ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, March 6, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 28



ቅዱስ_ቴዎድሮስ_ዘሮም

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ሃያ ስምንት በዚች ዕለት በነገሥታት መክሲሞስና መክስምያኖስ ዘመን ሮማዊ ቅዱስ ቴዎድሮስ በሰማዕትነት አረፈ። እርሱም ከእስያ አውራጃ አስጢር ከሚባል አገር ነው።
ይህንንም ቅዱስ በነገሥታት ዘንድ አማልክትን በማምለክ እርሱ እንደማይስማማ ወነጀሉት በዚያንም ጊዜ አስጠርተው ለአማልክት ለምን አትሰግድም አሉት እርሱም እኔ ክርስቲያን ነኝ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አላመልክም ብሎ መለሰላቸው።
የበርብዮስጦስ ልጅ ንጉሡም ለአማልክቶቼ ብትገዛ በጭፍራዎቼና በመኳንንቶቼ ሁሉ ላይ አለቃ አድርጌ እሾምሃለሁ ብዙ ወርቅና ብር የከበሩ ልብሶችንም እሰጥሃለሁ አለው ቅዱስ ቴዎድሮስም ወርቅህና ብርህ ለጥፋት ይሁንህ እኔስ በንጉሤ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለጸጋና አለቃ ነኝ አለው።
ንጉሡም ለአምላክህ ልጅ አለውን አለው የከበረ ቴዎድሮስም አዎን ከመለኮቱ ባሕርይ የተገኘ ከእርሱ ጋር ዓለምን የፈጠረ በእውነት ልጅ አለው ብሎ መለሰለት ንጉሡም አምላክህን ብናውቀው ልናገኘው እንችላለን አለው ቅዱስ ቴዎድሮስም ወደርሱ ከተመለስክ እንደ እኔ ጭፍራ ትሆናለህ የተወደደ መሥዋዕትም ያደርግሃል አለው።
ንጉሡም ነገር አታብዛ ብዙ ገንዘብ እሰጥህ ዘንድ ለአማልክቶቼ መሥዋዕትን አቅርብ እንጂ አለው የከበረ ቴዎድሮስም ንጉሡን ረገመው ጣዖታቱንም ሰደበ በዚያንም ጊዜ ንጉሡ ተቆጣ። ልብሱንም እንዲገፉት በትምህርቱም ከአመኑ አሕዛብ ጋር በጨለማ ቤት ያሥሩት ዘንድ አዘዘ። የከበረ ቴዎድሮስም ጸለየ በሌሊትም ወጣ ዕንጨቶችንም ሰብስቦ ጣዖቶችን ሁሉ አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጠላቸው እንዳይሰሙ በአገልጋዮቻቸው ላይ እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ አሳድሮባቸዋልና።
ለንጉሡም በነገሩት ጊዜ አጽንቶ አሠረውና ልዩ ልዩ በሆነ በጽኑ ሥቃይ አብዝቶ ያሠቃየው ዘንድ ለመኰንኑ ሰጠው መኰንኑም እንዲህ አለው ለንጉሥ ለምን አትታዘዘም ለአማልክቶችስ ለምን አትሠዋም የከበረ ቴዎድሮስም እኔስ ለረከሱ አማልክት አልሠዋም ለከሀዲ ንጉሥም አልታዘዝም ብሎ መለሰለት።
መኰንኑም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ከወንበሩም ላይ ተነሥቶ እንደ ነብር ተወርውሮ አንገቱን አነቀውና የከበረ ቴዎድሮስን በምድር ላይ ጥሎ ፊቱን ጸፋው በእግሮቹም ረገጠው እግዚአብሔርም ትዕግስቱን አይቶ የመላእክት አለቃ ገብርኤልን ላከለት መኰንኑንም ገድሎ ከምድር ዐዘቅት አሠጠመው ለከበረ ቴዎድሮስም በእስያ ሀገር ውስጥ እየተዘዋወረ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት እንዲአስተምር መንፈሳዊ ፀዓዳ ፈረስን ሰጠው።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ የከበረ ቴዎድሮስን ከነፈረሱ እንዲይዙት በትምህርቱም የአመኑትን ሁሉ እንዲገድሉ መቶ ፈረሰኞች ወታደሮቹን ላከ። ከሴቶችና ከልጆች በቀር ስድስት ሺህ አርባ ስምንት ሰውን ገደሉ። ሊይዙትም ወደ ቅዱስ ቴዎድሮስ በደረሱ ጊዜ ፈረሱ በላያቸው ተወረወረ ከአፉም እሳትን አውጥቶ አመድ እስኪሆኑ አቃጠላቸው ነገር ግን ሌሎች አግኝተው ያዙትና ወደ ንጉሥ ወሰዱት እርሱም ወደ እሥር ቤት እንዲአስገቡት እንዳይበላና እንዳይጠጣም ደጃፎችን እንዲዘጉበት አዘዘ።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጸለትና ቃል ኪዳን ሰጠው በዚያንም ጊዜ ከእሥር ቤት አውጥተው ዘቅዝቀው ሰቀሉት ደሙም እንደ ውኃ እስቲፈስ ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ ገረፉት ደሙ የነካቸውም ብዙ በሽተኞች ዳኑ ተአምራቱንም ያዩና የሰሙ በጌታችን አመኑ በዚያችም ቀን መቶ አርባ ስምንት ሰዎች ተገደሉ።
እሊህን የተገደሉትንም ሰማዕታት ወደ እሳት ማንደጃ ውስጥ ከእርሱ ጋር ጨመሩአቸው በዚያንም ጊዜ ነፋስ ነፈሰ መብረቅና ነጐድጓድም ሆነ እሳቱንም አቀዝቅዞት የከበረ ቴዎድሮስ ምንም ሳይነካው ከእሳት ውስጥ ወጣ።
ከዚህም በኋላ ንጉሡ የሚያደርግበትን በአጣ ጊዜ ኃምሣ አራት ልጥር የሚመዝን ልጓም አምጥተው አፉን እንዲለጒሙት እግሮቹንና እጆቹንም በችንካር ቸንክረው ለአንበሳ እንዲጥሉት አዘዘ። አንበሳውም ዕንባውን እያንጠባጠበ እንደ ሰው አለቀሰለት እንጂ ምንም አልነካውም። ጌታችንም ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ዕድል ፈንታውን ከርሱ ጋር በመንግሥተ ሰማያት ያደርግ ዘንድ ቃል ኪዳንን ሰጠው።
ከዚህም በኋላ የሁለት መቶ ሰው ሸክም ዕንጨት መቶ ልጥር ባሩድ መቶ ልጥር የዶሮማር መቶ ልጥር ነሐስ አመጡ ከማንደጃውም ጨምረው እጅግ እስከሚግል አነደዱት ጸሎቱንም ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስን ወደ ነደደው እሳት ወረወሩት ምስክርነቱንም ፈጸመ የመላእክት አለቆች ሚካኤልና ገብርኤል ነፍሱን ተቀበሉ በሦስት አክሊላትም አቀዳጁት ሥጋውንም አውሳብያ የተባለች የመኰንኑ ሚስት ወሰደች ዋጋው ብዙ በሆነ ሽቱም ገነዘችውና ወደ ገላትያ ወሰደችው በዕብነ በረድ ሣጥንም አድርጋ በዚያ ቀበረችው ቤተ ክርስቲያንም ሠራችለት ከሥጋውም ታላላቆች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጹ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages