ጣና ሐይቅ ገዳሟ ውስጥ የሚገኘው የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ቅዱስ ዐፅም! - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, November 3, 2022

ጣና ሐይቅ ገዳሟ ውስጥ የሚገኘው የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ቅዱስ ዐፅም!


 

ረድኤት በረከቷ ይይማረን፡፡
እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ያደረገችው ተአምር ይህ ነው፡- ‹‹ከዕለታትም በአንደኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ዕለተ ሞቷን እያሰበች በጣና ባሕር ውስጥ ቆማ ስታለቅስና ስትጸልይ ሣለች ዲያብሎስ በሊቀ ጳጳሳት ተመስሎ እጅግ አስደናቂና ግሩም በሆነ አርአያ ወደ እርሷ መጣ፡፡ እርሷም ልትሰግድለት ወደደች፣ ከኃዘኗ ያረጋጋት ዘንድ ከቅዱሳን አንዱ የመጣ መስሏት ነበርና፡፡ ነገር ግን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ፈጥኖ ደረሰና ‹ይህ ሰይጣን እንጂ ጳጳስ ወይም ከቅዱሳን አንዱ አይደለምና አትስገጂለት› ብሎ ወደኋላዋ መለሳት፡፡ ዳግመኛም ‹አሁንም እንደልማድሽ ሂጂና ጠይቂው ማን እንደሆነ ይነግርሻል› አላት፡፡ በዚህን ጊዜ ወደ እርሱ ሂደችና ‹እሰግድልህ ዘንድ አንተ ማን ነህ?፣ ስምህስ ማን ይባላል?› ስትል ጠየቀችው፡፡ እርሱም ‹የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ነኝ› አላት፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከእርሷ ጋር እንዳለ አላወቀም ነበርና፡፡ እርሱ በእርሷ ላይ ተንኮል ለመሥራት እንደተራቀቀ ሁሉ እርሷም ነቃችበት ተራቀቀችበት፡፡ ቀጥሎም ‹እንግዲያውስ አንተ ሚካኤል ከሆንክ እስቲ ስለ ጽድቅ ነገር አስተምረኝ› አለችው፡፡ በዚህም ጊዜ ፈጽሞ ተደሰተ ከዓላማዋ አሳስቶ በእጁ የገባችለት መስሎታልና፡፡ እንዲህም አላት፡- ‹ለምን ሰውነትሽን ታደክሚዋለሽ? ከዛሬ ጀምሮ ከዚህ ኃላፊ ዓለም ድካም ማረፍ ያስፈልግሻል፣ መጾምና መጸለይስ ለምን ይጠቅምሻል? በባሕርስ ውስጥ ቆሞ መጸለይና ሰውነትን ማድከም ማን አስተማረሽ?› አላት፡፡ በዚያን ጊዜ ‹አንተ የምትለውና መጻሕፍት የሚናገሩት የተለያየ ሆነሳ!?› አለችው፡፡ እርሱም ‹ማነው የለያየን?› አላት፡፡ እርሷም ‹ከአነጋገርህ የተነሣ እኔ ለየኋችሁ› አለችው፡፡ እርሱም ‹እስኪ ልዩነታችንን ንገሪኝ?› አላት፡፡ እርሷም ‹መጻሕፍት የጾመ፣ የጸለየ፣ የለመነም ሁሉ ፍጹም ዋጋውን ያገኛል ይላሉ፡፡ አንተ ግን አትጹሙ፣ አትጸልዩ ትላለህ› አለችው፡፡ ይህንንም ባለችው ጊዜ በእርሷ ላይ ፈጽሞ ተቆጣ፣ እጅግም አድርጎ አስደነገጣት፡፡ ዳግመኛም መለሰችና ‹በምን ትሸነፋለህ?› አለችው፡፡ አሁንም ቁጣውን አወረደባት፡፡ በሦስተኛው ጊዜ ከተቆጣ በኋላ ‹በእነዚህ በሦስቱ ነገሮች እሸነፋለሁ› ሲል መለሰላት፡፡ ‹አንደኛ ማንኛውም ሰው በዚህ ዓለም በሚኖርበት ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት እንግዳ ተቀብሎ የሚያስተናግድ፤ ሁለተኛው በራሱ ላይ ችግርና መከራ በመጣበት ጊዜ መከራውን ታግሦ የሚኖር፤ ሦስተኛው ቀድሞም ከመሬት የተገኘሁ ነኝ፣ ኋላም ተመልሼ ወደ መሬት እገባለሁ እሞታለሁ እፈርሳለሁ ብሎ በማሰብ ትሕትና የሚሠራና የመሳሰሉትን ሁሉ የሚያደርግ እርሱ ፈጽሞ ያሸንፈኛል› አላት፡፡ ይህንንም ከተናገረ በኋላ ክንፉን እያማታ ወደ አየር በረረ፡፡ እርሷም ከግርማው የተነሣ ፈጽማ ደነገጠች፣ በመሬትም ላይ ወደቀች፡፡ በዚያን ጊዜ ለጌትነቱ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ቅዱሳት በሚሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣት፡፡ ከዚያም ‹ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ! አይዞሽ አትፍሪው ነገር ግን ወደ ላይ ወደ ሰማይ አቅንተሽ ተመለከቺ› አላት፡፡
ወደ ሰማይ አቅንታ በተመለከተች ጊዜ የዲያብሎስ ክንፉ በሰማይ ላይ ከጽንፍ እስከ አጽናፍ ተዘርግቶ (መላው ዓለምን ሞልቶ) አየች፡፡ ቀጥሎም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹በእኔ በባሕርይ አባቴ በአብ በባሕርይ ሕይወቴ በመንፈስ ቅዱስ ያላመነ ሊያሸንፈው አይችልም› አላት፡፡ ዳግመኛም ‹ማንም ሰው ኃጢአት ቢኖርበት ወደቀደመ ኃጢአቱ ባለመመለስ ንስሐ ቢገባ ከወጥመዱ ያመልጣል› አላት፡፡››
ጌታችን ለቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የገባላት ልዩ ቃልኪዳን፡-
1.ጌታችን ለክርስቶስ ሠምራ ‹‹ሥጋሽን እንደ እናቴ ማርያም ሥጋ እቀድሰዋለሁ፣ ስምሽንም እንደ እርሷ ስም አከብረዋለሁ›› ብሎ ቃልኪዳን እንደሰጣት፡- ‹‹ካለችበት ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በክንፉ ተሸክሞ ወስዶ ከጣና ደሴት አደረሳት፡፡ በዚያም ሰውነቷ ተበሳስቶ የባሕር ዓሣ መመላለሻ እስከሚሆን ድረስ እንደ ተተከለ ዓምድ ሆና ሳትወጣ በባሕሩ ውስጥ አሥራ ሁለት ዓመት ቆማ ስትጸልይ ኖረች፡፡ ከዓሥራ ሁለት ዓመት በኋላ ከባሕሩ ውስጥ ቆማ ሳለች ጌታ ኢየሱስ ወደ እርሷ መጣ፡፡ ‹ሥጋሽን እንደ እናቴ ማርያም ሥጋ እቀድሰዋለሁ፣ ስምሽንም እንደ እርሷ ስም አከብረዋለሁ› ብሎ ሌላም ብዙ ቃልኪዳን ከሰጣት በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡››
2.ጌታችን ለክርስቶስ ሠምራ ዘላለማዊ መኖሪያሽ ከእናቴ ጋር ነው፣ ደረጃሽም ከእርሷ ቀጥሎ ይሁን ብሎ ቃልኪዳን እንደሰጣት፡- እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዲያቢሎስን ከጌታ ጋር ለማስታረቅ ብላ እርሱን ልትጠራው ብትሄድ እጁዋን ይዞ ሲኦል ቢከታት ቅዱስ ሚካኤል አድኗታል፡፡ ከእነርሱም ጋር በክንፋቸው ተንጠልጥለው ከሲኦል የወጡትን 10 ሺህ የሚሆኑን ነፍሳት ጌታችን አስራት አድጎ ሰጣት፡፡ ‹‹ከዚህም በኋላ ሚካኤልን ጠርቶ ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ውሰዳቸው›› አለው፡፡ ‹‹በዚህም ጊዜ ‹አቤቱ ፈጣሪዬ የእኔ መኖሪያ የት ነው?› አለችው፡፡ ጌታም ‹መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል ማርያም ጋር ነው፣ እነሆ በትረ ማርያም ብዬ ሰየምኩሽ፣ ደረጃሽን ከእርሷ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ፣ የባለሟልነት ግርማ አጎናጸፍሁሽ፣ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው› አላት፡፡››
3. የቅድስት ክርስቶስ ሠምራን መካነ መቃብር የተሳለመ የእናቱ የድንግል ማርያምን መካነ መቃብር እንደተሳለመ ይሆንለታል፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ይህን ቃልኪዳን ሰጣት፡- ‹‹በስምሽ ለተራበ ያበላ እኔ ዕለተ ዓርብ ከተቆረሰው ሥጋዬ አበላዋለሁ፣ በስምሽ ለተጠማ እፍኝ ውኃ ያጠጣውን እኔ በዕለተ ዓርብ ከጎኔ በፈሰሰው ደሜ አረካዋለሁ፡፡ እውነት እውነት እልሻለሁ ሥጋሽ ከተቀበረበት ሄዶ መካነ መቃብርሽን የተሳለመ የእናቴን የማርያምን መካነ መቃብር እንደተሣለመ ይቆጠርለታል፡፡››
የቅድስት እናታችን ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages