባኤውንም የእርሱንም ቃል አልተቀበሉም ስለዚህም ያ ጉባኤ ከሹመታቸው ሻራቸው።
እነርሱም ወደ ግብጽ ንጉሥ ሒደው በሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ ላይ በሐሰት ነገር ሠሩበት ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍንም ያመጡት ዘንድ ንጉሡ ወንድሙን ከጭፍራ ጋር ላከው። የንጉሡም ወንድም ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ በደረሰ ጊዜ ተበሳጨ ሊገለውም ወዶ ሰይፉን መዞ ሊቀ ጳጳሳቱን ሊመታው ሰነዘረበት ግን እጁ ወደ ሌላ አዘንብሎ ምሰሶ መትቶ ሰይፉ ተሰበረ እጅግም ተቆጥቶ ሌላ ሰይፍን መዝዞ በመላ ኃይሉ መታው ያን ጊዜም ሰይፉ ከአንገቱ ወደ ወገቡ ተመልሶ ልብሱንና ቅናቱን ብቻ ቆረጠ የንጉሡም ወንድም ከክፋት ንጹሕ እንደሆነ ስለዚህም አምላካዊት ኃይል እንደምትጠብቀው አሰበ አስተዋለም።
ወደ ንጉሡም በክብር አደረሰው ወንድሙ ለሆነ ንጉሥም በእርሱ በሊቀ ጳጳሳቱ ላይ የሆነውን ሁሉ ነገረው ንጉሡም ፈራው አከበረውም ከዚህም በኋላ ስለከሰሱት ስለ ሁለቱ ኤጲስቆጶሳት ጠየቀው እርሱም ስለ ክፉ ሥራቸው በጉባኤ እንደተሻሩ እውነቱን ለንጉሡ አስረዳው ያን ጊዜም ሐሰተኞች እንደሆኑ ንጉሥ አወቀ ይገድሏቸውም ዘንድ አዘዘ።
ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍም ንጉሡን እንዲህ ብሎ ማለደው ጌታችን በክፉ ፈንታ በጎ እንድናደርግ እኛን አዞናልና ስለ እግዚአብሔር ብለህ እሊህን ማራቸው እንጂ አትግደላቸው ንጉሡም ስለ የዋህነቱ አደነቀ ልመናውንም ተቀብሎ ማረለት።
ከዚህም በኋላ በሹማምንቱና በኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ ላይ የፈለገውን ያደረግ ዘንድ ቢፈልግ እንዲሾም ወይም እንዲሽር የሚቃወመው እንዳይኖር ደብዳቤ በመጻፍ ሥልጣንን ሰጠው።
በዚህም አባት ዘመን የኢትዮጵያ ንጉሥ ወደዚህ አባት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ እንዲህ ብሎ መልእክትን ላከ ለወንጌላዊ ማርቆስ መንበርና በላዩ ለመቀመጥ ለተገባው ቅድስናህ እጅ እነሣለሁ በእኔና በመንግሥቴ ላይ በመላው ወገኖቼ በኢትዮጵያ ሰዎች ላይ ይቅርታ እንድታደርግና አባታችንን አባ ዮሐንስን እንድትልክልን እለምንሃለሁ ከሀገራችን ሰዎች ከእውነት መንገድ የወጡና የሳቱ ጳጳሳችንን አባ ዮሐንስን እኔ ሳልኖርና ሳላውቅ አባረውታልና ስለዚህም በሀገራችን ቸነፈርና ድርቅ ሁኖ ከሰዎችም ከእንስሶችም ብዙዎች አለቁ።
አሁንም አባቴ ሆይ ስንፍናችንን ይቅር በል መሐሪና ይቅር ባይ ወደ ሆነ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልድልን ዘንድ በከበረች ጸሎቱም ከዚህ መከራ እንድን ዘንድ አባታችንን አባ ዮሐንስን ላክልን።
አባቴ ሆይ የተባረረበትን ምክንያት እኔ አስረዳሃለሁ እኔ ልጅህ ከአባቴ ከጳጳስ አባ ዮሐንስ ቡራኬ ተቀብዬ እርሱ ከሠራዊቴ ጋር በፍቅር አሰናብቶኝ ወደ ጦር ሜዳ ሔድሁ ከጦር ሜዳም በተመለስኩ ጊዜ አባቴን አባ ዮሐንስ ጳጳሱን አጣሁት ስለርሱም በጠየቅሁ ጊዜ በቀድሞ ዘመን ዮሐንስ አፈ ወርቅን ንግሥት አውዶክስያ እንዳሳደደችው በክፉዎች ሰዎች ምክር ንግሥቲቱ ሚስቴ ማሳደዷን የቀኖናውንም ትእዛዝ በመተላለፍ በፈቃዳቸው ሌላ ጳጳስ እንደሾሙ ነገሩኝ።
እርሱ አባ ዮሐንስም ከኢትዮጵያ በአሳደዱት ጊዜ ወደ አስቄጥስ በመሔድ አስቀድሞ በመነኰሰባት በአባ ሙሴ ጸሊም ገዳም በዚያ ተቀመጠ። የኢትዮጵያ ንጉሥ መልእክትም ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ በደረሰች ጊዜ አነበባት ስለ ኢትዮጵያ ንጉሥ የሃይማኖት ጽናት እጅግ ደስ አለው ፈጥኖም ወደ አስቄጥስ ገዳም መልእክተኞችን ልኮ አባ ዮሐንስን ወደርሱ አስመጥቶ አረጋጋው አጽናናው ከዚያም በኋላ ከደጋጎች ሰዎች ጋር ወደ ኢትዮጵያ አገር ላከው።
አባ ዮሐንስም ወደ ኢትዮጵያ አገር በደረሰ ጊዜ ቸነፈር ተወገደ ዝናብም ዘነበ ንጉሡና መላው የኢትዮጵያ ሰዎች ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑት። ይህም ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ መናፍቃንን የሚገሥጻቸው ሆነ ሕዝቡንም ከአባቶቻቸው በተቀበሏት በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ አስተማራቸው ከቅዱሳት መጻሕፍትም ለእነርሱም ሥውር የሆነውን ተርጉሞ ያስረዳቸዋል ያስገነዝባቸዋልም በትምህርቱና በጸሎቱም እንዲህ ጠበቃቸው ጌታችንም በእጆቹ ብዙዎች ተአምራትን አደረገ ያማረች ገድሉንም ፈጽሞ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም በፍቅር አረፈ ። መላ የሕይወቱም ዘመን ሰባ ስምንት ነው ከምንኲስና በፊት ሃያ አመት በምንኲስና ተጋድሎ ሠላሳ ዘጠኝ ዓመት በሊቀ ጵጵስና ሹመት ዓሥራ ዘጠኝ ዓመት ኖረ ።
ዳግመኛም በዚህች ቀን የከሀዲ ዱድያኖስ ንጉሥ ሚስት የከበረች እለእስክንድርያ መታሰቢያዋ ነው። ይኸውም ለጣዖቶቹ እንደሚሠዋ መስሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘበተበት ጊዜ ዝንጉዕ ዱድያኖስም ዕውነት መስሎት ራሱን ሊስም ተነሣ። ቅዱሱ ግን ለአማልክት ከመሠዋት አስቀድሞ አይሆንም ብሎ እንዳይስመው ከለከለው።
ከዚህ በኋላም ዱድያኖስ ወደ ቤተ መንግሥቱ አዳራሽ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስገባው በዚያም በንግሥት እለእስክንድርያ ፊት የዳዊትን መዝሙር በማንበብ ጸለየ። በሰማችም ጊዜ ይተረጒምላት ዘንድ ለመነችው ያን ጊዜም ተረጐመላት የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነቱን ገለጠላት ትምህርቱም በልቡዋ አድሮ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመነች።
ከዚህም በኋላ ሲነጋ ለአማልክት ወደሚሠዋበት ቅዱስ ጊዮርጊስን ወሰዱት እርሱም የረከሱ አማልክትን ትውጣቸው ዘንድ ምድርን አዘዛት ምድርም ዋጠቻቸው። ንጉሥ ዱድያኖስም አፈረ እየአዘነና እየተከዘ ወደ ሚስቱ ወደ እለእስክንድርያ ዘንድ ገባ። እርሷም ክርስቲያኖችን አትጣላቸው አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነው አላልኩህምን አለችው። ይህንንም ሰምቶ በእርሷ ላይ ተቆጣ ያሠቃዩዋት ዘንድ ጡቶቿንም ሠንጥቀው ይሰቅሏት ዘንድ አዘዘ። የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች።
በዚችም ቀን የቆሮንቶስ አገር ኤጲስቆጶስ ዲዮናስዮስ በዐላውያን ነገሥታት በዲዮቅልጥያኖስና በመክስምያኖስ ዘመን በሰማዕትነት አረፈ ይህንንም ቅዱስ በያዙት ጊዜ ብዙ ሥቃይን አሠቃዩት ማሠቃየቱንም በሰልቹ ጊዜ ራሱን በሰይፍ አስቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ።
ዳግመኛም በዚህች ቀን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተተክለው በደብረ ሊባኖስ የተሾሙት አቡነ ኤልሳ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ ሀገራቸው ሸዋ ነው፡፡ በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመን የነበሩ ሲሆን ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቀጥለው በደብረ ሊባኖስ ገዳም በእጨጌነት የተሾሙ የመጀመሪያ ዕጨጌ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከማረፋቸው በፊት ‹‹በእኔ ወንበር ኤልሳዕ ይሾም ነገር ግን ዘመኑ ትንሽ ስለሆነ ከእርሱ ቀጥሎ ፊሊጶስን ትሾማላችሁ›› ብለው ለቅዱሳን ተከታይ ሐዋርያቶቻቸው ተናግረው ነበር፡፡
በዚህም መሠረት አቡነ ኤልሳዕ ተሹመው ብዙም ሳይቆዩ አንድ ዲያቆን ሞተና ሊቀብሩት ሲወስዱት በመንገድ ላይ ሳለ ድንገት ከሞት ተነሥቶ ‹‹አባቴ ተክለ ሃይማኖት ኤልሳዕ አሁን ወደኔ ስለሚመጣ ፊሊጶስን ሹሙት ብለህ ተናገር ብለውኝ ነው›› ብሎ ከተናገረ በኋላ ተመልሶ ዐርፎ ተቀበረ፡፡ አቡነ ኤልሳዕም ወዲያው ዐርፈው አቡነ ፊሊጶስ 3ኛ ሆነው ተሾሙ፡፡ አቡነ ኤልሳዕ ከተጋድሎአቸው ብዛት የተነሣ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ጎናቸውን አሳርፈው ተኝተው አያውቁም ነበር፡፡ ነገር ግን ማረፍ ሲኖርባቸው በወንበር ላይ ተደግፈው ትንሽ ብቻ ያርፉ ነበር፡፡ አቡነ ኤልሳዕ በሞት ያረፉትም እንደልማዳቸው ጎናቸውን ሳያሳርፉ በወንበር ላይ እንደተደገፉ ነበር፡፡ አባታችን ስለዚህም ጉዳይ ሲናገሩ እንዲህ ይሉ ነበር፡- ‹‹ነፍስ ትጋትን ትወዳለች፣ ሥጋ ግን ይደክማል፡፡ ለመነኮሳትና ለእግዚአብሔር አገልጋዮች ሁሉ መኝታ ማብዛት አይገባቸውም፡፡ መኝታ ማብዛት ሕልምን ያመጣል፣ ነፍስን ይጎዳል፣ ሰውነትንም ያደክማል፡፡››
አቡነ ኤልሳዕ በዘመናቸው ወንጌልን በማስተማርና ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ይታወቁ ነበር፡፡ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ እሳቸውም ሙት አስነሥተዋል፡፡ ባሕር እየከፈሉ ቀደ መዛሙርቶቻቸውን ያሻግሩ ነበር፡፡ በጸሎታቸው የዠማን ወንዝም ለሁለት የከፈሉ ታላቅ አባት ናቸው፡፡
ለእግዚአብርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment