ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 2 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, May 11, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 2

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ሁለት በዚች ቀን ጻድቅ_ኢዮብ አረፈ፣ የመንፈሳዊ ማኀበር አባት የአባ ጳኵሚስ ረድእ የከበረ ቅዱስ_አባት_ቴዎድሮስ አረፈ።


ግንቦት ሁለት በዚች ቀን ጻድቅ ኢዮብ አረፈ። ለዚህም ጻድቅ በዘመኑ እንደርሱ ያለ ዕውነተኛ ደግ ሰው እንደ ሌለ በቅዱሳት መጻሕፍትም ስለርሱ እንደተነገረ እግዚአብሔር መሰከረለት።
ሰይጣንም ቀንቶበት በገንዘቡና በልጆቹ ላይ ያሠለጥነው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። የጻድቅ ኢዮብን ትዕግሥት እግዚአብሔር ስለሚያውቅ አሠለጠነው ለመጪ ትውልድም አርአያና ምሳሌ እንዲሆን ፈቀደለት።
ስለርሱም ሐዋርያ ያዕቆብ በመልእክቱ እነሆ የጻድቅ ኢዮብን ትዕግሥቱን ሰምታችኋል አለ። ከዚህ በኋላም በአንዲት ቀን ገንዘቡ ሁሉ ጠፋ ሥጋውም በደዌ ሥጋ ከራሱ እስከ እግሩ ድረስ ተመታ። በዚህም በአስጨናቂ ደዌ ውስጥ ኖረ እግዚአብሔርንም አመሰገነው።
አንዲት ቃልን እንኳ በፈጠረው እግዚአብሔር ላይ አላጉረመረመም ነገር ግን የተወለደባትን ቀን ረገመ። እንስሶቹና ገንዘቡ ሁሉ በጠፋ ጊዜ እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔርም ነሣ የእግዚአብሔርም ስም የተመሰገነ ይሁን አለ።
በዚህ መከራ በነበረበት ዘመናት በተራራ ላይ ተጥሎ ሳለ የወዳጆቹና የሚስቱ ዘለፋ በዝቶበት ነበረ። እርስዋ እንዲህ ብላ መከረችው እስከ መቼ ድረስ በሞኝነት ትኖራለህ እንግዲህስ ስደበውና ሙት ዳግመኛ እግዚአብሔርን ደጅ እጠናዋለሁ መከራውንም እታገሣለሁ የቀድሞ ኑሮዬን ተስፋ አደርጋለሁ ትላለህን አለችው።
እንዲህስ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼ ሞቱ እኔም ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ላይረቡኝ ላይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምኩ ።
አንተም በመግል ተውጠህ በትል ተከበህ ትኖራለህ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ እኔም እየዞርኩ እቀላውጣለሁ ካንዱ አገር ወዳንዱ አገር ካንዱ ቤት ወዳንዱ ቤት እሔዳለሁ ከድካሜ በኔ ላይ ከመጣው ከችግሬም አርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስቲገባ ድረስ እጠብቃለሁ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኸው ሙት አለችው።
ኢዮብም ሚስቱን እየተመለከተ ሰማት። ሥርዓት እንዳልተሠራባቸው ከአሕዛብ ሴቶች እንዳንዲቱ ተናገርሽን ከዚህ ቀድሞ በጎውን ነገር ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበልን ከዚህ በኋላ መከራውን አንታገሥምን አላት። በዚህ ባገኘው መከራ ሁሉ ኢዮብ ጌታን የበደለው በደል የለም።
ኢዮብም ወርቅ በእሳት እንዲፈተን ፈጽሞ ተፈተነ። እግዚአብሔርም በደመና ውስጥ ተነጋገረው። ከተናገረውም በኋላ ከደዌው ፈወሰው ጥሪቱን ሁሉ ከቀድሞ እጥፍ አደረገለት ሌሎች ልጆችንም ሴቶችና ወንዶችን ሰጠው።
ኢዮብም ከደዌው ከተፈወሰ በኋላ መቶ ሰባ ዘመን ኖረ የኖረውም ዘመን ሁሉ ሁለት መቶ አርባ ስምንት ዓመት ነው። በበጎ ሽምግልናም እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን የመንፈሳዊ ማኀበር አባት የአባ ጳኵሚስ ረድእ የከበረ አባት ቴዎድሮስ አረፈ።
ይህም አባት በገድል የተጠመደ ትሑት ቅን ታዛዥ በበጎ ሥራም ፍጹም ነበረ። ከአባ ጳኵሚስም ዘንድ ከታናሽነቱ ጀምሮ መነኰሰ ለፈጣሪውም እንደሚታዘዝ ይታዘዘው ነበረ።
ስለዚህም አባ ጳኵሚስ እጅግ ወደደው በላዩም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አድራበታለችና በአንድነት ለሚኖሩ መነኰሳት ሁሉ አጽናኝና አረጋጊ ሆነ። ጥበብና ዕውቀት ነበረውና በዕድሜው ሕፃን ሁኖ ሳለ አባ ጳኵሚስ ገሣጭና መካሪ አድርጎ ሾመው።
ከአባ ጳኵሚስም ዕረፍት በኋላ በአባቱ በአባ ጳኵሚስ ፈንታ አበ ምኔት ሆኖ ተሾመ። ይህም አባት ትሕትናው የበዛ ነው ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ክብር ይሸሽ ነበር የአገልግሎቱንም በጎ ሥራ ፈጽሞ ወደወደደው እግዚአብሔር ሔደ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለሁላችን ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages