ኅዳር 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን 4ቱ እንስሳ (ኪሩቤል)
2.ቅዱስ አፍኒን ሊቀ መላእክት
3.አባ ቅፍሮንያ ጻድቅ
4.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ንጉሥ (ዘምስለ ቅዱስ መስቀል)
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ስምንት በዚች ቀን ሥጋ የሌላቸው የአርባዕቱ_እንስሳ በዓላቸው ነው፣ ሊቀ መላእክት ቅዱስ_አፍኒን የተሾመበት ነው፣ ለንጉሥ_ቈስጠንጢኖስም መስቀል የተገለጸበት ነው፣ የአረማዊ መኰንን ልጅ የነበረ ቅዱስ_አባ_ቅፍሮንያ ያረፈበት ቀን ነው።
ኅዳር ስምንት በዚች ቀን ሥጋ የሌላቸው የአርባዕቱ እንስሳ በዓላቸው ሆነ።
እሊህም መንበሩን የሚሸከሙ የእግዚአብሔር ሠረገላዎቹ ናቸው። ስለ እሳቸውም ወንጌልን የጻፈ ዮሐንስ እንዲህ ሲል እንደመሰከረ በዚያ ዙፋን ፊት በረድ የሚመስል ባሕር አለ በዙፋኑም ዙሪያ አራት እንስሶች አሉ በፊትም በኋላም ዐይንን የተመሉ ናቸው።
የፊተኛው አንበሳ ይመስላል ሁለተኛውም ላም ይመስላል ሦስተኛውም የሰው መልክ ይመስላል አራተኛውም የሚበር አሞራ ይመስላል።
የእሊህም የአራቱ እንሰሶች እያንዳንዱ ክንፋቸው ስድስት ስድስት ነው ሁለንተናቸውም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው። የነበረ የሚኖር የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ጽኑዕ ክቡር ልዩ ነው እያሉ በመዓልትና በሌሊት ዕረፍት የላቸውም።
ሁለተኛውም ስለእርሳቸው ኢሳይያስ እንዲህ አለ ከዚህም በኋላ ንጉሡ ኦዝያን በሞተ ጊዜ አሸናፊ እግዚአብሔርን ሰፊ በሆነና ከፍ ከፍ ባለ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ብርሃኑም ቤቱን መልቶ ሱራፌልም በዙሪያው ቁመው አየሁት።
የአንዱም የአንዱም ክንፋቸው ስድስት ነው በሁለቱ ክንፋቸው ፊታቸውን በሁለቱ ክንፋቸው እግሮቻቸውን ይሸፍናሉ በሁለቱ ክንፎቻቸው ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይበራሉ። አንዱም አንዱም ከአንዱ ጋራ ፍጹም አሸናፊ የሆንክ እግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለህ የምትመሰገነው ምስጋናህ በምድርና በሰማይ የመላ ነው እያሉ ያመሰግናሉ።
ነቢይ ዳዊትም በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ አለ ሁለተኛም በኪሩቤል ላይ የተቀመጠ እርሱ ምድርን አናወጻት አለ። ሕዝቅኤልም እንዲህ አለ ከወደ ሰሜን እነሆ ጥቅል ነፋስ ሲመጣ አየሁ ታላቅ ደመና አለ በዙሪያውም ብርሃን አለ ከእሱም እሳት ቦግ ብሎ ይወጣል።
በደመናውም መካከል ባለ በእሳቱ ውስጥ እንደ አራት ራስ አሞራ መልክ የሚመስል አለ በመካከሉም እንደ አራቱ ኪሩቤል መልክ ያለ አለ። መልካቸውም እንዲህ ነው በውስጣቸው የሰው መልክ አላቸው የአንዱም የአንዱ ፊቱ አራት ነው ክንፉም አራት ነው።
እግራቸውም የቀና ነው ከእግራቸውም ክንፍ አላቸው ሰኮናቸው ግን እንደ ላም ሰኮና ነው ከሱም እሳት ቦግ ይላል እንደጋለ ብረት ፍንጣሪም ይበራል።
ወንጌላዊ ዮሐንስም ዳግመኛ እንዲህ አለ በዚያው ዙፋን ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ የእንስሶቹንም የእነዚያ አለቆችንም ቃል ሰማሁ ቁጥራቸውም እልፍ አለቆች ያሉአቸው ብዙ የብዙ ብዙ ነው።
ለዚያ ለተገደለው በግ ኃይልን፣ ባለጸግነትን፣ ጥበብን፣ ጽናትን፣ መንግሥትን፣ ክብርን፣ ጌትነትን፣ ምስጋናን ገንዘብ ሊያደርግ ይገባዋል ብለው በታላቅ ቃል ተናገሩ።
በሰማይና በምድር ከምድር በታች በባሕር ውስጥ በእነዚያም ውስጥ የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ጌትነት ክብር ኃይል በረከት በዙፋኑ ለተቀመጠው ለሱ ለበጉም ለዘላለሙ ይገባዋል አሉ። በእውነት ይገባዋል። እሊህም አራቱ እንስሶች አሜን ይላሉ። እሊያም አለቆች ይሰግዳሉ።
ስለ ልዕልናቸውና ስለ ክብራቸው ለእሊህ አርባዕቱ እንሰሳ ከብሉይና ከሐዲስ ብዙ መጻሕፍት መስክረዋል መሐሪና ይቅር ባይ እግዚአብሔርም ስለ ሁሉ የሰው ፍጥረት ይለምኑት ዘንድ ቀራቢዎቹ አደረጋቸው። ዳግመኛም እንዲህ ተባለ ገጸ ሰብእ ስለ ሰው ፍጥረት ይለምናል። ገጸ አንበሳ ስለ አራዊት ይለምናል ገጽ ላሕም ስለ እንስሳ ይለምናል ገጸ ንስርም ስለ አዕዋፍ ይለምናል ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት እጅግ የቀረቡ ናቸውና።
ስለዚህም በዓለሙ ሁሉ በስማቸው አብያተ ክርስቲያን እንዲታነፁ በዚችም ቀን መታሰቢያቸው እንዲደረግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ እነርሱ ስለ ሰው ወገን በእግዚአብሔር ዘንድ ይማልዳሉና።
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሊቀ መላእክት ቅዱስ አፍኒን የተሾመበት ዓመታዊ በዓሉ ነው፡፡ ይህም ሱራፌልና ከኪሩቤል ጋር የልዑልን የጌትነቱን ዙፋን የሚጠብቅ ነው፡፡ ስለዚህም ክቡር መልአክ ሄኖክ እንዲህ አለ፡- "…ያንን ቤት ሱራፌልና አፍኒን ዙሪያውን እየዞሩ ይጠብቁታል፣ እነርሱም የልዑልን የጌትነቱን ዙፋን ሲጠብቁ የማያንቀላፉ ናቸው፡፡" ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ "በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላእክትን አየሁ" (ራዕ 8፥2) እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቁጥር 7 ናቸው፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ፋኑኤልና ኅዳር 8 ቀን የተሾመበትን ዓመታዊ በዓሉን የምናከብርለት ቅዱስ አፍኒን ናቸው፡፡
በዚህችም ቀን ለንጉሥ ቈስጠንጢኖስም መስቀል ተገለጸለት።
ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያህል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም። ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒና ከአረማዊ አባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ።
ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ /የመከራ ጊዜ/ ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር። ክርስቲያኖችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በተደረገው የ40 ዓመታት ዘመቻ አብያተ-መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ። ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ። ሚሊየኖች በግፍ አለቁ።
የዚሕን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆንጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም። ምክንያቱም ምክንያቱም ይህን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ ቀርነ-ሃይማኖት የቆመው፣ ብዙ ሥርዓት የተሠራው፣ ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና።
ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት ሐዋርያትና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል። በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኖራለት፡ በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ በዚህች ቀን አርፏል።
ይህቺ ቀን ታላቁ ንጉሥ በፈለገ ኮቦር ቅዱስ መስቀልን የተመለከተባት ናት። መክስምያኖስን ሊወጋ ወደ ሮም በተጓዘ ጊዜ በሰማይ ላይ መድኅን መስቀል ተዘርግቶ በላዩ ላይ "ኒኮስጣጣን" የሚል በዮናኒ ልሳን ተጽፎበት ተመልክቷል።
ይህንንም "በዚህ ጠላትህን ድል ታደርጋለህ" ማለት ነው ብለው ተርጉመውለታል። እርሱም በጋሻው፣ በጦሩ፣ በሰይፉ፣ በፈረሱ ላይ የመስቀል ምልክትን አድርጐ ማሕደረ ሰይጣን መክስምያኖስን ድል ነስቶታል። እኛንም በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን።
በዚህችም ቀን የአረማዊ መኰንን ልጅ የነበረ አባ ቅፍሮንያ አረፈ። ከዕለታትም በአንዲቱ ስሙ መርቆሬዎስ የሚባል መነኰስ ከአባ ጳኵሚስ ገዳም ወደ ሀገሩ መጣ እርሱ ክርስቲያን እንደሚሆን በእርሱ ላይ ትንቢት ተናገረ።
ከጥቂት ወራትም በኋላ ገዳማትን ሊያጠፋ ምርኮንም ሊማርክ ሠራዊቱን ሰብሰቦ ወደ ግብጽ አገር ዘመተ ወደ አባ ጳኵሚስም ገዳም በደረሰ ጊዜ አበ ምኔቱ ወደርሱ ወጥቶ እኔ ነኝ አለው ቅፍሮንያም ሰምቶ አበምኔቱን ለብቻው አግልሎ እንዲአጠምቀውና የምንኵስናንም ልብስ እንዲአለብሰው ለመነው አበ ምኔቱም እሺ በጎ አለው።
ከዚህም በኋላ ሠራዊቱ ወደ ሀገራቸው በተመለሱ ጊዜ ብቻውን ቀረ በዚያንም ጊዜ የምንኵስናን ልብስ ለበሰ ተጋድሎውንም በመጾምና በመጸለይ ጀመረ። ሰይጣንም በእርሱ ላይ ቀንቶ ነገረ ሠሪ አስነሣበት በመኳንንቱም ዘንድ ወነጀለው እነርሱም አገራችንን ያጠፋ የመኰንን ልጅ ከዚህ አለ ብለው ገዳሙን ከበቡ እግዚአብሔርም ሠወረው በአጡትም ጊዜ ነገረ ሠሪውን ገደሉት።
ይህም ቅዱስ በገድል ተጠምዶ ኖረ በየሰባት ቀንም ይጾማል ያለ መራራ አደንጓሬ አይመገብም። በዚያም ወራት የምድር አውሬ እንስሶቻቸውን እየገደለ በገዳሙ ላይ ጥፋትን አደረሰ አባ ቅፍሮንያም ወደርሱ መጥቶ እንደ በግ ይዞ አሠረው ዐሥር ዓመትም ቆይቶ ሞተ።
ቅዱስ ቅፍሮንያም የእግዚአብሔር መልአክ እየመራው ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ በአንዲትም ቀን ደረሰ በዚያም ታላቅ ምሥጢርን አየ ከከበሩ ቦታዎችም ተባርኮ ወደ መኖሪያው ተመልሶ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ኪሩቤል፣ በቅዱሳን መላዕክት እና ሰማዕታት አማላጅነት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።
No comments:
Post a Comment