ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, June 17, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 11

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሰኔ ዐሥራ አንድ በዚችው ቀን የመላእክት አርአያ ያለው የከበረ ሰማዕት ገላውዴዎስ የተጋድሎው ፍጻሜ ነው፣ ኢትዮጵያዊው ታላቅ ጻድቅ አቡነ ገብረ ኢየሱስ ዕረፍታቸው ነው፡፡


ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
ሰኔ ዐሥራ አንድ በዚችው ቀን በጦርነት ድል አድራጊው ከቤተ መንግሥት ወገን የሆነ የመላእክት አርአያ ያለው የከበረ ሰማዕት ገላውዴዎስ የተጋድሎው ፍጻሜ ነው። ይህ ቅዱስ ምድራዊ መንግሥትንና የዚህን ዓለም ክብር የናቀ ነበረ መልካም ገድልንም ተጋደለ።
የማይጠፋ ሰማያዊ መንግሥትንና የማያልቅ ክብርንም ወረሰ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አብጥልዎስ ነው እርሱም ለሮም ንጉሥ ለኑማርያኖስ ወንድሙ ነው መልኩም እንደ እስራኤል ያዕቆብ ልጅ እንደ ዮሴፍ እጅግ ውብ ነበር።
እርሱም በጦርነት ላይ የበረታ ነበር የአንጾኪያ ተወላጆችም ይመኩበት ነበር። ስለ ደም ግባቱና ጽናቱ በሁሉ ዘንድ የተወደደ ነበር። እርሱንም ከመውደዳቸው ብዛት የተነሣ ጠላቶችን ድል እንዳደረጋቸው እነርሱም ድል ሁነው በውርደትና በብዙ ድንጋጤ ከፊቱ እንደሸሹ አድርገው ሥዕሉን ሥለው በከተማው መግቢያ በር ላይ ያኖሩት ነበር።
ቅዱስ ገላውዴዎስም የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዘወትር ያነብ ነበር። የሮም ንጉሥም ዜናውን ሰምቶ ሊያየው ወደደ ልጁ ገላውዴዎስንም ይልክለት ዘንድ ወደ አባቱ ላከ እርሱም ላከለት። በደረሰም ጊዜ በደስታ ሊቀበለው ንጉሡ ከሠራዊቱ ጋራ ወጣ በአየውም ጊዜ ደስ ተሰኘበት የሮሜ ከተማ ሰዎች ሁሉም ደስ አላቸው።
ከእነዚያ ወራቶችም በኋላ ከቍዝ አገር ሰዎችና ከአርማንያ ታላቅ ጸብ ተነሣ ይህም ቅዱስ ገላውዴዎስ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ታምኖ ወደ እነርሱ ወጣ ድልም አደረጋቸው ንጉሣቸውንም ያዘው ጣዖቶቻቸውንም ሰበራቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ተመለሰ ዲዮቅልጥያኖስም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ አምልኮ ጣዖትን በአጸና ጊዜ እጅግ አዘነ ፊቅጦር የሚባል የኀርማኖስ ልጅ ወዳጅ ነበረው ሁልጊዜም የመጻሕፍትን ቃል ይሰሙ ነበር ስለ ነፍሳቸውም ድኅነት ያነቡ ነበር።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደማቸውን ያፈሱ ዘንድ ተስማሙ። በዚያ ጊዜም ሰይጣን በሽማግሌ አምሳል ታያቸው ያዘነላቸውም መስሎ እንዲህ አላቸው ልጆቼ ሆይ መልካሞች ጎልማሶች ናችሁ የነገሥታት ልጆችም ናችሁ። ስለ እናንተ እፈራለሁ አዝንላችኋለሁም እኔም ከንጉሡ ጋር ትስማሙ ዘንድ ለአማልክትም ታጥኑ ዘንድ እመክራችኋችለሁ ሲአዝዛችሁም ትእዛዙን አትተላለፉ እናንተም ክርስቶስን በቤታችሁ አምልኩት ይህ ንጉሥ ኃይለኛ ርኅራኄም የሌለው ጨካኝ ነውና አላቸው።
ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር የሚነጋገራቸው ሰይጣን እንደሆነ አስገነዘባቸው ክፋትን ሁሉ የተመላህ የሐሰት አባት ሆይ ከእኛ ራቅ አንተ ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ሕግ ትቃረናለህና አሉት። ያን ጊዜም መልኩን ለውጦ እንደ ጥቁር ባሪያ ሆነ እንዲህም አላቸው እነሆ ከንጉሥ አጣልቼ ደማችሁን እንዲአፈሰስ አደርገዋለሁ ሰይጣኑም ይህንን ብሎ ወደ ዲዮቅልጥያኖስ ሔዶ ፊቅጦርንና ገላውዴዎስን ካልገደልካቸው በአንተ ላይ ይነሣሉ አንተንም ገድለው መንግሥትህን ይወስዳሉ እነርሱም የመንግሥት ልጆች ናቸውና አለው።
ስለዚህም ንጉሡ ወደ ቅዱስ ገላውዴዎስ ልኮ ወደርሱ አስመጣው ለጣዖታቱም እንዲሠዋ ለመነው የአባቱንም ሹመት ይሾመው ዘንድ ቃል ገባለት ሰምቶም አልታዘዘለትም። ንጉሡም ክፉ ቃልን ሊናገረው አልደፈረም ቅዱስ ገላውዴዎስ ግን በድፍረት ይናገረው ነበር ያለ መፍራትም ንጉሡንና የረከሱ አማልክቶቹን ሰደበ።
ኀርማኖስም ቅዱስ ገላውዴዎስን ወደ ግብጽ እንዲልከውና በዚያ እንዲገድሉት ንጉሡን መከረው እርሱ እንደ ልጄ እንደ ፊቅጦር ዐመፀኛ ነውና። ንጉሡም ወደ እንዴናው ገዥ እንዲህ ብሎ ጻፈ ገላውዴዎስ ትእዛዛችንን አልተቀበለም ቃላችንንም አልሰማም አንተም ወደ ትእዛዛችን ይመለስ እንደሆነ በብዙ ድካም ሸንግለው ይህ ካልሆነ ራሱን በሰይፍ ቁረጥ።
ቅዱስ ገላውዴዎስም ወደ እስክንድርያ ይወስዱት ዘንድ ንጉሡ እንደ አዘዘ በአወቀ ጊዜ የእኅቱ ባል የሆነ ሲድራማኮስን ጠርቶ ክብር ይግባውና ጌታችንን በማመን እንዲጸና ወገኖቹንም እንዲያጸናቸው አደራ አለውና በሰላምታ ተሰናበተው።
ወደ እንዴናው ገዥ ወደ አርያኖስም በደረሰ ጊዜ አርያኖስ አይቶ ደነገጠ ተነሥቶም እጁን ሳመው እንዲህም ብሎ ለመነው። ጌታዬ ገላውዴዎስ ሆይ ይህን ሥራ አትሥራ የንጉሥንም ትዕዛዝ አትተላለፍ።
ቅዱስ ገላውዴዎስም እንዲህ ሲል መለሰለት ንጉሥ ያዘዘህን ልትፈፅም እንጂ በነገርህ ልታስተኝ አልተላክሁም አለው። መኰንኑም እስከሚቆጣ ድረስ እንዲህ እርስበርሳቸው ይነጋገሩ ነበር በመኰንኑም እጅ ጦር ነበረ ቅዱስ ገላውዴዎስንም ወጋው ነፍሱንም ክብር ይግባውና በጌታችን እጅ ሰጠ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ።
ምእመናንም መጥተው የቅዱስ ገላውዴዎስን ሥጋ ወሰዱ በመልካም አገናነዝም ገነዙት ከቅዱስ ፊቅጦር ሥጋ ጋርም በሣጥን ውስጥ አኖሩት። የስደቱም ዘመን እስከሚፈጸም ጠበቁት። ከዚህ በኋላም የቅዱስ ፊቅጦር እናት ቅድስት ሶፍያ ወደ እንዴናው አገር መጣች የቅዱሳን ገላውዴዎስንና የፊቅጦርን ሥጋቸውንም ወስዳ ወደ አንጾኪያ አደረሰች።
የቅዱስ ገላውዴዎስ ሥጋ አስዩጥ በሚባል አገር ይኖራል የሚልም አለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ገብረ ኢየሱስ
ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ለግብፃውያን አባቶች ትንቢት ይነግሯቸው የነበሩት ኢትዮጵያዊው ታላቅ ጻድቅ አቡነ ገብረ ኢየሱስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ በሀገራችን ብዙ ተአምራትን በማድረግ ወንጌልን ሲሰብኩ ከኖሩ በኋላ የግብፅ ገዳማትን ለመሳለም ወደ ግብፅ ወርደው አባ መቃርስ ገዳም ገቡ፡፡ ከዚያም ወጥተው በአባ ዮሐንስ ሐፂር ገዳም ገብተው በዚያ ብዙ ጊዜ ተቀመጡ፡፡ አቡነ ገብረ ኢየሱስ ታላቅ የሆነ ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባት ስለሆኑ በዚህም ግብፃውያኑ ይቀኑባቸው ነበር፡፡
66ኛው የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብረ ክርስቶስ ባረፉ ጊዜ ኤጲስቆጶሳቱ ተሰብስበው ወደ አባ መቃርስ ገዳም ወደ አስቄጥስ መጥተው ለከበረች ሹመት የሚገባውን እየመረመሩ ሁለት ወር ተቀመጡ፡፡ በዚህም ጊዜ በአባ ዮሐንስ ሐፂር ገዳም ለሚኖሩት ለጻድቁ ለአቡነ ገብረ ኢየሱስ የታዘዘ መልአክ ተገልጦላቸው ‹‹ለኤጲስ ቆጶሳቱ ለዚህች ለከበረች ሹመት የሚገባ ስሙ ገአርጊ የሚባል በመካከላችሁ አለና እርሱን ሹሙት አትዘኑ›› በላቸው ብሎ ነገራቸው፡፡ አቡነ ገብረ ኢየሱስም ‹‹ከመካከላችሁ ስሙ ገአርጊ የሚባል ጻድቅ አለና እርሱን ሹሙት›› ብለው መልአኩ የነገራቸውን መልአክት ነግረዋቸው አባ ገአርጊን በማርቆስ መንበር ላይ 67ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡
አባ ገአርጊም ስማቸው አባ ቄርሎስ ተብሎ ከተሸሾሙ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ አገልግለዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው የግብፃውያኑ ንጉስ በጣም ብዙ ሚስቶች የነበሩት ቢሆንም አቡነ ገብረ ኢየሱስ ሄደው በድፍረት አስተምረውትና ገሥጸውት በአንድ ሚስት ብቻ እንዲጸና አድርገውታል፡፡ የጻድቁ አባታችን ገድላቸው በጣና ይገኛል፡፡ ዐርፈው የተቀበሩት ግን በዛው በግብፅ በቁስቋም ገዳም ነው፡፡ ግብፃውያን የቅድስና ማዕረግ ሰጥተዋቸው ታቦት ቀርጸውላቸው በዓላቸውን በሚገባ ያከብሩላቸዋል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages