ጥቅምት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አብላርዮስ ገዳማዊ
2.ቅድስት ጸበለ ማርያም
3.ቅድስት አውስያ
4.አባ ዻውሎስ ሊቀ ዻዻሳት
በ 24 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
3.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ)
6."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
7.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
8.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ አራት በዚህች ዕለት የቅድስት_ጸበለ_ማርያም መታሰቢያዋ ነው፣ መስተጋድል መነኰስ ቅዱስ_አባ_አብላርዮስ ያረፈበት ቀን ነው፣ የመፍቀሬ ነዳያን አባ_ዘግሩም ዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡።
በዚህች ዕለት ታስባ የምትውለውንና ጌታችን በደሃ ሰው ተመስሎ ተገልጦ ቁራሽ እንጀራ የለመናትን በኋላም በጀርባዋ አዝላ የሸኘችው ቅድስት ጸበለ ማርያም እረፍቷ መስከረም ፲፰ ቀን ነውና ጥር ፲፰ ቀንም በዓል ነው። እርሷም በጎኗ ተኝታ የማታውቅ፣ በጌታችን ፵ ጾም ወራት ከሰንበት በቀር ምንም የማትቀምስ፣ ነብሮች የእግሯን ትቢያ ይልሱላት የነበረች ታላቅ ኢትዮጵያዊት ቅድስት ናት። ይኽችውም ከነቢያት፣ ከሐዋርያትና ከሰማዕታት ዕድል የተሰጣት እናት ናት፡፡ ከደናግል መነኮሳትም ዕድል ተሰጣት መነኩሲትም ድንግልም ናትና፡፡
እናታችን ቅድስት ጸበለ ማርያም፡- ቅድስት ጸበለ ማርያም ትውልዷ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ቀሐ አካባቢ ነው፡፡ ወላጆቿ አባቷ እንድርያስና እናቷ መስቀል ክብራ ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማሩ በሃይማኖት በምግባር ኮትኮተው አሳደጓት፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ተከስተ ብርሃን የተባለ ደገኛ ባሕታዊ ወደ አባቷ ቤት መጥቶ ባደረበት መንፈስ ቅዱስ ኀይል የቅድስት ጸበለ ማርያምን ጸጋ አወቀ፡፡ ለወላጆቿም "ይኽቺ ልጅ ወደፊት ነፍሳት የሚድኑባት የከበረች ትሆናለች" ብሎ በእርሷ ላይ ትንቢት ተናገረ፡፡
ቅድስት ጸበለ ማርያም ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ ወላጆቿ በጋብቻ ሕግ እንድትወሰን ፈለጉ፡፡ ነገር ግን ቅድስት ጸበለ ማርያም "ቅዱስ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር አጭቶኛልና ፈጣሪዬን በድንግልና ለማገልገል ተስያለሁ" በማለት ተቃወመቻቸው፡፡ ወደ አንድ ደገኛ ባሕታዊም ዘንድ ሄዳ በጸሎቱ ከዚህ ነገር እንዲያድናት ተማጸነችው፡፡ እርሱም ፈቃደ እግዚአብሔርን በጸሎት ከጠየቀላት በኋላ ማድረግ የሚገባትንና ወደፊት የሚገጥማትን ሁሉ ነገራት፡፡ እርሷም ለዕጣን እንዲሆን ጌጧን ሁሉ አውጥታ ሸጠችና "መሥዋዕቴን አሳርግልኝ" ብላ ለባሕታዊው ሰጠችው፡፡ እርሱም ከጸለየላት በኋላ የጸሎቱን ምላሽ ነገራት፡፡
ወለጆቿም ያለፈቃዷ በሕግ ቢያጋቧትም ቅድስት ጸበለ ማርያም ግን በሌሊት ማንም ሳያያት ከጫጉላ ቤት ወጥታ ሄዳ በልዳው ፀሐይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ወደተሠራች ቤተክርስቲያን ሄዳ እያለቀሰች ጸሎት አደረገች፡፡ እመቤታችንም ከሚካኤል ወገብርኤል እንዲሁም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተገለጠችላትና እንዲጠብቋት ነገረቻቸው፡፡ ቤተሰቦቿም እንዳያዝኑባት ፈርታ ተመልሳ ወደ ባሏ ዘንድ ብትገባም ባሏ በግብር እንዳያውቃት መላእክቱ ይጠብቋት ነበር፡፡ ባሏንም ሰውነቷ እንደእሳት ያቃጥለው ነበር፡፡ እርሱም አእምሮውን ከሳተ ከ3 ቀን በኋላ ሲነቃ የደረሰበትን ለቤተ ዘመዶቹ ባስዳቸው ጊዜ "ከገዳም የመጣች ከሆነች ለእኛ ልትሆን አይገባም" አሉና አስጊጠውና ሸልመው መልሰው ወደ ቤተሰቦቿ ላኳት፡፡
አባቷም ዳግመኛ ወደ ባሏ እንድትመለስ በማስገደድ ብዙ አሰቃቂ ግርፋት ቢገርፋትም በተአምራት ምንም እንዳላገኛት ሆነች፡፡ ከዚኽም በኋላ ወጥታ ወደ ምድረ በዳ ሄደች፡፡ ወደ ገዳምም ሄዳ ዋሻ ውስጥ ገብታ ስትጸልይ አድራ አረፍ ስትል ነብር መጥቶ የእግሯን ትቢያ ይልሳት ነበር፡፡ ከዚያም ወጥታ ንህበት ወደሚባል ሀገር መጥታ ቶማስ ከሚባል መነኩሴ ጋር በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ ቆማ ስትጸልይ እንባዋ መሬቱን ያርስ ነበር ነገር ግን ሰው እንዳያውቅባት አፈር በላዩ ትጨምርበታለች፡፡ በአንድ ዕለትም በቤተክርስቲያን ቆማ ስትጸልይ በሁለቱ ማዕዘን የተቀበሩ ምውታን ሲጮኹ ሰማቻቸው፣ እነርሱ ግን በሲኦል ነበሩ፡፡ ጩኸታቸውንም በሰማች ጊዜ በእንባዋ ላይ እንባን በጸሎቷም ላይ ጸሎትን ጨምራ ስለ እነርሱ ለመነች፡፡ ስለእነርሱም ሱባኤ ያዘች፡፡ በባሕርይው ቸርና ይቅርባይ የሆነ ልዑል እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ እነዚያን ነፍሳት ማረላት፡፡
ቅድስት ጸበለ ማርያም በምግባርና በትሩፋት በጾም በጸሎት ጸንታ ከኖረች በኋላ የምንኩስና ቀንበርን ትሸከም (በምናኔ ትኖር) ዘንድ በብሕትውና ወደሚኖረው ታላቁ አባት ወደ አቡነ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ ዘንድ ሄደች፡፡ እርሱም ማኅሌተ ጽጌን ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር የደረሰው ነው፡፡
አቡነ ገብረ ማርያምም ካስተማራትና በኋላ አመነኮሳትና ስሟን "ጸበለ ማርያም" ብሎ ሰየማት፡፡ ከዚኽም በኋላ ተጋድሎዋን እጅግ በማብዛት ትሕርምትን ገንዘብ አደረገች፡፡ ከዕንጨት ፍሬዎች ውጭ የማትመገብ ሆነች፡፡ በተቀደሰችው የጌታችን ፵ ጾም ወራት ግን ከሰንበት በቀር እርሱንም ፈጽሞ አትቀምስም፣ እስከ ፋሲካም ድረስ ከበዓቷ ስለማትወጣ ማንም አያያትም ነበር፡፡ ከመነኮሰችም ጊዜ ጀምሮ በጎኗ ተኝታ አታውቅም፡፡ ባመማት ጊዜም ተቀምጣ ታንቀላፋ ነበር፡፡ በውርጭ ቅዝቃዜ መከራን እየተቀበለች በባሕር ውስጥም ቆማ እየጸለየች ታድራለች፡፡ በስግደቷም በቀን እስከ 8 እልፍ ትሰግድ ነበር፡፡ ከወንድሟ ቶማስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ተማረች፡፡ የዮሐንስን ወንጌልና የራእዩን መጽሐፍ ዘወትር በማንበብ ትጸልያለች፡፡ የእመቤታችን በዓል በሆነ ጊዜ አርጋኖን ውዳሴዋን በቀን ሦስት ጊዜ ታነባለች፣ አንቀጸ ብርሃንንም በየሰባቱ ጊዜ ትጸልያለች፡፡ የዳዊትንም መዝሙር በፈጸመች ጊዜ የጌታችንን መከራ ግርፋት እያሰበች ራሷን ሺህ ጊዜ ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም አገዛዛቸው መልካም ይሆን ዘንድ ስለ ጳጳሱና ስለ ንጉሡ አንድ አንድ ሺህ ጊዜ፣ ስለ መነኮሳትም ሺህ ጊዜ፣ ስለኃጥአንም ሺህ ጊዜ ራሷን ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም ነጭ ዕጣን በእጇ ይዛ ሰባት ቀን እስኪሆን ድረስ ዕንባዋን ታፈስበታለች፣ ያም ነጭ ዕጣን ከዕንባዋ ብዛት የተነሣ ጥቁር ይሆናል፡፡ በዓል በሚሆንበት በሰባተኛው ቀን አስቀድማ ዐውቃ በመሠዊያ ያሳርገው ዘንድ ያን ዕጣን ለቄሱ ትሰጠዋለች፡፡ እግዚአብሔርም እንደሱራፌል የጽናሕ መዐዛና እንደኪሩቤል ዕጣን ሽታ አድርጎ ከቄሱ እጅ ሲቀበል በግልጽ ታያለች፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ቅድስት ጸበለ ማርያም እየጸለየች ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቆሰለ ችግረኛ ደሃ ሰው ተመስሎ ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገልጦ ወደ እርሷ በመምጣት ቁራሽ እንጀራ ለመናት፡፡ እርሷም ፈጥና ይዛ መጥታ ሰጠችው። እንጀራውንም ተቀብሎ ሲያበቃ "በመንገድ ብዛት ደክሜአለሁና በጀርባሽ አዝለሽ ትሸኚኝ ዘንድ እወዳለሁ" አላት፡፡ እርሷም ለድሆች አዛኝ ናትና አዝላው የድንጋይ መወርወሪያ ያህል እንደወሰደችው ቁስሉ ይድን ጀመር፡፡ ወዲያውም ቁስሉ ድኖ ምንም እንዳላገኘው ፍጹም ደህነኛ ሰው ሆነ፡፡ ያንጊዜም ፊቱ እንደፀሐይ አበራ፣ ሁለንተናውም ተለወጠ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ከጀርባዋ ወርዶ በፊት ለፊቷ ቆመና "የከበርሽ አገልጋዬ ጸበለ ማርያም ሆይ! ምን እንዳድርግልሽ ትወጃለሽ?" አላት፡፡ እርሷም ከድንጋጤዋ የተነሣ እንደበድን ሆና መሬት ላይ ወደቀች፡፡ ጌታችንም አበረታትና እጇን ይዞ አነሣትና "የልብሽን መሻት ለምኚኝ" አላት፡፡ እርሷም "አምላኬ ሆይ! በፊትህስ ሞገስ ካገኘሁ በሲኦል ያሉ ነፍሳትን ይቅር በላቸው" አለችው፡፡ በዚኽም ምክንያት በጌታችን ቸርነትና በእርሷም አማላጅነት ብዙ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፡፡ ጌታችንም ሰላምታ ሰጥቷት በክብር ዐረገ፡፡
ዳግመኛም ጌታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ሦስት በትሮችን ሰጥቷት በእነርሱ እየተመረኮዘች እስከሲኦል ድረስ ትሄድና ነፍሳትን ታወጣና ታስምር እንደነበር ራሷ ተናገረች፡፡ ዳግመኛም ስትናገር "ሰማያውያን ብዙ ስሞች አወጡልኝ፣ 'የወይን ፍሬ' እያሉ ይጠሩኛል፣ 'የበረከት ፍሬ' የሚሉኝም አሉ፣ 'የገነት ፍሬም' ይሉኛል" አለች፡፡ ዳግመኛም ከልዑል ዘንድ ብዙ ጸጋዎች እንደተሰጣት በሕይወት ሳለች ለአንደ ደገኛ ቄስ ነገረችው፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት እመቤታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገለጠችላትና "ስሜን የተሸከምሽ ጸበለ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን" አለቻት፡፡ እመቤታችንም ብዙ ምሥጢርን ከነገረቻት በኋላ ጡቶቿንም አጠባቻትና በጸጋ የከበረች አደረገቻት፡፡ በስሟም ብዙ ተአምራትን የምታደርግ ሆነች፡፡
ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም ከነቢያት፣ ከሐዋርያትና ከሰማዕታት ዕድል የተሰጣት እናት ናት፡፡ እንደነቢያት የሚመጣውን ሁሉ እንዳለፈ አድርጋ ትናገራለች፡፡ ዳግመኛም የትምህርታቸውን ፍለጋ ስለተከተለችና ለሕጋቸው ስለተገዛች ከሐዋርያት ጋር ዕድል ተሰጣት፡፡ ሦስተኛ ግድ ሳይሏት በፈቃዷ ስለተቀበለቻቸው ግርፋቶቿና ስላገኛት መከራ የሰማዕታት ዕድል ተሰጣት፡፡ ከደናግል መነኮሳትም ዕድል ተሰጣት መነኩሲትም ድንግልም ናትና፡፡ ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም መልካም የሆነውን ተጋድሎዋን ከፈጸመችና ጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ከገባላት በኋላ በሰላም ዐርፋለች፡፡ እንደ ንግሥት ዕሌኒም የሞቷን መስቀል ተሸክማ ተጠብቆላት ወዳለ ተስፋዋ በክብር ሄደች፡፡
ዳግመኛም በዚህች ቀን መስተጋድል መነኰስ አባ አብላርዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ጋዛ ከሚባል አገር ነው ወላጀቹም አረማውያን ናቸው የዮናናውያንንም ትምህርታቸውንና ፍልስፍናቸውን አስተማሩት ሰውነቱ ለጥበብ ማደሪያዋ እስከሆነ ድረስ በዕውቀቱ ከጓደኞቹ በላይ ሆነ።
ከዚህም በኋላ ከሀገሩ የሌለ መልካም የሆነ ጥበብን ከውጭ አገር መማርን ወዶ ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ ሀገር ሔደ መምህራንም ሁሉ ከሚኖሩበት ቦታ ገብቶ ከእሳቸው ዘንድ ብዙ ትምህርትን ተማረ በዚያንም ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለመማር ተነሣሥቶ ቸኰለ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ብዙዎቹን አነበበ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስም ይተረጕምለትና ያስረዳው ነበር።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የክርስትናን ጥምቀት ተጠመቀ ከዚያም መንኵሶ በምንኵስና ሕግ ጸንቶ ገድልን ተጋደለ ወደ አባ እንጦንዮስም ሔዶ መንፈሳዊ የሆነ የትሩፋትን ሥራ እየተማረ በእርሱ ዘንድ ብዙ ወራት ኖረ።
ወላጆቹም እንደሞቱ በሰማ ጊዜ ሒዶ የተዉለትን ገንዘባቸውን ሁሉንም ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች መጸወተ ከዚህም በኋላ ከሶርያ ገዳማት ወደ አንዱ ገዳም ገባ በዚያም በጾም በጸሎት በስግደት በመትጋት ፍጹም ገድልን ተጋደለ በየሰባት ቀን እስቲመገብ ድረስ ምግቡም የዱር ሣር ነበር።
እግዚአብሔርም ሀብተ ትንቢትን ሰጥቶት ልቡናው ብሩህ ሆነ ድንቆች ተአምራትንም የሚያደርግ ሆነ ኤጲፋንዮስንም ያመነኰሰውና ለደሴተ ቆጵሮስም ኤጲስቆጶስ እንደሚሆን ትንቢት የተናገረለት እርሱ ነው።
የዚህም አባት መላ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት ነው ከክርስትናውና ከምንኵስናው በፊት ዐሥራ ሰባት ዓመት በምንኵስናም ስልሳ ሦስት ዓመት ነው ክብር ይግባውና እግዚአብሔርንም ካገለገለ በኋላ በሰላም አረፈ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም አመስግኖታል ሁለተኛም ቅዱስ ባስልዮስ በመጻሕፍቱ አመስግኖታል።
ዳግመኛም በዚህች ቀን የመፍቀሬ ነዳያን አባ ዘግሩም ዓመታዊ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ አባታቸው ገርዜነ ጸጋ የተባለ ደገኛ ካህን ሲሆን እናታቸው ደግሞ ነፍስተ እግዚእ ትባላለች፡፡ እነዚህም ደገኛ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ሕግ ጸንተው ብዙ ዘመን ሲኖሩ የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ይለመኑት ነበር፡፡ ልዑል እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ የተባረከ ልጅ እንደሚወልዱ አበሰራቸው፡፡ አባ አብርሃምም በመልአኩ ብሥራት ግንቦት ሃያ አራት ቀን በተወለዱ ጊዜ ወላጆቻቸው ብርሃነ መስቀል ብለው ጠሩት፡፡ በኋላ የተጠራበት ስመ ጥምቀቱ ግን ማኅፀንተ ሚካኤል ነው፡፡ ወላጆቹም በመንፈሳዊ አስተዳደግ ስላሳደጉት ከልደቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር አደረበት፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አደገ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያንም መሄድን አላስታጎለም፡፡ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል ከታናሽነቱ ጀምሮ በእግዚአብሔር ቤት አድጓልና፡፡
አድጎ ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን፣ መጻሕፍተ ነቢያትን፣ መዝሙረ ዳዊትን ይማር ዘንድ አባቱ ለመምህር ሰጠው፡፡ ሕፃኑም በትምህርቱ አስተዋይ ሆነ፡፡ ሳያቋርጥ ሁልጊዜ ከመምህሩ መረዳትን ያበዛ ነበር፡፡ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል የጸና ሆነ፡፡ ዲቁናም ከተሾመ፡፡
ከዚህም በኋላ እናቱና አባቱ ያለ ፈቃዱ ሚስት ያጩለት ዘንድ ወደዱ፡፡ በመጽሐፍ ‹‹የልጅ ልጅህን ታያለህ፣ አንተ ብፁዕ ነህ፣ መልካምም ይሆንልሃል›› የሚል በመጽሐፍ ተጽፏልና፡፡ ስለዚህም ያጋቡት ዘንድ አቻኮሉት፤ እርሱ ግን ዓለመን ፍጹም ንቆ በምንኩስና በተጋድሎ መኖርን ወደደ፡፡
ለምንኩስናም ስሙ አባ ክርስቶስ ይባርከነ ወደተባለ አንድ መነኩሴ ወዳለበት ገዳም ሲሄድ በመንገድ መደራ በተባለች ቦታ በታላቅ ገዳም ውስጥ ከእንግዶች ጋር አደረ፤ በሌሊት በነቃ ጊዜ አንድ ድኃ በዚያች ቤት ውስጥ አገኘ፤ የድኃውን ልብስ ወስዶ የእርሱን ልብስ ሰጥቶተ በሌሊት ወጥቶ መንገዱን ሔደ፡፡ በነጋም ጊዜ ያ ድኃ ያደረገለትን ለሰዎቹ ተናገረ፡፡ ‹‹በእንግዳ ማደሪያ ከእኔ ጋር አብሮ ያደረ አንድ ሰው እኔ የለበስሁትን ልብስ ወስዶ የእርሱን መልካም ልብስ ተወልኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹… የእግዚአብሔር ሰው ነውና መልካም ሥራ አደረገልህ አንተ ግን ሔደህ ስለ እርሱ ጸልይለት›› አሉት፡፡
አባ አብርሃም ግን ከአባ ክርስቶስ ይባርከነ ከቀድሞ ቤቱ በደረሰ ጊዜ በዚያም አላገኘውም፤ ውኃ ከሌለበት፤ ፀጥታ ከሰፈነበት ምድረ በዳም ሔደ፡፡ የፀሐይ ወቅት ነበረና በዚያ ሲመላለስ ሳለ ውኃ ጥም ያዘው፡፡ ያን ጊዜም በገዳሙ ውስጥ ባዶ ወጭት አገኘና በፊቱ አስቀምጦ ወደ እግዚአብሔር በጸለየ ጊዜ ወዲያው ብዙ ዝናም ዘነመ፤ በወጭቷም አጠራቀመና እስኪበቃው ድረስ ከእርሷ ጠጣ፡፡ ከዚያም አባታችን ክርስቶስ ይባርከነን አገኘውና ሊያደርግ የሚፈልጋቸውን ምሥጢሩን ሁሉ ነገረው፡፡
የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አባታችንን ‹‹…በደመና ተጭነህ ወደ ዳሞት አገር ሂድ›› አለው፤ አባታችንም በደመና ተጭኖ ፍራጽ ከተባለ ገዳም ደረሰ፤ በዚያም ምድርን ባረኮ ውሃ አፈለቀ፤ መልአኩም ወደ ቀኝህ ተመልከት አለው፡፡ ወደ ቀኙ ሲያይ ዐደልን ብርሃን ከቧት ተመለከተ፤ ዕፅዋትም ጭፍቅ ያሉ ነበሩ፤ አባ ዘግሩምም ይህች ቦታየ ናት አለ፤ የጻሕናንን ምድር እየባረከም ይሄድ ዘንድ ወደደ፡፡ ብዙ ውሃ አፈለቀ፤ ዐደልም ደረሰ፤ በዚያም ውሃ አፈለቀ፤ አባታችን ዘግሩም ወደ ውስጧ ገባ በዚያም ተቀመጠ፣ የገዳሙ አራዊትም በዚህ ተደሰቱ፡፡ ሙሴ ጽላትን እንደተቀበለ ሁሉ ጥቅምት ሃያ አራት ቀን የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ አመጥቶ የብርሃን መስቀልና የመድኃኔዓለምን ታቦት ሰጠው፡፡ ዳግመኛም የእግዚአብሔር መልአክ የተዘጋጀ ኅብስትና የተቀዳ ጽዋን፤ ለመሥዋዕት የሚሆነውንም ሁሉ ሰጠው፤ አባታችንም ከካህናት ጋር በዚያች ቤተ ክርስቲያን ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን ሰጣቸው፡፡
በቤተ ክርስቲያን አጠገብ አንዲት የዋንዛ ዛፍ ነበረች፤ ሕዝቡም ይሰበሰቡባትና በሥሯ ተቀምጠው ክፉ ሥራ ይሠሩ ነበር፤ አባታችንም ‹‹ለምን እንዲህ የማይገባ ሥራ ትሠራላችሁ? ሲላቸው እነርሱ ግን አልሰሙም፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችንም ያቺን ዛፍ ‹‹ከበታችሽ ካሉት ሕዝብ ጋር ተነሥተሽ ሒጂ›› ብሎ በቃሉ አዘዛት፡፡ ያን ጊዜም ያች ዛፍ ከሕዝቡ ጋር ተነሥታ የሁለት ጦር ውርወራ ያህል ሔደች፡፡ ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ ‹‹የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ቢኖራችሁና ይችን ሾላ ተነስተሽ ወደዚህ ነይ ብትሏት ትመጣለች፤ ይህን ተራራ ከዚህ ሂድ ብትሉት ይሄዳል›› እንዳለ አባታችን አባ ዘግሩምም ይህንን አደረጉ፡፡
ከአባታችን ይባረኩ፤ እጅ ይነሡም ዘንድ አርባ አራት ቅዱሳን በደመና ተጭነው አባታችን ካለበት ቦታ ወደ ዐደል መጡ፡፡ ሶምሶን ከአህያ መንጋጋ፤ ሙሴ ከዐለት ውሃ እንዳፈለቁ ሁሉ ለሚያስፈልጋቸው ነገር ይጠቀሙበት ዘንድ አባታችንም በጸሎቱ በአንድ ጊዜ አርባ አራት የውሃ ምንጮችን አፍልቆ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ይህን አይተው አደነቁ፤ ስምህ ዘግሩም ይሁን አሉት፤ ስለዚህም አባታችን አባ ዘግሩም ተባለ፤ ምንጮቹም ድውያንንና ሕሙማንን የሚፈውሱ ሆኑ፡፡
ዳግመኛም ለአባታችን የሚገለገልበት አንድ አህያ ነበረው፤ የሚጭነው ሰው ሳይከተለው ለሁለት ቀናት ሔዶ ወደ ጫነው ሰው ቤት ይመለስ ነበር፤ የአገሩ ሰዎችም ይህን አይተው ያላቸውን ሁሉ ይጭኑትና ብቻውን ሔዶ ወደ አባታችን ይመለስ ነበር፡፡
የአቡነ ብርሃነ መስቀልን ተአምራቱን ዜናውን በሰማ ጊዜ ከንጉሡ ባለሟሎች አንዱ መጣ፡፡ ሌላም በቤቱ አጠገብ የሚኖር አንድ ሰው መጣና ‹‹ጨው ጭኜ ወደ ገበያ እወስድበት ዘንድ አህያህን ስጠኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ የተቸገሩትን ለመርዳት የሚልከው አንድ አህያ ነበረውና አባ አብርሃምም ‹‹የጨው መጠን ምን ያህል ነው?›› አለው፡፡ ያ ሰውም ‹‹በሰቅል ስሳ ይሆናል›› አለው፡፡ አባታችን አብርሃምም ‹‹ውሰደው ከተናገርኸው በላይ ግን አትጫነው›› አለው፡፡ ሰውየውም አህያውን ወስዶ አባታችን እንዳለው ጫነው፤ ለአባታችን ያልነገረውን በቤቱ የተረፈውን ግን ያ ሰውና ወንድሙ ተሸከሙት፡፡
እነርሱም ተካፍለው ተሸክመው መንገዳቸውን እየሄዱ ሳለ ከአገር ብዙ በራቁ ጊዜ ወንድሙን ‹‹ና አህያውን እንጫነውና እንደፈቀድነው እንሒድ የሚያየን የለምና›› አለው፡፡ በዚሀመ ምክራቸው መሠረት ተሸክመውት የነበረውነ በአህያው ላይ ጫኑት፡፡ ነገረ ግን አህያው መንቀሳቀስን ፈጽሞ እምቢ አለ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ ሲገፉትና ሲደበድቡት ብዙ ደከሙ፤ እንዲህ እያደረጉ ሳሉ አንድ አገልጋይ የንጉሥ መልእክት ይዞ መጣ፡፡ እኒህን ስሕተተኞችም አገኛቸውና ‹‹ጌቶቼ ለምን ትደክማላችሁ?›› አላቸው፡፡
እነርሱም ‹‹ይህ አህያ አልሄድም አለን›› አሉት፤ የንጉሡ መልእክተኛም መንፈስ ቅዱስ አነሳሳውና ከፊታቸው ቆመና ‹‹የዚህ ነገር ምክንያቱ ምንድን ነው?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ይህን አህያ ከአንድ መንፈስ ቅዱስ ካደረበት ቀሲስ አመጣነው፤ በዚህ ቀሲስ ቃል ላይ በጨመርን ጊዜ መሔድን እምቢ አለን›› በማለት የሠሩትን ነገሩት፡፡ ‹‹እስኪ የጨመራችሁትን ቀንሱለት›› አላቸው፤ ቀነሱለትና ያን ጊዜ አህያው ተነሥቶ እነርሱም ወደሚፈልጉበት ቦታ ሔዱ፡፡ ይህንንም ሁለት ጊዜ ሦስት ጊዜ ደጋግመው አደረጉ እምቢም አላቸው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የቅዱሱን ቃል በመተላለፋቸው እንደሆነ አወቁ፤ ያም የንጉሡ አገልጋይ ተደንቆ ‹‹ኑ ይህ ቅዱስ ካለበት አድርሱኝ›› አላቸው፡፡ አባታችን ካለበት ቦታም ደርሶ ከእርሱ ዘንድ ተባረከ፡፡
ያም አህያውን የወሰደው ሰው ከአቡነ ብርሃነ መስቀል እግር ሥር ተንበርክኮ ‹‹በፊትህ በድያለሁና ቃልህንም አሳብያለሁና አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ፤ አህያውም መሄድን እምቢ አለ፤ የጨመርንበትን ሸክም በቀነስንለት ጊዜ ግን ይሄዳል›› አለው፡፡ ዳግመኛም ‹‹…እኔ ግን እንደ እኔ አይነት ሰው ነህ መስሎኝ ቃልህን አፈረስሁ፤ አንተ ግን በፍቅርህ ገመድ ሳብኸኝ›› አለው፡፡ አባታችን ብርሃነ መስቀልም ‹‹ለምን ሐሰት ተናገርህ? መጽሐፍ ‹ሐሰት የኀጢአት መጀመሪያ ናት፤ ሐሰተኞችም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም› ይል የለምን?›› በማለት ከመከረው በኋላ በሰላም ወደቤቱ እንዲሔድ ነገረው፡፡
ያም ሰው ከአቡነ ብርሃነ መስቀል ዘንድ ወጥቶ መንገዱን ሔደ፤ ያ የንጉሡ መልእክተኛም አብርሃም ከተባለ ከአቡነ ዘግሩም ዘንድ ተባርኮ ወጣ፤ የቤተ ክርስቲያኗንም አሠራር አይቶ የአባታችን የአብርሃምን ተአምር አደነቀ፤ የንጉሡን ትእዛዝ ይፈጽም ዘንድም መንገዱን ሄደ፡፡ ከብዙ ቀናት በኋላ ያ መልእክተኛ ከንጉሡ ዘንድ ደረሰ፤ ስመ መንግሥቱ ቆስጠንጢኖስ ለተባለ የእግዚአብሔር ወዳጅ ለሆነ ለንጉሥ ዳዊት ነገሩን ነገረው፡፡ ‹‹ጻድቅ ንጹሕ የሆነ ቀሲስ አለ፤ በዚህ ዘመን በመንግሥትህ ሀገር ሁሉ እንደርሱ ያለ ሰው የለም፤ ሥራው ሁሉ እንደቀደሙት አባቶች ነውና›› አለው፡፡
በዐይኑ ያየውን፤ በጆሮው የሰማውን ሁሉ ስለሠራት ቤተ ክርስቲያንም ነገረው፤ ንጉሡም ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በልቡ ተደሰተ፤ በመንፈሱም ሐሴትን አደረገ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነው፤ እንዲህም አለ፡- ‹‹በዘመነ መንግሥቴ የተሰወረውን የሚያውቅ፤ ተአምራትን የሚያደርግ እንዲህ ያለ ጻድቅ ሰውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ስሙ ይክበር፡፡ አባቴ ቤተ ክርስቲያን ማነጽ በፈለግህ ጊዜ ወደ እኔ ለምን አልላክህም ብሎ ላከበት፤እኔ ከደቀ መዛሙርትህ እንደ አንዱ አይደለሁምን በረከትህን በተቀበልሁ ነበር አለ፡፡ በዚህ የመንግሥት ዙፋን ላይ ያለሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው እንጂ በራሴ ፈቃድ ይመስልሃልን በእስረኞች መካከል ሳለሁ ከእስረኞች መካከልም ተኝቼ ሳለ ከዚያ አውጥቶ በአባቶቼ በሰይፈ አርዕድና በዐምደ ጽዮን ዙፋን ላይ አስቀመጠኝ፡፡ አንተ ግን በኀጢአቴ አትናቀኝ፤ ለቤተ ክርስቲያን የምትፈልገውን ይህን ገንዘብ ውሰድ፡፡›› ዳግመኛም ለአባታችን ልብስ ላከለት፤ ሚስቱም እንዲሁ ላከች ‹‹በጸሎትህ አትርሳን›› አሉት፡፡
ከዚህም በኋላ ይመነኩስ ዘንድ ወደደ፤ የመላእክትና የቅዱሳን ልብስ የምትሆን የምንኩስና ልብስን ያለብሰው ዘንድ የአቡነገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድእ ወደ ሆነው ወደ አባ ብሶይ መጣ፡፡ ወደ እርሱ ደርሶ ሥርዐተ ምንኩስና ከፈጸመለት በኋላ አባታችን አብርሃም ‹‹የቀድሞ ስሜን ተውልኝ›› አለው፤ አባ ብሶይም ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን ስም እንደ ለወጠላቸው ስምህን እለውጣለሁ እንጂ አይሆንም›› አለው፡፡ ‹‹ስምህንም አብርሃም፣ ጳውሎስ፣ ዮሐንስ ከሚሉት መካከል ዕጣ በማጣጣል እሰይምሃለሁ›› አለው፡፡
ሦስት ጊዜም ዕጣ ጣሉ፤ አብርሃም የሚለውም ስም ወጣ፤ ይህ ነገር ከእግዚአብሔር እንደሆነ አወቀ፡፡ከታናሽነቱ ጀምሮ የአብርሃም ምግባር የሆነውን እንግዳ መቀበልን፣ እግር ማጠብንና የተራበውን ማብላት ጀመረ፤ ስለዚህ አብርሃም መባል ተገባው፡፡ ‹‹ከታናሽነቴ ጀምሮ የአብርሃምን ሃይማኖት እንደወደድሁ፣ እንግዳ በመቀበል እንደ ኖርሁ ይህን ስም የሰጠኝ እግዚአብሔር ይመስገን›› አለ፡፡ መንኩሶ በፈቃዱ አብርሃም ተብሎ ተጠርቷልና በብዙ ገድልና በትሕርምት በዚያች ቦታ ኖረ፡፡
የነዳያን ፍቅር በልቡ ውስጥ አለ፤ ሁል ጊዜ ስለ ምግባቸውና ስለ ልብሳቸው ያስብ ነበር፤ ለሚያስፈልጋቸው ነገርም ገንዘብ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ለድኆች ልብሱን ያካፍላል፤ ለእነርሱም ሰጥቶ እርሱ ራቁቱን ይቆማል፤ ልጆቹም ይመጣሉ፤ ‹‹ልብስህ ወዴት ነው?›› ይሉት ነበር፤ እርሱም ‹‹ሌቦች በማያገኙበት ቦታ አለ›› ይላቸው ነበር፡፡ ልጆቹ ግን ሥራውን አያውቁም ነበር፤ ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንበት ሁሉን ይሠውር ነበር፤ አይገልጥላቸውም ነበር፤ ድኃ ባየ ጊዜ አጽፉን ይሰጥ ነበር፤ አጽፉን ይቅርና ምንም ልብስ አያስቀርም ነበር፡፡
አንድ ቀን አንድ ድኃ መጥቶ ስለ እግዚአብሔር ስም ምግብና ልብስ ለመነው፡፡ አባታችን ያን ድኃ ባየው ጊዜ አጽፉን ሰጠው፤ ዳግመኛ አንድ ድኃ መጣ፤ በቤቱም የሚሰጠውን አጣ፤ መጠምጠሚያውን አውርዶ እርሷንም ለድኃው ሰጠውና በቤቱ ተቀመጠ፡፡ አንድ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ መጥቶ ራቁቱን አገኘውና ተቆጣበት፤ ‹‹ክቡር አባቴ ሆይ! ለምን እንዲህ ትሆናለህ? አለው፡፡ ‹‹ለምትበላውና ለምትለብሰው ሳታስቀር ያለ አቅምህ ለምን ምጽዋት ትሰጣለህ? ልብስህንና መጎናጸፊያህን ሰጥተህ አንተ ራቁትህን ትሆናለህ፡፡›› አባታችንም ‹‹ልጄ ሆይ! ፈጽሞ ስለሚያረጅና ስለሚጠፋ የዚህ ዓለም ልብስ ፈንታ የብርሃን መጎናጸፊያ የሚያለብሰኝ አምላኬ አለልኝ›› አለ፤ ልጆቹም ሌላም ልብስ አምጥተው አለበሱ፡፡ ‹‹ይህንም እንደ ቀደመው አታድርግ›› አሉት፤ እርሱ ግን ስለ ድኆችና ስለ ችግረኞች ፍቅር ብዙ ጊዜ ምጽዋት ያደርግ ነበር፤ ቅብዓት በሰውነት፣ ውሃ በአንጀት እንዲገባ የነዳያን ፍቅር ወደ ልቡ ገባ፡፡
የነዳያንን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ከልቡ ደስታ የተነሣ ለመነሣት ይፈልጋል፤ ከማእድ ላይ ቢሆንም እንኳን ድምፃቸውን ከሰማ እጁን ወደ ማእድ አያወርድም ነበር፤ ይሰጣል እንጂ ምንም ነገር አያተርፍም ነበር፡፡ ነዳያን ግን ዘወትር ጩኸትና ልመናን አያቋርጡም ነበር፤ አባታችን ስለ ምግባቸውና ስለ ልብሳቸው እንደሚያስብ አውቀው ከቤቱ አይርቁም ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ አንዲት ታላቅ ሀገር ሔዶ ከዚያ ደረሰ፤ በሰንበት ምሽት ለእሑድ አጥቢያ ከዚያ አደረ፤ ሥርዓተ ቁርባን ከተፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሩን ‹‹ልጄ የምንበላው ነገር አለህ ወይስ የለህም?›› አለው፤ ያ ደቀ መዝሙርም ‹‹አባቴ አዎን አለኝ›› አለው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ያያቸውን ታላላቅ መነኮሳት ሰበሰበ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መምህራን ነበሩ፡፡ የተዘጋጀ ምግብና ጠላ ያን ጊዜ እነርሱም ከቤታቸው እንጀራ አመጡ፤ ሁለት ያመጣ አለ፤ ሦስትም ያመጣ አለ፤ ሁላቸውም እንደ አቅማቸው አመጡ፤ አባታችንም ጸሎት ያደርግ ዘንድ ተነሣ፤ ባረከላቸውም፡፡
ደቀ መዝሙሩንም ‹‹ጠላውን አምጣው›› አለው፤ ሁለት መነኮሳትም እንሥራውን አመጡት፤ ከመካከላቸው አንዱን ጠጣ አለው፤ ቀምሶም ለአባታችን ሰጠው፤ ጣዕሙ ደስ ባሰኘው ጊዜ አባታችን ከሩቅ ሀገር የመጡ የተራቡ ሰዎች ከቤቱ ደጃፍ እንዳሉ አወቀ፡፡ መነኮሳቱንም ‹‹አባቶቼ፣ ወንድሞቼና ልጆቼ ፈቃዳችሁ ከሆነስ ለክርስቶስ እንሰጠው ዘንድ ለነዳያንና ለችግረኞች እንስጣቸው›› አላቸው፡፡
በቤተ ክርስቲያን የተሰበሰቡ ወንድሞች መነኮሳት፣ ክቡራን ካህናት፣ ዲያቆናትና ሕዝቡ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ፣ በወንጌል ወተት ያደገ፣ የእግዚአብሔር ሰው የሆነ የአባታችንን ትሕትና፣ ትሩፋትና ቅድስና ባዩ ጊዜ አዘኑበት፡፡ ምንም ቃል አልመለሱለትም፤ በቦታቸው ወይም በቤታቸው አልነበሩምና፤ በልባቸው ‹‹እኛስ ከሩቅ ሀገር የመጣን አይደለምን?›› አሉ፡፡ እነርሱ ግን ከዚያው ይኖሩ ነበር፤ አባታችን ግን ነዳያንን ሰብስቦ ያንን ምግብ ሰጣቸው፡፡
ወደ ቤቱ ተጠርተው የመጡ እነዚያ መነኮሳትም አንዲት ቃል አልተናገሩም፤ ነገር ግን በልባቸው ተቆጡ፤ በጣምም አዘኑ፤ አባታችን ግን ደቀ መዛሙርቱን ሌላ ማእድ ያቀርቡ ዘንድ አዘዘ፤ ከመንገድ ስንቅ ይመገቡ ነበርና ጥቂት አመጡ፡፡ ገና ሳይቀምሱም ከሕዝብ አንዱ ‹‹አባቴ ሆይ! ጸልይልኝ፤ ይህን ጥቂት በረከትም ተቀበል›› ብሎ ብዙ ጠላ ላከ፤ እነዚህ መነኮሳት ግን ይህን ባዩ ጊዜ ፈጽመው ተደነቁ፤ ፈጽመው ፈሩ፤ ተንቀጠቀጡም፡፡ አባታችንም ተነሥቶ ለክርስቶስ ሰጠሁት፤ ለተራቡትም አስቀደምሁ፤ ለድኆች የሚሰጥ ለእግዚአብሔር ያበድራል የሚል ተጽፏልና አላቸው፡፡
እነዚህ መነኮሳትም ‹‹አባታችን መምህራችን ሆይ! ይቅር በለን አንተ ብዙ ሐዘንን ታውቃለህና፤ እኛ ስለሆዳችንና ስለልብሳችን አዘንን፤ አንተ ግን እንደ ጌታህ ክርስቶስ የድኆችና የችግረኞች ወዳጅ ነህና›› አሉት፡፡ ‹‹አላወቅንምና አባታችን ይቅር በለን፤ አንተ ፈቃደ እግዚአብሔርን ትፈጽማለህ፤ እርሱም ልመናህን ይሰማልና›› አሉት፡፡ ‹‹እንዲሰጥህ አላወቅንም፤ ነገር ግን ጎተራህን ሁሉ እንደሚሞላልህ ሰምተን ነበር፤ የተዘጋጀ ምግብንም እንዳወረደልህ ሰምተን ረሳን፤ አሁንም አባታችን ይቅር በለን፤ ባንተ ላይ ተቆጥተን ነበር፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንደሆነ አላወቅንም፤ አንተ ግን አስቀድመህ ለተራቡት ሰጠህ፤ ቀጥሎም ከአምላክህ በረከት ለእኛ ለመብላት ለተዘጋጀን ሰጠኸን›› አሉት፡፡ አባታችን ዘግሩምም ‹‹ወንድሞቼና ልጆቼ ይህን የማደርገው ለሰው ልታይ ብዬ አይደለም፤ ለትምክህትም አይደለም፤ እግዚአብሔር የሰጠኝ ሀብት ነው እንጂ›› አላቸው፡፡ ‹‹እኔ እሰጣለሁ፤ እርሱም የሚያስፈልገኝን ነገር አላሳጣኝም›› አላቸው፤ እነርሱም ከእርሱ ተባረኩ፤ ከዚህም በኋላ ታላላቅ ተአምራትና ድንቅ ነገርን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን ገናናነት ተነጋገሩ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀንም አባ ዘግሩም ቆሞ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጣ፤ ቅድስት የሆነች የጎኑን መወጋትና ቁስሎቹን ሁሉ አሳየው፡፡ በደሙ መፍሰስም ተደሰተ፤ ሰግዶም እንዲህ አለ፤ ‹‹ጌታየ የሚፈሰውን ደምህን እዳስስ ዘንድ ፍቀድልኝ›› አለው፤ ጌታችንም ቅዱስ የሆነ ደሙን ይዳስስ ዘንድ ፈቀደለት፤ እንደ ቶማስም ጎኑን ዳሰሰ፤ ቶማስስ ደቀ መዛሙርቱን ስላላመነ ነበር፤ ይህ አባታችን ግን ጌታችን ‹‹ሳያዩኝ የሚያምኑኝ ብፁዓን ናቸው›› ብሎ እንደተናገረው ሳያይ ያመነ ነው፡፡ ይህ አባታችን ግን ሳያይ አመነ፤ በቅዱስ ደሙ መፍሰስም ደስ አለው፤ ወንድሞቼ ሆይ ለአባታችን የተሰጠውን ጸጋ ተመልከቱ፤ የመድኃኒታችንን ቁስሎች ዳስሷልና፤ ለድኆች የማዘን ፍሬው ይህ ነው፤ ‹‹ለድኆች የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል›› ተብሏልና፡፡
ለሰው ልጅ የሚሰጥ ታላቅ ጸጋን አገኘ፤ ከሀገሮች ሲመለስም ወደ ደብረ ጽዮን ለመሄድ ግባ ከተባለ ታላቅ ወንዝ ደረሰ፤ ከፈሳሹ ብዛት የተነሣ ስትበረታታ አገኛት፡፡ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ የሚያደርጉትንም አጡ፤ ብፁዕ አባታችን ግን ከወንዙ ዳር ቆመ፤ በምርጉዙም በባሕሩ ላይ አማተበ፤ ያን ጊዜ ወንዙ ወዲያና ወዲህ ተከፈለ፤ በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተሻገሩ፡፡ ነቢዩ ሙሴ የኤርትራን ባሕር በከፈላት ሕዝቡንም በመራ ጊዜ እንደ ተሻገሩ ሁሉ ተሻግረዋልና እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ይህም አባታችን ባሕርን በየብስ አሻገራቸው፤ ከዚህ በኋላ በሰላም ወደ ቤቱ ደረሰ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment