ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ ያለው ሰኞ - ማዕዶት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, April 20, 2023

ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ ያለው ሰኞ - ማዕዶት






ከትንሳኤ ሌሊት አንድ ሰዓት ወይም ቅዳሴ ውጪ ዠምሮ እስከ ዳግም ትንሳኤ ያለው ስምንት ቀን የፋሲካ ምሥጢር ከግብፅ ወደ ፍልስጤም ፤ ከሲዖል ወደ ገነት መሻገር ነው። ለፋሲካ የሚታረደውም በግ ፋሲካ ይባላል። (ዘዳ. ፲፮፥፪ ፣ ፭)። በዚህ ሣምንት ውስጥ ያሉት ዕለታት እያንዳንዳቸው ልዩ ልዩ ስም አላቸው። ይኸውም በቅዱስ ያሬድ አጠራር ነው። ሰኞ ማዕዶት (ፀአተ ሲኦል)ይባላል፦ ነፍሳት ከሲኦል የወጡበት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩበት ማለት ነው ፤ የፋሲካም ትርጉም ይኸው ነው። ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነው። እስራኤላውያን በግብፅ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይም በመቃኑ እንዲቀባ ሙሴ ለሕዝቡ ተናገረ ፤ ሁሉሞ እንደታዘዙት ፈጸሙ። መቅሰፍት ከእግዚአብሔር ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የእስራኤላውያንን ቤት እያየ ማለፉን ለማመልከት ነው። በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያ ወራቸው ሚያዝያ በአሥራ አራተኛው ቀን በግ እያራዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ (ዘጸ. ፲፪፥፮)።

የጌታችን ምሳሌ የሆነውን የፋሲካውን በግ ምሥጢር እንመልከት (ዘጸ. ፲፪፥፩-፴፮ ፣ ዮሐ. ፲፪፥፱ ፣ ኢሳ. ፶፫፥፯ ፣ የሐዋ. ፰፥፴፪ ራዕ. ፯፥፱-፲፪) ንጹሕ ቀንዱ ያልከረከረ ፣ የእግሩ ጥፍር ያልዘረዘረ ፣ ጠጉሩ ያላረረ ፣ ዓመት የሆነው በግ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። ቀንዱ ያልከረከረ ፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረ ፣ ጠጉሩ ያላረረ የሚለው በጭንቅላቱ ትዕቢት ፣ በእጁ በደል ፣ ሁለተናዊ ንጹሕ ተብሎ ይተረጎማል። ያ ንጹሕ እንደሆነ ክርስቶስ ምንም ሥጋ ለብሶ ሰው ቢሆን በነገሩ ሆነ በተግባሩም ኃጢአት አልተገኘበትም።(ኢሳ. ፶፫፥፱ ዮሐ. ፰፥፵፮ ፣ ፲፬፥፴)። ያን በግ አርደው በታዘዙት መሠረት የሚኖሩበትን የቤታቸውን መቃን መድረኩን ደሙን መቀባታቸው ለጊዜው የግብፃውያንን ከሰው እስከ እንስሳ የመጀመሪያ ልጅ የሚታደግ መቅሰፍት ወይም ሞተ በኩር በታዘዘ ጊዜ ደሙን አይቶ የእስራኤልን እንዲተው እንዲድኑ ነው።

ፍጻሜው ግን በበግ የተመሰለ የክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን ለሚቀበሉ ምእመናን አጋንንት አይጸኑባቸውም (፩ኛ ጴጥ. ፩፥፲፰-፳፪)። ጥሬውንም አትብሉ ማለት ሥጋውን ደሙን ስትቀበሉ መለኮት የተለየው ነፍስ የተዋሐደው ነው አትብሉ ሲል ነው።

በእሳት ጠብሳችሁ ብሉት ማለቱም በእሳት የተጠበሰ ሙቀት እንዳይለየው ደሙም መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው ነው ብላችሁ እመኑ ሲል ነው። በውኃ የተቀቀለውን አትብሉ ማለቱም በባሕርይ አምላክ በክርስቶስ ሙስና መቃብር ማለት እንደ ፍጡራን መፍረስ መበስበስን መለወጥ አለበት አትበሉ ሲል ነው። መጣጣ አረብሩቡበት ማለቱም ሥጋውን ደሙን ከመቀበላችሁ በፊት አሥራ አምስት ሰዓት ጾማችሁ ለአፋችሁ ምሬት ሲሰማው ተቀበሉ ሲል ነው። ኩፌት ደፍታችሁ ማለቱም አክሊለ ሶክን እያሰባችሁ ኑሩ ሲል ነው። ወገባችሁን ታጥቃችሁ ማለቱም በንጽሕና ሆናችሁ ኑሩ ሲል ነው (፩ጴጥ. ፫፥፲፭)

ጫማችሁን እንደአጠለቃችሁ ማለቱም በሕገ ወንጌል ፣ ምግባረ ወንጌል እየሠራችሁ ማለቱ ነው። በትራችሁን በእጃችሁ እንደያዛችሁ ማለቱም ነገረ መስቀሉን እያሰባችሁ ኑሩ ሲል ነው። እየቸኮላችሁ ብሉት ማለቱ ደግሞ በንስሐ ኃጢአት ነጽታችሁ ዕለተ ሞታችሁን እያሰባችሁ ነቅታችሁ ኑሩ ሲል ነው (ማቴ. ፳፬፥፵፫-፶፩ ፣ ፳፭፥፩-፲፬)። የበላችሁትን በልታችሁ የቀረውን በእሳት አቃጥሉት ማለቱ የመረመራችሁትን ምሥጢር መርምራችሁ የቀረውን ከአቅማችሁ በላይ ያለውን መንፈስ ቅዱስ ያውቃል በሉ ሲል ነው።

በየዓመቱ በግ እያረዱ የእስራኤል ልጆች በመጀመሪያ ወራቸው በ፲፬ኛው ቀን የፋሲካን በዓል ሲያከብሩ ከዚያም ምሽት እስከ አንድ ሣምንት ድረስ የቦካውን ነገር ለመብላት ስላልተፈቀደላቸው የሙሉ ሣምንት በዓል የቂጣ በዓል ተባለ። የቂጣ እንጀራ መብላት የእስራኤልን ልጆች በችኮላ ከግብጽ እንደወጡ የመታሰቢያ ምልክት ነው።(ዘጸ. ፲፪፥፲፰-፳ ፣ ፴፫፥፳፬ ዘዳ. ፲፮፥፩-፫)። ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ሣምንት የፋሲካ ሣምንት ነበረ (ሉቃ. ፳፪፥፲፬-፲፮ ፣ ዮሐ. ፲፰፥፴፰-፵)። እርሱም ንጹሕ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ደሙን ስላፈሰሰልን ፋሲካችን ተባለ (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፯)። ለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ በዓል ፋሲካ ተብሎ ይጠራል። ብሉይ የሐዲስ አምሳል ነው ፤ ይኸውም ሙሴ የክርስቶስ ፣ እስራኤል የነፍሳት ፣ 430 ዘመን የ5500 ዓመተ የፍዳ ፣ ምድረ ርስት የገነት ፣ ግብፅ የሲዖል ፣ ባሕረ ኤርትራ የገሃነመ እሳት ፣ ፈርኦንና ሠራዊቱ የዲያብሎስ የአጋንንት ምሳሌ ናቸው። ፈርኦን ከሠራዊቱ ጋር ከግብፅ ወጥቶ ባሕረ ኤርትራ መስጠሙ በፍጻሜ ዓለም ዲያቢሎስ ከሠራዊቱ ጋር ወደ ገሃነመ እሳትም መጣሉን ያመለክታል።

ምንጭ፦ "መዝሙረ ማኅሌት ወቅዳሴ"

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages