ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 30 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, June 10, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 30

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ግንቦት ሠላሳ በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አባ ሚካኤል አረፈ፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሐዋርያ ቆሮስ አረፈ፣ የእናታችን ቅድስት ዜና ማርያም መታቢያ ነው፣ ተጋዳይ የሆነች ፍትወተ ሥጋን ድል ያደረገች በበጎ ሥራዋም እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘች ቅድስት አርዋ አረፈች፣ እናታችን ቅድስት ወለተ ማርያም መታሰቢያዋ ነው፡፡

አባ ሚካኤል ሊቀ ጳጳሳት
ግንቦት ሠላሳ በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ ስምንተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አባ ሚካኤል አረፈ። ይህም አባት የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ስለ ተማረ አዋቂ ነበር። በልቡም አጠናቸው በቃሉም አጠናቸው።
ከዚህም በኋላ ንጽሕት ሰውነቱ ከአምላክ በተገኘ የምንኵስና መንገድ በመጋደል ክብር ይግባውና የክርስቶስ ጭፍራ ልትሆን ወደደች። ወደ አስቄጥስ ገዳም ሒዶ በውስጡ ብዙ ዓመታት ኖረ ቅስናም ተሾመ።
ከዚህም በኋላ በግብጽ አገር ወደ አለ ወደ ሠንጋር ወጣ በዚያም በዋሻ ውስጥ ራሱን እሥረኛ አድርጎ አርባ ዓመት ኖረ ከዚያም የሚበዛ ኖረ በዚያም ዋሻ ውስጥ ታላቅ ተጋድሎ ተጋደለ።
የትሩፋቱ የጽድቁና የዕውቀቱ ወሬ በተሰማ ጊዜ በእስክንድርያ አገር ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ ኤጲስቆጶሳት ተስማው ወዲያውኑ ይዘው በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።
በተሾመም ጊዜ በጎ አካሔድን ሔደ የዚህን ዓለም ጥሪት ሁሉ ንቆ ተወ። ከሚገባው ከሚአመጡለት ገጸ በረከት አንድ ዲናር ወይም አላድ ጥሪት አድርጎ አላኖረም። ከእርሱ በየጥቂት እየተመገበ የቀረውን ለድኃና ለጦም አዳሪ ይሰጣል ለአብያተ ክርስቲያናትም ለንዋየ ቅድሳትና ለቅዱሳት መጻሕፍት መግዣ ያደርገዋል።
ሕዝቡንም ያስተምራቸውና ይገሥጻቸው ይመክራቸውም ነበር። አንድ ጊዜ ከመጻሕፍት አንድ ጊዜም ከቃሉ። መልካም አገልገሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ከዚህ ዓለም ድካም ሊያሳርፈው የሕይወትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ሊሰጠው ወዶ የአንዲት ቀንና የአንዲት ሌሊት ሕመም በላዩ አመጣ።
ከቶ አልተናገረም በሚሞትበትም ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን አመሰገነው ፊቱንም በመስቀል ምልክት አማተበ። ነፍሱንም ክብር ይግባውና በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ መላ ዕድሜውም ዘጠና ዓመት ከስምንት ወር ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ሐዋርያው ቅዱስ ቆሮስ
በዚህችም ዕለት ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሐዋርያ ቆሮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ጌታችን በሚያስተምርበት ወራት ሦስት ዓመት አገልግሎታል ከዕርገቱ በኋላም ሐዋርያትን አገልግሏቸዋል ከእሳቸውም ጋራ መንፈስ ቅዱስን ተቀበለ።
ከዚህም በኋላ ከሐዋርያ ጳውሎስ ጋራ በመሆን መልእክቶቹንም ወደ ብዙ አገሮች ተሸክሞ በመውሰድ አገለገለው። ከአይሁድና ከአሕዛብም ብዙዎቹን አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው።
ከዚህ በኋላም በምሥራቅ ወዳሉ አገሮች ሔደ ከመኵራቦችም ብዙ መከራ ደርሶበት አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም
በዚህች ዕለት የእናታችን ቅድስት ዜና ማርያም መታቢያ ነው፡፡ ከአባቷ ከገብረ ክርስቶስ ከእናቷ አመተ ማርያም በ11መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት በምድ ነጋሲ በጎጃም ምድር ግንቦት 30ቀን የተወለደች ሲሆን ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ በንፅህ ድንግልና በምድረ ሂንፍራንስ ጣራ ገዳም አካባቢ በሚገኘው በአቡነ እንድርያስ ዋሻ ለ25ዓመት በጾም በፀሎት ምንም አይነት የላመ የጣፈጠ እህል ሳትቀምስ በቅል ውስጥ የሚገኘውን መራራ ፍሬ ከኮሶ ጋር በአንድነት ደርጣ (አዋህዳ) በመዘፍዘፍ ከ3 ቀን በኃላ በመመገብ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ ላይ የቀመሰውን መራራ ሐሞትን በማሰብ ሙሉ ሕይወቶን እየተመገበች ታላቅ ተጋድሎዋን ፈፅማለች፡፡ ከዚህ የተነሳ ሸክላ ማርያም ተብላ ትጠራ የነበረችው ቦታ ስያሜ ተቀይሮ ደሪጣ ዜና ማርያም ዋሻ ተብሎ እስከ አሁን ድረስ በስሞ እየተጠራ ይገኛል፡፡
ከአቡነ እድርያስ ዋሻ በመቀጠል ከአዲስ አበባ ተነስተን ስንጓዝ አዲስ ዘመን ከተማ በስተቀኝ በኩል ተገንጥለን 15ኪሜ ያክል የጥርጊያ መንገድ እንደተጓዝን በስሞ የተሰየመውን ደሪጣ ጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ገዳም ላይ ቀሪ ሕይወቶን ምንም አይነት ዋሻ ባልነበረበት በከፍተኛ ተራራ ላይ እጅግ አስቸጋሪ ቀዝቃዛ አየር ባለበት ብርዱን፣ ፀሐዩን፣ ቁሩን፣ ረኃቡንና ጥሙን በመቋቋም ራቁቶን በመሆን መራራ ምግቦችን አዋህዳ በመመገብ በጾም በፀሎት በመትጋት አስቸጋሪ የሆነውን ተጋድሎዋን በመፈፀም በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ነሐሴ 30 ቀን በታላቅ ክብር አርፋለች፡፡
በዚህም ወቅት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከእልፍ አላፋት ቅዱሳ መላዕክት ጋር እንዲሁም ከሐዋርያት ፣ ከሰማዕታት ፣ ከጻድቃን ፣ ከደናግል ጋር በመሆን ከሰማይ በመውረድ በታላቅ ክብር ዕረፍቷን አክብሮላታል ታላቅ ኪዳንም ገብቶላታል፡፡
በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ላይ ወይንም በአሁኑ ሰዓት መቃብሯ በሚገኝበት ዋሻ ቤተመቅደስ አካባቢ በተጋድሎዋ ጊዜ ራቁቷን በሆነች ሰዓት መላ ገላዋን የሸፈነላት ፀጉር በእየ ዛፎቹ ላይ እስከ አሁን ድረስ አለ ፡፡ ይህም የጸጉር አምሳያ ከገዳሙ በመውሰድ ብዙ ሰዎች በቤታቸው በመታጠን ከአስም እንዲሁም ከተለያዩ በሽታዎች እየተፈወሱና እየዳኑ ሲሆን ታላላቅ ታምራትን እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህ ገዳም ከሌሎች ገዳማት ለየት የሚያደርገው ታሪክ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ በመውረድ ራሱ የባረከው ልዩ ታሪክ ያለው ጠበል የሚገኝ ሲሆን ይህም ጠበል በቦታው ላይ ሆኖ የተጠመቀ ፣ የጠጣ ፣ አልያም በአለበት ቦታ ሆኖ የተጠቀመ እስከ አሁን ድረስ መካን የሆኑ ሰዎች በፍጥነት ልጅ የሚያገኙ ከመሆናቸው ባሻገር ከማንኛውም ከተለያዩ በሽታዎች በመፈወስ ታላላቅ ታምራትን እየሰራ ይገኛል፡፡
በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ላሊበላ በጌታችን በአምላካችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ መሰረት ወደዚሁ ታላቅ ስፍራ በመምጣት የጻድቋ ማረፈያ/መታሰቢያ ዋሻ ቤተ መቅደስ በመፈልፈል የሰራላት ሲሆን በመቀጠል አፄ ይስሐቅ በ14ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይህን ገዳም በስሟ በመገደም በዚሁ ዋሻ ውስጥም የጻድቋ የቅድስት ዜና ማርያም መቃብሯ እንዲሁም የመታሰቢያዋ ፅላት የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር በአካባቢው ያሉት ሕዝበ ክርስትያን ከካህናት ጋር በመሆን ሥርዓተ አምልኮ በመፈፀም እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡
ይህ ዋሻም አስቀድሞ ሦስቱ ቅዱሳን ማለትም አቡነ እንድርያስ ዘጣራ ገዳም ፣አቡነ ተክለኃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ፣ ጻድቋ ቅድስት ዜናማርያም ዘደሪጣ ውስጥ ለውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በፀጋ እግዚአብሔር ይገናኙበት የነበረ ሲሆን በአሁን ሰዓትም እግዚአብሔር የመረጣቸው ቅዱሳን ይመላለሱበታል፡፡
ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም የተሰጠ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር አምላክ መርጦና ፈቅዶ በጻድቋ አማላጅነት ካለበት ስፍራ ተነስቶ የጻድቋ ደጃን የረገጠ ለ3 ግመል ጭነት ጤፍ ወይም የሦስት አህያ ጤፍ ያህል ነፍሳትን እምርልሻለሁ፤ ከሲዖልም እሳት ነፍሳትን አወጣልሻለሁ
የሚል ቃል ኪዳን ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ተሰቶታል። ከእናታችን ቅድስት ዜና ማርያም ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቷም ይማረን!።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
እናታችን ቅድስት አርዋ
በዚችም ዕለት ተጋዳይ የሆነች ፍትወተ ሥጋን ድል ያደረገች በበጎ ሥራዋም እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘች ቅድስት አርዋ አረፈች። ቅድስት አርዋ በስነ ገድላቸው ከደመቁ የቀደመው ዘመን ቅዱሳት አንስት አንዷ ናት:: በሕጻንነቷ የሚገባውን የክርስትና ትምሕርት ተምራለችና ምርጫዋ ሰማያዊው ሙሽርነት ሆነ::
ለሰዎች ሕይወት እንቅፋት እየሆኑ ከሚያስቸግሩ ነገሮች አንዱ መልክ ነው:: እግዚአብሔር የፈጠረውን ደም ግባት (ቁንጅና) በማይገባ ተጠቅመው የአጋንንት ራት የሆኑ: ሌሎችንም አብረው ያጠፉ ሰዎች ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ነው:: ቅድስት አርዋ ግን ይሕ ቀረሽ የማይሏት ውብ ብትሆንም እርሷ ለዚሕ ቦታ አልነበራትም:: ገና በለጋ እድሜዋ በክርስቶስና በድንግል እናቱ ፍቅር ተጠመደች እንጂ::
ቅድስት አርዋ ሁሉ ያላት ስትሆን ስለ መንግስተ ሰማያት ሁሉን ንቃለች:: በተለይ ደግሞ ሥጋዊ ፍትወትን ትገድል ዘንድ ያሳየችው ተጋድሎ በዜና ቤተ ክርስቲያን የተደነቀ በመሆኑ "መዋኢተ ፍትወት" (የሥጋን ፍላጎት ድል የነሳች) አስብሏታል::
የሚገርመው የቅድስቷ እናታችን ሕይወት በጾምና በጸሎት ብቻ የተወሰነ አልነበረም:: በሰው ሁሉ ፊት ብርሃን መሆን የቻለ የደግነት: ርሕራሔ: የፍቅርና የምጽዋት ሕይወትም ነበራት እንጂ::
አንድ ቀን በተንኮለኞች የሐሰት ምስክር ያለ ጥፋቷ ለፍርድ ቀረበች:: ፍርደ ገምድል ዳኛ ሞት ፈረደባት:: በአደባባይ በጭካኔ ቅድስት እናታችንን ገደሏት:: እግዚአብሔር ግን ድንቅ ነውና ከሞት አስነስቷት ገዳዮቿ እንዲጸጸቱ አድርጉዋል:: ከዚሕ በሁዋላም በንጹሕ አኗኗሯ ቀጠለች::
አንድ ቀን ግን ከባድ ፈተና መጣባት:: አንድ በደም ግባቷ ተማርኮ ሲፈልጋት የኖረ ጐልማሳ አሳቻ ሰዓትና ቦታ ላይ አገኛት:: የሥጋ ፈቃዱን ይፈጽም ዘንድ አስገደዳት::
እርሱን መታገሉ ከአቅሟ በላይ ስለሆነባት እርሱ ልብሱን እያወለቀ እርሷ ከወደቀችበት ሆና ወደ ፈጣሪዋ ለመነች:- "ጌታየ ሆይ! የእኔንም ድንግልና ጠብቅ: እርሱንም ኃጢአት ይሠራ ዘንድ አትተወው:: ስለዚሕም ነፍሴን ተቀበላት" ብላ አለቀሰች::
እመቤታችን እንደ ዐይን ጥቅሻ ወርዳ ነፍሷን አሳረገች:: ጐልማሳው ወደ ጣላት ቅድስት ዘወር ቢል ሙታ አገኛት:: እርሱም ተጸጸተ:: ወገኖቿ በዝማሬ እናታችን ቅድስት አርዋን ቀብረዋታል::
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት ወለተ ማርያም ዘጎንደር
በዚህች እለት እናታችን ቅድስት ወለተ ማርያም መታሰቢያዋ ነው፡፡ ትውልዷ ጎንደር ሲሆን በዐፄ ወናአግ ሰገድ ዘመን የነበረች ከቤተ መንግሥት ወገን የሆነች ጻድቅ እናት ናት፡፡ ደብረ ሊባኖስ ሄዳ ከመነኰሰች በኋላ ወደ ጣና ገዳም ገብታ በጣና ባሕር ውስጥ ለ11 ዓመት ቆማ የጸለየች ድንቅ እናት ናት፡፡ ከእናታችን ከቅድስት ወለተ ማርያም ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን እኛንም በጸሎቷ ይማረን።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages