ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 7 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, November 16, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 7

 ኅዳር 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት (ቅዳሴ ቤቱ)
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ እስክንድርያዊ
3.ቅዱሳን ዘኖቢስና ዘኖብያ (ሰማዕታት)
4.ቅዱስ ሚናስ ዘተመይ
5.ቅዱሳን መርቆሬዎስና ዮሐንስ (ጻድቃን ወሰማዕት)
6.አባ ናሕርው ሰማዕት

ወርሐዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ሰባት በዚህችም ቀን የቅዱስ_ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕት ቅዳሴ ቤቱ፣ ከእስክንድርያ አገር የሆነ ቅዱስ_ጊዮርጊስ በሰማዕትነት አረፈ፣ አቡነ_ገብረ_እንድርያስ_ዘወለቃ የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው፣ አባ_ናህርው በሰማዕትነት አረፈ፣ የአባ_ሚናስ_ዘተመይ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ ቅዱሳን_ዘኖቢስ እና እናቱ ቅድስት_ዘኖብያ እንዲሁም ቅዱስ_ሐዲስ_መርቆሬዎስ እና ወንድሙ ቅዱስ_ዮሐንስ በሰማዕትነት አረፉ።


ኅዳር ሰባት በዚህችም ቀን የልዳ ሀገር የሆነ የሰማዕታት አለቃ የታላቁ መስተጋድል የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው ዳግመኛም ጌታችን በውስጧ ላደረገው ድንቅ ተአምር መታሰቢያ ሆነ።
ይህም እንዲህ ነው በውስጧ ድንቆች ተአምራት እንደሚሠሩ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ሊአፈርሳት አሰበ ስሙ አውህዮስ የሚባለውንም መኰንን ከብዙ ሠራዊት ጋር ላከው፤ ያም መኰንን በደረሰ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ወዳለበት አዳራሽ በትዕቢት ሆኖ ገባ። በሥዕሉም ፊት በብርጭቆ መቅረዝ መብራት ነበረ በቤተ ክርስቲያኒቱና በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ እየዘበተ በእጁ በያዘው በትር የመብራቱን መቅረዝ መትቶ ሰበረው የመቅረዙም ስባሪ ወደ ከሀዱው ራስ ደርሶ መታው ራሱንም ታመመ ፍርሃትና እንቅጥቅጥም መጣበት ወድቆም ተዘረረ ባልንጀሮቹም ወደ አገሩ ሊወስዱት ተሸከሙት በክፉ አሟሟትም ተጐሳቊሎ ሞተ ወስደውም ከባሕር ጣሉት ወገኖቹም ወደ ሀገራቸው አፍረው ተመለሱ።
ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ በልዳ ሀገር ያለች የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን ያፈርሳት ዘንድ ራሱ ተነሥቶ ሔደ በዚያንም ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መታው ሰባት ዓመት ያህልም ዐይኖቹ ታውረው አእምሮውንም አጥቶ ቁራሽ እንጀራም እየለመነ ኑሮ ሞተ።
ክብር ይግባውና ጌታችንም የቤተ መንግሥቱን ሰዎች አስነሣበት እርሱን አስወግደው ጻድቅ ሰው ቁስጠንጢኖስን በእግዚአብሔር ፈቃድ አነገሡት እርሱም በአዋጅ የጣዖታትን ቤቶች ዘግቶ አብያተ ክርስቲያናትን ከፈተ ለክርስቲያን ወገኖችም በሁሉ ዓለም ተድላ ደስታ ሆነ።

በዚህች ቀን የእስክንድርያ አገር የሆነ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰማዕትነት አረፈ።
የዚህም ቅዱስ አባቱ በእስክንድርያ አገር በንግድ ሥራ የሚኖር ነው ልጅም አልነበረውም የልዳዊው ቅዱስ ጊዮርጊስም ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት የበዓልዋ መታሰቢያ ኅዳር ሰባት በደረሰ ጊዜ ልጅን ይሰጠው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲማልድለት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመነው ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ ይህን ልጅ ሰጠው ስሙንም በታላቁ ሰማዕት ስም ጊዮርጊስ ብሎ ስም አወጣለት።
የዚህም ልጅ እናቱ ለእስክንድርያ አስተዳዳሪ ለአርማንዮስ እኅቱ ናት ከዚህም በኋላ እናትና አባቱ አረፉ እርሱም ከእናቱ ወንድም ዘንድ ተቀመጠ ሃያ አምስት ዓመትም በሆነው ጊዜ በጎ ሥራ የሚሠራ ሆነ ድኆችን እጅግ ይረዳቸው ይወዳቸውም ነበረ የሚራራና የሚመጸውት ሆነ ወደ ቤተክርስቲያን መገሥገሥንም ይወዳል። ለመኰንን አርማንዮስም አንዲት ብቻዋን ሴት ልጅ አለችው ቦታዎችንም በመጐብኘት ደስ ይላት ዘንድ ከባልንጀሮቿ ጋር ወጣች ወደ ደብረ ቊስቋምም ስትደርስ ጣዕም ባለው ድምጽ በመዘመር ሲያመሰግኑ የተሰበሰቡ መነኰሳትን አገኘቻቸው ምስጋናቸውና መዝሙራቸውም ወደ ልቡዋ ገብቶ ተቀረጸ።
የአባቷ እኅት ልጅ የሆነ ጊዮርጊስንም መነኰሳቱ ስለሚዘምሩት ያስረዳት ዘንድ ጠየቀችው እርሱም ወደማይጠፋ ዕረፍትና ተድላ እንደሚያደርሳቸው ትርጓሜውንና ጥቅሙን ሊያስረዳትና ሊያስገነዝባት ጀመረ።
ወደ አባቷም አርማንዮስ በተመለሰች ጊዜ በፊቱ ቁማ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነች አባቷም ሊሸነግላት ጀመረ ልጄ ሆይ ይህን አታድርጊ አላት ነገሩን ባልተቀበለች ጊዜ ራሷን በሰይፍ አስቆረጠ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች።
ከዚህም በኋላ ልጅህን ያሳታት የእኅትህ ልጅ ጊዮርጊስ ነው ብለው ለመኰንኑ ነገሩት እርሱም ሰምቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይዞ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ጭካኔውንም አይቶ ወደ ሀገረ እንጽና ሰደደው በዚያም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃይተው ቅድስት ራሱን በሰይፍ ቆረጡ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ።
በዚያም ሳሙኤል የሚባል ዲያቆን ነበር የቅዱስ ጊዮርጊስንም ሥጋ አንሥቶ ወደ ሀገረ መኑፍ ወሰደው። የአርማንዮስም ሚስት በአወቀች ጊዜ መልእክተኞችን ልካ አስመጣችው ከልጅዋም ሥጋ ጋር በአንድነት በእስክንድርያ አገር አደረገችው።

ዳግመኛም በዚህች ቀን አቡነ ገብረ እንድርያስ ዘወለቃ የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው። የትውልድ ሀገራቸው ወሎ ቦረና ጋስጫ ነው፡፡ አባታቸው ተንሥአ ክርስቶስ እናታቸው አርሴማ ይባላሉ፡፡ ሁለቱም ደጋግ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ለመምህር ሰጧቸው፡፡ መምህሩም ጸጋ እግዚአብሔር እንዳደረባቸው ዐውቀው ‹‹ብዙዎችን የምታድን ጻድቅ ትሆናለህ›› ብለው ትንቢት ነግረዋቸዋል፡፡ የመጻሕፍትንም ትርጓሜ በሚገባ ካስተማሯቸው በኋላ ንፍታሌም ይባል የነበረውን ስማቸውን ለውጠው ገብረ እንድርያስ አሏቸው፡፡
ጻድቁ በአቡነ ዮሐንስ ከማ ገዳም ለረጅም ጊዜ በታላቅ ተጋድሎ አገልግለዋል፡፡ አባታችን ሙታንን በማስነሣትና ድውያንን በመፈወስ ብዙ ተአምራትን ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ ብዙ አባቶች ሱባኤ ይይዙበት በነበረው በሰኮሩ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጸሎት ሲያደርጉ ቅዱስ ዑራኤል በወርቅ ጽዋ ሰማያዊ ወይንና ኅብስት መግቧቸዋል፡፡ እመቤታችንም ሦስት ጽዋ ማየ ሕይወት ሰጥታቸው በእርሱ ብዙ ሕሙማንን ፈውሰውበታል፡፡
ጻድቁ በስማቸው የፈለቀው ጸበል እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ጸበሉ ውስጥ እንጨት ሲነከርበት እንጨቱ በተአምራት ነጭ መቁጠሪያ
ሆኖ ይወጣል፡፡ ይህም እስከዛሬ ድረስ በግልጽ ይታያል፡፡ ጸበሉ ውስጥ ማታ የነከሩትን እንጨት ጠዋት ላይ መቁጠሪያ ሆኖ ያገኙታል፡፡ እጅግ አስገራሚ ነው በእውነት! መቁጠሪያውም ለእንቅርትና ለልዩ ልዩ ሕመሞች መድኃኒት ነው፡፡ ነገር ግን ጸበሉ ያለበት አካባቢው በመርዛማና አደገኛ እባቦች የተሞላ ነው፡፡ ሆኖም ግን እባቦቹ የጻድቁ ግዝት ስላለባቸው በገዳሙ ውስጥ ብቻ ማንንም አይነኩም፡፡ ጸበሉ ደግሞ የሚገኘው ከገዳሙ የአንድ ሰዓት ተኩል መንገድ ርቀት ላይ ነው፡፡
አባታችን እግዚአብሔር ኃጥአንን እንድምርላቸው ጣቀት ወንዝ ከተባለው ቦታ በአንገታቸው ላይ በጣም ትልቅ ድንጋይ እየተሸከሙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በዚህ ይጸልዩበት ከነበረው ወንዝ ውስጥ ነው በተዓምራት መቁጠሪያ የሚሠራው ጸበል የፈለቀላቸው፡፡ ደቡብ ወሎ ወግዲ ወረዳ የሚገኘው አቡነ ገብረ እንድርያስ ገዳም ከአባ ጽጌ ድንግል ገዳም በእግር የ3 ሰዓት መንገድ ያስኬዳል፡፡
ጻድቁ አቡነ ገብረ እንድርያስ ዓርብ ዓርብ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ወደ ኢየሩሳሌም ይመላለሱ የነበረው በትልቅ ድንጋይ ላይ እንደ ደመና ተጭነው ነበር፡፡
ጻድቁ በአየር ላይ ሲጓዙ ድንጋዩን እንደ ሠረገላ ዋርካውን እንደ ጥላ ይጠቀሙበት ነበረ፡፡ ያ እንደ ሠረገላ ሆኖ ያገለግላቸው የነበረው ትልቅ ድንጋይ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው ውስጥ ይገኛል፡፡ ታሪኩም በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡

በዚህችም ቀን ዳግመኛ ከግብፅ አገር ከፍዩም መንደር አባ ናህርው በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ እግዚአብሔርን እጅግ የሚፈራው ነው በእስክንድርያ ሀገር የሚሠቃዩ የሰማዕታትን ዜና በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ስሙ ሊሞት ወደደ በራእይም ወደ አንጾኪያ ሀገር ሒደህ በዚያ ትሞት ዘንድ አለህ አለው።
ወደዚያ መድረስ እንዴት ይቻለኛል በማለት የሚያስብ ሆነ ሊሳፈርም መርከብን ፈለገ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር መልአኩን ቅዱስ ሚካኤልን ላከለት በክንፎቹም ተሸክሞ ወደ አንጾኪያ ሀገር አደረሰው።
በዲዮቅልጥያኖስም ፊት ቀርቦ በእግዚአብሔር ታመነ ንጉሡም ስሙንና አገሩን ጠየቀው እርሱም ከግብጽ አገር እንደሆነ አስረዳው ንጉሡም ቃሉን ሰምቶ ለጣዖታቱ ቢሠዋለት ብዙ ገንዘብና የግምጃ ልብሶችን ሊሰጠው ማለለት እርሱ ግን ቃሉን አልሰማም ንጉሱም እኔ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይሃለሁ የሚል ቃልን ደግሞ ተናገረው ከሥቃዩም የተነሳ አልፈራም ትእዛዙንም አልሰማም።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ናህርውን በብዙ አይነት ስቃይ እንዲአሰቃዩት ንጉሱ አዘዘ አንድ ጊዜ ለአንበሶች ጣሉት አልነኩትም አንድ ጊዜ ከእሳት ጨመሩት አልተቃጠለም ሌላ ጊዜም በወጭት ቀቀሉት ከማሠቃየትም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ ንጉሡ አዘዘ።
ይህ አባ ናህርውም በግብጽ አገር በሰማዕትነት ስለሞቱ ስለ አንጾኪያ አገር ሰማዕታት ፈንታ በአንጾኪያ አገር በሰማዕትነት አረፈ።

በዚህችም ቀን ከገምኑዲ አውራጃ የሀገረ ተመይ ኤጲስቆጶስ የአባ ሚናስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ደጎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ዜናቸውም በቅዱሳን አባቶች ዘንድ እስከ ተሰማ ድረስ በጾማቸው በጸሎታቸው በገድል በመጸመዳቸው የመነኰሳትን ሥራ የሚሠሩ ናቸው።
እነርሱም ያለ ፈቃዱ ልጃቸውን ሚስትን አጋቡት ሙሽራዪቱም ወዳለችበት የጫጒላ ቤት ገባ ድንግልናቸውንም ሳያጠፉ ሥጋቸውን በንጽሕና ይጠብቁ ዘንድ ከእርሷ ጋር ተስማሙ ሁለቱም በበጎ ተጋድሎ እየተጋደሉ በአንድነት ኖሩ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚናስ የምንኲስና ልብስ ሊለብስ ወዶ ሚስቱን እንዲህ አላት በዓለም እያለን የምንኲስና ሥራ ልንሠራ ለእኛ አግባብ አይደለም እነርሱ ከልብሳቸው ውስጥ ማቅ በመልበስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተደረሱ መጻሕፍትን በማንበብና ለጸሎት በመትጋት ሌሊቱን ሁሉ ይቆሙ ነበርና ከዚህም በኋላ ሰላምታ ሰጥታ ሸኘችው አሰናበተችውም።
እርሱም ወደ አባ እንጦንዮስ ገዳም ሔደ ከወላጆቹ ሊርቅ ወዶአልና እነርሱ ወደ ሚስቱ ይመልሱት ዘንድ በንጉሥ ትእዛዝ በቦታ ሁሉ እየፈለጉት ነበርና እግዚአብሔር ሠውሮታልና ከቶ አላገኙትም በዚያም ገዳም በገድል ተጠምዶ ብዙ ጊዜ ኖረ በእስክንድርያም ሊቀ ጳጳሳት የሆነው አባ ሚካኤል ከእርሱ ጋር በምንኵስና ነበር።
ከዚህም በኋላ ሁለቱ ብሩሃን ከዋክብት አባ አብርሃምና አባ ገዓርጊ በነበሩበት ወራት ከነበረበት ወጥቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ። ይህ ቅዱስ አባ ሚናስም ተወዳጅ ልጅን ሆናቸው ከእርሳቸውም ዘንድ በበዓታቸው የሚኖርና የሚያገለግላቸው ሆነ የምንኲስናንም ሥራ ጨመረ ከእርሳቸውም ትምህርታቸውን ተጋድሏቸውን በመማር ከብዙዎች በተጋድሎውና በአምልኮቱ ከፍ ከፍ አለ አባ አብርሃምና አባ ገዓርጊ ሌሎችም አባቶች ከእርሱ ተጋድሎ የተነሣ ያደነቁ ነበር።
ሰይጣን ግን በእርሱ ቀንቶ በታላቅ አመታት እግሮቹን መታው ሁለት ወርም በምድር ላይ ወድቆ ኖረ ። ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋት በጤና አሥነሣው።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ መርጦ ጠራው የሊቀ ጳጳሳቱም መልእክተኞች ወደርሱ መጡ ከመነኰሳት የሚለይ በመሆኑ ታላቅ ኀዘንን አዘነ ቅዱሳን አባቶችም ይህ ሥራ ከእግዚአብሔር ነው አትዘን አሉት።
እርሱም ለእግዚአብሔር ትእዛዝ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከሊቀ ጳጳሱ መልክተኞች ጋር አብሮ ሔደ ሊቀ ጳጳሱም ተመይ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾመው ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት በሽተኞችን የሚፈውሳቸው ሆነ በሽታ ያለባቸውም ሁሉ ወደርሱ ይመጣሉ እርሱም ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ይፈውሳቸዋል።
ሁለተኛም የተሠወረውን የማወቅ ሀብተ ጸጋ እግዚአብሔር ሰጠው በሰው ልቡና የታሰበውንም የሚያውቅ ሆነ ኤጲስቆጶሳቱም ሁሉ ከየሀገሮቻቸው በመምጣት ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚታዘዙለትና ትምህርቱን የሚቀበሉ ሆኑ አሕዛብም ሁሉ ትምህርቱን ይሰሙ ዘንድ ይመጡ ነበር እርሱም ለአራት ሊቃነ ጳጳሳት አባት ሆነ። በሚሾሙ ጊዜ እጁን በላያቸው ጭኖአልና እሊህም በእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑ እለእስክንድሮስ፣ ቆዝሞስ፣ ቴዎድሮስ፣ ሚካኤል ናቸው።
ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ሊለየው በፈቀደ ጊዜ የሚለይበትን ቀን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ በሀገረ ስብከቱ ያሉትን ሕዝቡን ሁሉ ልኮ አስመጣቸው። በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ የከበረ የወንጌልንም ትእዛዝ እንዲጠብቁ አዘዛቸው ከዚህም በኋላ ለእውነተኛው ጠባቂያቸው ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰጣቸውና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ተለይቶ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ ሕዝቡም አለቀሱለት ቸር ጠባቂያቸውም ከእርሳቸው በመለየቱ እጅግ አዘኑ እንደሚገባም ገንዘው እርሱ ራሱ በአዘዛቸው ቦታ አኖሩት።

በዚህችም ቀን ቅዱሳን ዘኖቢስና እናቱ ዘኖብያ በሰማዕትነት አረፉ እሊህም ቅዱሳን ተበይስ ከምትባል አገር ከታላላቆቿ ናቸው። እነርሱ ክርስቲያን እንደሆኑ በንጉሥ ዘንድ ወነጀሏቸው ንጉሥም ወደርሱ እንዲአቀርቧቸው አዘዘና ሲቀርቡ እንዲህ አላቸው የምትጠበቁት ከምንድን ነው አገራችሁስ ወዴት ነው እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱለት እኛ ጣዖታትን ከማምለክ እንጠበቃለን እምነታችንም በክርስቶስ ነው ሀገራችንም ተበይስ ይባላል።
መኰንኑም ለአማልክት ሠዉ አላቸው ቅዱሳንም እኛ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንሠዋለን እንጂ ለጣዖታት አንሠዋም አሉት መኰንኑም ተቆጣ ልብሳቸውንም ገፈው በራሳቸው ጠጒር ሰቅለው ይደበድቧቸው ዘንድ አዘዘ ወደ እግዚአብሔርም ጸለዩ በዚያንም ጊዜ ማሠሪያቸው ተፈታ የብርሃንንም ልብሶች ለብሰው ሕዝቡ አዩአቸው መኰንኑም ወንበሩን ተሸክሞ በኋላቸው ሲከተል ነበር ። ሕዝቡም ይህን በአዩ ጊዜ እንዲህ እያሉ ጩኸው አመሰገኑ ልዩ ጽኑዕ ምስጉን አሸናፊ እግዚአብሔር የጌትነትህ ክብር በሰማይና በምድር የመላ የክርስቲያን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይልህ ታላቅ ነው።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ተቆጣ እርስበርሳቸው እንዲተያዩ አድርገው በሁለት መስቀሎች እንዲሰቅሏቸው አዘዘ ያን ጊዜም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው በማግሥቱም የእግዚአብሔርን ቃል ሲያስተምሩ መኰንኑ አገኛቸው ሕዝቡም አይተው እኛ በክርስቲያኖች አምላክ እናምናለን እርሱ ታላቅ ነውና እያሉ በአንድ ቃል ጮኹ።
ሁለተኛም እንዲህ ብሎ አዘዘ ሁለት ወንበሮችን እንዲሠሩ በውስጣቸውም ብረቶችን እንዲተክሉ እሊህንም ቅዱሳን በላዩ አስተኝተው ከእሳት ምድጃ ውስጥ እንዲጨምሩአቸው አዘዘ ጌታችን ኢየሱስም አዳናቸው በእነዚያ ወንበሮችም ላይ ተቀምጠው ሕዝቡን ሲያስተምሩ አገኙአቸው።
መኰንኑም በአየ ጊዜ ቁጣን ተመላ ቁመቱና ጐኑ ሃያ ሃያ ክንድ የሆነ ጒድጓድን ቆፍረው እሳትን እንዲአነዱበትና በውስጡ እንዲጨምሩአቸው አዘዘ ወደ እግዚአብሔርም በጸለዩ ጊዜ ያ እሳት ጠፋ ጒድጓዱም እንደተሸለመ ቤት ሆነላቸው።
መኰንኑም የውሽባ ቤት ጠባቂውን ጠርቶ እሳትን እንዲያነድ አዘዘው ቅዱሳኑንም ከውስጡ እንዲጨምሩአቸው። ወደ እግዚአብሔርም በጸለዩ ጊዜ የውሽባ ቤቱ ውኃ ሆነ መኰንኑም ውኃ የተመላበትን ጋን ተሸክሞ ነበር ይህንንም ድንቅ ሥራ ሕዝቡ በአዩ ጊዜ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ በሚሠራው ሥራ የተደነቀ ነው እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
መኰንኑም ምን እንደሚያደርጋቸው በተቸገረ ጊዜ እንዲገድሏቸውና እስከ ነገ ድረስ በድናቸውን ጠብቀው በእሳት እንዲአቃጥሏቸው በነፋስም ውስጥ እንዲበትኑአቸው አዘዘ። በገደሏቸውም ጊዜ ነጐድጓድ መብረቅ ንውጽውጽታና ዝናም ሆነ በዚያ ንውጽውጽታም ብዙዎች ኃምሣ አራት ያህል ሰዎች ሞቱ በሌሊትም ምእመናን መጥተው በሥውር ሥጋቸውን ወስደው ቀበሩአቸው።
በማግሥቱም መኰንኑ በድናቸውን በፈለገ ጊዜ የሆነውን ሁሉ ተአምር ነገሩት ያም መኰንን አደነቀ በጌታችንም አምኖ ክርስቲያን ሆነ።

በዚህችም ቀን ቅዱሳን ሐዲስ መርቆሬዎስና ወንድሙ ዮሐንስ በሰማዕትነት አረፉ። እነዚህ ቅዱሳን እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ለሚያመልኩ ክርስቲያኖች ሰዎች ልጆች ናቸው የታላቁም ስሙ "መናሂ" ነበር የምንኲስና ልብስ በለበሰ ጊዜ መርቆሬዎስ ብለው ሰየሙት የታናሹም ስሙ "አቡፈረዥ "ነበር እርሱንም በሚመነኲስ ጊዜ ዮሐንስ ብለው ሰየሙት።
በአደጉም ጊዜ ወደ ሊቀ ሰራዊት ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም ሔዱ በዚያም እግዚአብሔርን ለሚያገለግል አረጋዊ ጻድቅ ሰው የሚታዘዙ ሁነው ኖሩ ለገዳሙ በሚአሻው ስራ መነኰሳቱንም በማገልገል የክረምቱን ቅዝቃዜና የበጋ ቃጠሎ ታግሠው የምድሩን ፍሬዎች የሚሰበስቡና ወደዚያች ገዳም የሚያመጡ ሆኑ።
ለራሳቸው ግን በዓለም ውስጥ ምንም ምን ጥሪትን አላደረጉም ዳግመኛም በዓለም ውስጥ ጣዕም ካላቸው ከመብል ከመጠጥ ከእንቅልፍ የራቁ ናቸው በየሁለትና በየሶስት ቀን ይጾማሉ። ዳግመኛም በቅብጢና በዓረብ ቋንቋ ጽሕፈት ተማሩ የምንኲስናንም ሕግና ሥርዓት ፈጸሙ።
በአንዲት ቀንም በአንድነት እያሉ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ወደ እነርሳቸው መጥቶ እነርሱ ወደ ምስክርነት አደባባይ እንደሚደርሱ ነገራቸው ያን ጊዜ ደስ አላቸው በመንፈስ ቅዱስም በረቱ ተነሥተውም በችኰላ ተጒዘው ወደ አገራቸው ደረሱ። የአገራቸውም ሰዎች በአገሩ ገዥ ዘንድ ወነጀሏቸው እርሱም ለብህንሳው ገዥ አሳልፎ ሰጣቸው እርሱም በውኑ እናንተ ጣዖትን የምታመልኩ ናችሁን ብሎ ጠየቃቸው ። ቅዱሳን ግን ይህ በእኛ የሚነገር አይደለም እኛ በግልጥ ክርስቲያን የሆን የረከሱ ጣዖታትን የማናመልክ ነንና እውነተኛውን አምላክ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመልከዋለን እንጂ አሉት።
መኰንኑም ይህን በሰማ ጊዜ ቊጣን ተመላ በአንገቶቻቸውም ሰንሰለት አስገብተው ከተማውን ሁሉ አዙረው ከዚያ በኋላ በወህኒ ቤት እንዲአስሩአቸው አዘዘ በዚያም ሳሉ የእግዚአብሔር መልአክ ብዙ ጊዜ የሚጐበኛቸው ሆነ።
ከአምስትም ወር በኋላ መኰንኑ ከእስር ቤት አውጥቶ በፊቱ አቆማቸውና ሃይማኖታችሁን ተዉ አላቸው። አይሆንም በአሉትም ጊዜ ሥጋችሁን በእሳት አቃጥላለሁ ብሎ አስፈራራቸው እነርሱ ግን ምንም አልፈሩትም የልባቸውን ጥንክርና አይቶ ወደ ወህኒ ቤት መለሳቸው።
ከብዙ ወራት በኋላ ሌላ መኰንን መጣ እርሱም ሊአድናቸውና ሊተዋቸው ወደደ የአገር ሰዎች ግን ተቃወሙት እነዚህን ካልገደልካቸው በንጉሥ ዘንድ እንከስሃለን አሉት ያንጊዜም ሊአስፈራራቸው እሳትን ያነዱ ዘንድ አዘዘ እነርሱ ግን ወደ እሳቱ ለመግባት ተደፋፈሩ ዳግመኛም ራርቶላቸው ወደ ወህኒ ቤት መለሳቸው ሁለተኛም አምጥተው በተሳሉ ሰይፎች ያስፈራሩአቸው ዘንድ አዘዘ የእዚህ ቅዱሳን ልብ ግን አልደከመም ቃላቸውም አልተለወጠም።
ከዚህም በኋላ ህዝቡን ከመፍራት የተነሳ ራሳቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ በመጀመሪያም የዮሐንስን ራስ ቆረጡ ያን ጊዜም ራሱ ከሥጋዋ ላይ ዘለለች ከእርሷም እንደ ደስታ ቃል ያለ የሰሙ ሁሉ እስኪያደንቁ ድረስ ታላቅ ድምፅ ወጣ።
ዳግመኛም የቅዱስ መርቆሬዎስን ራስ ቆረጡ ሥጋቸውንም ከእሳት ውስጥ ጨመሩ በዚያንም ጊዜ እሳቱ ጠፋ ሥጋቸውንም ልብሳቸውንም አልነካም መኰንኑም በአየ ጊዜ ክርስቲያኖች እንዳይሰርቋቸው ጠብቁ ብሎ አዘዘ በማግስቱም የዐዘቅት ውኃ በአገኙ ጊዜ ከውስጧ ጨመሩአቸው ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages