ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 1 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, May 8, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 1

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

በግንቦት አንድ በዚህችም ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም ተወለደች፣ የከበረ አባ_ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ የእመቤታችንን ቅዳሴ የደረሰበት ነው፡፡


በግንቦት አንድ በዚህችም ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኀነት የሆነባት ናት። ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ሐና ይባላሉ። ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ በዚያ ወራት የመካኖችን መብዓ ካህናቱ አይቅበሉም ነበርና።
እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኅዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር። ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ኀሳባቸውን ተመለከተ።
ክቡር እያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኀነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው።
በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ስለትን ተሳለች። ከዚህም በኋላ ይቺን የከበረች ሕፃን ፀንሳ ወለደች ስሟንም ማርያም ብላ ሰየመቻት ትርጓሜውም እመቤት ነው ደግሞም ሀብትና ስጦታ ማለት ነው።
በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ናት ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የከበረ አቡነ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ የእመቤታችንን ቅዳሴ የደረሰበት ነው፡፡ ሕርያቆስ ማለት ‹‹ኅሩይ-የተመረጠ›› ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ምሥጢረ ሥላሴን ከሁሉ ይልቅ አራቆ ይናገራልና አባቶቻን ሕርያቆስ ማለት ‹‹ረቂቅ›› ማለት ነው ይሉታል፡፡ ‹‹አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ›› ብሎ አመስግኗልና አሁንም ሕርያቆስ ማለት ‹‹ፀሐይ›› ማለት ነው ይሉታል፡፡ ደግሞም የምእመናንን ልቡና በትምህርቱ ብሩህ አድርጓልና ሕርያቆስ ማለት ‹‹ብርሃን›› ማለት ነው፡፡ አንድም ደግሞ ሕርያቆስ ማለት ‹ንብ› ማለት ነው፡፡ ንብ የማትቀምሰው አበባ እንደሌለ ሁሉ ሕርያቆስም ያልቀሰመው ሰማያዊ ዕውቀት የለምና እርሱን የማይጠቅሰው ሊቅ የለም፡፡
አባ ሕርያቆስ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ እና ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ የሚያመሰጥረውን እመቤታችንን በተለያዩ ምሳሌያት እየመሰለ የሚያመሰግንበትን ድንቅ የሆነውን ድርሰቱን ‹‹ቅዳሴ ማርያምን›› ሰማያዊ ምሥጢር ወለል ብሎ ተከፍቶለት ደርሶታል፡፡ የብሕንሳው ኤዺስቆዾስ ስላረፉ በእሳቸው ምትክ የሚሾሙትን ሲያፈላልጉ መንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስን መረጣቸው፡፡ የከበሩ ሐዋርያት ‹‹የተማረና ግብረ ገብ የሆነ ይሾም›› ብለው ሥርዓት ሠርተዋል፡፡ ደግሞም ‹‹ሁለቱን አስተባብሮ የያዘ ባይገኝ የተማረ ከሆነ ይሾም›› ብለዋል፡፡ ምክንያቱም በትምህርቱ መናፍቃንን ተከራክሮ ይመልሳልና ነው፡፡ ደግሞም ‹‹ግብረ ገብም ከሆነ ይሾም›› ብለዋል፡፡ ምክንያቱም በጸሎቱ ይጠብቃል በትሩፋቱ ያጸድቃልና ነው፡፡ በዚህም መሠረት አባ ሕርያቆስ ያልተማረ ነገር ግን ግብረ ገብ ነውና ‹‹ትምህርቱን ውሎ አድሮ ያደርገዋል›› ብለው ሾሙት፡፡ አባ ሕርያቆስም የተማረው ለጸሎት ለቅዳሴ ያህል ትንሽ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ይህ ቅዱስ አባት በብሕንሳ ገዳም በ10000 መነኮሳት እና በ10000 መነኮሳይያት ላይ ተሹሞ የገዳሙ አስተዳዳሪ ሆነ፡፡
አባ ሕርያቆስ እመቤታችንን እጅግ ከመውደዱ የተነሣ ስሟን እንኳን ሲጠራ በመስጦ ልቡናው ይሰወርበት ነበር፡፡ ዘወትር ፍቅሯ ከማሰብ በቀር ሌላም አያስብም ነበር፡፡ እርሱ የነበረበት ዘመን የሊቃውንት ዘመን ስለነበር ሁሉም ለትምህርት ሲተጉ አባ ሕርያቆስ ግን ለጸሎትና ለደግነት ብቻ ይተጋ ነበር፡፡ የአባ ሕርያቆስ የሌት ተቀን ሞኞቱ ‹‹እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤታችን ምስጋና እንደ ባሕር አሸዋ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ እንደልብስ ለብሼም እንደ ምግብ ተመግቤው›› የሚል ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮም እጅግ ስለሚወዳት እመቤታችንም ትጠብቀው ነበር፡፡ ከዕለታት በአንደኛው ቀን አባ ሕርያቆስ በበረኃ ብቻውን እየተጓዘ ሳለ የእመቤታችንን ፍቅር በልቡ ሲያመላልስ ስሟን እያነሣ ሲዘምር በተመሥጦ ውስጥ ሆኖ መንገድ ሳተና ከታላቅ ገደል ጫፍ ደርሶ ሳያስበው ወደቀ፡፡ ከገደሉም ጫፍ ደርሶ ከወደቀ በኋላ እጅግ ደንግጦ ራሱን ቢመለከት አካሉ ሳይጎድል ልብሱ ሳይቆሽሽ አገኘው፡፡ በዚህም ተገርሞ ያለበትን አካባቢውን ቢያማትር ራሱን ብርሃንን በተሞላ የልብስ ዘርፍ ላይ አገኘው፡፡ ያም ብርሃንን የተሞላ የልብስ ዘርፍ የእመቤታችን የቀሚሷ ዘርፍ ነው፡፡ በዚህም እጅግ ደንግጦ ‹‹እመ ብርሃን›› ብሎ ጮኸ፡፡ እመቤታችንም ከፊቱ ቁማ ተገለጠችለት፡፡ እርሱም የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክን በገሃድ በዐይኑ አጠገቡ ቆማ ቢያያት በደስታ ዘለለ፡፡ እመቤታችንም በቃሏ አነጋግራው ባርካው ተሰወረችው፡፡ እርሱም ፍቅሯ ጣዕሟ ቢመስጠው ከሰው ሳይገናኝ ምግብም ሳይበላ እዚያው እገደሉ ውስጥ አንድ ዓመት በምስጋና ብቻ በተመስጦ ኖሯል፡፡ በኋላም እመቤታችን ድጋሚ ተገልጣለት ከገደሉ አውጥታ ወደ ሀገሩ አድርሳዋለች፡፡
ከዚህም በኋላ አባ ሕርያቆስ እርሱ በተሾመባ በብሕንሳ ገዳም ሴትና ወንድ ያልተለየባት ገዳም ነበረችና በዚህች ገዳም የተሾመው አባ ሕርያቆስ ብዙም ትምህርት ስላልነበረው ይንቁት ነበር፡፡ ‹‹ከመጠምጠም መማር ይቅደም›› እንዲሉ ‹‹ከመሾም በፊት መማር አይቀድምም›› እያሉም ይዘብቱበት ነበር፡፡ እርሱ ግን እንደጠሉኝ ልጥላቸው ሳይል በፍቅር በትሕትና ይመክራቸው ነበር፡፡ እነርሱ ግን ‹‹በምን ምክንያት እንሻረው›› እያሉ ይመክሩ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ‹‹ቀድሰህ አቁርበን እንበለውና አይሆንም ካለን በዚህ ምክንያት እንሻረው?›› ብለው መከሩ፡፡ እርሱም ሥርዓተ ቅዳሴውን ፈጽሞ ወደፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ የትኛውን ከባድ ቅዳሴ ቀድስ እንበለው?›› እያሉ ይመካከሩ ጀመር፡፡ እርሱ ግን ከቅዳሴ ሐዋርያት በቀር የሚያውቀው አልነበረም፡፡ አባ ሕርያቆስ እያዘነ ወደ መንበሩ ዞሮ ‹‹እመቤቴ ሆይ! መናቄን መገፋቴን ተመልከች›› ሲል ወዲያው እመቤታችን ወርዳ ጠራችውና በዘርፋፋው ቀሚሷ ላይ ረቂቅ የሆነ ቅዳሴን አሳየችው፡፡ የለመኗትን የማትነሣ፣ የነገሯትን የማትረሣ የብርሃን እናቱ እመቤታችንም የልቡን መሻት ተመልክታ ‹‹ጎስዐ ልብየ ቃለ ሠናየ ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ›› በማለት ጀምሮ ‹‹ዛሬም አብን ወልድንና መንፈስ ቅዱስን እናመስግን›› እስከሚለው ድረስ ሰተት አድርጋ አስደርሳዋለች፡፡ እነርሱም ይህንን ግሩም የሆነውን ቅዳሴውን አደነቁ፡፡
የሚንቁትና የሚጠሉት ‹‹ይህ የነገሩትን ቀለም እንኳን አከናውኖ መናገር የማይችል ዛሬስ እንግዳ ድርሰት እደርሳለው ብሎ አገኝ አጣውን የቆጥ የባጡን ይቀባጥራል›› ብለው ተደነቁበት፡፡ የሚወዱትና የሚያከብሩት ግን ‹‹ከመንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እንዲህ ያለ ምሥጢር ከእሩቅ ብዕሲ ይገኛልን!›› ብለው አደነቁለት፡፡ ወዲያው የሚወዱት የሚያከብሩት ‹‹ጽፈን ደጉሰን አንይዘውምን!?›› አሉ፡፡ የሚንቁት የሚጠሉት ደግሞ ‹‹ማን ተናገረው ብለን እንይዘዋለን?›› አሉ፡፡ እንደ ልማዱ አድርገን አንይዘውም አሉ፡፡ ለሃገራቸው እንግዳ ድርሰት የተደረሰ እንደሆነ ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ይጥሉታል፡፡ ከእሳት ደህና ሆኖ የወጣ እንደሆነ ከውሃ ይጥሉታል፡፡ ከውኃም ደህና ሆኖ የወጣ እንደሆነ ከድውይ ሰው ላይ ይጥሉታል፡፡ ከእሳት ገብቶ ባይቃጠል፣ ከውኃ ገብቶ ባይርስ በመጨረሻም ድውይ የፈወሰ እንደሆነ ‹‹ደገኛ ድርሰት ነው›› ብለው ይይዙታል፡፡ ይህንንም ቅዳሴ ማርያምን ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ላይ ጣሉት፣ ከእሳት ደህና ወጣ፡፡ ከውኃ ላይ ጣሉት-ከውኃ ደህና ሆኖ ወጣ፡፡ ከደውያን ላይ ጣሉት-ድውይ ፈወሰ፡፡ ይልቁንም ሙት አስነሣ፡፡ ከዚህም በኋላ ‹‹ደገኛ ድርሰት ነው›› ብለው ጽፈው ደጉሰው ይዘውታል፡፡ በጥራዝም 14ኛ አድርገው ጠርዘውታል፡፡ ቅዳሴ ከዚያ በፊት 13 ነበርና አሁን ግን 14ኛ አድርገው ጽፈውታል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ከ14ቱም ቅዳሴ ተአምራት ያልተደረገበት የለም፡፡
ይህም ቅዳሴ ማርያም ስለ እመቤታችን እጅግ በጠለቀ ሁኔታ የሚያመሰጥር በመሆኑ በሰሙነ ፍልሰታ ይተረጎማል፡፡ ዕለቱን የሚመለከቱ ምሥጢራትም በዕለቱ ይተረጎማሉ፡፡ ምሳሌ ነሐሴ ሦስት የበዓታና፣ ነሐሴ ሰባት የፅንሰታ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የበዓታ ‹‹ድንግል ሆይ! አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ልጆች በጨዋታ ያደግሽ አይደለሽም፡፡ በቅድስና፣ በንጽሕና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ…›› የሚለውን ይመለከቷል፡፡ ነሐሴ ሰባትም ‹‹ድንግል ሆይ! ኃጢአት በሆነ ሩካቤ የተፀነስሽ አይደለሽም….›› የሚለውን ይመለከቷል፡፡
አባ ሕርያቆስ የእመቤታችንን ቅዳሴ እጅግ ድንቅ አድርጎ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀደሰው በልደቷ ቀን ነው፡፡ ይኸውስ እንዴት ታወቀ ቢሉ አንድ ምግባር ሃይማኖቱ የቀና በትሩፋት የበለጸገ ደገኛ ባሕታዊ ነበርና ከተጋድሎውና ለእመቤታችን ካለው ፍቅር የተነሣሳ እመቤታችን ተገለጠችለት፡፡ እርሱም ‹‹ከ33ቱ በዓላት ማንን ትወጃለሽ?›› ብሎ ጠየቃት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ኪዳነ ምሕረትን፣ ልደታን፣ አስተርአዮን፣ ፍልሰታን›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ከእነዚ ከ4ቱስ ማንን ትወጃለሽ?›› ቢላት እመቤታችን ‹‹ከጠባብ ወደ ሰፊ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የወጣሁበት ነውና ልደቴን እወዳለው›› አለችው፡፡ ‹‹ቀድሞ እኔ ሳልወለድ እናትና አባቴን መባችሁን አንቀበልም ብለው አዝነው ተክዘው ነበር፡፡ የእነርሱ ሃዘን ሃዘኔ ነውና እኔን ከወለዱ በኋላ መባቸውን ተቀብለዋቸው ደስ ብሎዋቸዋል፡፡ የእነርሱ ደስታ ደስታዬ ነውና›› ብላዋለች፡፡
ይህንን ድንቅ የሆነውን የአባ ሕርያቆስን ቅዳሴ እመቤታችን ለሌላኛው ወዳጇ ለኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ገልጣለታለች፡፡ እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን ከሶርያ፣ አባ ሕርያቆስን ከብሕንሳ በደመና ጠቅሳ ቅዱስ ያሬድ ካለበት አድርሳ ‹‹አንተ ውዳሴዬን፣ አንተ ቅዳሴዬን ነግራችሁት በዜማ ያድርስ›› ብላቸው እነርሱም ለቅዱስ ያሬድ ነግረውት በዜማ አድርሶታል፡፡ ከዚሁም ጋር አያይዞ 13ቱንም ቅዳሴ በዜማ ደርሷል፡፡
በእመቤታችን በዓሏ ዕለት ጌታችን ተገልጦላቸው ቅዳሴዋን እንዲቀድሱ ነግሯቸው ለዚህም የሚሆን ከሰማይ ኅብስትና ጽዋ አውርዶላቸዋል፡፡ በዕለቱም ቅዳሴዋን ሲቀድሱ የከበሩ ሐዋርያት በቀኝ በግራ እየተራዷቸው ሲቀድሱ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ ኅብስቱንና ጽዋውን ጋርዶታል፡፡ በሌላ ጊዜም አቡነ ሳሙኤል ጊዜአቸው ደርሶ ከማረፉ በፊት ቅዱስ ሚካኤል ነሐሴ 16 ቀን ወደ ገነት ነጥቆ ወስዶ ከእመቤታችን ፊት አቁሞ አስባርኳቸዋል፡፡
ቅዱሳን አባቶቻችን የእመቤታችንን ቅዳሴዋን ሲቀድሱ ከምድር ከፍ ብለው ይታዩ ነበር፡፡ የዋልድባው አቡነ ሳሙኤል ቅዳሴ ማርያምን እየደገሙ ሲሄዱ ክንድ ከስንዝር ከመሬት ከፍ ይሉ ብለው ይሄዱ ነበር፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ዕለት ውኃውን ቢባርኩት ውኃው ኅብስት ሆኖላቸው ተመግበው ምእመናንንም መግበዋቸዋል፡፡ እመቤታችንም የፍቅር ምልክት ሁለት ንዋያት ከጠቻቸው በኋላ ‹‹ውዳሴዬን ከቅዳሴዬ ጋራ አንድ አድርጎ የሚደግመውን ሰው አንተ ከገባህበት ውሳጤ መንጦላዕት አገባዋለው›› ብላ ተስፋቸውን ነግራዋለች፡፡ ይህንንም መሠረት ነማድረግ ልጆቻው ዛሬ በዋልድባ ያጠና በቃሉ፣ ያላጠና በመጽሃፍ ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን ሳይደግም የሚውል የለም፡፡ ይህም ተስፋ ውዳሴዋን ከቅዳሴዋ ጋር አንድ አድርጎ ለሚደግም ሰው ሁሉ ነው እንጂ ለእነርሱ ብቻ አይደለም፡፡ ዳግመኛም ሃይማኖት ምግባሩ የቀና ያ ደገኛ ባሕታዊ እመቤታችንን ‹‹ከምስጋናሽ ሁሉ ማንን ትወጃለሽ?›› ብሎ ቢጠይቃት እርሷም ‹‹ልጄ ዳዊትን፣ አቡነ ዘበሰማያትን ቢደግሙለት እንዲወድ እኔም ውዳሴዬን ቅዳሴዬን ቢደግሙልኝ ወዳለሁ›› ብላዋለች፡፡
አባ ሕርያቆስ የብርሃን እናቱ እመቤታችን ድንቅ ምሥጢርን ከገለጠችለትና ከባረከችው በኋላ በዘመኑ ቁጥር አንድ ሊቅ ሆኖ እጅግ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል፡፡ ቁጥራቸው እጅግ የበዙ ተግሣጻትን ጽፏል፡፡ አጠቃላይ ድርሰቶቹ ከ10 ሺህ በላይ ናቸው፡፡ በእንዲህ ያለ ንጽሕናና ቅድስና ሲያገለግል ኖሮ ጥቅምት 2 በሰላም ዐርፏል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን::

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages