ኢትየጵያዊዉ ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ/ም በአክሱም ከተማ ተወለደ፡፡እናቱ ታዉክሊያ/ክርስቲና/አባቱ ደግሞ ይስሐቅ/አብድዩ/ይባላሉ፡፡አባቱ የ አክሱም ጽዮን ቄሰ ገበዝ ነበር፡፡ያሬድ ሰባት ዓመት ሲሆነዉ አባቱ ስለሞቱበት እናቱ ት/ቤት ለማስገባት ወደ አጎቱ መምህር ጌዲዮን ጋር ወሰደችዉ፡፡አባ ጌድዮንም በአክሱም ቤተ ቀጢን(ቤተ ጉባኤ)መምህር ነበሩ፡፡ያሬድ ያኔ በትምህርቱ የሚያሳየዉ ዉጤት ደካማ ስለነበር ከሌሎች ህጻናት ጋር ሊወዳደር አልቻለም፡፡መምህሩ ጌዴዎን ለተግሣጽ ቢቀጡትም መታገስ ተስኖት ተስፋ ቆርጦ ከአክሱም ከተማ ወጥቶ ወደ እናቱ መንደር መደባይ ወለል ተጓዘ፡፡
ህጻን ያሬድ ከዛፍ ስር ተቀምጦ በምን ምክንያት ገጓደኞቹ በታች እንደሆነ ሲያዝን ሲተክዝ ቆየ፡፡ታደሰ አለማየሁ‹‹የቤተ ክርስቲያን ብርሀን ቅዱስ ያሬድ››በሚለዉ መጽሐፉ‹‹አንድ ትል የዛፉን ፍሬ ለመመገብ ፈልጎ ወደላይ እየወጣና እየወደቀ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በሰባተኛዉ ጊዜ ወጥቶ ፍሬዋን ሲመገብ ተመለከተ፡፡ያሬድም የዚህ ትል ተስፋ አለመቁረጥ ትዕግስቱን ጽናቱን ተመልክቶ‹እኔም ተስፋ ሳልቆርጥ ብዙ ጥረት ካደረኩ እንደዚህ ሊሳካልኝ ይችላል›ብሎ ወደ መምህሩ ለመመለስ ወሰነ ይላል››ያሬድ የ አጎቱ ምክርና ተግሣጽ ለሕይወቱ የሚጠቅም መሆኑን በመረዳቱ ትምህርቱን በትጋት ቢማርና ቢያጠና ያሰበዉ ደረጃ ለመድረስ እንደሚችል በመገንዘብ ወደ መምህሩ ጌዲዮን ጉባኤ ቤት ተመለሰ፡፡መምህሩም ተቀብለዉ አስተማሩት፡፡በአጭር ጊዜ አልገባ ያለዉ ትምህርት ተገልጾለት ትምህርቱን በሚገባ አጠናቀቀ፡፡በኋላም የብሉይና የሐዲስ መምህር ሆኖ በመምህሩ በጌዲዮን ወንበር ተተካ፡፡
የቅዱስ ያሬድ ዜማ እና ዓይነቶቹ
የቅዱስ ያሬድ ዜማ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተገለጸለት ለመሆኑ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ቅዱስ ያሬድ ዜማዉን ያዘጋጀዉ በሦስት ዓይነት ድምፅ ማለትም በግእዝ፣በዕዝል፣እና በዓራራይ ዜማ ነዉ፡፡እነዚህ የዜማ አይነቶች የአንዱ ድምፅ ከሌላኛዉ ድምፅ ያልተደበላለቀ ወጥ የሆነ ድምፅ አላቸዉ፡፡ዜማዎቹንም በስምንት ምልክቶች ቀምሮታል፡፡የምልክቶች አገልግሎትም በትምህርት ሂደት ጊዜ የጠቋሚነት ሚና በመጫወት ለዜማዉ መጠበቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸዉ፡፡
ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀል
ቅዱስ ያሬድ የተነሳዉ ዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት ዘመን ነዉ፡፡በዘጠኙ ቅዱሳን የተተረጎሙት ቅዱሳን መጻሕፍት
በቅዱስ ያሬድ የድርሰት ስራ ዉስጥ ጉልህ ድርሻ ነበራቸዉ፡፡ቅዱስ ያሬድ ከመጻሕፍቱ ያገኛቸዉን ምስጢራት ቃል በቃል እየጠቀሰ እንዲሁም ሐሳባቸዉን ጨምቆ በመዉሰድ በራሱ ቋንቋ እያራቀቀ ለድርሰቱ ተጠቅሞባቸዋል፡፡/ሰሎሞን ወንድሙ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ሕይወት፤1998 ገጽ15/፡፡
ቅዱስ ያሬድ ሙራደ ቃልበተባለ ቦታ ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲያዜም ንጉሱ አፄ ገብረ መስቀል ከነሰራዊቶቻቸዉ ንግስቲቱ ከነደንገ ጡሮቿ ፣መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ሊቃዉንቱና ካህናቱ አየመጡ ያዳምጡ ነበር ይላሉ ርእሰ ደብር ጥዑመ ልሳን ካሣ በመጽሐፋቸዉ፡፡
ቅዱስ ያሬድ በግእዝ፣በዕዝል በዓራራይ ዜማ ዝማሜ እየደረሰ እያለ ንጉሱ አፄ ገብረ መስቀል ተገኝተዉ ነበር፡፡በዜማዉ ተመስጠዉ አይን አይኑን እያዩ እንደ እርሱ እዘምማለሁ ብለዉ በያዙት የብረት ዘንግ ሳያዉቁት ቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ቸከሉት፡፡ሁለቱም በተመስጦ ስለነበሩ የሆነዉን ነገር አላስተዋሉትም ነበር፡፡ዜማዉ አብቅቶ ሁለቱም ከተመስጧቸዉ ሲነቁ የቅዱስ ያሬድ እግር ዘንጋቸዉ ተሰክቶ ብዙ ደም ፈሶት ነበር፡፡ንጉሡም ደንግጠዉ እጅግም አዝነዉ‹‹ደምህን አፍስሻለሁና የምትፈልገዉን ማንኛዉንም ነገር ጠይቀኝ እሰጠሃለሁ››ሲሉ ቃል ገቡለት፡፡ቅዱስ ያሬድም‹‹ይምለምነዉ አንድ ነገር አለ እርሱን ፈጽምልኝ››አላቸዉ፡፡‹‹የፈለከዉን ጠይቅ ፈቅጄልሃለሁ››አሉት፡፡እርሱም‹‹እስካሁን እግዚአብሔር በፈቀደልኝ መሰረት በዚህ ከተማ ከእርሰዎ ጋር ቆይቻለሁ፡፡ብዙ ደቀ መዛሙርትም ተክቼያለሁ፡፡ከእንግዲህ በኋላ የቀረኝን ዘመን በጸሎትና በብሕትዉና መኖር እንድችል ከከተማዉ ራቅ ወዳለ ቦታ ሔጄ ፈጣሪየን ማገልገል እፈልጋለሁ››ብሎ የንጉሱን ፈቃድ ጠየቀ፡፡
አፄ ገብረ መስቀልም የቅዱስ ያሬድን ቃል ሰማተዉ በዚያኑም በገቡለት ቃል መሰረት ፈቀዱለት፡፡ከዚያም ጉዞዉን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ሰሜን ተራሮች አደረገ፡፡በዚያም አሁን በስሙ የታነጸዉ ቤተ ክርስቲያን ባለበት ቦታ ላይ በምናኔ ተወስኖ ፈጣሪዉን በብሕትዉና እያገለገለ ኖረ፡፡ምናኔ ደብረ ሐዊ ከተባለዉ ተራራ ላይ ብዙ ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ በጸለምት ዋሻ በአንዱ ግንቦት 11 ቀን በ571 ዓ/ም ተሰወረ፡፡
የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች
ቅዱስ ያሬድን ብቸኛ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ መስራች አድርጎ ለማየት በቂ ምክንያት አለን፡፡እንዲያዉም የግእዝ ስነ ጽሑፍ መስራች ከማለት ይልቅ የኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ መሥራች ልንለዉ ይገባል፡፡/ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ኃይሌ የቅዱስ ያሬድ ታሪክና የግእዝ ስነ ጽሑፍ፤1999፤ገጽ3/ፕሮፌሰሩ በዚሁ ጥናታቸዉ እንዳብራሩት የግእዝ ስነ ጽሑፍን ለሁለት ልንከፍለዉ እንችላለን ይላሉ፡፡ምክንያቱን ሲያብራሩ፡-አንዱ ክፍል ከባህር ማዶ ተጽፈዉ ወደ ግእዝ የተተረጎሙትን መጻሕፍት ይይዛል፡፡ሁለተኛዉ ክፍል በቀጥታ በግእዝ የተደረሱትን ድርሰቶች ያጠቃልላል፡፡እነዚህም፡-የቅዱስ ያሬድ፣የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣የርቱዐ ሃይማኖት፣የ አፄ ዘርአ ያዕቆብ፣የ ዐርከ ሥሉስ፣የ አባ ባሕርይ ድርሰቶች የሚቀድም በ ግእዝ ቋንቋ የተደረሰ ድርሰት እስከ አሁን አለመገኝቱን ጥናቱ ያሳያል፡፡/1999፡3/
ቅዱስ ያሬድ ድርሰቶችን ሲያዘጋጅ ከቅዱሳን መጻሕፍት የወሰዳቸዉን ርእሰ ጉዳዮች በፈርጅ በፈርጁ እየለየ በድርሰት ሥራዎቹ እንደ ፈርጥ ተጠቅሞባቸዋል፡፡ብሉያትን ከሐዲሳት፣ከሊቃዉንት እያጣቀሰ ያለምንም ችግር የድርሰት ሥራዉን ሊያከናዉን ችሏል፡፡የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች መንፈሳዊ ይዘት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡በድርሰቶቹ የሚታዩት የቃላት አመራረጥ፣የ ዐረፍተ ነገር አወቃቀር፣የሚስጥር፣የዘይቤ አገላለጥ ቅዱስ ያሬድ ከፍተኛ የስነ-ጽሑፍ ተሰጥኦ እንደነበረዉ ለመረዳት ይቻላል፡፡በቅዱስ ያሬድ የተደረሱት የዜማ መጻሕፍት አምስት ናቸዉ፡፡እነርሱም ድጓ፣ጾመ ድጓ፣ዝማሬ፣ምሥዋዕትና ምዕራፍ ናቸዉ፡፡
ድጓ፡-የቅዱስ ያሬድ ትልቁ የዜማ መጻሕፍ ነዉ፡፡ድጓ ማለት ስብስብ ማለት ነዉ፡፡በዉስጡ የዓመቱን በዓላትና የሳምንታት መዝሙራት ሰብስቦ የያዘ ነዉ፡፡ይህ መጽሐፍ በዐበይት በዓላት በዜማ የሚቀርበዉን ምስጋና ሰብስቦ የያዘ የዜማ መድብል ነዉ፡፡ ድጓ በአራት ትልልቅ ክፍሎች ይከፈላል፡፡ይኸዉም፡-የዮሐንስ ድጓ፣አስተምህሮ ድጓ፣ጾመ ድጓ፣የፋሲካ ድጓ ተብሎ ይታወቃል፡፡
ጾመ ድጓ፡-ሁለተኛዉ የዜማ መጽሐፍ ሲሆን የሚጠናና ለመምህርነት የሚያበቃ ነዉ፡፡ድጓ ቁጥሩ ከአስተምህሮ ሲሆን በዐቢይ ጾም የሚደርስ ራሱን የቻለ መጽሐፍ ነዉ፡፡
ዝማሬ፡-ሦስተኛዉ የዜማ መጽሐፍ ነዉ፡፡ዝማሬ ምስጋና ማለት ነዉ፡፡ዝማሬ በጸሎተ ቅዳሴ ከድርገት በኋላ በቅዳሴ ማብቂያ አካባቢ የሚዜም የሚዘመር የጸሎተ ቅዳሴዉን ዓላማ ተከትሎ የሚሔድ ማለት ነዉ፡፡መጽሐፈ ዝማሬ በይዘቱ አምስት ነገሮች አሉት፡፡እነርሱም ኅብስት፣ጽዋ፣መንፈስ፣አኮቴት እና ምስጢር ናቸዉ፡፡
መሥዋዕት፡አራተኛዉ የዜማ መጽሐፍ ነዉ፡፡መሥዋዕት የቃሉ ትርጓሜ ሁለት ዓይነት ነዉ፡፡አንደኛዉ ምልልስ ማለት ነዉ፡፡በግራና በቀኝ እየተመላለሰ ወይም እየተቀባበለ የሚባል ስለሆነ ነዉ፡፡የመሥዋዕት ሁለተኛዉ ትርጉሙ ደግሞ የነፍስ መመላለስ(መሸጋገሪያ )ማለት ነዉ፡፡የ ኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀትን፣ሞቱን፣ትንሣኤዉን፣ዕርገቱን የሚያስረዳ ነዉ፡፡የመሥዋዕት አገልግሎት ለሙታን ጸሎተ ፍትሐት ለማድረስ በበዓላትና በአጽዋማት ደግሞ ስብሐተ ነግሕ ለማድረስ ነዉ፡፡
ምዕራፍ፡-የቅዱስ ያሬድ አምስተኛዉና የመጨረሻዉ የዜማ መጽሐፍ ነዉ፡፡የምዕራፍ ቀጥተኛ ትርጉሙ ማረፊያ ወይም ማሳረፊያ ማለት ነዉ፡፡ምዕራፍ ከመዝሙረ ዳዊት የተዉጣጣ ድርሰት ሲሆን የዳዊት መዝሙራትን በመስመር(ምዕራፍ)እየከፋፈለ የዜማዉን አይነትና ማሳረፊያ ይገልጻል፡፡
የቅዱስ ያሬድ አስተዋጽኦ
ቅዱስ ያሬድ ለቤተ ክርስቲያን ለሀገርም ያደረገዉ አስተዋጽኦ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡በቤተ ክርስቲያንበ እያንዳንዱ አገልግሎት የሚወሳ ነዉ፡፡ሊቀ ሊቃዉንት ታፈሰ ደሳለኝ ስለ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት አስተዋጽኦ ሲገልጹ‹‹የቤተ ክርስቲያናችን አምድ፣የውስጥ ማኅቶት፣የአፍ መብራት፣ በጠቅላላዉ የቤተ ክርስቲያን መንቀሳቀሻ ሕይወት ነዉ፡፡››በማለት ጽፈዋል፡፡/አይከብር፤1988፣18/፡፡ዶ/ር ዉቤ ካሣየም ቅዱስ ያሬድ ለሀገር ያበረከተዉን አስተዋጽኦ ሲገልጹ‹‹የቅዱስ ያሬድ ዜማ የመጠቁ፣የምንኮራባቸዉ፣የእኛን ማንነት ሊገልጹ የሚችሉ እና በድርሰቶቹ ዉስጥ ያሉት መልዕክቶች እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ፣ከመጥፎ ነገር እንድንቆጠብ፣በጎ ነገርን እንድንይዝ፣ጥበብን እንድንፈልግ፣ሰላም እንዲኖረን የሚያስተምሩ ናቸዉ፡፡››ድርሰቶቹ ከመንፈሳዊዉ አስተምህሯቸዉ በተጨማሪ ሌሎች ሁኔታወችን በማንሳት የሚያብራሩ ናቸዉ፡፡››ብለዋል
የቅዱስ ያሬድ ት/ቤት በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቅዱስ ያሬድ ብዙ የተጻፈለት፣የሚጻፍለት፣የተነገረለትና የሚነገርለት ኢትዮጵያዊ ቅዱስ የለም ማለት ይቻላል፡፡ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ያሬድ ጽኑና ታላቅ ፍቅር የተነሣ ንጽሕናዉን‹ቅድስናዉንናመንፈሳዊ አገልግሎቱን አይታ በስሙ ጽላት ቀርጻ፣ቤተ ክርስቲያን አንጻ፣ገድል ጽፋ፣ ስታከብረዉና ስታመሰግነዉ ትኖራለች፡፡ሰሎሞን ወንድሙ‹‹ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ሕይወት››በሚለዉ መጽሐፉ ቤተ ክርስቲያን 1500 ዓመታት ያህል ለቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት ሳትወጣ ተማሪ ቤት ከፍታ፣ወንበር ዘርግታ፣ዜማዉን ለትዉልድ እያስተማረች ስትገለገልበት መኖሯን ያስረዳል፡፡ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ኃይሌ ከዚህ የተለየ አስተያየት አላቸዉ፡፡‹‹የቅዱስ ያሬድ ታሪክና የግእዝ ስነ ጽሁፍ››በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት‹‹የቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያ ታሪክ ሰዉ ሆኖ ሳለ ሊቃዉንቶቻችን ትምህርቱን ዓመታት እያሳለፉ፣መምህራን እያፈራረቁ፣በቅናት በጥንካሬና በኩራት ሲማሩ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ያሬድ ማን እንደሆነ ለማወቅና እኛንም ለማሳወቅ የሚገባዉን ምርምር ሲያደርጉ አልታየም፡፡››በማለት ያለዉን ክፍተት ያሳያሉ፡፡/1993፤3/፡፡ይሁን እንጅ አያሌ ኢትዮጵያንም የቅዱስ ያሬድን ዜማ ሲማሩና ሲያስተምሩ የሚያሳልፉትን ቤተ ክርስቲያን አክብራ፣ጠብቃ ስላቆየቻቸዉ ነዉ፡፡በቤተ ክርስቲያን የሊቅነት መስፈሪያ መለኪያ መስፈርት ሆነዉ ከሚቀርቡት ነገሮች አንዱ የያሬዳዊ ዜማ ዕዉቀት ነዉ፡፡ቤተ ክርስቲያኗ ለቅዱስ ያሬድ ያላትን አክብሮት ለመግለጽ በስሙ የሚጠራ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ምርያም ቅጽር አቋቁማለች፡፡ለመንግስትም ታሪኩን በማሳወቅ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 30 ቀን 1963 ዓ/ም በስሙ የሚጠራ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲከፈት አድርጋለች፡፡የሙዚቃ ት/ቤቱ ሲመረቅ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ‹‹ይህ ትምህርት ቤት እንዲቋቋም ያስቻለን ምክንያት ለዉጭዉ ሀገር ት/ቤት ብቻ አይደለም፡፡በመጀመሪያ የሀገራችን የዜማ ባሕልና ሥነ ሥርዓት ተጠብቆ በዚህ እንዲደራጅ በማሰብ ነዉ፡፡››በማለት ትምህርት ቤቱ የተከፈተበትን ምክንያት ገልጸዉ ነበር፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም የመጀመሪያዉ ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ዜማዉም ሆነ የዜማዉ መሳሪያ በ ዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ብዙ መሠራት ያለበት መሆኑን፣ቤተ ክርሰቲያኒቱም ከቀድሞዉ በበለጠ ትኩረት መስጠት እንዳለባት የምሁራኑ ጥናት ያሳያል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የአባታችን የቅዱስ ያሬድ በረከት ይደርብን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment